የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 9/1 ገጽ 27-30
  • ካታራውያን ክርስቲያን ሰማዕታት ናቸውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ካታራውያን ክርስቲያን ሰማዕታት ናቸውን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ ውስጥ የነበረው ሃይማኖታዊ ቅራኔ
  • ተጓዥ ሰባኪዎች
  • ካታራውያን እነማን ነበሩ?
  • ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው አመለካከት
  • ክርስቲያኖች አይደሉም
  • የጭፍጨፋ ዘመቻ
  • ኢንኩዊዚሽኑ የማጥፋት ዘመቻውን ዳር አደረሰው
  • ዎልደንሳውያን—ከመናፍቅነት ወደ ፕሮቴስታንትነት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
  • ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ ክፍል 15:- ከ1095-1453 እዘአ​—ሰይፍ መምዘዝ
    ንቁ!—1996
  • የአምላክ ቃል ለብዙኃኑ እንዳይዳረስ የተደረገ ጥረት
    ንቁ!—2011
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 9/1 ገጽ 27-30

ካታራውያን ክርስቲያን ሰማዕታት ናቸውን?

“ሁሉንም ፍጁአቸው፤ አምላክ የራሱ የሆኑትን ያውቃል።” በ1209 በዚያ የበጋ ወቅት በደቡብ ፈረንሳይ የምትገኘው የቤዚዬ ከተማ ነዋሪዎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ተጨፈጨፉ። ዘመቻውን ባካሄዱት ካቶሊኮች ላይ የሊቀ ጳጳሳቱ ወኪል ሆኖ የተሾመው መነኩሴው አርኖልድ አማልሪክ ምንም ዓይነት ምሕረት አላሳየም። በሥሩ የነበሩት ሰዎች ካቶሊኮቹንና መናፍቆቹን መለየት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ሲጠይቁት ከላይ የተጠቀሰውን የሚሰቀጥጥ መልስ ሰጣቸው። ካቶሊክ የሆኑ ታሪክ ጸሐፊዎች “ምንም አትጨነቁ። የሚለወጡ ይኖራሉ ብዬ አላምንም” በማለት ምላሹን ቀለል አድርገው አስቀምጠውታል። የሰጠው መልስ ምንም ይሁን ምን በዚህ ሳቢያ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት አመራር ሰጪነት ወደ 300,000 በሚጠጉ ዘማቾች እጅ ቢያንስ ቢያንስ 20,000 ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ተጨፍጭፈዋል።

የዚህ ጭፍጨፋ መንስኤ ምንድን ነው? ይህ ጭፍጨፋ ሊቀ ጳጳሳት ሣልሳዊ ኢኖሰንት በደቡብ መካከለኛው ፈረንሳይ በሎንግዶክ ግዛት በሚኖሩ መናፍቃን በሚባሉ አልቢጄኒሳውያን ላይ ያስነሱት የማጥፋት ዘመቻ የመጀመሪያ ክፍል ነበር። ይህ የማጥፋት ዘመቻ ወደ 20 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ከማብቃቱ በፊት አንድ ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች ማለትም ካታራውያን፣ ዎልደንሳውያንና አልፎ ተርፎም ብዙ ካቶሊኮች ሕይወታቸውን እንዳጡ ይገመታል።

በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ ውስጥ የነበረው ሃይማኖታዊ ቅራኔ

በ11ኛው መቶ ዘመን እዘአ በንግዱ ዓለም የነበረው ፈጣን እድገት በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ ውስጥ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋሞች ረገድ ታላላቅ ለውጦችን አስከትሏል። ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የሄደውን ባለሙያዎችና የንግድ ሰዎች ለማስተናገድ ብዙ ከተሞች ተቆረቆሩ። ይህም አዳዲስ ሐሳቦች እንዲፈልቁ በር ከፈተ። በአውሮፓ ውስጥ በየትኛውም ቦታ ያልታየ ጠንካራ መሠረት ያለውና ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ የደረሰ ሥልጣኔ በታየባት በሎንግዶክ ሃይማኖታዊ ቅራኔ ሥር ሰደደ። በሎንግዶክ ውስጥ የምትገኘው ቱሉዝ የተባለችው ከተማ በአውሮፓ ውስጥ በብልጽግናዋ የሦስተኛነትን ደረጃ የያዘች ትልቅ ከተማ ነበረች። ትሮባደርስ የተባሉት ገጣሚዎችና አቀንቃኞች ያቆጠቆጡባት ከተማ ነበረች፤ እነዚህ ሰዎች ከደረሷቸው ግጥሞች መካከል አንዳንዶቹ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚጠቅሱ ነበሩ።

በ11ኛውና በ12ኛው መቶ ዘመናት የነበረውን ሃይማኖታዊ ሁኔታ ሲገልጽ ረቪዉ ዲስትዋር ኤ ደ ፊሎዞፊ ረሊዢየዝ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ከዚያ በፊት በነበረው መቶ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በ12ኛው መቶ ዘመንም የቀሳውስቱ ሥነ ምግባር፣ ያካበቱት ከፍተኛ ሀብት፣ ጉቦኝነታቸውና ምግባረ ብልሹነታቸው ተቃውሞ እያስነሳባቸው ነው፤ ከሁሉ ይበልጥ የተተቸው ግን ሀብታቸውና ሥልጣናቸው፣ ሕገ ወጥ ለሆነ ዓላማ ከዓለማዊ ባለ ሥልጣናት ጋር የፈጠሩት ቁርኝትና ለእነሱ ማጎብደዳቸው ነው።”

ተጓዥ ሰባኪዎች

በአውሮፓ ውስጥ በተለይ ደግሞ በደቡባዊ ፈረንሳይና በሰሜናዊ ኢጣሊያ ተቃዋሚዎችና ተጓዥ ሰባኪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ እንዲሄዱ ምክንያት የሆነው ነገር በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተስፋፋው ምግባረ ብልሹነት እንደሆነ ሊቀ ጳጳሳት ሣልሳዊ ኢኖሰንት እንኳ ሳይቀሩ ያውቁ ነበር። ከእነዚህ ሰባኪዎች መካከል አብዛኞቹ ካታራውያን አለዚያም ዎልደንሳውያን ነበሩ። “ልጆቹ ዳቦ ዳቦ ሲሉ ዳቦውን ቆርሳችሁ ልታካፍሏቸው አልፈለጋችሁም” ብለው በመናገር ሊቀ ጳጳሳቱ ሕዝቡን ባለማስተማራቸው ቀሳውስቱን ነቅፈዋቸዋል። ይሁንና ለሕዝቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ማስፋፋት ሲገባቸው ኢኖሰንት የሰጡት ሐሳብ ግን የሚከተለው ነበር፦ “መለኮታዊው ቅዱስ ጽሑፍ የያዘው ሐሳብ በጣም ጥልቀት ያለው በመሆኑ ተራውና ያልተማረው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን አስተዋዮቹና የተማሩትም እንኳ መልእክቱን ለመረዳት የሚያስችል የተሟላ ብቃት የላቸውም።” መጽሐፍ ቅዱስን ከቀሳውስቱ በቀር ማንም ሰው እንዲያነብ አይፈቀድለትም ነበር፤ እንዲሁም በዚያን ጊዜ መጽሐፉን ማንበብ የሚቻለው በላቲን ብቻ ነበር።

ተቃዋሚዎቹ ከቦታ ወደ ቦታ እየሄዱ የሚያካሄዱት ስብከት ግቡን እንዳይመታ ለማድረግ ፍራየርስ ፕሪቸርስ ወይም ዶሚኒካንስ የተባለ ሃይማኖታዊ ማኅበር እንዲመሠረት የቀረበውን ሐሳብ ሊቀ ጳጳሳቱ ደግፈውታል። እነዚህ የፍራየር ማኅበር አባላት ከፍተኛ ሀብት ካካበቱት የካቶሊክ ቀሳውስት በተለየ መልኩ የካቶሊክ እምነትን በደቡባዊ ፈረንሳይ ይገኙ ከነበሩት “መናፍቃን” የመከላከል ተልዕኮ የነበራቸው ተጓዥ ሰባኪዎች ነበሩ። በተጨማሪም ሊቀ ጳጳሳቱ ካታራውያንን አሳምነው ወደ ካቶሊክ ሃይማኖት እንዲመልሷቸው ለማድረግ ወኪሎቻቸውን ልከዋል። እነዚህ ጥረቶች ሊሰምሩ ስላልቻሉና ከወኪሎቻቸው መካከል አንዱ መናፍቅ ነው በተባለ ሰው በመገደሉ ሣልሳዊ ኢኖሰንት በ1209 አልቢጄኒሳውያንን የማጥፋት ዘመቻ እንዲካሄድ ትእዛዝ አስተላለፉ። አልቢ ካታራውያን በብዛት ከሚገኙባቸው ከተሞች አንዷ ነበረች፤ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዘጋቢዎች ካታራውያንን አልቢጄኒሳውያን (በፈረንሳይኛ አልቢዥዋ) ብለው መጥራት መርጠዋል፤ ይህንንም መጠሪያ ዎልደንሳውያንን ጨምሮ በዚያ ክልል የነበሩትን “መናፍቃን” በሙሉ ለመግለጽ ተጠቅመውበታል። (ከታች ያለውን ሣጥን ተመልከት።)

ካታራውያን እነማን ነበሩ?

“ካታር” የሚለው ቃል “ንጹሕ” የሚል ትርጉም ካለው ካታሮስ ከተባለው የግሪክኛ ቃል የመጣ ነው። ካታሪዝም ከ11ኛው እስከ 14ኛው መቶ ዘመን በተለይ በሰሜናዊ ኢጣሊያ በምትገኘው በሎምባርዲና በሎንግዶክ ተሰራጨ። የካታር እምነቶች ዱዋሊዝም (ሰው በቃላት ሊገለጹ የማይችሉ የሁለት ነገሮች ጥምረት ውጤት ነው የሚል እምነት) የተባለውን የሩቅ ምሥራቅ እምነትና ግኖስቲሲዝምን (ቁስ አካል መጥፎ ነው፤ ከዚህ መላቀቅ የሚቻለው መንፈሳዊውን ምሥጢራዊ እውቀት በመረዳት ነው የሚል እምነት) አጣምረው የያዙ ናቸው፤ እነዚህ እምነቶች ወደዚህ አካባቢ የገቡት ከውጪ አገር በመጡ ነጋዴዎችና በሚስዮናውያን ሳይሆን አይቀርም። ዘ ኢንሳይክሎፔዲያ ኦቭ ሪሊጂን ካታር ዱዋሊዝም “ሁለት ኃይሎች” አሉ ብሎ ያምናል ሲል ገልጿል። እነርሱም “አንደኛው ጥሩ ሲሆን መንፈሳዊ የሆነውን ነገር ሁሉ የሚገዛ ነው፤ ሌላው ደግሞ ክፉ ሲሆን የሰውን አካል ጨምሮ ቁሳዊውን ዓለም የሚቆጣጠር ነው።” ካታራውያን የማይሻር የጥፋት ፍርድ የተፈረደበትን ቁሳዊውን ዓለም የፈጠረው ሰይጣን ነው ብለው ያምናሉ። ተስፋቸው ከዚህ ክፉ ቁሳዊ ዓለም መዳን ነው።

ካታራውያን ፍጹማንና አማኞች ተብለው በሁለት ይከፈሉ ነበር። ፍጹማን የሚባሉት ኮንሶላሜንተም የሚባል የመንፈሳዊ ጥምቀት ሥነ ሥርዓት ይፈጽማሉ። ይህ አንድ ሰው ለአንድ ዓመት ከተፈተነ በኋላ በራሱ ላይ እጅን በመጫን የሚፈጸም ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው። ይህ ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሚከናወነው ግለሰቡን ከሰይጣን አገዛዝ ነፃ ለማውጣት፣ ከማንኛውም ኃጢአት ለማንጻትና በመንፈስ ቅዱስ እንዲሞላ ለማድረግ ታስቦ ነው። ይህ ሥነ ሥርዓት የአማኞቹ አገልጋዮች ሆነው የሚሠሩትና በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታዩ አነስተኛ የሆኑት ምርጥ ሰዎች የሚጠሩበትን “ፍጹም” የሚል መጠሪያ ያሰጠዋል። ፍጹማን የሚባሉት ያረክሳሉ ከሚባሉ ነገሮች ለመራቅ፣ ድንግል ሆነውና በድህነት ተቆራምደው ለመኖር መሐላ ይፈጽማሉ። ካታራውያን የመጀመሪያው ኃጢአት የጾታ ግንኙነት ነው ብለው ስለሚያምኑ ፍጹም የሚለውን ስያሜ ያገኘ አንድ ሰው ያገባ ከሆነ የትዳር ጓደኛውን መፍታት ይኖርበታል።

አማኞች የሚባሉት የባሕታዊ ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች ባይሆኑም የካታርን ትምህርቶች የተቀበሉ ግለሰቦች ናቸው። ፍጹማን በሚባሉት ፊት በአክብሮት ስሜት ተንበርክኮ ሜሊዮራሜንተም የተባለውን ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት በመፈጸም አማኙ ኃጢአቱ ይቅር እንዲባልለትና ቡራኬ እንዲያገኝ ይጠይቃል። አማኞቹ የተለመደውን ዓይነት ኑሮ መኖር እንዲችሉ ፍጹማን ከሚባሉት ጋር አንድ ኮንቬኔንዛ ወይም ስምምነት ይፈራረማሉ፤ በስምምነቱ መሠረት አማኞቹ ሲሞቱ ፍጹማን የሚባሉት መንፈሳዊውን ጥምቀት ወይም ኮንሶላሜንተም ይፈጽሙላቸዋል።

ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው አመለካከት

ምንም እንኳ ካታራውያን ከመጽሐፍ ቅዱስ ብዙ ሐሳቦችን የሚጠቅሱ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስን የምሳሌያዊ አባባሎችና የአፈ ታሪኮች ምንጭ አድርገው ይመለከቱታል። ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች መካከል አብዛኛው ከዲያብሎስ የመነጨ ነው ብለው ያምናሉ። ከግሪክ ቅዱሳን ጽሑፎች መካከል ሥጋንና መንፈስን እያወዳደሩ የሚናገሩትን የመሳሰሉ አንዳንድ ክፍሎችን ሰው በቃላት ሊገለጹ የማይችሉ የሁለት ነገሮች ጥምረት ውጤት ነው የሚለውን ፍልስፍናቸውን ለመደገፍ ይጠቀሙባቸዋል። የጌታን ጸሎት ሲጸልዩ “የዕለት እንጀራችንን” በሚለው ፋንታ “ከሥጋዊው መብል የላቀውን እንጀራችንን” (“መንፈሳዊ እንጀራችንን” ማለት ነው) ስጠን ብለው ይጸልያሉ፤ በእነሱ አመለካከት ሥጋዊ ምግብ መጥፎ ቢሆንም እንኳ የግድ አስፈላጊ የሆነ ነገር ነው።

ብዙ የካታር ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በቀጥታ የሚጋጩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ነፍስ አትሞትም በሚለው እምነትና አንድ ሰው ከሞተ በኋላ እንደገና በሌላ መልክ ሕያው ሆኖ ይወለዳል በሚለው እምነት (በሪኢንካርኔሽን) ያምኑ ነበር። (ከመክብብ 9:5, 10 እና ከሕዝቅኤል 18:4, 20 ጋር አወዳድር።) እምነቶቻቸውም በአዋልድ ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ይሁን እንጂ ካታራውያን የተወሰኑ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎችን በአካባቢው በስፋት በሚነገረው ቋንቋ በመተርጎማቸው በመካከለኛው ዘመን በተወሰነ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ እንዲታወቅ አድርገዋል።

ክርስቲያኖች አይደሉም

ፍጹማን የሚባሉት ትክክለኛ የሐዋርያት ወራሾች እኛ ነን ብለው ያስቡ ነበር፤ በመሆኑም ራሳቸውን “ክርስቲያኖች” ብለው ይጠሩ ነበር፤ ይህንንም “እውነተኛ” ወይም “ጥሩ” የሚል ቃል በመጨመር ጠበቅ አድርገው ይገልጹት ነበር። ይሁን እንጂ እውነቱን ለመናገር ከሆነ ብዙዎቹ የካታር እምነቶች ለክርስትና ባዕድ ናቸው። ምንም እንኳ ካታራውያን ኢየሱስ የአምላክ ልጅ ነው ብለው ቢያምኑም ሥጋ ለብሶ መምጣቱንና የከፈለው መሥዋዕት ከኃጢአት የሚቤዥ መሆኑን አይቀበሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ሥጋንና ዓለምን በማውገዝ የሚሰጠውን ሐሳብ በተሳሳተ መንገድ በመተርጎም ቁስ አካል ሁሉ የመጣው ከክፉው ነው ብለው ያምናሉ። ስለዚህ ኢየሱስ መንፈሳዊ አካል ብቻ እንደነበረውና በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ሥጋዊ አካል ያለው መስሎ ይታይ እንደነበረ አድርገው ያስቡ ነበር። ልክ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ከሃዲዎች ካታራውያን “ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የማያምኑ ናቸው።”—2 ዮሐንስ 7

ኤም ዲ ላምበርት ሜዲቫል ኸሬሲ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ካታሪዝም “ክርስቲያናዊውን የሥነ ምግባር መሠረታዊ ሥርዓት ግዴታ በሆነው የብሕትውና ኑሮ ተክቶታል፤ . . . [የክርስቶስ ሞት] ያለውን የማዳን ኃይል በመካድ በኢየሱስ ሞት ከኃጢአት መንጻት ይቻላል የሚለውን እምነት አጣጥሎታል።” ላምበርት “ፍጹማን የሚባሉት በሩቅ ምሥራቅ ከሚገኙት ባሕታዊ አስተማሪዎች፣ ከቡድሂስት መነኩሴዎችና በቻይና ወይም በህንድ ከሚገኙት ከቦታ ወደ ቦታ የሚሄዱ የሂንዱ ባሕታውያን፣ ኦርፈስ የተባለው ግሪካዊ ባለቅኔ ያስተማራቸውን መሠረተ ትምህርቶች ጠንቅቀው ከሚያውቁት ጠበብቶች ወይም ከግኖስቲሲዝም አስተማሪዎች ጋር ያላቸውን ተመሳሳይነት” አጥንተዋል። በካታር እምነት መሠረት መዳን ሊገኝ የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሳይሆን በኮንሶላሜንተም ወይም በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅ ነው። በዚህ መንገድ የነጹትን ሰዎች ሞት ከቁስ አካል ነፃ ያወጣቸዋል።

የጭፍጨፋ ዘመቻ

ቀሳውስቱ ከሚገባቸው በላይ አልፈው እንዲሟላላቸው በሚጠይቁት ነገርና በጣም በተስፋፋው የሥነ ምግባር ውድቀት የተሰላቸው ተራው ሕዝብ በካታራውያን አኗኗር ስሜቱ ተማረከ። ፍጹማን ተብለው የሚጠሩት የካቶሊክን ቤተ ክርስቲያንንና መሪዎቿን በራእይ 3:9 እና 17:5 ላይ የሚገኙትን ሐረጎች በመጠቀም የ“ሰይጣን ማኅበር” እና “የጋለሞታዎች . . . እናት” ብለው ይጠሯቸው ነበር። ካታሪዝም እየተስፋፋ በመሄድ በደቡባዊ ፈረንሳይ ይገኝ የነበረውን ቤተ ክርስቲያን መቀናቀን ጀመረ። ሊቀ ጳጳሳት ሣልሳዊ ኢኖሰንት የሰጡት ምላሽ አልቢጄኒሲያን ክሩሴድ የተባለውን የማጥፋት ዘመቻ ማስጀመርና አስፈላጊውን ወጪ መሸፈን ነበር፤ ይህም ሕዝበ ክርስትና ክርስቲያኖች ነን በሚሉ ሰዎች ላይ ያደራጀችው የመጀመሪያው የማጥፋት ዘመቻ ነበር።

ሊቀ ጳጳሳቱ ደብዳቤዎችንና ወኪሎቻቸውን በመላክ በአውሮፓ ውስጥ ያሉትን የካቶሊክ ነገሥታት፣ መኳንንት፣ መሳፍንትና የጦር ሹማምንት ቁጣ አነሳሱ። “ማንኛውንም መንገድ በመጠቀም” ይህን መናፍቅነት ለማጥፋት የሚዋጉ ሁሉ የኃጢአት ይቅርታና በሎንግዶክ ውስጥ ያለውን ሀብት እንደሚያገኙ ቃል ገቡ። ያቀረቡት ጥሪ ምላሽ አልተነፈገውም። በካቶሊክ ጳጳሳትና መነኩሴዎች መሪነት ከተለያዩ ቦታዎች የተውጣጡ ዘማቾችን ያቀፈ ሠራዊት ከሰሜናዊ ፈረንሳይ፣ ከፍላንደርስና ከጀርመን ተነስቶ በሮሆን ሸለቆ አድርጎ ወደ ደቡብ ተመመ።

በቤዚዬ የደረሰው ጥፋት ሎንግዶክን በእሳት ነበልባል እንድትለበለብና በደም ጎርፍ እንድትጥለቀለቅ ያደረገው የድል አድራጊነት ጦርነት መጀመሩን የሚያመለክት ነበር። አልቢ፣ ካርካሶን፣ ካስትር፣ ፍዎ፣ ናርቦን፣ ቴርምና ቱሉዝ ሁሉም ደም በተጠሙት ዘማቾች እጅ ወደቁ። እንደ ካሴ፣ ሚነርቭና ሎቩር ባሉት ካታራውያን በብዛት በሚገኙባቸው ቦታዎች ፍጹማን ከሚባሉት መካከል በመቶዎች የሚቆጠሩት በቆመ ግንድ ላይ ታስረው በእሳት ተቃጥለዋል። መነኩሴውና ታሪክ ዘጋቢው ፒየር ዴ ቮ ደ ሴርኔ እንዳለው ከሆነ ዘማቾቹ ‘ፍጹማኑን ከነሕይወታቸው በእሳት ሲያቃጥሏቸው ልባቸው በደስታ ይፈነድቅ ነበር።’ ሎንግዶክ ለ20 ዓመታት በተካሄደ ብጥብጥ እንዳልነበረች ከሆነች በኋላ በ1229 በፈረንሳይ የዘውድ አገዛዝ ሥር ወደቀች። ሆኖም ጭፍጨፋው ገና አላበቃም ነበር።

ኢንኩዊዚሽኑ የማጥፋት ዘመቻውን ዳር አደረሰው

በ1231 ሊቀ ጳጳሳት ግሪጎሪ ዘጠነኛ ለትጥቅ ትግሉ እገዛ ለማድረግ በጳጳሳት የሚመራ ኢንኩዊዚሽን እንዲካሄድ አደረጉ።a ይህ ኢንኩዊዚሽን ይካሄድ የነበረው በመጀመሪያ በመንቀፍና በማስገደድ ነበር፤ በኋላ ደግሞ በተለያየ መንገድ በማሠቃየት ነበር። ዓላማው ከሰይፍ ያመለጡትን ለማጥፋት ነበር። በአብዛኛው የዶሚኒካንና የፍራንሲስካን ማኅበር አባላት የሆኑት የኢንኩዊዚሽኑ ዳኞች ከሊቀ ጳጳሳቱ በቀር ማንም ለምን እንዲህ አደረግህ ብሎ የሚጠይቃቸው አልነበረም። ለመናፍቅነት የሚበየነው ሕጋዊው ፍርድ ግለሰቡ በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት የሚያደርግ ነበር። ኢንኩዊዚሽኑን ያካሄዱት ሰዎች ያሳዩት የነበረው ይህን የመሰለ የአክራሪነት መንፈስና ጭካኔ የተሞላበት ተግባር ዓመፅ ካስነሳባቸው ቦታዎች መካከል አልቢና ቱሉዝ ይገኙበታል። በአቪንዮኔ ኢንኩዊዚሽኑን ያካሄደው ኮሚቴ አባላት በሙሉ ተጨፍጭፈዋል።

ተሰድደው በሞንትሴጎር ተራራ ተሸሽገው የነበሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፍጹማን የሚባሉት ሰዎች በ1244 እጃቸውን መስጠታቸው ካታሪዝም ያበቃለት መሆኑን የሚጠቁም ነበር። ወደ 200 የሚጠጉ ወንዶችና ሴቶች በቆመ ግንድ ላይ ታስረው በእሳት ተቃጥለው ሞቱ። ለብዙ ዓመታት ይህ ኢንኩዊዚሽን የተቀሩትን ካታራውያን የገቡበት ገብቶ እያደነ አጠፋቸው። የመጨረሻው ካታር በ1330 በሎንግዶክ በቆመ ግንድ ላይ ታስሮ በእሳት እንደተቃጠለ ተዘግቧል። ሜዲቫል ኸሬሲ የተባለው መጽሐፍ “የካታሪዝም ውድቀት ኢንኩዊዚሽኑ ያስመዘገበው ከሁሉ ጎልቶ የሚታይ ታላቅ ክንውን ነበር” ሲል ገልጿል።

ካታራውያን እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዳልነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን በመንቀፋቸው የተነሳ ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ መጨፍጨፋቸው ተገቢ ነውን? ያሳደዷቸውና በግፍ የገደሏቸው ካቶሊኮች አምላክንና ክርስቶስን ከማቃለላቸውም በላይ እነዚህን በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ሲያሠቃዩና በግፍ ሲጨፈጭፉ እውነተኛ ክርስትናን በሐሰት ወክለዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በመካከለኛው መቶ ዘመን ስለተካሄደው ኢንኩዊዚሽን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው የሚያዝያ 22, 1986 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት ከገጽ 20–3 ላይ የሚገኘውን “አሠቃቂው ኢንኩዊዚሽን” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ዎልደንሳውያን

በ12ኛው መቶ ዘመን እዘአ መጨረሻ አካባቢ ፒየር ቫልደስ ወይም ፒተር ዎልዶ የተባለ አንድ ሀብታም የልዮንስ ነጋዴ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በደቡብና በደቡብ ምሥራቅ ፈረንሳይ በስፋት በሚነገረው የፕሮቬኒካል ቋንቋ የተለያዩ የአነጋገር ዘይቤዎች ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲተረጎሙ አስፈላጊውን የገንዘብ ወጪ ሸፍኗል። ቅን ልብ የነበረው ይህ ካቶሊክ ሥራውን ተወና አብዛኛውን ጊዜውን ለወንጌሉ ስብከት ለማዋል ወሰነ። በቀሳውስቱ ምግባረ ብልሹነት ከፍተኛ ጥላቻ ያደረባቸው ብዙ ሌሎች ካቶሊኮችም እርሱን ተከትለው ተጓዥ ሰባኪዎች ሆኑ።

ሊቀ ጳጳሳቱን በመጎትጎት በሕዝብ ፊት የሚሰጠውን ምሥክርነት ያሳገዱበት የአካባቢው ቀሳውስት ብዙም ሳይቆይ ዎልዶን ክፉኛ ተቃወሙት። “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” ብሎ እንደመለሰላቸው ተዘግቧል። (ከሥራ 5:29 ጋር አወዳድር።) ዎልዶ በያዘው አቋም በመግፋቱ ከቤተ ክርስቲያኒቱ እንዲገለል ተደረገ። ዎልደንሳውያን ወይም የልዮንስ ድሆች የሚባሉት ተከታዮቹ ሁለት ሁለት እየሆኑ በየሰዉ ቤት በመስበክ የእሱን ምሳሌ ለመከተል ቅንዓት የተሞላበት ጥረት ያደርጉ ነበር። በዚህም የተነሳ ትምህርቶቻቸው በከፍተኛ ፍጥነት በደቡብ፣ በምሥራቅና በአንዳንድ የሰሜን ፈረንሳይ ክፍሎች እንዲሁም በሰሜናዊ ኢጣሊያ ሊሰራጩ ችለዋል።

የጥንቱ ክርስትና እምነቶችና ልማዶች እንደገና እንዲያንሰራሩ ለማድረግ ቆርጠው የተነሱ ነበሩ። አጥብቀው ካወገዟቸው ትምህርቶች መካከል መንጽሔ፣ ፍታት፣ የማርያም አምልኮ፣ ወደ “ቅዱሳን” የሚቀርቡ ጸሎቶች፣ ለመስቀል አምልኮታዊ ክብር መስጠት፣ የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት መደረግ አለባቸው የሚባሉት ነገሮች፣ ሥርዓተ ቅዳሴና የሕፃናት ጥምቀት ይገኙበታል።b

የዎልደንሳውያን ትምህርቶች ብዙውን ጊዜ ከእነርሱ ጋር አንድ መስለው ግራ ከሚያጋቡት ከካታራውያን ክርስቲያናዊ ያልሆኑ የዱዋሊዝም ትምህርቶች በእጅጉ የተለዩ ናቸው። ይህ ግራ መጋባት የተፈጠረው ሆን ብለው ዎልደንሳውያን የሚሰብኩትን ትምህርት ከአልቢጄኒሳውያን ወይም ከካታራውያን ትምህርቶች ጋር ለማመሳሰል ጥረት ባደረጉት የካቶሊክ እምነት ተከታይ በሆኑ ተቃዋሚዎች ሳቢያ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

b * ስለ ዎልደንሳውያን ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በነሐሴ 1, 1981 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 12–15 ላይ የወጣውን “ዎልደንሳውያን መናፍቃን ናቸው ወይስ እውነት ፈላጊዎች?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የማጥፋት ዘመቻውን ያካሄዱት ሰዎች 20,000 ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በጨፈጨፉባት በቤዚዬ ሰባት ሺህ ሰዎች የሞቱት በሴይንት ሜሪ ማግዳሊን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነበር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ