“ወደፈለገበት አቅጣጫ ቢነፍስ ለውጥ የለውም”
“የሚደርስበትን ወደብ ለማያውቅ ሰው ነፋሱ ወደፈለገበት አቅጣጫ ቢነፍስ ለእርሱ ለውጥ የለውም።” እነዚህን ቃላት የተናገረው የመጀመሪያው መቶ ዘመን የሮማ ፈላስፋ ሉክዩስ አኒዩስ ሴኔካ ሲሆን ሕይወት ዓላማ እንዲኖረው ግብ አስፈላጊ ነው የሚለውን አንጋፋ እውነት የሚያረጋግጡ ቃላት ናቸው።
ነገር ግን የአብዛኞቹ ሰዎች ሕይወት ዓላማ የለውም። ብዙዎች በዕለት ተዕለት ኑሮ የሚያጋጥሟቸውን አለቶችና አዙሪቶችን በመሸሽ ብቻ ይረካሉ። አንድ የተወሰነ አቋም ስለሌላቸው “በነፋስ እየተገፋ አንድ ጊዜ ወደፊት ወዲያው ደግሞ ወደ ኋላ እንደሚመለስ” ማዕበል ሆነዋል። (ያዕቆብ 1:6 “ፊሊፕስ”) ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች “ነፋሱ ወደፈለገበት አቅጣጫ ቢነፍስ ለውጥ የለውም።”
መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች በሞዴልነት ሊያገለግሉ የሚችሉ ከፊታቸው ግብ ያስቀመጡ ሰዎችን ምሳሌ ያቀርብልናል። ሙሴ “ብድራቱን ትኩር ብሎ ተመልክቶአል።” (ዕብራውያን 11:26) ጳውሎስ “ሽልማቴንም ለማግኘት በፊቴ ወዳለው ግብ እሮጣለሁ” በማለት የጻፈ ሲሆን “ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ሊኖረን ይገባል” በማለት መሰል አማኞችን አበረታቷቸዋል።—ፊልጵስዩስ 3:14, 15 የ1980 ትርጉም
ዓይናችንን መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጣቸው ተስፋዎች ላይ በማተኮር ከፊታቸው ግብ የማስቀመጥ ልምድ ያላቸውን እነዚህን የመሳሰሉትን ሰዎች እምነት ልንኮርጅ እንችላለን።—ከዕብራውያን 13:7 ጋር አወዳድር።