የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 10/1 ገጽ 29-31
  • ሲንጋፖር የአምልኮ ነፃነት ተጋፋች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሲንጋፖር የአምልኮ ነፃነት ተጋፋች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • በብሔራዊ ኅብረትና አንድነት ላይ የሚፈጥሩት ስጋት የለም
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 10/1 ገጽ 29-31

ሲንጋፖር የአምልኮ ነፃነት ተጋፋች

የካቲት 24, 1995 ምሽት ላይ በሲንጋፖር ከተማ ውስጥ አራት ቤቶች በፖሊሶች ተከበቡ። በጠቅላላ 69 የሚሆኑ ሰዎች ታሰሩ።a ከእነዚህ መካከል አንዲት የ71 ዓመት ሴትና ሁለት የ15 ዓመት ልጃገረዶች ይገኙባቸዋል። ይህ የሆነው ለምን ነበር? ወንጀል ወይም ፖለቲካዊ ሴራ ፈጽመው ነውን? አይደለም። አንዳቸውም ቢሆኑ በትንሹም እንኳ ቢሆን አደገኛ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ወይም የሕዝቡን ሰላም የሚያደፈርስ ነው ሊባል የሚችል ነገር አልፈጸሙም። እንደነሱው የሲንጋፖር ዜጎች የሆኑትን ሰዎች የሥነ ምግባር ሥርዓቶችና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር አላደረጉም። ያም ሆኖ ግን ፖሊሶቹ አራቱን ቤቶች በደንብ ከፈተሹ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናትና አንድ ላይ ሆነው ለመጨዋወት የተሰበሰቡትን 69 ሰዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው። እዚያው ታስረው አደሩ፣ የፖሊስ ምርመራ ተደረገባቸው፣ አሻራቸው ተወሰደ፣ ፎቶግራፍም አነሷቸው፤ አዎን፣ ልክ እንደ ወንጀለኞች አስጨነቋቸው! አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ሥር 18 ሰዓታት ያሳለፉ ሲሆን በዚህ ጊዜ ሕግ ዐዋቂዎችን ማማከር እንዳይችሉ ተከልክለው ነበር፤ ሌላው ቀርቶ የት እንዳሉ ለቤተሰብ አባሎቻቸው ስልክ ደውለው ለመንገር እንኳ አልተፈቀደላቸውም ነበር። ይህ ፈጣን እርምጃ እነዚህን ሰላማዊና ሕግ አክባሪ ዜጎች ምን ያህል ስሜታቸውን እንደሚጎዳው ማንም ሰው መገመት ይችላል!

ይህ ድርጊት በአስፈሪው የናዚ ጀርመን ዘመንና በሶቭየት ኅብረትና በምሥራቅ አውሮፓ በነበረው አረመኔያዊ የኮሙኒስት ዘመን የነበሩትን ሁኔታዎች ያስታውሰናል። ሲንጋፖርን የሚጎበኝ ሰው በዚያች ንጹሕና የበለጸገች ዘመናዊ ከተማ ውስጥ ይህን የመሰለ ሁኔታ ይኖራል ብሎ አይገምትም። ሲንጋፖር በ20ኛው መቶ ዘመን በጣም አስደናቂ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት የታየባት አገር ለመባል በቅታለች። ለዜጎቹ የመናገር፣ የሃይማኖትና የመሰብሰብ ነፃነትን ጨምሮ መሠረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ዋስትና የሚሰጠውን ሕገ መንግሥት የያዘ ዲሞክራሲ ታውጆአል።

ሆኖም በየካቲት ወር የታሰሩት ሰዎች ይህ ድርጊት የተፈጸመባቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናትና በክርስቲያናዊ የወዳጅነት መንፈስ ለመተናነጽ አንድ ላይ የሚሰበሰቡ የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆኑ ብቻ ነው። የተመሠረተባቸው ክስ “ሕጋዊ ያልሆነ ማኅበር በሚያካሄደው ስብሰባ ላይ መገኘት” የሚል ነው።

እርግጥ የይሖዋ ምሥክሮች በሲንጋፖር ሕጋዊ ዕውቅና የተነፈጋቸው ከሕጋዊው መዝገብ ላይ ከተሰረዙበት ከ1972 ጀምሮ ነው፤ በዚያ ጊዜ በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የሚታተሙትን መጽሐፍ ቅዱሶች ጨምሮ ጽሑፎቻቸው ታገዱ። እርምጃው የተወሰደባቸው ያለ ምክንያት መሆኑን መግለጽ የሚችሉበት እድል አልተሰጣቸውም። በቅርቡ፣ የተከለከሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ይዛችሁ ተገኝታችኋል ተብለው የካቲት 1994 ላይ ተወንጅለው የነበሩት አራት ምሥክሮች ጉዳይ በሲንጋፖር ፍርድ ቤቶች ይታይ በነበረበት ወቅት መንግሥት የወሰደው ይህ የአድሎአዊነት እርምጃ ሕጋዊ አይደለም የሚል ተቃውሞ ገጥሞት ነበር። የተፈረደባቸውን ፍርድ በመቃወም የቀረበው ይግባኝ ነሐሴ 1994 ተሰማና ወዲያውኑ ውድቅ ተደረገ። የከፍተኛው ፍርድ ቤት የመሐል ዳኛ የሆኑት ዮንግ ፐንግ ሆው በሚቀጥለው ወር ላይ መግለጫ ሰጡ። ሃይማኖታዊ ነፃነትን የሚጻረር ነገር እንዳልተፈጸመና የይሖዋ ምሥክሮች በወታደራዊ አገልግሎት የማይሳተፉ መሆናቸው ለብሔራዊ ደህንነት አደጋ ስለሚፈጥር የተሰጠው ፍርድ ተገቢ ነው ሲሉ ገለጹ። የካቲት 17, 1995 አራቱ ምሥክሮች ይህን የተሳሳተ ውሳኔ በመቃወም ለሲንጋፖር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ይግባኝ ለማለት ፈቃድ ጠየቁ። የጠየቁት ፈቃድ ተቀባይነት አላገኘም።

በመንግሥት ሥር ያለው የሲንጋፖር ጋዜጣ ይህን የመጨረሻ ውሳኔ በተመለከተ በስፋት አትቷል። ይህ የፍርድ ቤት ውሳኔና የውሳኔው ይፋ መሆን ከዚያ በኋላ የተፈጸሙትን ነገሮች ከወዲሁ የሚጠቁም ነበር። ይግባኝ በተባለ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ስልሳ ዘጠኙ ምሥክሮች ተያዙ። ከእነዚህ መካከል ይገኙ በነበሩትና የብሪታንያ፣ የፈረንሳይና የሉክሰምበርግ ዜጎች በሆኑት አራት ምሥክሮች ላይ ተመሥርቶ የነበረው ክስ በኋላ ተነስቷል። ይሁን እንጂ በእነዚህም ምሥክሮች ላይ ቢሆን የደረሰው ነገር አስደንጋጭ ነበር። ከእነርሱ መካከል አንዱ ከሚስቱ ጋር በሲንጋፖር ውስጥ በሥራው ዓለም ተሰማርቶ ለብዙ ዓመታት ኖሯል። እነዚህ ባልና ሚስት ከሥራቸውና ተከራይተው ይኖሩበት ከነበረው ቤት እንዲወጡና ብዙ የቅርብ ጓደኞቻቸውን ተለይተው እንዲሄዱ ተደርጓል።

የተቀሩት 63 ሰዎች የአንድ የታገደ ማኅበር አባላት ናቸው ተብለው ተከሰሱ፤ እንዲሁም አንዳንዶቹ የተከለከሉ ጽሑፎችም ይዘው ተገኝተዋል የሚል ክስ ቀረበባቸው። እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ እስራት አለዚያም 3,000 የሲንጋፖር ዶላር (2,100 የአሜሪካ ዶላር) መክፈል ወይም ደግሞ ሁለቱም ዓይነት መቀጮ ይጠብቃቸው ነበር። ሁለቱ የ15 ዓመት ልጃገረዶች ደግሞ በወጣት ጥፋተኞች ፍርድ ቤት ፊት ቀርበዋል።

በብሔራዊ ኅብረትና አንድነት ላይ የሚፈጥሩት ስጋት የለም

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በሚኖሩባቸው ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በጨዋነታቸው፣ በሐቀኝነታቸውና በሕግ አክባሪነታቸው የታወቁ ሰዎች ናቸው። በማንኛውም ዓይነት ሴራም ሆነ ፀረ መንግሥት እንቅስቃሴ ለመካፈል አሻፈረኝ በማለት በሚያሳዩት የጸና አቋም ይታወቃሉ፤ ይህ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ድርጊት ሊያስወግዳቸው ወይም ከሃይማኖታቸው እንዲገለሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። በእርግጥም የሲንጋፖር መንግሥት በእነርሱ ላይ ስጋት እንዲያድርበት የሚያደርግ ምንም ነገር የለም። በሲንጋፖር ብሔራዊ ደህንነት ላይ ወይም በብሔራዊ ኅብረትና አንድነቷ ላይ ምንም የሚፈጥሩት ስጋት የለም። (ሮሜ 13:1–7) ይህ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዘዳንት ሚልተን ጂ ሄንሽል መጋቢት 21, 1995 ለሲንጋፖሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ለጎ ቾክ ቶንግ በጻፈው ደብዳቤ ላይ በግልጽ ሰፍሯል። ይህ ደብዳቤ አንባቢዎቻችን ሊያነቡት እንዲችሉ በዚሁ ጽሑፍ ላይ ወጥቷል።

በንግዱ ዓለም፣ በመንግሥትና በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ነፃነትን የሚሹ ሰዎች ይህ ሁኔታ በሲንጋፖር ውስጥ ምን መልክ እየያዘ እንደሚሄድ ለማየት በጉጉት ይከታተላሉ። የሲንጋፖር መንግሥት የራሱ ሕገ መንግሥትና የዓለም አቀፍ ብሔራት ማኅበረሰብ ከሚያራምዷቸው መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነት ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስድ ይሆን? በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በሲንጋፖር የሚገኙት የአምልኮ አጋሮቻቸው የሚገኙበት ሁኔታ በጣም እንደሚያሳስባቸው ጥርጥር የለውም። በጸሎታቸው ያስቧቸዋል፤ “ይሖዋ ፍትሕን ይወድዳል፤ ከእሱ ጎን በታማኝነት የቆሙትን አገልጋዮቹንም አይተዋቸውም” የሚሉትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የማጽናኛ ቃላትም አይዘነጓቸውም።—መዝሙር 37:28 አዓት

[የግርጌ ማስታወሻ]

a እነዚህ 69 ምሥክሮች ከታሰሩ በኋላ በነበሩት ወራት ሌሎች 11 ምሥክሮች ተይዘው ታሰሩና ሕጋዊ ያልሆነ ጽሑፍ ይዛችሁ ተገኝታችኋል የሚል ክስ ቀረበባቸው።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መጋቢት 21, 1995

ጎ ቾክ ቶንግ

ጠቅላይ ሚኒስትር

ኢስታና አኔክሴ

ሲንጋፖር 0923

የሲንጋፖር ሪፑብሊክ

ሊ ኩዋን ዩ

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ

ተቀዳሚ ሚኒስትር

460 አሌክሳንድራ ጎዳና

37–00 ፒ ኤስ ኤ ሕንፃ

ሲንጋፖር 0511

የሲንጋፖር ሪፑብሊክ

ክቡር ሆይ፦

በቅርቡ የካቲት 25, 1995 ቀን ከሲንጋፖር የተላለፈው የሮይተር ሪፖርት በጣም የሚረብሽ ነበር። ሪፖርቱ የይሖዋ ምሥክሮች እያካሄዷቸው የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስብሰባዎች በፖሊሶች እንደተቋረጡና 69 ሰዎች እንደታሰሩ ዘግቧል። ይህ ሪፖርት የዓለም ሕዝብ ትኩረቱን ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ሥራቸውና ጽሑፎቻቸው በታገደበት በሲንጋፖር በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታ ላይ እንዲያሳርፍ አድርጎታል።

የተሟላ ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በይፋ የሚንቀሳቀስ አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት የዲሞክራሲን መሠረታዊ ሥርዓቶች በምታራምደው አገር በሲንጋፖር ውስጥ ለምን መታገድ እንዳስፈለገው ለመረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። የሲንጋፖር ሕገ መንግሥት ለዜጎቹ የአምልኮ ነፃነት ዋስትና የሚሰጥ መሆኑ ሲታይ ደግሞ ሁኔታው ይበልጥ ግራ ያጋባል።

የይሖዋ ምሥክሮች በየትም ቦታ ብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥል ችግር ፈጥረው አያውቁም። እንዲያውም በዓለም ዙሪያ ሰላማውያን፣ ተግተው የሚሠሩ፣ ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸውና ሕግ አክባሪዎች ናቸው የሚል ስም አትርፈዋል። እነዚህን ባሕርያት ደግሞ እርስዎም በአገርዎ እንደሚያስፋፉ እርግጠኛ ነኝ።

እርግጥ ነው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ክርስቲያኖችን የሚመለከቱ መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ ስለሚከተሉ አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች አቋም የተሳሳተ ትርጉም ይሰጠዋል። ይሁን እንጂ የክርስትና መሥራች የሆነውም ሰው በወቅቱ የነበረው መንግሥት ማለትም የ“ቄሳር” ተቃዋሚ እንደሆነ ተደርጎ በተሳሳተ መንገድ ተወንጅሎ አልነበረምን? የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስንና የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ምሳሌ ይከተላሉ። የሚኖሩበትን አገር መንግሥት ያከብራሉ፤ ቀረጥ ይከፍላሉ፤ እንዲሁም ጥሩ ሥነ ምግባሮችን ያስፋፋሉ። ትጉዎችና ንጹሕ ዜጎች ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች በየትኛውም አገር በማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ ሴራ ተሳትፈው አያውቁም። የይሖዋ ምሥክሮች በሲንጋፖር ውስጥ መኖራቸው በአገርዎ ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ምንም የሚፈጥሩት ስጋት እንደሌለ ላረጋግጥልዎ እወዳለሁ።

መንግሥትዎ በሲንጋፖር በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የወሰደውን የኃይል እርምጃ በቅርቡ የመገናኛ ብዙሃን በዘገቧቸው ሪፖርቶች አማካኝነት ብዙዎች ሰምተውታል። በተለይ ደግሞ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን 12 ሚልዮን የእምነት አጋሮቻቸውን በጣም የሚያሳስባቸው ጉዳይ ሆኗል። ባለዎት ሥልጣን ተጠቅመው ለችግሩ እልባት እንዲፈጥሩለትና በአገርዎ ውስጥ ለሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች በሕገ መንግሥቱ ላይ የጸደቀውን የአምልኮና የሕሊና ነፃነት ይሰጧቸው ዘንድ እለምንዎታለሁ።

ከይሖዋ ምሥክሮች ወኪሎች ጋር የሚደረግ ግልጽ የሆነ ውይይት ስለ ድርጅታችንና ስለ ሥራችን ያለውን ማንኛውንም የተሳሳተ አመለካከት ለመቅረፍ እንደሚረዳና የሲንጋፖር መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ምንም ዓይነት ስጋት ሊያድርበት እንደማይገባ ሊያረጋግጥልዎ እንደሚችል አምናለሁ። እንዲህ ዓይነቱን ስብሰባ ለማመቻቸት ፈቃደኛ ነኝ።

ምላሹን በጉጉት እጠባበቃለሁ።

አክባሪዎ

ሚልተን ጂ ሄንሽል

ፕሬዘዳንት

[ምንጭ]

Nik Wheeler/H. Armstrong Roberts

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ