በዘመናዊቷ አቴንስ ውስጥ ለሚገኙ ሁሉም ዓይነት ሰዎች መመሥከር
ጳውሎስ በ50 እዘአ ገደማ አቴንስን ሲጎበኝ ምንም እንኳ ከተማዋ ጥንት የነበራትን ክብር ብታጣም እስከዚያን ጊዜ ድረስ ከፍተኛ የንግድ ማዕከል ነበረች። አንድ ታሪካዊ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፦ “[አቴንስ] የግሪክ መንፈሳዊና ሥነ ጥበባዊ መናኸሪያ እንዲሁም በዚያን ዘመን የነበሩ የተማሩና ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ሊጎበኟት የሚጓጉ ከተማ መሆኗን ቀጥላለች።”
ጳውሎስ እዚያ በነበረበት ጊዜ ለአይሁዶች፣ አረማዊ ለሆኑት አቴናውያንና ከተለያየ ቦታ ለመጡ ሰዎች የመመሥከር አጋጣሚ ሳይከፈትለት አልቀረም። ንቁና ጥሩ ችሎታ ያለው አስተማሪ ስለሆነ አንድ ጊዜ በሰጠው ንግግር ላይ አምላክ ‘ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ’ እንደሚሰጥ፣ ‘የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ እንደፈጠረ’ እንዲሁም ‘በዓለሙ ላይ ስለሚፈርድ በየትም ቦታ ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ መግባት እንዳለባቸው’ ገልጿል።—ሥራ 17:25–31
የተለያዩ ሰዎች የሚኖሩበት ክልል
ቅርብ በሆኑት አሥርተ ዓመታትም ሰዎች ከተለያዩ ቦታዎቸ ወደ አቴንስ ከተማ እየጎረፉ ነው። የውጪ አገር ዲፕሎማቶችና ወታደሮች ተልዕኳቸውን ለማከናወን ወደዚች ከተማ መጥተዋል። ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አቴንስ ውስጥ ይኖራሉ። ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከምሥራቅ አውሮፓ አገሮች የፈለሱ ሠራተኞች ወደዚህ ጎርፈዋል። ብዙ የፊሊፒንስ ዜጎችና የደቡባዊ ምሥራቅ እስያ ነዋሪዎች የቤት ሠራተኛ ለመሆን ወደ አቴንስ መጥተዋል። በተጨማሪም ከአጎራባች አገሮችና በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ችግር ያለባቸው አካባቢዎች ስደተኞች ያለማቋረጥ ይጎርፋሉ።
ይህ ሁኔታ በአካባቢው ለሚኖሩ የመንግሥቱ ምሥራች ሰባኪዎች አንድ አስቸጋሪ ነገር ይፈጥርባቸዋል። አብዛኞቹ ጊዜያዊ ነዋሪዎች እንግሊዝኛ ቢናገሩም አንዳንዶቹ የሚናገሩት የትውልድ ቦታቸውን ቋንቋ ብቻ ነው። እነዚህ ሰዎች ብዛት ካላቸው የተለያዩ ባሕሎችና ሃይማኖቶች የመጡ ናቸው። ከእንግዶቹ መካከል ስመ ክርስቲያኖችን፣ ሙስሊሞች፣ ሒንዱዎችን፣ ቡዲሂስቶችን፣ ጣዖት አምላኪዎችን፣ ስለ አምላክ ማወቅ አይቻልም ባዮችንና አምላክ የለም የሚሉ ሰዎችን ማግኘት ትችላላችሁ። የይሖዋ ምሥክሮች አቀራረባቸውን የተለያየ ዓይነት አመለካከት ካላቸው ከእነዚህ ሰዎች ጋር ማስማማት አለባቸው።
እነዚህ አዳዲስ ሰዎች አስቸጋሪ ጊዜያት ስላሳለፉ ብዙውን ጊዜ ስለ ሕይወት ዓላማና ወደፊት ስላለን ተስፋ ይጠይቃሉ። አንዳንዶቹ ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ዋጋ ከመስጠታቸውም በላይ በውስጡ የተጻፈውን ለመቀበል አይቸግራቸውም። የተለያዩ ዓይነት ሰዎች በሚገኙበት በዚህ ክልል ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ትሑት፣ የዋህና እውነትን የተራቡ ናቸው። ከቤተሰባቸውና ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀው ስለመጡ እውነትን የሚፈልጉት በነፃነት ነው።
ይህንን ክልል ለመሸፈን በ1986 አቴንስ ውስጥ የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ ጉባኤ ተደራጀ። እድገቱ የሚያስደንቅ ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት 80 የሚያህሉ አዳዲስ ሰዎች ተጠምቀዋል። በውጤቱም አቴንስ ውስጥ አረብኛ ተናጋሪ ጉባኤ፣ ፖሊሽ ተናጋሪ ቡድን ከመቋቋሙም በላይ ለተወሰነ ጊዜ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ቡድን ተቋቁሞ ነበር። አንዳንዶቹ በሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ተሰሎንቄ፣ በሄራከሊዎን፣ ክሪቲ እና የአቴንስ ወደብ በሆነችው ፒሬፍስ የሚገኙትን ጉባኤዎችንና ቡድኖችን ለመርዳት ከእንግሊዝኛ ጉባኤ ወደ ሌላ ቦታ ተዛውረዋል። አቴንስ ውስጥ እውነትን ካወቁት ሰዎች መካከል ከአንዳንዶቹ ጋር ለመተዋወቅ ትፈልጋለህን?
ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጡት እየመጡ ነው
ቶማስ ኤርትራ ውስጥ አሥመራ ከተማ የተወለደ ሲሆን ያደገው ቀናተኛ ካቶሊክ ሆኖ ነው። በ15 ዓመቱ ገዳም ገባ። አንዱን አበምኔት “አንድ አምላክ እንዴት ሦስት አምላክ ይሆናል?” ብሎ ጠየቃቸው። አበምኔቱም “ምክንያቱም መንፈሳዊ ነገሮችን በተመለከተ ሊቀ ጳጳሳቱ ያሉትን እንቀበላለን። ከዚህም በላይ ይህ ምሥጢር ከመሆኑም በተጨማሪ አንተ ይህንን ለመረዳት ገና ልጅ ነህ” ብለው መለሱለት። ቶማስ በገዳሙ አምስት ዓመት ካሳለፈ በኋላ በቤተ ክርስቲያኑ ተግባርና ትምህርቶች ግራ በመጋባትና በመበሳጨት ገዳሙን ጥሎ ወጣ። ቢሆንም እውነተኛውን አምላክ መፈለጉን አላቆመም ነበር።
ወደ አቴንስ ከሄደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ አንድ ቀን “ጤንነትና ደስታ ልታገኛቸው የምትችላቸው ነገሮች ናቸው” የሚል የሽፋን ርዕስ ያለው አንድ መጠበቂያ ግንብ በሩ ላይ አገኘ። ደጋግሞ አነበበው። በዚሁ መጽሔት ላይ የአምላክን መንግሥትና ጽድቁን ማስቀደም እንዳለብን የሚናገር ሐሳብ አነበበ። (ማቴዎስ 6:33) ይህንን ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አምላክ እንዲያሳየው የሚከተለውን ቃል በመግባት ተንበርክኮ ለመነ፦ “መንግሥትህን መፈለግ የሚቻልበትን መንገድ ካሳየኸኝ አንተን ማገልገል የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ለመማር ስድስት ወር እመድባለሁ።” እንዲህ ብሎ በጸለየ በአራተኛው ሳምንት ሁለት ምሥክሮች ቤቱን አንኳኩ። ቶማስ ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረና ከአሥር ወር በኋላ ተጠመቀ። “ይሖዋ ጸሎቴን በመስማት ምሥክሩ የመሆን አጋጣሚ ሰጥቶኛል። ይሖዋ ያሳየኝ ፍቅር በሕይወቴ ውስጥ መንግሥቱንና ጽድቁን ከሁሉ አስቀድሜ እንድፈልግ አነሳስቶኛል” በማለት ተናግሯል።
ሌሎች ሁለት ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሰበኩ ሳለ ከደውሉ ጎን አንድ የውጪ አገር ሰው ስም ተመለከቱ።
“ምን ትፈልጋላችሁ?” የሚል የአንዲት ሴት ድምፅ በመነጋገሪያው ተሰማ።
ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለማወቅ ፍላጎት ያላቸው እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሰዎች እየፈለጉ እንደሆነ አንዷ ምሥክር ተናገረች።
“ሃይማኖታችሁ ምንድን ነው?” በማለት ሴትየዋ ጠየቀች።
“የይሖዋ ምሥክሮች ነን።”
“በጣም ጥሩ ነው! ወደ መጨረሻው ፎቅ ኑ።”
እንዳለቻቸው አደረጉ፤ የአሳንሰሩ በር ሲከፈት ተቃዋሚ የሚመስል በጣም ግዙፍ ሰው ቆሞ ነበር። ነገር ግን ሴትየዋ ከውስጥ ሆና ተናገረች።
“አስገባቸው። ከእነርሱ ጋር መነጋገር እፈልጋለሁ።”
ከባለቤቷ የስፖርት ቡድን ጋር ዓለምን እንደዞረችና የይሖዋ ምሥክሮችን ለማግኘት ከአንድ ቀን በፊት ጸልያ እንደነበር ነገረቻቸው። ስለዚህ ወዲያውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረ። ግሪክ የሚቆዩት ለተወሰነ ጊዜ ስለነበረ በሳምንት ሦስቴ ለማጥናት ዝግጅት ተደረገ፤ ለዘላለም መኖር የተባለው መጽሐፍ በአሥር ሳምንት ተጠናቀቀ።
በሚቀጥለው የስፖርት ወቅት ተመልሰው ወደ ግሪክ መጡ። ሚስትየው ጥናቷን እንደገና ጀመረችና በጣም ጥሩ እድገት አደረገች። ከጥቂት ወራት በኋላ ያልተጠመቀች አስፋፊ በመሆን በስብከቱ ሥራ ከምሥክሮቹ ጋር ተባበረችና ወዲያው የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዋን ማስጠናት ጀመረች። የምታሰጠናው ማንን ነበር? በምሥክሮቹ ሁኔታና እርሷ ባደረገችው ለውጥ የተነካውን ባሏን ነበር።
አለን የፕሮቴስታን ቄስ ልጅ ሲሆን ያደገው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተገለጠ ራእይ እንደሆነ ከልጅነቱ ጀምሮ ያምን ነበር። በሃይማኖቱ ሳይረካ በመቅረቱ ወደ ፍልስፍናና ፖለቲካ ዞር ቢልም ከምንጊዜውም ይበልጥ ባዶነት እንዲሰማው አደረገው። ወደ ግሪክ ከተዛወረ በኋላ የሚሰማው የባዶነት ስሜት እየጨመረ ሄደ። ወዴት እንደሚወስድ በማያውቀው መንገድ ላይ እየተጓዘ እንዳለና ሕይወቱ ምንም ዓላማ እንደሌለው ሆኖ ይሰማው ነበር።
አንድ ቀን ምሽት የሆነ ነገር ተፈጠረ። “በጉልበቴ ተንበርክኬ በውስጤ ያለውን ለአምላክ ነገርኩት” በማለት አለን ይናገራል። “ስላሳለፍኩት ሕይወት በሐዘን እያነባሁ ወደ እውነተኛ ተከታዮቹ እንዲመራኝ አምላክን ጠየቅሁት። መመሪያውን እንደምከተል ቃል ገባሁ።” በዚያው ሳምንት አንድ ሱቅ ውስጥ ሳለ የሱቁ ባለቤት ከሆነች አንዲት ሴት ጋር መነጋገር ጀመረ። ይህች ሴት የይሖዋ ምሥክር ነች። ይህ ውይይት የአለንን ሕይወት በእጅጉ የለወጠ ነበር። “በሚቀጥሉት ቀናት መጽሐፍ ቅዱስ የማያስተምራቸው እንደ ሥላሴ፣ እሳታማ ሲኦልና የነፍስ አለመሞት የመሳሰሉት አጥብቄ አምንባቸው የነበሩት እምነቶች ስህተት እንደሆኑ ደረስኩበት።” በመንግሥት አዳራሹ አንድ ባልና ሚስት ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና ግብዣ አቀረቡለት። ግብዣውን ተቀበለና ፈጣን እድገት አደረገ። አለን “እውነት በደስታ እንዳነባ አድርጎኛል እንዲሁም ነፃ አውጥቶኛል” በማለት ያለፈውን ያስታውሳል። ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠመቀ። በአሁኑ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ዲያቆን በመሆን በደስታ ያገለ ግላል።
ከናይጄሪያ የመጣችው ኤልዛቤት በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አምላክን ለማግኘት ፍለጋ ብታደርግም አልረካችም ነበር። ከሁሉ ይበልጥ የሚያስፈራት በሲኦል እሳት ውስጥ ለዘላለም ስለመሰቃየት የሚሰጠው ትምህርት ነበር። ከቤተሰቧ ጋር ወደ አቴንስ ስትመጣ ሁለት ምሥክሮች በሯን አንኳኩና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩ። ኤልዛቤት አምላክ ሰዎችን እንደማያሰቃይ ከዚህ ይልቅ በምድራዊ ገነት ውስጥ የዘላለም ሕይወት እንደምናገኝ ተስፋ እንደሰጠ ስታውቅ በጣም ተደሰተች። አራተኛ ልጅዋን እርጉዝ የነበረች ሲሆን ለማስወረድ ትፈልግ ነበር። ይሖዋ ለሕይወት ቅድስና ያለውን አመለካከት ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማረች። አሁን ቆንጅዬ ሴት ልጅ አለቻት። ኤልዛቤት ፈጣን እድገት ከማድረጓም በተጨማሪ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቀች። ምንም እንኳ አራት ልጆችና የሙሉ ቀን ሥራ ቢኖራትም አብዛኛውን ወራት በረዳት አቅኚነት ለማሳለፍ ችላለች። ባሏ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲጀምር በማየት ተባርካለች። “በመጨረሻ እውነተኛውን አምላክና እውነተኛውን አምልኮ ስላገኘሁ ይሖዋንና አፍቃሪ የሆነ ድርጅቱን አመሰግናለሁ” ብላለች።
የተለያዩ ሰዎች በሚኖሩበት በዚህ ክልል ውስጥ የሚገኙ ብዙዎቹ ሰዎች የተገኙት ከመንገድ ወደ መንገድ ምሥክርነት ቢሆንም ፍላጎታቸውን ለማሳደግ ጽናት ይጠይቃል። ከሴራ ሊዮን በመጣችው ሳሌ በተባለች ወጣት ላይ ያጋጠመው ይህ ሁኔታ ነው። አንዲት ምሥክር ትራክት ሰጥታት አድራሻዋን ወሰደችና ለተመላልሶ መጠየቅ ቀጠሮ ያዘች። ሳሌ በነገሩ ተደስታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ብትጀምርም ሥራዋና ሌሎች አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚያሳድሩባት ተጽዕኖ የተነሳ የምታጠናው አልፎ አልፎ ነበር። ሳሌ አዲሱን አድራሻዋን ሳትናገር በድንገት ወደ ሌላ ቦታ ተዛወረች። ምሥክሯ ሳሌ ቀድሞ ትኖርበት ወደነበረው ቤት ሁልጊዜ ትሄድ የነበረ ሲሆን በመጨረሻ ምሥክሯ ወደ አዲሱ ቤቷ እንድትመጣ መልእክት ላከችላት።
ሳሌ ልትወልድ ተቃርባ የነበረ ቢሆንም ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ በቋሚነት ታጠና ጀመር። ከወለደች በኋላ ያልተጠመቀች አስፋፊ ሆነች። ይህንን ሁሉ ማድረግ ቀላል ቢመስልም አስቸጋሪ ነበር። ከጠዋቱ 12:30 ተነስታ በአውቶቡስ ግማሽ ሰዓት በመጓዝ ልጅዋን መዋዕለ ሕፃናት ታደርስና ተጨማሪ አንድ ሰዓት ወደ ሥራዋ በአውቶቡስ ትጓዛለች። የጽዳት ሥራዋን ካከናወነች በኋላ ወደ ቤቷ ትመለሳለች። ምንም እንኳ ባሏ ቢቃወማትም ጉባኤ በሚደረግባቸው ወይም መስክ አገልግሎት በምትወጣባቸው ምሽቶች ለነጠላ ጉዞ ብቻ አንድ ሰዓት የሚወስድ መንገድ በአውቶቡስ ትጓዛለች። ለባሏ ፍቅርና ትዕግሥት እያሳየች እድገት አደረገችና ራሷን ወስና ተጠመቀች። ባሏስ እንዴት ሆነ? በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ ከመገኘቱም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምሯል።
በመልካም ውጤቶች መባረክ
አብዛኞቹ ሰዎች አቴንስ የሚቆዩት ለጊዜው ነው። ብዙዎቹ ምሥራቹን ለዘመዶቻቸውና ለጓደኞቻቸው ለማካፈል ወደ ተወለዱበት ቦታ ተመልሰዋል። ሌሎቹ ወደተለያዩ የምዕራብ አገሮች ሄደው እዚያ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። እዚያው ግሪክ የቆዩት ደግሞ እንደነርሱ ወደዚያ አገር ለሚመጡት የአገራቸው ሰዎች በመስበክ ጥሩ ጥሩ ውጤቶች አግኝተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ እንግዶቹ ወደ ሌላ አገር ሄደው እዚያ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ሲገናኙ የእውነት ዘር ያፈራል።
ይህ ሁሉ ይሖዋ እንደማያዳላ ያሳያል። እርሱን የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚወዱትን ሰዎች ሁሉ ይቀበላል። (ሥራ 10:34, 35) እነዚህን የመሳሰሉ በግ መሰል ሰዎች ቁሳዊ ጥቅማ ጥቅሞችን ለማግኘት ወደ ሌላ አገር መዛወራቸው ስለ እውነተኛው አምላክ ይሖዋና ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚኖረው የዘላለም ሕይወት የተሰጠውን ተስፋ በማወቅ ካሰቡት እጅግ የላቁ በረከቶች አስገኝቶላቸዋል። በእርግጥም በዘመናዊቷ አቴንስ ውስጥ የውጪ አገር ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች ለመመሥከር የሚደረገውን ጥረት ይሖዋ አብዝቶ ባርኮታል!
[በገጽ 16 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ከተለያዩ አገሮች የመጡ ሰዎች አቴንስ ውስጥ እውነትን እየሰሙ ነው