የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w95 12/15 ገጽ 4-7
  • ስጦታ የማበርከት መንፈስ አለህን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስጦታ የማበርከት መንፈስ አለህን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ውለታ እንዲውልልህ የምትፈልገው ሰው አለን?
  • ስጦታ የምትሰጠው በራስህ ፍላጎት ተነሳስተህ ነውን?
  • ከፍ አድርገህ የምትመለከተው ዕለቱን ነው ወይስ የፍቅር መግለጫ መሆኑን?
  • ዓመቱን ሙሉ የሚታይ የልግስና መንፈስ
  • ከሁሉ የላቀ ስጦታ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • “እስከ ዛሬ ከተሰጡኝ ስጦታዎች ሁሉ የሚበልጥ ስጦታ”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • ከሁሉ የላቀው የአምላክ ስጦታ—ውድ የሆነበት ምክንያት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2017
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2003
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
w95 12/15 ገጽ 4-7

ስጦታ የማበርከት መንፈስ አለህን?

ሰዎች ስጦታ ለመስጠት የሚገፋፋቸው ነገር የተለያየ እንደሆነ አስተውለሃልን? ስጦታ የፍቅር፣ የልግስና፣ የአድናቆት መግለጫ ሊሆን ይችላል። ቢሆንም አንድ ሰው እንደ ውለታ እንዲታይለት በመፈለግ ስጦታ ሊሰጥ እንደሚችል ልብ ብለሃልን? አለዚያም ማድረግ እንዳለበት ስለተሰማው ወይም ሰጪው በምላሹ አንድ ነገር እንዲደረግለት ስለሚፈልግ ብቻ ስጦታ ሊሰጥ ይችላል።

ስጦታው የሚያምር ሪበን የታሰረበት የታሸገ ዕቃ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን እቅፍ አበባ፣ ጥሩ ምግብ ወይም በደግነት መንፈስ የሚደረግ እርዳታ ስጦታ አይሆንምን? ከሁሉ የላቀ ዋጋ የሚሰጣቸው ስጦታዎች ብዙውን ጊዜ መሥዋዕትነትን ይጠይቃሉ።

ውለታ እንዲውልልህ የምትፈልገው ሰው አለን?

አንድ ሰው አንድ ነገር እንዲያደርግለት ለሚፈልገው ሰው ስጦታ መስጠቱ የተለመደ ነው። በአንዳንድ አገሮች የእጮኛውን ልብ ለመማረክ የፈለገ ወጣት አበባ ሊያበረክትላት ይችላል። ቢሆንም ጥበበኛ ሴት ከስጦታው በስተጀርባ ያለውን ነገር ትመለከታለች። በፍቅር ተነሳስቶ ማድረጉንና ወደፊት ጥሩ ባል አንደሚሆን የሚያሳይ መሆኑንና አለመሆኑን ታመዛዝናለች። እንዲህ ያለው ስጦታ አምላካዊ ባሕርይን የሚያንጸባርቅ ከሆነ ለሰጪውም ሆነ ለተቀባዩ ከፍተኛ ደስታ ሊያመጣ ይችላል።

ዳዊት በእስራኤል ላይ እንዲነግሥ አምላክ ያጨው ሰው መሆኑን ያወቀችው የናባል ሚስት አቢግያ ፈጠን ብላ ልግስና የተሞላበት ስጦታ ለዳዊት እንዳዘጋጀች መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። አንድ ውለታ እንዲውልላት ፈልጋ ነበር። ባሏ ዳዊትን ከመቃወሙም በላይ ከዳዊት ጋር የነበሩትን ሰዎች ዘልፏቸው ነበር። 400 መሣሪያ የታጠቁ ሰዎችን ይመራ የነበረው ዳዊት ናባልንና ቤተሰቡን ለማጥፋት ወሰነ። አቢግያ ጣልቃ ገባችና ከዳዊት ጋር አብረውት ላሉት ሰዎች የሚሆን ምግብ በፍጥነት አዘጋጅታ ልግስና የተሞላበት ስጦታ ላከችለት። ስጦታዋን ከላከች በኋላ ራሷ ሄዳ ባሏ ላደረገው ነገር በትሕትና ይቅርታ የጠየቀች ሲሆን ለዳዊት አሳማኝ ሐሳብ በማቅረብ ከፍተኛ ማስተዋል እንዳላት አሳይታለች።

ዕቅዷ አስተዋይነት የተሞላበት የነበረ ሲሆን ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ዳዊት ስጦታዋን ተቀበለና “በደኅና ወደ ቤትሽ ሂጂ፤ እነሆ፣ ቃልሽን ሰማሁ፣ ፊትሽንም አከበርሁ” አላት። እንዲያውም ናባል ከሞተ በኋላ ዳዊት አቢግያን ለጋብቻ ጠይቋት ሐሳቡን በደስታ ተቀብላለች።—1 ሳሙኤል 25:13–42

ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው እንዲደረግለት የሚፈልገው ነገር አድልዎ ማድረግን ወይም ፍትሕ መጓደልን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ስጦታው ጉቦ ነው። ሰጪው የሚጠቀም ቢመስለውም የአእምሮ ሰላሙን በገዛ እጁ ያጣል። ሌሎች የተፈጸመውን ነገር ቢደርሱበት ተጠያቂ እሆናለሁ ብሎ ይሰጋል። የፈለገው ነገር ቢፈጸምለትም እንኳ ይህ ሰው ምግባሩ አጠያያቂ ነው የሚል ስም እንዳተረፈ ሊሰማው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከእንዲህ ዓይነት ስጦታዎች እንድንርቅ በማስጠንቀቅ አምላካዊውን ጥበብ ያንጸባርቃል።—ዘዳግም 16:19፤ መክብብ 7:7

ስጦታ የምትሰጠው በራስህ ፍላጎት ተነሳስተህ ነውን?

በራስህ ፍላጎት ተነሳስተህ ለምትወደው ሰው ስጦታ መስጠት ሌሎች ገፋፍተውህ የምትሰጠው ስጦታ ከሚያስገኘው ደስታ ይበልጥ እንደሚያስደስት ጥርጥር የለውም።

ቁሳዊ ችግር ላጋጠማቸው ክርስቲያኖች የሚሆን ዕርዳታ መሰብሰብን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ አምላካዊ በሆነ መንገድ ልግስና ማድረግ የሚቻልባቸውን አንዳንድ ግሩም መሠረታዊ ሥርዓቶች አውጥቶ ነበር። “በጎ ፈቃድ ቢኖር፣ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም” በማለት ጽፏል። በተጨማሪም “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” ብሏል። (2 ቆሮንቶስ 8:12፤ 9:7) ስለዚህ ይበልጡኑ የተመካው በአንተ ላይ ነው። ስጦታዎችን ለመግዛት ብድር ውስጥ ከመግባት ይልቅ አቅምህ የሚፈቅድልህን ታደርጋለህን? በማኅበራዊ ኑሮ ወይም የንግዱ ዓለም በሚያሳድረው ተጽዕኖ ተገፋፍተህ ስጦታ ከመስጠት ይልቅ ራስህ ያሰብከውን ታደርጋለህን? ጳውሎስ ይህንን አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ስላዋሉ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “ለቅዱሳን በሆነው አገልግሎት እንዲተባበሩ ይህን ቸርነት [“የመርዳት ዕድል እንዳይነፈጋቸው” የ1980 ትርጉም] በብዙ ልመና ከእኛ ይለምኑ ነበር” ብሏል።—2 ቆሮንቶስ 8:4

ይህ ሁኔታ የኅዳር/ታኅሣሥ 1994 ሮያል ባንክ ሌተር ከገና በፊት ስላሉት ሳምንታት ከተናገረው ጋር ሲነጻጸር ጉልህ ልዩነት አለው። “ጊዜው ሸማቹ ባይወተወት ኖሮ የማይገዛቸውን ነገሮች እንዲገዛ በሚጎተጉቱ የንግድ እንቅስቃሴዎች አማካኝነት አርቲፊሻል ደስታ የሰፈነበት መስሎ ይታያል” ብሏል። ስጦታው የተገዛው በተወሰነ ጊዜ ውስጥ በሚከፈል ብድር ከሆነ ብድሩ ተጠናቆ የሚከፈልበት ጊዜ ሲደርስ ስጦታውን በማበርከት የተገኘው ማንኛውም ደስታ ወዲያው ይከስማል።

ከፍ አድርገህ የምትመለከተው ዕለቱን ነው ወይስ የፍቅር መግለጫ መሆኑን?

ብዙውን ጊዜ ስጦታ የምታበረክተው ስጦታ መስጠት አስፈላጊ መስሎ በሚታይባቸው ጊዜያት ነውን? እንዲህ ከሆነ ባልታሰበ ወቅት ስጦታ መስጠት ሊያስገኝ የሚችለውን አብዛኛውን ደስታ አጥተህ ሊሆን ይችላል።

ወቅት እየጠበቁ የሚሰጡ ስጦታዎች የማያስደስቷቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ደራሲ የሆነች አንዲት የልጆች እናት ስጦታ የሚሰጥባቸው ወቅቶች በደረሱ ቁጥር ልጆቿ ስስት እንደሚያድርባቸው ተናግራለች። ራሷም ብትሆን ይሰጠኛል ብላ የጠበቀችውን ነገር ሳይሆን ሌላ ስጦታ ስታገኝ ቅር እንደሚላት ሳትሸሽግ ገልጻለች። በተጨማሪም ድግስና የስጦታ ልውውጥ ያለባቸው በዓላት የስሜት ውጥረትና የአልኮል መጠጦችን ከመጠን በላይ የመጠጣት ሁኔታ በእጅጉ የሚንፀባረቅባቸው ጊዜያት እንደሆኑ ብዛት ያላቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

በበዓላት ቀን ስጦታ መለዋወጥ እንደ ትልቅ ነገር ተደርጎ መታየቱ አንዳንድ ጊዜ በልጆች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ያስተዋሉ አንድ የሳይኮሎጂ ፕሮፌሰር ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ በተባለው ጋዜጣ ላይ “ከበዓላት ውጪ አንዳንድ ስጦታዎችን መስጠት እንዲህ ዓይነቱን ጭንቀት እንደሚቀንስ አድርጋችሁ ተመልከቱት” በማለት ምክር ሰጥተዋል። ይህ ጥሩ ውጤት ይኖረዋል ብለህ ታስባለህ?

ገናንም ሆነ የልደት ቀናትን የማያከብር ቤተሰብ ያላት የ12 ዓመቷ ታሚ “ባልጠበቃችሁት ጊዜ ስጦታ ማግኘት ይበልጥ ያስደስታል” በማለት ጽፋለች። ወላጆቿ ለእርሷና ለወንድሟ በዓመት ውስጥ አንዴ ወይም ሁለቴ ብቻ ሳይሆን ብዙውን ጊዜ ስጦታ እንደሚሰጧቸው ተናግራለች። ቢሆንም ከእነዚህ ስጦታዎች አብልጣ የምታየው ሌላ ነገር አለ። ይህም ምን እንደሆነ ስትናገር “በጣም ደስተኛ ቤተሰብ አለኝ” ብላለች።

ሴክሬትስ ኦቭ ስትሮንግ ፋሚሊስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ በማለት በግልጽ ይናገራል፦ “ብዙዎቻችን በልደት ቀናት፣ በመታሰቢያ በዓላት ወይም በማንኛውም በዓላት ጊዜ ለምንወዳቸው ሰዎች የምንሰጣቸውን እጅግ ተስማሚ ስጦታዎች ለመምረጥ በዓመት ውስጥ ብዙ ጊዜና ገንዘብ እናጠፋለን። ከሁሉ የተሻለው ስጦታ ገንዘብ አይጠይቅም። መጠቅለልም አያስፈልግህም። እንደ አብዛኞቹ ሰዎች ሕይወትህን ካሉህ ንብረቶች ሁሉ የላቀ ዋጋ እንዳለው አድርገህ የምትመለከተው ከሆነ ካለህ ጊዜ ጥቂቱን ለሌሎች መስጠት ከስጦታዎች ሁሉ የላቀ ነው። ለምንወዳቸው ሰዎች ጊዜያችንን በሰጠን መጠን ይህንን ስጦታ እናበረክታለን።”

ይህንን ስጦታ የቤተሰብህ አባል ላልሆኑ ሰዎች ጭምር ማበርከት ትችላለህ። ሌሎች ያሉባቸውን በግልጽ የሚታዩ ችግሮች ለማሟላት ባልጠበቁት ወቅት ስጦታ መስጠት ልዩ እርካታ ሊያመጣ ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅራዊ አሳቢነት ለድሆች፣ ለአካለ ስንኩላንና ለዓይነ ስውራን እንድናሳይ ከማሳሰቡም በተጨማሪ “የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ [“ደስተኛ” አዓት] ትሆናለህ” ብሏል።—ሉቃስ 14:12–14

ሮክላንድ ጆርናል–ኒውስ (ዩ ኤስ ኤ) የተባለ ጋዜጣ እንዲህ የመሰለውን ልግስና የሚያሳይ አንድ ምሳሌ በቅርቡ ሪፖርት አድርጓል። አንዲት በዕድሜ የገፉ ዓይነ ስውር ሴት ቤታቸው በፈረሰ ጊዜ ወዳጆቻቸው አዲስ ቤት ሠሩላቸው። በአካባቢው ያሉ በርካታ መሥሪያ ቤቶች እርዳታ ከመስጠታቸውም በላይ በአካባቢው ያለ የመንግሥት ወኪል ገንዘብ ሰጥቷቸው ነበር። “ከሁሉ በላይ ግን” አለ ጋዜጣው “አብዛኞቻቸው ሀቨርስትሮ ተብሎ የሚጠራው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አባላት የሆኑ 150 ወይም ከዚያ የሚበልጡ ሰዎች ቤቱን ለመሥራት ጊዜያቸውን ለግሰዋል።”

ጽሑፉ በመቀጠል፦ “ቤቱ በሚሠራበት ቦታ ከነበረው በምግብ የተሞላ ጠረጴዛ ጎን የተለያዩ ቁሳቁሶች ነበሩ። ሠራተኞቹ በሁለት ቀን ውስጥ ሁለት ቤተሰብ መያዝ የሚችል ባለ ሦስት ፎቅ ቤት ሠሩ። . . . የይሖዋ ምሥክሮች በአጭር ጊዜ ሕንፃዎችን በመገንባት በኩል ባላቸው ችሎታ የታወቁ ናቸው። . . . ሥራቸውን በአጭር ጊዜ ቢያከናውኑም ተልእኳቸው ግን ዘለቄታነት ያለው ነው። ይህ ተልዕኮ ፍቅር የተሞላበት ዘላቂ ሥራ ሠርቶ ማለፍ ነው። ወይዘሮ ብላክሊት አዲሱን ቤታቸውን ማየት አይችሉ ይሆናል፤ ቢሆንም እጃቸው ሊዳስሰው ከመቻሉም በላይ በዚህ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ተግባር ልባቸው ምን ያህል እንደተነካ ያውቁታል።”

ዓመቱን ሙሉ የሚታይ የልግስና መንፈስ

እውነተኛ የልግስና መንፈስ ያላቸው ሰዎች የተለዩ ቀናትን አይጠብቁም። ሕይወታቸው በራሳቸው ጥቅም ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም። አንድ ጥሩ ነገር ሲያገኙ ከሌሎች ጋር በመካፈል ይደሰታሉ። እንዲህ ሲባል ስጦታ የሚሰጡት በግዴታ ነው ማለት አይደለም። ቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ እስኪወድቁ ድረስ ይሰጣሉ ማለት አይደለም። ስጦታው በተቀባዩ ላይ የሚያስከትለውን ውጤት ሳያመዛዝኑ ይሰጣሉ ማለት አይደለም። ነገር ግን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ‘ሰጪዎች’ እንዲሆኑ ያስተማረውን ትምህርት በመከተል እነርሱም ይህንን ያደርጋሉ።—ሉቃስ 6:38

በዕድሜ የገፉ፣ የታመሙ ወይም ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው ጓደኞቻቸው ወይም ጎረቤቶቻቸው ያሉበትን ሁኔታ ያውቃሉ። “ስጦታቸው” መላላክ ወይም የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማገዝ ሊሆን ይችላል። እንጨት መፍለጥ ወይም ግቢ ማጽዳት ሊሆን ይችላል። ምግብ አዘጋጅቶ ይዞ መሄድ ወይም ጊዜ መድቦ መጠየቅና አብሮ ማንበብ ሊሆን ይችላል። ብዙ ሥራ ያለባቸው ሊሆኑ ቢችሉም ሌሎችን መርዳት እስከማይችሉ ድረስ በሥራ የተወጠሩ አይደሉም። “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ” አዓት]” እንደሆነ በተግባር አይተውታል።—ሥራ 20:35

እርግጥ ነው ታላቁ ሰጪ ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ ነው። “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣል።” (ሥራ 17:25) ክፋትን፣ በሽታንና ሞትን ለማጥፋት እንዲሁም ይህችን ምድር ገነት ለማድረግ ዓላማ እንዳለው በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት እንድናስተውል አድርጎናል። (መዝሙር 37:10, 11፤ ራእይ 21:4, 5) የልግስና መንፈስ ያላቸው ሰዎች ይህንን ዓላማ ሲያውቁ ይህንን ምሥራች ለራሳቸው ብቻ ይዘው አይቀመጡም። አንዱ ከፍተኛ ደስታ የሚያስገኝላቸው ነገር ይህንን ምሥራች ለሌሎች ማካፈል ነው። በእርግጥም አምላካዊ የሆነ የመስጠት መንፈስ አላቸው። አንተስ እየኮተኮትክ ያለኸው ይህንን መንፈስ ነውን?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጣም ውድ ከሆኑት ስጦታዎች መካከል አንዳንዶቹ ገንዘብ የሚጠይቁ አይደሉም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ