በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተመሠረተው ክስ ውሳኔ ተሰጠበት
ቀጠሮው በተደጋጋሚ ጊዜያት ለሌላ ቀን ሲተላለፍ ከቆየ በኋላ በተሰሎንቄ ግሪክ የሚገኘው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሰኔ 8, 1995 በአራት ሴት የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተመሠረተውን ክስ ለመስማት ተቀምጦ ነበር። የተከሰሱበት ጉዳይ ምን ነበር? የሰዎችን ሃይማኖት ማስቀየር እንደማይቻል የሚደነግገውንና ከሃምሳ ለሚበልጡ ዓመታት የቆየውን የግሪክ መንግሥት ሕግ ተላልፋችኋል የሚል ነበር።
ሆኖም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ለማየት በተቀመጠበት ወቅት ለአቃቤ ሕጉ ዋንኛ ምሥክር የነበረው ማለትም በአራቱ ሴቶች ላይ ክስ እንዲመሠረት ያደረገው ቄስ ሞቶ ነበር። በእሱ ምትክ ሌላ ቄስ ለመመሥከር ቢፈልግም ፍርድ ቤቱ ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀረ። ስለዚህ ጉዳዩን ለመስማት የፈጀው ጊዜ 15 ደቂቃ ብቻ መሆኑ አያስደንቅም! ዳኛው ሌሎች የአቃቤ ሕጉን ምሥክሮች ከመረመረ በኋላ ተከሳሾቹ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በመስበክ ጥፋተኛ እንዳልሆኑ ፈረደ። ይህ ውሳኔ የግሪክ ፍርድ ቤቶች የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በ1993 ያሳለፈውን ውሳኔ ለማክበርና በሥራ ላይ ለማዋል ፈቃደኛ እንደሆኑ ያሳያል።
በጣም የሚገርመው ለአቃቤ ሕጉ ምሥክሮች የነበሩት ሦስት ሴቶች ወደ ተከሳሾቹ የይሖዋ ምሥክሮች ቀርበው ከልባቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋቸዋል። ከእነዚህ ሴቶች መካከል አንዷ “ለደረሰባችሁ ነገር ሁሉ ይቅርታ እንድታደርጉልን እንጠይቃችኋለን” ብላለች። አክላም እንዲህ አለች፦ “ጥፋቱ የእኛ አይደለም። ቄሱ እንድንከሳችሁ አስገደደን። አሁን በሕይወት የለም፤ ወደ ሰፈራችንና ወደ ቤታችን እንድትመጡ እንፈልጋለን።”
ስለዚህ በግሪክ ውስጥ ይሖዋ ለሕዝቦቹ እንደገና አስደናቂ ድል አጎናጽፏቸዋል። በ1938 እና በ1939 በግሪክ ውስጥ ሃይማኖትን ማስቀየርን የሚከለክሉ ሕጎች ወጥተው ነበር። በ1993 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በዚህ ሕግ ተጠቅሞ የይሖዋ ምሥክሮችን ማሳደድ ስሕተት መሆኑን አጽድቋል።—መስከረም 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ ገጽ ከ27–31 ተመልከት።