ብርሃናችሁ ይብራ!
አረጋዊው ሰው ሲጠበቅ የነበረውን መሲሕ ከረጅም ጊዜ በኋላ ለማየት በቃ! ስምዖን ‘በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንደማያይ’ የሚገልጽ መለኮታዊ ራእይ ተመልክቶ ነበር። (ሉቃስ 2:26) ይሁን እንጂ ስምዖን ወደ ቤተ መቅደሱ በገባበት ወቅት ማርያምና ዮሴፍ ሕፃኑን ሲያስታቅፉት ምንኛ ተደስቶ ነበር! ለአምላክ የሚከተለውን ውዳሴ አቀረበ፦ “ጌታ ሆይ፣ አሁን . . . ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ . . . ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።”—ሉቃስ 2:27-32፤ ከኢሳይያስ 42:1-6 ጋር አወዳድር።
ኢየሱስ በ30 ዓመቱ ከተጠመቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የዓለም “ብርሃን” ሆኗል። ይህን ያደረገው በምን መንገዶች ነው? የአምላክን መንግሥትና ዓላማዎች በመስበክ መንፈሳዊ ብርሃን አብርቷል። የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ከማጋለጡም በተጨማሪ የጨለማ ሥራዎችን በግልጽ ለይቶ አሳውቋል። (ማቴዎስ 15:3-9፤ ገላትያ 5:19-21) ስለዚህ ኢየሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” በማለት በትክክል ሊናገር ይችል ነበር።—ዮሐንስ 8:12
ኢየሱስ በ33 እዘአ ሞተ። በዚያን ጊዜ ብርሃኑ ጠፍቶ ነበርን? ፈጽሞ አልጠፋም! ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱን “ብርሃናችሁ . . . በሰው ፊት ይብራ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 5:16) በዚህ መሠረት ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ተከታዮቹ ብርሃኑን ማብራታቸውን ቀጥለዋል።
በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች ኢየሱስን በመምሰል በስብከቱ ሥራ የይሖዋን ብርሃን ያንጸባርቃሉ። የክርስቲያናዊ አኗኗር አንጸባራቂ ምሳሌዎች መሆናቸውን በማስመስከር ‘እንደ ብርሃን ልጆች መመላለሳቸውን ይቀጥላሉ።’—ኤፌሶን 5:8