የመንግሥት ዜና ለማሰራጨት የተካሄደ የተሳካ ዘመቻ
“የሰው ሕይወት በችግር የተሞላው ለምንድን ነው?—ችግር የሌለበት ገነት ሊመጣ ይችል ይሆን?” ባለፈው ዓመት በሚያዝያና በግንቦት ወራት በ139 ቋንቋዎች በመላው ዓለም የተሰራጨው ባለ አራት ገጽ የመንግሥት ዜና ቁጥር 34 ትራክት ርዕስ ይህ ነበር። በጃማይካ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን የአገልግሎት ዘመቻ “ከዓመቱ ዐበይት ክንዋኔዎች አንዱ” በማለት ገልጸውታል። በቤልጅየም የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች “ወንድሞች በጣም ተደስተውበታል” ብለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በቼክ ሪፑብሊክ ውስጥ የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት የማሰራጨት አጋጣሚ ሲያገኙ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮው “ዘመቻው የቅንዓት መንፈስና የጋለ ስሜት ቀስቅሷል” ሲል ሪፖርት አድርጓል። ሌሎች ብዙ አገሮችም ተመሳሳይ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል።
የመንግሥት ዜና ቁጥር 34 በሃይማኖት ስም በተፈጸሙ አስጸያፊ ነገሮች ሳቢያ ለሚያዝኑና ለሚተክዙ ሰዎች አንድ ልዩ መልእክት ይዞ ነበር። (ሕዝቅኤል 9:4) ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነው በዚህ ‘አስጨናቂ ዘመን’ ምክንያት በችግር ለሚሠቃዩ ሰዎች የሚሆን ማጽናኛም ይዞ ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ትራክቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በመመርኮዝ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙን ችግሮች በቅርቡ እንደሚወገዱ ጠቁሟል። ችግር የሌለበት ገነት እንደሚመጣ ምንም አያጠራጥርም። (ሉቃስ 23:43) የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት ያነበቡ ብዙ ሰዎች የያዘውን መልእክት አሳማኝ ሆኖ አግኝተውታል። በቶጎ የሚኖር አንድ ሰው “የገለጻችሁት ነገር የማያከራክር ነው” በማለት ለአንድ ምሥክር ተናግሯል።
የመንግሥት ዜና የተባለው የዚህ ትራክት ስርጭት ከወትሮው የተለየ ትኩረት እንደሳበ ምንም አያጠያይቅም። በዴንማርክ ውስጥ አንድ የይሖዋ ምሥክር ለአንድ ሰው ትራክት ሲያበረክትለት ሰውዬው እንዲህ የሚል ምላሽ ሰጥቶታል፦ “ከዩናይትድ ስቴትስ ገና አሁን መመለሴ ነው። ወደዚህ ልመጣ ስል አንድ ሰው ትራክታችሁን ሰጥቶኛል። አሁን ደግሞ ገና ከመምጣቴ በዴንማርክ ቋንቋ የተጻፈውን ይኽንኑ ትራክት ሰጠኸኝ!”
ለዘመቻው በጋለ ስሜት የተሰጠ ድጋፍ
በመላው ዓለም የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ትራክቱን በማሰራጨቱ ተግባር በጋለ ስሜት ተሳትፈዋል። የመንግሥት ዜና የተባለው ትራክት በተሰራጨባቸው ወራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ሪፖርት ካደረጉት ብዙ አገሮች መካከል ኦስትሪያ፣ ኤል ሳልቫዶር፣ ሃይቲ፣ ሃንጋሪ፣ ኢጣሊያ፣ ኒው ካሊዶንያ ጥቂቶቹ ነበሩ።
በዛምቢያ ውስጥ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ዲቦራ የተባለች የሦስት ዓመት ልጁን ከቤት ወደ ቤት እየሄደች እንዴት ጽሑፎችን ማበርከት እንደምትችል አሠልጥኗት ነበር። ዲቦራ የመንግሥት ዜና ቁጥር 34 በዘመቻ በሚበረከትበት ወቅት ከ45 በላይ ትራክት አበረከተች። ዲቦራ የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት ያበረከተችላቸውን አንዳንድ ሰዎች እናትዋ ማስጠናት ጀምራለች።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥ አንዲት በአሥራዎቹ ዕድሜ የምትገኝ ልጅ ካሽያ ለተባለች የትምህርት ቤት ጓደኛዋ ትራክቱን አበረከተችላት። ካሺያ ትራክቱን ካነበበች በኋላ “በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር እጅግ አስደሳች ነገር ነው! ከዚህ በፊት ስለዚህ ጉዳይ ለምን አልነገርሽኝም?” አለቻት። ለካሽያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት። ካሽያ በዚሁ ሳምንት ሌላ ትራክት ደረሳት። ሁለተኛው ትራክት የደረሳት በቆጵሮስ ውስጥ ከምትገኘው የሮማ ካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ ከሆነች የብዕር ጓደኛዋ ነበር። የብዕር ጓደኛዋ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ሐሰት የሆኑበትን ምክንያት ለካሽያ ካብራራችላት በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት እንዳሰበች ገለጸችላት። ይህም ካሽያ ጥናቷን ለመቀጠል ያደረገችውን ውሳኔ ይበልጥ አጠናከረላት።
በስዊዘርላንድ ውስጥ የሚኖር አንድ የአሥር ዓመት ልጅ ከእናቱ ጋር ሆኖ ትራክቱን ያሰራጭ ነበር። አንድ ትራክት ለአንዲት ወጣት ሰጣትና በደንብ እንድታነበው አበረታታት። ወጣቷ በትራክቱ ሽፋን ላይ ባለው ሥዕል ላይ የተገለጸውን በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ በእርግጥ ያምንበት እንደሆነ ልጁን ጠየቀችው። ልጁ ምን መልስ ሰጣት? “አዎን አምንበታለሁ፣ ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም” አላት። ከዚያም ወጣቷ በምትከተለው ሃይማኖት ውስጥ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ በጣም ብዙ ነገሮች ስላሉ እውነተኛውን እምነት በመፈለግ ላይ እንደነበረች ገለጸች። በተመላልሶ መጠየቅ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት።
ፈጣን ምላሾች
የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት በማንበብ ፈጣን የሆነ ምላሽ ያሳዩ ሰዎችም አሉ። በቤልጅየም የምትገኝ አንዲት የ11 ዓመት ልጅ ትራክቱን ካነበበች በኋላ ከገበያ አዳራሾች ዕቃ ትሰርቅ እንደነበረ ለአንዲት የይሖዋ ምሥክር ነገረቻት። የልጅቷ እናት ነገሩ እንዳይገለጥ ፈልጋ የነበረ ቢሆንም ልጅቷ ያነበበችው ነገር ሕሊናዋ እንዲወቅሳት ስላደረጋት ወደ ገበያ አዳራሹ ሄዳ ለኃላፊው ለመንገር ወሰነች። በመጨረሻም እናቷ ልጅዋ ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ወደ ገበያ አዳራሹ እንድትሄድ ተስማማች። ኃላፊው ልጅቷ ጥፋቷን በመናገሯ በጣም ተገረመ። ኃላፊው ይህን እንድታደርግ የገፋፋት የመንግሥት ዜና የተባለው ትራክት እንደሆነ ሲገነዘብ ይህን ያህል ግፊት ሊያሳድርባት የቻለው ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ትራክቱን ወሰደ። በአሁኑ ወቅት ይህች ልጅ መጽሐፍ ቅዱስ በማጥናት እድገት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
በካሜሩን የሚገኝ አንድ የይሖዋ ምሥክር ለአንድ ሰው የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት ካበረከተለት በኋላ ስለ ተፈጸመው ሁኔታ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ስንመለስ ትራክቱ ላይ አስምሮበት ብዙ ጥያቄዎችን ይዞ ጠበቀን። አጥጋቢ መልሶችን ካገኘ በኋላ ‘ሃይማኖት የሰው ልጅ ለደረሰበት ሐዘን አስተዋጽኦ ያደረገ መሆኑ ፈጽሞ የማይካድ ነገር ነው። ትራክታችሁ ብዙ ነገር እንድረዳ አድርጎኛል፤ ሆኖም የበለጠ ማወቅ እፈልጋለሁ።’” በአሁኑ ጊዜ ይህ ሰው ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ ላይ ነው።
በኡራጓይ አንድ የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ሰዎችን ሲያነጋግር ለአንድ ሰው ትራክት አበረከተለት። ምሥክሩ የስብከት ሥራውን በመቀጠል በዚያ መደዳ ያሉትን ቤቶች እያንኳኳ መጀመሪያ ወዳነጋገረው ሰው ቤት ጀርባ ደረሰ። ሰውዬው ትራክቱን ይዞ እየጠበቀው እንዳለ ሲመለከት በጣም ተገረመ። ሰውዬው ትራክቱን አንብቦ ጨርሶ ስለ ነበር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ፈልጎ ነበር። ወዲያውኑ ጥናት ተጀመረለት።
ሰዎች በማሰራጨቱ ተግባር እርዳታ አበርክተዋል
በጃፓን ውስጥ አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር በ50ዎቹ ዕድሜ ወደሚገኙ አንድ ሰው ቀርቦ ትራክቱን አስተዋወቃቸው። ሰውዬው “ማየት የተሳናቸው ሰዎች ቢያጋጥሙህ ምን ታደርጋለህ?” በማለት ጠየቁት። ምሥክሩ ምን ማድረግ እንዳለበት እንደማያውቅ ተናገረ። ሰውዬው ትንሽ ቆየኝ አሉና ወደ ቤታቸው ሄዱ። የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት ይዘው መጡና እንዲህ አሉት፦ “ፓምፍሌቱ ቀደም ሲል ደርሶኛል። በጣም አስደሳችና ጠቃሚ የሆነ ትምህርት እንደያዘ ስለተሰማኝ በብሬል ጻፍኩት። እባክህ ዓይነ ስውራን ሲያጋጥሙህ በዚህ ተጠቀም።” ሰውዬው ዓይነ ስውራን ትራክቱ የያዘው መልእክት እንዳያመልጣቸው ሲሉ የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት በብሬል ለመጻፍ ብዙ ሰዓታት አጥፍተዋል።
በስሎቫኪያ ውስጥ አንድ ሰው ትራክቱ በጣም ስላስደሰተው 20 የፎቶ ኮፒ ቅጂዎች ካዘጋጀ በኋላ እነዚህን ጥቁርና ነጭ ቅጂዎች ራሱ አሰራጭቷል። በስዊዘርላንድ የሚገኝ አንድ አስፋፊ ለአንድ ቤተሰብ የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት ካበረከተ በኋላ በዚያ አፓርታማ የሚኖሩ ሌሎች ሰዎችን ለማነጋገር ወደ ላይኛዎቹ ፎቆች ወጣ። ወደ ታች ሲመለስ የዚያ ቤተሰብ አባል የሆነ አንድ ልጅ አገኘውና 19 ተጨማሪ ትራክቶች እንዲሰጠው ጠየቀው። ልጁ በሚማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ሰዎች ስላሉባቸው ችግሮችና ለችግሮቹ መፍትሔ ለማግኘት ስለ ተደረጉት ጥረቶች ጽፈው እንዲመጡ ተነግሯቸው ነበር። ልጁ ለክፍል ጓደኞቹ በሙሉ የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት አንድ አንድ ቅጂ ለመስጠት ፈልጎ ነበር።
ሁሉም ሰው እንዲደርሰው ጥረት ተደርጓል
በዘመቻው የተካፈሉ ሰዎች ሁሉም ሰው እንዲደርሰው ለማድረግ ጥረዋል። በኒው ካሊዶንያ ውስጥ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት ቅጂዎች ለማሰራጨት ራቅ ባለ ስፍራ የሚገኝ አንድ ጎሣ ወዳለበት ቦታ ሄደው ነበር። በአገልግሎት ላይ ሳሉ አንድ መንገድ ተመለከቱ። መንገዱ ሰው ረግጦት የሚያውቅ አይመስልም ነበር። ሆኖም በአካባቢው ሰዎች መኖራቸውን ለማረጋገጥ ወሰኑ። መኪናቸውን አቆሙና መንገዱን ይዘው አድካሚ የእግር ጉዞ አደረጉ። ከዚያም የተወሰኑ ጅረቶችን አቋርጠው ከሄዱ በኋላ አንድ ቤት አገኙ። እዚህ ቤት ውስጥ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ፈጽሞ ሰምተው የማያውቁ አንድ ባልና ሚስት ይኖሩ ነበር፤ እነዚህ ሰዎች የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት ወሰዱ። ከጊዜ በኋላ አስፋፊዎቹ ተመላልሶ መጠየቅ በሚያደርጉላቸው ወቅት ባልና ሚስቱ ምሥክሮቹ እቤቱ ድረስ በመኪናቸው ለመምጣት እንዲችሉ መንገዱን እንደጠገኑትና በርካታ አነስተኛ ድልድዮችን እንደሠሩ ሲመለከቱ በጣም ተደነቁ። ባልና ሚስቱ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላቸው።
በፖላንድ ውስጥ አንድ የይሖዋ ምሥክር ለአንድ የቤት ባለቤት የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት ለማበርከት ግንባታ በሚካሄድበት አንድ ቦታ ያልፍ ነበር። ተመልሶ የሕንፃ ግንባታ በሚካሄድበት ቦታ ሲያልፍ ሠራተኞቹ ተመለከቱት። ከዚያም ከሠራተኞች አንዱ ጠራውና እኛንም አትርሳን አለው። ወደ እነሱ ሄዶ ትራክቱን ሲያስተዋውቃቸው ሥራቸውን አቁመው በጥሞና አዳመጡት። የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት ቅጂዎችና መጽሔቶችን ወሰዱ፤ በሌላ ጊዜ ተመላልሶ መጠየቅ ሲደረግላቸው መጽሐፎች ወሰዱ።
በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ የመንግሥት ዜና ቁጥር 34 ቅጂዎች በብዙ ቋንቋዎች ተሰራጭተዋል። የመንግሥት ዜና የተባለው ትራክት የያዘው መልእክት ከፍተኛ ውጤት አስገኝቷል። ብዙዎች ከችግር ነፃ የሆነ ገነት እንደሚመጣ ተገንዝበዋል። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ መስጠታቸውን እንዲቀጥሉና በመጨረሻም ‘ምድርን ወርሰው በብዙ ሰላም ከሚደሰቱት ገሮች’ መካከል እንዲሆኑ እንጸልያለን።—መዝሙር 37:11
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መጽሔቶች ማሰራጨታችሁን ቀጥሉ!
በ1995 በሚያዝያና ግንቦት ወራት የተካሄደው የመንግሥት ዜና ቁጥር 34 የተባለውን ትራክት የማሰራጨት ዘመቻ በከፍተኛ ደረጃ ተሳክቷል። በተጨማሪም በእነዚህ ሁለት ወራት መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ተሰራጭተዋል። ለምሳሌ ያህል በቼክ ሪፑብሊክ የሚገኝ አንድ ወንድም የመንግሥት ዜና የተባለውን ትራክት 250 ቅጂዎችና 750 መጽሔቶችን አበርክቷል። በጓዴሎፕ ውስጥ ቅዳሜ ሚያዝያ 15 መጽሔት የማበርከት ዘመቻ የሚካሄድበት ልዩ ቀን እንዲሆን ተመርጦ ነበር። በዚያን ቀን በአገሪቱ የሚገኝ እያንዳንዱ አስፋፊ በዚህ አገልግሎት ተሳትፎ ነበር ማለት ይቻላል! በሚያዝያ ወር ስሎቫኪያ መጽሔት በማበርከት ረገድ አዲስ ከፍተኛ ቁጥር አስመዝግባለች። ሌሎች ብዙ አገሮችም ተመሳሳይ ሪፖርቶች አድርገዋል።
ታዲያ በ1996 በሚያዝያና በግንቦት ወራት መጽሔት የማበርከት ዘመቻ ለማካሄድ ለምን እቅድ አታወጡም? ጉባኤዎች መጽሔት የማበርከት ዘመቻ የሚካሄድባቸው ቀናት ሊመድቡ ይችላሉ። አስፋፊዎች በረዳት አቅኚነት ሊካፈሉ ይችላሉ። በእነዚህና በሌሎች መንገዶች መጽሔቶች በብዛት እንዲሰራጩ ማድረግ ይቻላል፤ በተጨማሪም በመንግሥት ዜና ቁጥር 34 አማካኝነት የታወጀው እጅግ አስፈላጊ የሆነ መልእክት መሰራጨቱን ይቀጥላል። ይሖዋ ባለፈው ዓመት እንዳደረገው ሁሉ በመጪው ጊዜም የምናሳየውን የቅንዓት መንፈስ እንደሚባርክ አያጠራጥርም።—2 ጢሞቴዎስ 4:22