የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w96 4/15 ገጽ 22-27
  • በይሖዋ በረከት የተገኘ ጭማሪ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በይሖዋ በረከት የተገኘ ጭማሪ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • በጣም አስደሳች ፕሮግራም
  • ለአምላክ አገልግሎት እንዲውሉ የተደረጉት ሕንፃዎች
  • ተጨማሪ ቤቶች ያስፈለጉበት ምክንያት
  • ከ90 ሳንድዝ በስተጀርባ ያለው ታሪክ
  • የይሖዋ በረከት በግልጽ ታይቷል
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
w96 4/15 ገጽ 22-27

በይሖዋ በረከት የተገኘ ጭማሪ

መስከረም 18, 1995 ምሽት ላይ አዲስ ሕንፃዎችን ለአምላክ አገልግሎት ለማዋል የተደረገው የምረቃ ፕሮግራም ይሖዋ አምላክ ምሥክሮቹ በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ያደረጉትን ጭማሪ መባረኩን አጉልቶ የሚያሳይ ነበር።

ከ6,000 በላይ የሆኑ ሰዎች አዲስ ሕንፃዎችን ለአምላክ አገልግሎት ለማዋል የተደረገውን ፕሮግራም ተከታትለዋል። አድማጮቹ ፕሮግራሙ በተካሄደበት በብሩክሊን ውስጥም ሆነ በፓተርሰንና በዎልኪል ኒው ዮርክ አቅራቢያ ባሉት ትላልቅ ሕንፃዎችና በቶሮንቶ ካናዳ አቅራቢያ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮአቸው ተሰብስበው ነበር። ከብሩክሊን ውጪ በሌሎች ቦታዎች የሚገኙት ፕሮግራሙን የተከታተሉት አንድ ላይ በተያያዙ የቴሌፎን መስመሮች አማካኝነት ነበር።

በጣም አስደሳች ፕሮግራም

በዓለም ዙሪያ ከ16,400 በላይ የሚሆኑ አባላትን ካቀፈው የቤቴል ቤተሰብ መካከል የሆኑ ቤቴላውያን ተብለው የሚጠሩ በርካታ የነፃ አገልግሎት ሠራተኞች ፕሮግራሙን ተከታትለዋል። እነዚህ አባላት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ከ78,600 በላይ በሚሆኑ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በሚታተሙበትና ለዚህ ሥራ ድጋፍ የሚሰጡ ጠቃሚ አገልግሎቶች በሚከናወኑባቸው ወደ አንድ መቶ ገደማ በሚሆኑ አገሮች ውስጥ ያገለግላሉ።

አዲስ ሕንፃዎችን ለአምላክ አገልግሎት ለማዋል የተደረገው የምረቃ ፕሮግራም በ12:30 በመዝሙርና በካርል ክላይን ጸሎት በጀመረበት ወቅት ሁሉም በከፍተኛ ጉጉት ይጠባበቁ ነበር። የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው ሎይድ ባሪ ሞቅ ባለ ስሜት እንኳን ደህና መጣችሁ ካለ በኋላ ስለ ፕሮግራሙ ዓላማ አጭር ማብራሪያ ሰጠ። አልበርት ሽሮደር የሳምንቱን መጠበቂያ ግንብ ትምህርት ከከለሰ በኋላ ዳንኤል ሲድሊክ “የቤቴል ቅዱስ አገልግሎታችን” በሚል ጭብጥ ንግግር አቀረበ። እነዚህ በፕሮግራሙ መጀመሪያ የቀረቡት ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባላት ነበሩ።

“ከ1974-1995 ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የሚሄደውን የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት መወጣት” እና “በብሩክሊን የተደረገው የቤቴል እድሳትና ግንባታ ጎላ ያሉ ገጽታዎች” በሚል ርዕስ የቀረቡት ቀጣዮቹ ሁለት የፕሮግራሙ ክፍሎች ለአምላክ አገልግሎት እንዲውሉ የተደረጉትን ሕንፃዎች ግንባታ ወይም የተገዙበትና የታደሱበትን ሁኔታ በተመለከተ ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎች ተሰጥተውባቸዋል። አስተያየቶቹ በአሁኑ ጊዜ የአንድ ሺህ ቤቴላውያን መኖሪያ በሆነው በቅርቡ በተጠናቀቀው የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ያተኮሩ ነበር። በ90 ሳንድዝ ጎዳና የሚገኘው ይህ 115 ሜትር ከፍታ ያለው መኖሪያ ከማተሚያው ፋብሪካ ሕንፃ ጋር የተያያዘ ነው።

የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት ሚልተን ሄንሽል ያቀረበው የምረቃ ንግግር የፕሮግራሙ አንዱ ክፍል ነበር። ለይሖዋ አገልግሎት ስለ ተወሰኑ ሕንፃዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌዎችን ጎላ አድርጎ ገለጸ። መዝሙር ከተዘመረ በኋላ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ኬሪ ባርበር ባቀረበው ጸሎት አዲስ ሕንፃዎችን ለአምላክ አገልግሎት ለማዋል የተደረገው የምረቃ ሥነ ሥርዓት ተጠናቀቀ። ይሁን እንጂ የፕሮግራሙ ጎላ ያሉ ገጽታዎች የትኞቹ ነበሩ?

ለአምላክ አገልግሎት እንዲውሉ የተደረጉት ሕንፃዎች

የቤቴላውያን መኖሪያ ሕንፃዎች የበላይ ተመልካች የሆነው ጆርጅ ካውች ግንቦት 2, 1969 በብሩክሊን ውስጥ የመጨረሻው የቤቴል መኖሪያ ለአምላክ አገልግሎት እንዲውል ከተደረገ በኋላ 17 የመኖሪያ ሕንፃዎች እንደታከሉ አብራራ።a ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ አዲስ የተሠሩ ቤቶች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ተገዝተው እድሳት የተደረገላቸው ሕንፃዎች ናቸው። በዚህ ወቅት ለአምላክ አገልግሎት እንዲውሉ የተደረጉት እነዚህ 17 የመኖሪያ ሕንፃዎች፣ በ1940ዎቹ ተገዝተው የቤቴል መኖሪያዎች እንዲሆኑ ተሻሽለው የተሠሩት ሁለት አነስተኛ ሕንፃዎች እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በመጋቢት 15, 1982 ለአምላክ አገልግሎት እንዲውሉ ከተደረጉ በኋላ የተሠሩት ወይም የተገዙት የፋብሪካና የቢሮ ሕንፃዎች ነበሩ።b

ለአምላክ አገልግሎት እንዲውሉ ከተደረጉት ሕንፃዎች ውስጥ ትልቁ በፈርማን ጎዳና 360 የሚገኘው ሕንፃ ነው። ሕንፃው በመጀመሪያ የተሠራው በ1928 ሲሆን መጋቢት 15, 1983 የይሖዋ ምሥክሮች ከገዙት በኋላ ሙሉ በሙሉ እድሳት ተደርጎለታል። ወለሉ 93,000 ካሬ ሜትር ወይም 9 ሄክታር የሚጠጋ ስፋት አለው። ለአምላክ አገልግሎት እንዲውሉ ከተደረጉት ሌሎች ሕንፃዎች መካከል በ175 ፐርል ጎዳና ያለው ፋብሪካና በቅርብ ዓመታት የተገነቡት ትላልቅ ጋራዦች ይገኙበታል።

ተጨማሪ ቤቶች ያስፈለጉበት ምክንያት

በ1969 የመጨረሻው የብሩክሊን መኖሪያ ሕንፃ ለአምላክ አገልግሎት እንዲውል በተደረገበት ወቅት በመላው ዓለም 1,336,112 የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ይሰብኩ ነበር። ሆኖም በ1995 ከሦስት ተኩል እጥፍ በላይ የሆኑ 5,199,895 የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ሥራ ተሳትፈዋል! ይህም በመሆኑ እያደገ የሄደውን የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ጥያቄ ለማሟላት የብሩክሊን ቤቴል ቤተሰብ ቁጥር በ1969 ከነበረበት ከ1,042 ተነሥቶ በአሁኑ ጊዜ በ22 ሕንፃዎች ውስጥ ወደሚኖሩ ከ3,360 በላይ የሆኑ ቋሚ አባላት ከፍ ብሏል!

ጆርጅ ካውች ከ1974 እስከ 1995 ባሉት ዓመታት ያስፈልጉ የነበሩት ተጨማሪ የመኖሪያ ቤቶች እንዴት እንደተገኙ አብራራ። በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ እያደገ የመጣውን የቤቴል ቤተሰብ ለማስተናገድ እንዲቻል በርካታ ፎቅ ያለውን የታወርስ ሆቴል የይሖዋ ምሥክሮች በሊዝ ተከራይተው ነበር። በታኅሣሥ 1973 በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች ፕሬዚዳንት የነበረው ናታን ኖር ማኅበሩ ‘ጥቅምት 1, 1974 ከታወርስ ሆቴል ለመልቀቅ’ እንዳቀደ ለቤቴል ቢሮና ለታወርስ አስተዳዳሪዎች ጻፈ።

በታወርስ ሆቴል የነበሩት ቤቴላውያን ከዚያ ወጥተው ሌላ የሚኖሩበት ሕንፃ ስላልነበረ ወንድም ካውች ውሳኔው በጣም አስገርሞት እንደነበር ተናገረ። ሆቴሉን የሚያንቀሳቅሱት ከማኅበሩ በሚያገኙት የክራይ ገንዘብ ስለ ነበር የታወርስ አስተዳደሪዎችም ቢሆኑ በዚህ ሁኔታ ተደናገጡ። በመጨረሻም የታወርስ ሆቴል አስተዳደር የይሖዋ ምሥክሮች ሆቴሉን እንዲገዙት ጠየቀ። “እኛ ጎረቤታችሁ ከሆንበት ጊዜ አንሥቶ እንዳየነው ቁጥራችሁ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለሚሄድ ሕንፃው ያስፈልጋችኋል” አሉ።

የማኅበሩ ተወካዮች “በሆቴሉ ውስጥ ብዙ ተከራዮች አሉ። ሆቴሉን ከገዛነው የራሳችን ሰዎች ብቻ እንዲኖሩበት እንፈልጋለን” ሲሉ መለሱ።

የታወርስ ሆቴል አስተዳደር “ተከራዮቹን ወደ ሌላ ቦታ እናዛውራቸዋለን” በማለት ቃል ገባልን። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የታወርስን ሕንፃ በተመጣጣኝ ዋጋ ገዙት። “ወንድም ኖር ደብዳቤውን የጻፈው ለምን ነበር?” በማለት ካውች በተመስጦ ያዳምጡት የነበሩትን አድማጮች ጠየቀ። “ምናልባት ራሱም ቢሆን ምክንያቱን አያውቅ ይሆናል፤ የሆነው ሆኖ የታወርስ ሆቴል ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተሸጠው በዚህ መንገድ ነበር።”

በተጨማሪም ቀደም ሲል ዝነኛው የማርጋሬት ሆቴል ይገኝበት የነበረውን 97 ኮሎምቢያ ሃይትስ የተባለውን ቦታ የይሖዋ ምሥክሮች እንዴት እንደገዙት ገልጿል። ይህ ቦታ የመጀመሪያ የቤቴላውያን መኖሪያ ካለበት ስፍራ ከመንገድ ባሻገር ይገኛል። ከዋናው መንገድ ሥር መተላለፊያ በመሥራት ቦታውን በቀላሉ ከዋናው የቤቴል ሕንፃ ጋር ማገናኘት ስለሚቻል የቦታው አቀማመጥ በጣም አመቺ ነበር። በየካቲት 1980 ሕንፃው ተሻሽሎ እየተሠራ ሳለ ተቃጠለ። ከዚያ ባለቤቱ እንደገና አዲስ ሕንፃ ለመሥራት ስላልቻለ ቦታውን ለይሖዋ ምሥክሮች ሸጠላቸው።

“በመሠረቱ እነዚህ ሕንፃዎች በሙሉ አንድ ነገር የሚጠቁም አስገራሚ ታሪክ አላቸው፤ የሚታየው ምድራዊ ድርጅቱ ሕንፃዎቹን እንዲያገኝ ይሖዋ አምላክ እንደመራው ያሳያሉ” በማለት ወንድም ካውች ገልጿል።

ከ90 ሳንድዝ በስተጀርባ ያለው ታሪክ

ከሁሉም አዲስ የሆነውና ትልቁ መኖሪያ 90 ሳንድዝ ጎዳና ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ንብረት በታኅሣሥ 1986 በገዙበት ወቅት በ160 ጄይ ጎዳና የነበረው ትልቅ ፋብሪካ ወደዚያ ተዛወረ።c ፋብሪካው ፈረሰና ነሐሴ 30, 1990 እዚያ ቦታ ላይ 30 ፎቅ ያለው የመኖሪያ ሕንፃ ለመሥራት እንደ ተፈቀደ ለቤቴል ቤተሰብ ማስታወቂያ ተነገረ።

የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ቴዎዶር ጃራዝ በመራው ቃለ ምልልስ ላይ የማኅበሩ የብሩክሊን ፋብሪካ የበላይ ተመልካች ማክስ ላርሰን በ90 ሳንድዝ ጎዳና የሚገኘውን ሕንፃ ለመሥራት እንዴት ፈቃድ እንደ ተገኘ አብራራ። ወንድም ላርሰን በ1965 በጣም ወሳኝ የሆነ ነገር እንደ ተፈጸመ ገለጸ።

በወቅቱ ማኅበሩ በዚያ ካሉት ሌሎች ፋብሪካዎች አጠገብ ባለ አሥር ፎቅ ፋብሪካ ለመሥራት ቢፈልግም በአካባቢው ከሁለት ፎቅ በላይ መሥራት አይፈቀድም ነበር። አንድ መሐንዲስ አዲስ ሊሠራ ለታሰበው ፋብሪካ ፕላኑን ለመንደፍ ቢስማማም እንኳ “ፕላኖቹን ለቦርዱ ሳቀርብ ችግር ውስጥ ለመግባት አልፈልግም” አለ። የገማቾች ቦርድ ለዚያ አካባቢ ያወጣቸውን የአከላለል ሥርዓቶች ፈጽሞ እንደማይለውጥ አምኖ ነበር። የሕንፃው ፕላን ተቀባይነት ሲያገኝ በመገረም “እንዴት ሊፈቀድላችሁ ቻለ?” በማለት ጠይቋል።

ላርሰን በመቀጠል ይህ የሆነው አካባቢው እንደገና ሲከለል የነበረን ባለ አሥር ፎቅ ሕንፃንና 160 ጄይ ጎዳና ሕንፃን ጨምሮ በአቅራቢያው ያሉ ሌሎች አካባቢዎች ጭምር እንደገና በመከለላቸው ነው። በተጨማሪም የሚያስገርመው ይህ አካባቢ እንደገና መከለሉ ሆቴል ለመሥራት የሚያስችል ሆነ። ሆኖም ቢያንስ ከ25 ዓመታት በኋላ አዲስ የቤቴላውያን መኖሪያ ሕንፃ የምንሠራበትን ቦታ መፈለግ እስከ ጀመርንበት ጊዜ ድረስ ይህንን ማንም እንዳላስተዋለው ላርሰን ገልጾ ነበር። ከዚያም በዚህ አካባቢ መሥራት የሚፈቀደው ምን ዓይነት ሕንፃ እንደሆነ ታወቀ።

ወንድም ላርሰን ምን እንደ ተፈጸመ ሲናገር እንዲህ አለ፦ “30 ፎቅ ያለው መኖሪያ ለመሥራት ፕላን አዘጋጅተን ፕላኑን ወደ ማዘጋጃ ቤት ስንወስደው ‘እዚያ ቦታ የመኖሪያ ሕንፃ ልትሠሩ አትችሉም። ቦታው ለፋብሪካዎች መሥሪያነት ብቻ የተከለለ ከመሆኑም በተጨማሪ የገማቾች ቦርድ ደንቡን ሊለውጥ አይፈልግም’ ተባልን።

“‘መለወጥ አያስፈልጋቸውም። ቦታው ለሆቴል መሥሪያ የተመደበ ነው’ በማለት ለባለ ሥልጣኖቹ ነገርናቸው። መረጃዎቹን ሲመለከቱ ማመን አቃታቸው! 30 ፎቅ ያለውን ሕንፃ ለመሥራት የቻልነው በዚህ መንገድ ነበር” በማለት ላርሰን ሐሳቡን አጠቃለለ።

የይሖዋ በረከት በግልጽ ታይቷል

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ መዝሙራዊ “እግዚአብሔር ቤትን ካልሠራ፣ ሠራተኞች በከንቱ ይደክማሉ” ብሏል። (መዝሙር 127:1) ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲሠሩት ያዘዘውን ዓለም አቀፍ የስብከትና የማስተማር ሥራ በቅልጥፍና ለማከናወን እንዲችሉ የይሖዋ ምሥክሮችን የግንባታ ሥራዎች ይሖዋ እንደባረከ በግልጽ ለመረዳት ይቻላል።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

መስከረም 18, 1995 ፕሮግራሙን ለመስማት መብት ያገኙ ሰዎች በይሖዋ አገልጋዮች ዋና መሥሪያ ቤት እንዲህ ዓይነቱን በረከት በግልጽ በማየታቸው ተደስተዋል። የይሖዋ ሕዝቦች ትእዛዙን ማድረጋቸውን በቀጠሉ መጠን ያለ ማቋረጥ የእርሱን በረከት እንደሚያገኙ እርግጠኞች ሊሆኑ ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ሰኔ 15, 1969 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 379-82 ተመልከት።

b ታኅሣሥ 1, 1982 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 23-31 ተመልከት።

c የታኅሣሥ 22, 1987 የእንግሊዝኛ ንቁ! ከገጽ 16-18 ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

90 ሳንድዝ ጎዳና • 1995

[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ለአምላክ አገልግሎት እንዲውሉ የተደረጉ ሌሎች የመኖሪያ ሕንፃዎች

97 ኮሎምቢያ ሃይትስ • 1986

ቦዘርት ሆቴል፣ 98 ሞንታጉ ጎዳና • 1983

34 ኦሬንጅ ጎዳና • 1945

ስታንዲሽ ሆቴል፣ 169 ኮሎምቢያ ሃይትስ • 1981

67 ሊቪንግስተን ጎዳና • 1989

108 ጆሬልሞን ጎዳና • 1988

ታወርስ ሆቴል 79-99 ዊሎው ጎዳና • 1975

[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

175 ፐርል ጎዳና • 1983

69 አዳምስ ጎዳና • 1991

360 ፈርማን ጎዳና • 1983

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ