በታላቁ ስም የተጠቀመበት ምክንያት
“የትርጉም ሥራዬን ከገመገሙት ሰዎች አንዱ እንደተናገረው ከሆነ ለብዙ መቶ ዘመናት ይሖዋ ለሚለው ቃል ምትክ ሆኖ ሲያገለግል በቆየው ‘ጌታ’ በሚለው በተለመደው ቃል መጠቀም ሲገባኝ ‘ይሖዋ’ የሚለውን ቃል በማስገባቴ ኃጢአት ሠርቻለሁ።”
ይህ ጄ ጄ ስቲዋርት ፐሮን ለመጀመሪያ ጊዜ በ1864 በታተመው የመዝሙር መጽሐፍ ትርጉሙ ሁለተኛ እትም መቅድም ላይ የሰጠው አስተያየት ነበር። ገምጋሚው ሐምሌ 2, 1864 በወጣው ሳተርዴይ ሪቪው ጋዜጣ ላይ በጻፈው አስተያየት አይሁዳውያንም ሆኑ የክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በስሙ መጠቀማቸውን ስላቆሙ በትርጉሙ ውስጥ የአምላክን ስም መጠቀሙን ተቃውሞ ነበር። ይሖዋ የተባለው ስም ከአይሁዳውያን ጋር በቅርብ የተቆራኘ እንደሆነና “ከተወሰነ አካባቢ ወይም ብሔር ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን” እንደ “ጌታ” ወይም “አምላክ” ያሉትን ሌሎች ቃላት መጠቀም እንደሚገባ ተናገረ።
ፐሮን አምላክ ለሰዎች ከገለጸላቸው እውነት ውስጥ “አንድም ፊደል እንኳ ለማውጣት አልፈልግም” በማለት በእነዚህ መከራከሪያ ነጥቦች እንደማይስማማ ገልጿል። የዕብራይስጡን መለኮታዊ ስም “ጌታ” ብለው የተረጎሙት ተርጓሚዎች በሁለቱ የዕብራይስጥ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት ለማስቀመጥ አልቻሉም በማለት በትክክል ተከራክሯል።
ከዚህም በላይ መለኮታዊው ስም ወደ ቀድሞው ቦታው መመለሱን የደገፉ ብቃት ያላቸው ምሁራን እንዳሉ ፐሮን በግልጽ አስረድቷል። ታዋቂው የእንግሊዝ ባለ ቅኔ ሳሙኤል ቴይለር ኮለሪጅ የጻፉትን የሚከተለውን ሐሳብ ጠቅሷል፦
“በሴፕቱጀንት አማካኝነት ዕብራይስጡን ወደ እንግሊዝኛ መተርጎም መቀጠል ያስፈለገው ለምንድን ነው? ይሖዋ የተባለውን የዕብራይስጥ ቃል አልተቀበልንምን? በሴፕቱጀንት ትርጉም ውስጥ Κύριος ወይም ጌታ ተብሎ የተተረጎመው ቃል ቁጥር ስፍር ለሌለው ጊዜ ለሚገኘው ይሖዋ ለሚለው የዕብራይስጥ ቃል የግሪክኛ ምትክ አይደለምን? ታዲያ የመጀመሪያውን ቃል ወደ ቀድሞ ቦታው የማንመልሰው፣ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ይሖዋ የሚለውን ቃል ይሖዋ ብለን በታማኝነት የማንተረጉመውና አዲስ ኪዳን ከብሉይ ኪዳን በሚጠቅስበት በእያንዳንዱ ጥቅስ ላይ የዕብራይስጡን ቃል የማንጠቀመው ለምንድን ነው?”
ምንም እንኳ ፐሮን የአምላክ ስም አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ትክክለኛ አነባበብ እንደማይታወቅ ቢያምንም የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝሯል፦ “የአይሁድ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ስም መጠቀም ያቆመው በአጉል እምነት የተነሣ ብቻ ከሆነና የእኛ [እንግሊዝኛ] ትርጉሞች ከግሪክኛ የላቲን ትርጉሞች በጭፍን በመገልበጣቸው ምክንያት ስሙ ከጠፋ እነዚህ ምክንያቶች በመጀመሪያው ቃል እንዳንጠቀም የሚያደርጉ በቂ ምክንያቶች አይሆኑም።” ፐሮን “ይሖዋ” በሚለው ቃል ለመጠቀም የመረጠው ቃሉ በስፋት የሚታወቅ በመሆኑ ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሌሎች ብዙ ዘመናዊ ትርጉሞችም በመለኮታዊው ስም ተጠቅመዋል። የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ይሖዋ የሚለውን ስም በዕብራይስጡና በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከ7,200 ጊዜ በላይ ተጠቅሞበታል።
ፐሮን በመዝሙር መጽሐፍ ትርጉሙ ውስጥ “በፈሊጣዊ አነጋገሮቹም ሆነ በሐረጎቹ የስዋሰው አሰካክ የዕብራይስጡን የአጻጻፍ ስልት አጥብቆ” ለመከተል ሞክሯል። መዝሙር 69 ቁጥር 5 እና 6ን በሚተረጉምበት ወቅት እንዲህ በማለት “አምላክ” (ኤሎሂም)፣ “ጌታ” (አዶናይ) እና “ይሖዋ” በሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት መግለጽ አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል፦ “አቤቱ፣ አምላክ [ኤሎሂም] ሆይ፣ አንተ ስንፍናዬን ታውቃለህ፣ ጥፋቴም ከአንተ አልተሰወረም። አቤቱ፣ የሠራዊት ጌታ [አዶናይ] ይሖዋ (አምላክ) ሆይ፣ ተስፋ የሚያደርጉህ በእኔ አይፈሩ፤ የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ የሚሹህ በእኔ ምክንያት አይነቀፉ።”