“ይህ የይሖዋ ሥራ ነው”
እነዚህ ቃላት ሞንቴሬ በምትባል የሜክሲኮ ከተማ ውስጥ በሚታተም ኤል ኖርቴ በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ የአንድ ዓምድ ርዕስ ናቸው። ዓምዱ የሚናገረው አዲስ ስለ ተሠራ ስለ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ነው።
ሞንቴሬ በሰሜናዊ ሜክሲኮ የምትገኝ 2,300,000 ነዋሪዎች (በከተማዋ ዳር ዳር የሚኖሩትን ጨምሮ) ያሏት ከተማ ስትሆን 19,200 የመንግሥቱ አስፋፊዎች አሏት። የይሖዋ ምሥክሮች ጉልበታቸውን አስተባብረው አንድ ዓመት ተኩል በሚያክል ጊዜ ውስጥ ምቾት ያላቸው 3,000 ወንበሮች እንዲሁም የአየር ማቀዝቀዣ ያለው ውብና ተስማሚ የሆነ የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ ሠሩ። የይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር አካል አባል የሆነ ወንድም አዳራሹን ለአምላክ አገልግሎት ለማዋል የቀረበውን ንግግር ሲሰጥ የአካባቢው ምሥክሮች ተደስተው ነበር። በፕሮግራሙ ውስጥ በሞንቴሬ የነበረውን የሥራ እንቅስቃሴ የዳሰሰ አጭር ታሪክ ከመቅረቡም በተጨማሪ በግንባታው ተሳትፎ ላደረጉ ወንድሞች ቃለ መጠየቅ ተደርጎላቸው ነበር። ከዚያም በስብሰባው ላይ የተገኙ 4,500 ሰዎች አዳራሹን ለአምላክ አገልግሎት ለማዋል የቀረበውን ንግግር አዳምጠዋል።
“የበለጠ፣ ሰፊና የተሻለ የመንግሥት አዳራሽ እንዲሁም የትልቅ ስብሰባ አዳራሽ” በሚለው ዘመቻ ሜክሲኮ ውስጥ በቅርቡ ከተሠሩት የትልቅ ስብሰባ አዳራሾች ይህ ሦስተኛው ነው።
ሜክሲኮ ውስጥ ያሉት አስፋፊዎች 443,000 ሲሆኑ በ1995 በመታሰቢያው በዓል 1,492,500 ሰዎች ተገኝተው ነበር። ስለዚህ በሞንቴሬ እንደተሠራው ዓይነት የትልቅ ስብሰባ አዳራሾች መለኮታዊውን ዓላማ ለማራመድ ያገለግላሉ።