የ1996 “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” የአውራጃ ስብሰባ
በጥንት ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች በየዓመቱ ሦስት ዋና ዋና በዓላት ያከብሩ ነበር። በጊዜያችንም በይሖዋ ስም የሚጠሩት ሕዝቦች በዓመት ሦስት ጊዜ አንድ ላይ በመሆን የሚደሰቱባቸው ስብሰባዎች ያደርጋሉ። አንድ ቀን በሚወስደው የልዩ ስብሰባ ቀን፣ ሁለት ቀን በሚፈጀው የወረዳ ስብሰባና ለሦስት ወይም ለአራት ቀናት በሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ይገናኛሉ። በዚህ ዓመት የሚደረገው የአውራጃ ስብሰባ “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” በሚል ጭብጥ ላይ የተመሠረተ ነው።
እንዴት ያለ ተስማሚ ጭብጥ ነው! አምላካችን ይሖዋ ‘የሰላም አምላክ’ ነው። አዎን፣ “ሰላም የሚሰጥ አምላክ ነው።” መሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‘የሰላም ገዢ’ ከመሆኑም በተጨማሪ የይሖዋ አገልጋዮች የሚናገሩት መልእክት ስለ አምላካዊ ሰላም የሚገልጽ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:9፤ ሮሜ 15:33 አዓት፤ ኢሳይያስ 9:6፤ ናሆም 1:15) በስብሰባው ላይ የሚገኙ ሁሉ አምላካዊ ሰላም ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንዲገነዘቡ የሚያደርግ ግሩም ፕሮግራም ተዘጋጅቷል።
በዚህ ዓመት በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ 198 የአውራጃ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። እርስዎ በሚኖሩበት አካባቢ አንድ የአውራጃ ስብሰባ መኖሩ አይቀርም። ስብሰባው መቼና የት እንደሚደረግ በአካባቢዎ ከሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጠይቀው በስብሰባው ላይ ለመገኘት ለምን ዕቅድ አያወጡም? እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ለማግኘት ለሚፈልጉ ሁሉ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ሞቅ ያለ ግብዣ እናቀርብላቸዋለን።