እውነተኞቹ የሰላም መልእክተኞች እነማን ናቸው?
ግንቦት 31, 1996 የዜና ምንጮች የሰላም መልእክት ስለ መሰላቸው አንድ ነገር አወጁ። ከዚህ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ለመሆን የተመረጡት ቤንያሚን ኔታንያሁ “ፍልስጤምን ጨምሮ በእስራኤልና በአጎራባቾቿ አገሮች መካከል ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የተጀመረውን የሰላም ሂደት እንደሚገፉበት” መናገራቸውን የሚያረጋግጥ ይፋዊ መግለጫ ወጥቶ ነበር።
በዜና ማሰራጫዎች ብዙ የተባለለት የኔታንያሁ መመረጥ ብዙዎችን በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ሰላም እውን ሊሆን ይችላል ብለው እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። እንዲህ ከሆነ ሌሎች መንግሥታትም ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን በመተው የእስራኤልን አርአያ ይከተሉ ይሆን?
እርግጥ ሰላምን ከማምጣት ይልቅ የሰላም ተስፋ መስጠት ቀላል ነው። ብዙዎች ይህን በመገንዘባቸው ሰላም ሊመጣ ስለ መቻሉ ተጠራጥረዋል። ሄሚ ሻሌቭ የተባሉ ጋዜጠኛ እንዳሉት “በአሁኑ ወቅት ከእስራኤል ሕዝብ ውስጥ ግማሹ የተሐድሶ ዘመን ቀርቧል ብለው የሚያምን ሲሆን ግማሾቹ ደግሞ እስራኤል ብዙ መከራ ወዳለበት ሊያመልጡት ወደማይቻል አስፈሪ ረመጥ ውስጥ እየገባች ነው ብለው ያምናሉ።” “አንዳንዶች ሲደሰቱ ሌሎች ያለቅሳሉ” ሲሉ ጋዜጠኛው ሁኔታውን በአጭሩ ገልጸውታል።
እንግዲህ የሰው ልጅ ሰላም ለማምጣት የሚያደርገው ጥረት ሁኔታ ይኸው ነው። የአንድ መሪና የደጋፊዎቹ ድል ለተቃዋሚው ቡድን ሽንፈት ማለት ነው። ሰዎች በሆነ ነገር ሳይረኩ ሲቀሩ ይበሳጫሉ፤ ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ወደ ዓመፅ ይመራል። በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በላቲን አሜሪካ፣ በምሥራቅ አውሮፓም ይሁን በሌላ ቦታ የሰው ልጆች ሰላም ለማምጣት የሚያደርጓቸው ጥረቶች ምን ጊዜም የማይጨበጡ ናቸው።
በቅርቡ እውነተኛ ሰላም ይመጣል!
ስለ መካከለኛው ምሥራቅ ሰላም የሚወራው ወሬ በተጧጧፈበት ወቅት ሌላ የሰላም መልእክት ተደምጦ ነበር። ይህ የሰላም መልእክት ከፍተኛ ቅስቀሳ የተደረገለት የፖለቲካ ንግግር አይደለም። በብሔራት መካከል በሚደረግ ስምምነት የሚመጣ ሰላምም አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይህ መልእክት በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ብቻ ስለሚመጣ ሰላም የሚገልጽ ነበር። ይህ መልእክት የተደመጠው የት ነበር? የይሖዋ ምሥክሮች በ1996/97 በመላው ዓለም ባካሄዷቸው “የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” የተሰኙ ከ1,900 በላይ የሆኑ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ነበር።
በእነዚህ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ማንኛውም ሰብዓዊ መንግሥት እውነተኛ ሰላምና ደህንነት ሊያመጣ እንደማይችል ግልጽ ተደርጓል። ለምን አይችልም? ምክንያቱም ይህን ሰላም ማምጣት በየቀኑ ሰላማችንን የሚያውኩ ነገሮችን ማጥፋትን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው። እውነተኛ ሰላም ማለት በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት ሲነሡ ጦርነት ወይም የዓመፅ ድርጊት ይኖራል ከሚል ስጋት ነፃ መሆን ማለት ነው። ወንጀል፣ በርን መቆለፍ፣ በመንገድ ላይ ሲጓዙ መፍራትና የቤተሰብ መለያየት የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ ማለት ነው። ይህን ሁሉ ሊያደርግ የሚችለው የትኛው ምድራዊ መንግሥት ነው? እንዲህ አደርጋለሁ ብሎ ቃል እንኳ ሊገባ የሚደፍር የትኛው ምድራዊ መንግሥት ነው?
ሆኖም የአምላክ መንግሥት እነዚህን ነገሮች ሊያመጣ ይችላል፤ ደግሞም ያመጣል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ተስፋ ይሰጣል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” (ራእይ 21:3, 4) ይህ በሥቃይ ላይ ላለው የሰው ዘር እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል!
ይሖዋ አምላክ የሰጠው ተስፋ ከንቱ ተስፋ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም፣ ይጸጸትም ዘንድ የሰው ልጅ አይደለም። እርሱ ያለውን አያደርገውምን? የተናገረውንስ አይፈጽመውምን?” (ዘኁልቁ 23:19) አዎን፣ አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ይፈጸማሉ። ይህም በእሱ ጎን ለተሰለፉ ሰዎች ሁሉ በረከት የሚያስገኝ ይሆናል።
የአምላክ የሰላም መልእክተኞች
የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት በቅንዓት በመስበካቸው በሰፊው የታወቁ ናቸው። በየዓመቱ በድምሩ በቢልዩን የሚቆጠር ሰዓት በማጥፋት የመጽሐፍ ቅዱስን አስደሳች መልእክት ለሌሎች ሰዎች ያዳርሳሉ። ይህም “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት ፍጻሜ ነው። (ማቴዎስ 24:14) የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሰራጩት መልእክት የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ መሆኑን ስለሚገልጽ በእርግጥም “ምሥራች” ነው። በተጨማሪም ወደፊት አስተማማኝ ተስፋ እንዲኖረን የሚያደርግ መልእክት ነው!
የአምላክ መንግሥት አሁንም እንኳ ቢሆን በዜጎቹ መካከል እውነተኛ የሰላም ማሰሪያና ወንድማማቻዊ መዋደድ እንዲኖር አድርጓል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መሠረታዊ የእውነተኛ ክርስትና ብቃት አሟልተው ለመኖር ጥረት ያደርጋሉ። በዚህም ምክንያት አይሁዳውያንን ከአረቦች፣ ክሮአቶችን ከሰርቦች እንዲሁም ሁቱዎችን ከቱትሲዎች ጋር አንድ ያደረገ አስደናቂ ወንድማማችነት አላቸው። በአሁኑ ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች በሕልማቸው ብቻ ሊያዩት የሚችሉትን እንዲህ ዓይነቱን ሰላም በመላው ዓለም የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ጨብጠውታል።
“የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ፕሮግራም ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመላለሳችንና የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበካችንን እንድንቀጥል ከፍተኛ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ካደረጉት ከዚህ ስሜት ቀስቃሽ የሆነ የሦስት ቀናት የአውራጃ ስብሰባ የተገኘውን የሚቀጥለውን ሪፖርት እንድታነብ እንጋብዝሃለን።