የአንባብያን ጥያቄዎች
ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ አርማጌዶን መቼ እንደሚመጣ ያውቃልን?
ያውቃል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ይመስላል።
አንዳንዶች ጥያቄው እንኳ በመነሳቱ ይገረሙ ይሆናል። ይህም የሆነው ምናልባት ኢየሱስ በማቴዎስ 24:36 ላይ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” በማለት ስለተናገረ ሊሆን ይችላል። “ልጅም ቢሆን” የሚለውን ሐረግ ልብ በል።
ይህ ጥቅስ “ንገረን፣ ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?” በማለት ሐዋርያቱ ላቀረቡለት ጥያቄ ኢየሱስ የሰጠው መልስ ክፍል ነው። (ማቴዎስ 24:3) በዘመናችን ታዋቂ የሆነው “ምልክት” ስላካተታቸው ክስተቶች በተናገረው ትንቢት ላይ ጦርነት፣ የምግብ እጥረት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የእውነተኛ ክርስቲያኖች መሰደድና መገኘቱን የሚጠቁሙ ሌሎች ሁኔታዎች በምድር ላይ እንደሚከሰቱ ገልጿል። በዚህ ምልክት አማካኝነት ተከታዮቹ መጨረሻው እንደቀረበ ያውቃሉ። መጨረሻው መቅረቡን እንዴት ማወቅ እንደሚቻል በምሳሌ ሲያስረዳ በለስ ሲያቆጠቁጥ በጋ መቅረቡን እንደሚያሳይ ተናገረ። በመቀጠልም “እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ” አለ።—ማቴዎስ 24:33
ሆኖም ኢየሱስ መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ ለይቶ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ በማቴዎስ 24:36 ላይ የሚገኘውን ተናገረ። ጥቅሱ የተወሰደው በ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም ሲሆን የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም እና ሌሎች አያሌ ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱሶች ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ ያስተላልፋሉ። በአንዳንድ የጥንት ትርጉሞች ላይ ግን “ልጅም ቢሆን” የሚለው ሐረግ አይገኝም።
ለምሳሌ የካቶሊኩ ዱዌይ ቨርሽን “ስለዚያች ቀንና ሰዓት ግን ከአባት በቀር የሰማይ መላእክት ቢሆኑ ወይም ሌላ ማንም አያውቅም” ይላል። የኪንግ ጄምስ ቨርሽን መጽሐፍ ቅዱስም ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው። “ልጅም ቢሆን” የሚለው ሐረግ በማርቆስ 13:32 ላይ ሰፍሮ እያለ እዚህ ጥቅስ ላይ ያልገባው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚህ ትርጉሞች በ17ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሲዘጋጁ ተርጓሚዎቹ የተጠቀሙባቸው የብራና ጽሑፎች በዚህ ሐረግ አይጠቀሙም ነበር። ከዚያ ወዲህ ግን ረጅም ዕድሜ ያላቸው የግሪክ የብራና ጽሑፎች ተገኙ። እነዚህ የማቴዎስ ወንጌል የመጀመሪያ ቅጂ ወደተጻፈበት ጊዜ የሚቃረቡ የብራና ጽሑፎች በማቴዎስ 24:36 ላይ “ልጅም ቢሆን” የሚለውን ሐረግ ይዘዋል።
የሚያስገርመው የካቶሊክ ጀሩሳሌም ባይብል “ልጅም ቢሆን” የሚለውን ሐረግ ከመጨመሩም በላይ በግርጌ ማስታወሻው ላይ የላቲኑ ቩልጌት ይህን ሐረግ ያስቀረው “ከሃይማኖታዊ ትምህርት ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ሳይሆን አይቀርም” ይላል። ሊሆን የሚችል ነው! በሥላሴ የሚያምኑ ተርጓሚዎች ወይም ገልባጮች ኢየሱስ አባቱ የሚያውቀውን ሁሉ እንደማያውቅ የሚጠቁመውን ሐረግ ለማውጣት ተፈትነው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስና አባቱ አንድነት በሦስትነት ያለው አምላክ ክፍል ከሆኑ መጨረሻው መቼ እንደሆነ እንዴት አያውቅም?
ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ በ ቢ ኤም ሜስገር የተዘጋጀው ኤ ቴክስቹዋል ኮሜንታሪ ኦን ዘ ግሪክ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “‘ልጅም ቢሆን’ የሚሉት ቃላት ከጊዜ በኋላ የተዘጋጀውን የባይዛንታይን ጽሑፍ ጨምሮ በአብዛኞቹ የማቴዎስ ወንጌል ማረጋገጫዎች [የብራና ጽሑፎች] ላይ አይገኝም። በሌላ በኩል ዋነኛ ተጠቃሽ በሆኑት በአሌክሳንድሪያ፣ በዌስተርንና በሲዛሪያን ጽሑፎች ውስጥ ይህ ሐረግ ይገኛል። እነዚህ ቃላት [ማርቆስ 13:32 ላይ] ተጨምረዋል ብሎ ከማሰብ ይልቅ በሃይማኖታዊ ትምህርት ላይ ችግር ስለሚፈጥሩ ከማቴዎስ 24:36 ውስጥ ተሰርዘዋል ማለት ይሻላል”።—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
እነዚህ የጥንት የብራና ጽሑፎች ‘ዋነኛ ተጠቃሾች’ የመጨረሻውን ሰዓት መጀመሪያ ማን ቀጥሎ ማን እንደሚያውቅ የሚያሳየውን ሐረግ ይደግፋሉ። ቅደም ተከተሉ ከአባት ብቻ በቀር ልጅም ቢሆን መላእክትም ቢሆኑ የሚያውቅ የለም ይላል። ይህም በማቴዎስ 20:23 ላይ ከሚገኙት የኢየሱስ ቃላት ጋር ይስማማል። እዚህ ላይ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው እርሱ ሳይሆን አባቱ እንደሆነ ተናግሯል።
ስለዚህ ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ‘የዓለም መጨረሻ’ መቼ እንደሆነ እንደማያውቅ ራሱ የተናገራቸው ቃላት ያሳያሉ። በአሁኑ ጊዜ ያውቃልን?
ራእይ 6:2 ኢየሱስን በነጭ ፈረስ ላይ እንደተቀመጠ ጋላቢ እንዲሁም ‘ድል እየነሣ እንደወጣና ሙሉ በሙሉ ድል እስኪነሳ ድረስ ግልቢያውን እንደሚቀጥል’ አድርጎ ይገልጸዋል። ቀጥለው የወጡት ፈረሰኞች በ1914 ከተጀመረው አንደኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ያየናቸውን ጦርነቶች፣ ችጋርና መቅሰፍቶች ያመለክታሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ በ1914 የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ እንደሆነና በቅርቡ በምድር ላይ ባሉ ክፉዎች ላይ የሚከፈተውን ጦርነት በግንባር ቀደምትነት እንደሚመራ ያምናሉ። (ራእይ 6:3-8፤ 19:11-16) ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በአምላክ ስም ድል እንዲነሣ ሥልጣን ስለተሰጠው መጨረሻው መቼ እንደሚመጣና ‘ሙሉ በሙሉ ድል የሚነሣው መቼ’ እንደሆነ አባቱ ነግሮታል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ይመስላል።
በምድር ላይ የምንኖረው ግን ቀኑ ስላልተነገረን “ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ፤ ትጉ፤ . . . ለእናንተም የምነግራችሁን ለሁሉ እላለሁ፤ ትጉ” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት አሁንም በእኛ ላይ ይሠራሉ።—ማርቆስ 13:33-37