በኢኳቶሪያል ጊኒ ውስጥ በመታየት ላይ ያለ እድገት
አንድ መንገደኛ የተሳፈረበት አውሮፕላን በኢኳቶሪያል ጊኒ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ከሁሉ አስቀድሞ ስሜቱን የሚማርኩት በዚያ የሚገኙ ልምላሜን የተላበሱ ዛፎች ናቸው። የአውሮፕላን መንደርደሪያው በጣም ግዙፍ በሆኑ ዛፎች የተከበበ ነው፤ ከዛፎቹ ግዙፍነት የተነሳ የአውሮፕላን ማረፊያው ሕንጻዎች ትንንሽ መስለው ይታያሉ። በ1980ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ላይ ይዘንብ በነበረው ከፍተኛ ዝናብና ዓመቱን ሙሉ በነበረው ጥሩ የአየር ንብረት የተነሳ ከባህር ዳርቻዎች አንስቶ እስከ ተራሮች ጫፍ ድረስ አካባቢው በለምለም አረንጓዴ ተክሎች የተሸፈነ ነው።
በኢኳቶሪያል ጊኒ ውስጥ ሌላም ከፍተኛ እድገት ይኸውም ‘አምላክ የሚሰጠው እድገት’ እየታየ ነው። (ቆላስይስ 2:19) የፊልጶስን እርዳታ ፈልጎ እንደነበረው ኢትዮጵያዊ ባለ ሥልጣን ሁሉ በዚህች አገር ያሉ ብዙ ሰዎች የቅዱሳን ጽሑፎችን እውቀት ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። (ሥራ 8:26-39) በዚህች አገር ውስጥ በመንገድ ላይ አንድ ሰው አንድን የይሖዋ ምሥክር ቀርቦ በማነጋገር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠናው መጠየቅ የተለመደ ነገር ነው። በኢኳቶሪያል ጊኒ ውስጥ የሚገኙት ወደ 325 የሚጠጉ ምሥክሮች ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እያስጠኑ ነው።
ቀደም ባሉት ዘመናት ዘሩን መዝራት
በአፍሪካ ውስጥ ካሉት አገሮች በጣም አነስተኛ የሆነችው ኢኳቶሪያል ጊኒ ከናይጄሪያና ከካሜሩን በስተ ደቡብ የምትገኝ አገር ናት። (ካርታውን ተመልከት።) ምሥራቹ በዚህች አገር ውስጥ በመጀመሪያ የተሰበከው በካካዎ እርሻዎች ውስጥ ለመሥራት በመጡ የናይጄሪያ ምሥክሮች አማካኝነት ነበር። ምንም እንኳ በርከት ያሉ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤዎች ተቋቁመው የነበረ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ እነዚህ ወንድሞች ወደ ናይጄሪያ ሲመለሱ ጉባኤዎቹ ተበታተኑ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ አገሪቷ በ1968 ነፃ ስትወጣ ሦስት ጥንድ ባልና ሚስት የሆኑ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሚስዮናውያን በዚች አገር ተመደቡ። በነበረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት ለረጅም ጊዜ መቆየት ባይችሉም እንኳ የምሥክርነት ሥራቸው ጥሩ ውጤት አስገኝቷል።
ከሚስዮናውያኑ አንዱ የሆነው ሳንቲያጎ ረጅምና ፈርጣማ የሆነውንና የአካባቢው ሰዎች ጉልበተኛው እያሉ የሚጠሩትን ብዌናቬንቹራን አነጋገረው። ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ያለው የሃይማኖት ሰው የነበረ ቢሆንም ግልፍተኛ ነበር። አንድ ሰው ትንሽ ከተናገረው ከመማታት አይመለስም። ቡና ቤት ውስጥ እሱ በሚናደድበት ጊዜ ሰዉ ሁሉ የእሱን ቡጢ ላለመቅመስ በመስኮት ሳይቀር እየዘለለ ይወጣል። ከሳንቲያጎ ጋር ይነጋገር በነበረበት ጊዜም እንኳ ሳንቲያጎ ለተናገረው ነገር አሳማኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ሊያቀርብለት ባይችል ኖሮ ሊመታው ተዘጋጅቶ ነበር። ‘እንደ እኔ ያለውን ኃያል ሰው ማንም ሊያታልል አይችልም’ የሚል ስሜት አድሮበት ነበር። የሰማው ነገር በተለይ ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ስለሚኖረው የዘላለም ሕይወት ተስፋ የተነገረው ነገር ስሜቱን በጣም ስለማረከው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማማ።
ብዌናቬንቹራ በጥናቱ እየገፋ ሲሄድ በገነት ውስጥ ለዘላለም ለመኖር ያለው ፍላጎት እየጨመረ ከመሄዱም በላይ እንዲህ ዓይነቱን ሽልማት ለማግኘት ሕይወቱን ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ማስማማት እንዳለበት ተረዳ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘በክፉ ፋንታ ክፉ’ መመለስ እንደሌለባቸው በመገንዘቡ የግልፍተኛነት ባሕሪውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመረ።—ሮሜ 12:17
አንድ ቀን ቡና ቤት ውስጥ ሳያውቅ አንድ ሰው እየጠጣበት የነበረውን ብርጭቆ ሲሰብር ትልቅ ፈተና አጋጥሞት ነበር። ሰውየው ተናደደና መታው። ወዲያውኑ በቡና ቤቱ ውስጥ የነበሩት ሰዎች ጠብ ይነሳል ብለው በማሰብ ተበታተኑ። ሆኖም ብዌናቬንቹራ በትህትና ለሰበረው ብርጭቆ በመክፈል ለሰውየው የሚጠጣውን ነገር እንደገና ካዘዘለት በኋላ ለፈጸመው ጥንቃቄ የጎደለው ድርጊት ይቅርታ ጠየቀው። በአካባቢው የሚኖሩት ሰዎች እንዲህ ዓይነት ለውጥ እንዲያሳይ ያደረገው መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቱ እንደሆነ ሲገነዘቡ ብዙዎቹ ከእሱ ጋር ጥናት ለመጀመር ፈቃደኞች ሆኑ። ብዌናቬንቹራ በተጠመቀበት ወቅት አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ነበሩት። ላለፉት አምስት ዓመታት ሽማግሌ ሆኖ አገልግሏል፤ ሰዎች አሁንም ለቀልድ ያህል ጉልበተኛው እያሉ ይጠሩታል።
“በመንፈሳዊ የጎደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው”
በ1970ዎቹ ዓመታት የአገሪቱ ተወላጆች የሆኑ ጥቂት ምሥክሮች የሚችሉትን ያህል መስበክና አንድ ላይ መሰብሰብ ቀጠሉ። ከጊዜ በኋላ የስፔይን ተወላጅ የሆኑ በርከት ያሉ ባልና ሚስት ሚስዮናውያን እርዳታ ለመስጠት መጡ። በኢኳቶሪያል ጊኒ ለ12 ዓመታት ያገለገለው አንድሬስ ቦቴያ ወደዚች አገር እንደመጣ ሰዎቹ ምን ያህል “በመንፈሳዊ የጎደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው” ሰዎች እንደሆኑ ሲመለከት በጣም እንደተደነቀ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ያስታውሳል። (ማቴዎስ 5:3 አዓት) “እንዲህ ዓይነት አድናቆት ካላቸው ሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጣም የሚያስደስት ነበር” ሲል ተናግሯል።
ሜሪ የተባለች አንዲት ስፔናዊት እህት ማሪያ ከምትባል አንዲት ወጣት ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ታጠና ነበር፤ ማሪያ፣ ፍራንሲስኮና ፋውሳታ የተባሉት ወላጆቿም ማጥናት እንደሚፈልጉ ነገረቻት። ሆኖም ሜሪ በወቅቱ 15 ጥናቶችን እያስጠናች ስለነበረና የማሪያ ወላጆች የሚኖሩት ራቅ ባለ ሥፍራ ስለነበር እነርሱን ሄዳ ሳታነጋግራቸው በርከት ያሉ ሳምንታት አለፉ።
በመጨረሻ ሜሪና ሴራፊን የሚባለው ባሏ እነዚህን ወላጆች ሲያገኟቸው ሰዎቹ አስቀድመው በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህa የተባለውን መጽሐፍና መጽሐፍ ቅዱስ አግኝተው የነበረ ከመሆኑም በላይ ጥናት ለመጀመር ከፍተኛ ፍላጎት አድሮባቸው ነበር። በመሆኑም ወዲያውኑ ጥናት ጀመሩ። ሴራፊን የማሪያ ወላጆች ትምህርቱን በሚገባ እንደሚያውቁት ተገነዘበ። በሚቀጥለው ጊዜም ሁለተኛውን ምዕራፍ ሲያጠኑ ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። ሴራፊን “ከሁለት የተጠመቁ ምሥክሮች ጋር የማጥናት ያህል ነበር” ሲል ያስታውሳል። ከሁኔታቸው ለመረዳት እንደተቻለው ጽሑፉን ቀደም ብለው በሚገባ ያነበቡት በመሆኑ በሦስተኛው ጥናታቸው ወቅት ሴራፊን ትምህርቱ ምን ያህል እንደገባቸው ለማየት ብቻ ጥናቱ በጥያቄና መልስ እንዲካሄድ ሐሳብ አቀረበ። በኋላም ፍራንሲስኮና ፋውስቲያ መጽሐፉን ራሳቸው ከዳር እስከ ዳር አጥንተው እንደጨረሱት ለመረዳት ቻለ!
አዲስ ያገኙት እውቀት ምን ለውጥ አሳደረባቸው? ከተማሩት ትምህርት ጋር የሚስማማ እርምጃ በመውሰድ መናፍስታዊ ድርጊቶች በሚፈጸሙባቸው ስብሰባዎች ላይ መካፈል ከማቆማቸውም በላይ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋረጡ። ከዚህም በላይ ፍራንሲስኮ ማጨስ አቆመ፤ ደሙ በሚገባ ያልፈሰሰ ሥጋም መብላት አቆሙ። የተማሩትን ሁሉ በሥራ በመተርጎማቸው እውቀታቸውን ለሌሎች ማካፈል እንዲጀምሩ ማበረታቻ ተሰጣቸው። ወዲያውኑ ለጎረቤቶቻቸው መስበክ ጀመሩ። በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ለጥምቀት ብቁዎች ሆኑ። ፍራንሲስኮ በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ አገልጋይ ነው፤ በእነርሱ ጥሩ ምሳሌነትና በስብከቱ ሥራ ባላቸው ቅንዓት የተነሳም ሦስቱ ሴቶች ልጆቻቸው በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ፣ ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው ደግሞ በስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። ሌሎች ስድስት ዘመዶቻቸው ደግሞ እያጠኑ ነው።
ፍራንሲስኮ ከተጠመቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የንዋየ ቅዱሳት ግምጃ ቤት ኃላፊ ሆኖ የሚያገለግል ፓብሎ የሚባል አንድ ቀናተኛ ካቶሊክ አገኘ። ቄሱ በሚቀርበት ጊዜ ሁሉ ስብከቱን የሚያካሂደው ፓብሎ ነበር። አንድ የቤተ ክርስቲያኑ አባል ከታመመ ሄዶ ይጠይቅ ነበር፤ አንድ ሰው ከቤተ ክርስቲያኑ ከቀረ ፓብሎ ሄዶ ያበረታታው ነበር፤ ሰው ሲሞት ደግሞ ቤተሰቡን ለማጽናናት የሚችለውን ሁሉ ያደርግ ነበር። የደብሩ ሕዝብ በሙሉ ፓብሎን ይወደው እንደነበር በግልጽ መረዳት ይቻላል።
ፓብሎ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት ስለነበረው ከእሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠና ፍራንሲስኮ ያቀረበለትን ሐሳብ በደስታ ተቀበለው። ፓብሎ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምን ያህል ምክንያታዊ እንደሆነ ወዲያውኑ ተረዳ፤ ማጥናት ከጀመረ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ከተማራቸው ጥቅሶች መካከል አንዳንዶቹን አንድን የታመመ የቤተ ክርስቲያን አባል “በእረኝነት በሚጠይቅበት” ጊዜ ሊጠቀምባቸው ወሰነ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ፓብሎ እሁድ እሁድ በሚሰጠው የስብከት ንግግር አንድ ቀን ይሖዋ በሚለው የአምላክ ስም የመጠቀምን አስፈላጊነትና በምስሎች መጠቀም የሌለብን ለምን እንደሆነ ገለጸ።
እሱ እውነትን ወዲያውኑ እንደተቀበለ ሁሉ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኑ አባላትም ተመሳሳይ ምላሽ ያሳያሉ ብሎ ጠብቆ ነበር። ሆኖም ፓብሎ ይህን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ስብከት ለሦስትና ለአራት ጊዜ ያህል ከሰጠ በኋላ ሕዝቡ ባቀረበው ትምህርት እንዳልተደሰቱ ተገነዘበ። ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኑን ለቅቆ በመውጣት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አዘውትሮ ለመሰብሰብ ወሰነ። በጥቂት ወራት ውስጥ ለጥምቀት ብቁ ሆነ፤ በአሁኑ ጊዜ ቀናተኛ የምሥራቹ ሰባኪ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። ምንም እንኳ የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ሆኖ ማገልገል ያልቻለ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ አሥር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመምራት ላይ ነው።
አንድ ላይ በመሰብሰብ እድገትን ማፋጠን
በኢኳቶሪያል ጊኒ የሚገኙት ምሥክሮች አንድ ላይ መሰብሰባችሁን አትተዉ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ በቁም ነገር ይመለከቱታል። (ዕብራውያን 10:25) ሥራው እንደገና በመንግሥት ሕጋዊ እውቅና ካገኘበት ከ1994 ጀምሮ ወንድሞች ተስማሚ የሆኑ የመንግሥት አዳራሾችን ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። እንዲያውም አብዛኞቹ ጉባኤዎች የራሳቸውን አዳራሾች ሠርተዋል ወይም በመሥራት ላይ ናቸው።
እሁድ እሁድ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ብዙውን ጊዜ የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር ከአስፋፊዎቹ ቁጥር ከሁለት እጥፍ በላይ በሚሆንበት በሞንጎሞ ጉባኤው አንድ ትልቅ መሰብሰቢያ ለመገንባት በትጋት ሲሠራ ቆይቷል። በሞንጎሞ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ሃይማኖቶች ብዙውን ጊዜ ቤተ ክርስቲያኖቻቸውን ለመገንባት ሠራተኞች ቀጥረው ነው የሚያሠሩት፤ በመሆኑም በአካባቢው የሚገኙት ምሥክሮች ሥራ የሰዎችን ትኩረት መሳቡ አልቀረም። አንድ ቀን የኢግለሲያ ኑአቫ አፖስቶሊካ (አዲስ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን) ቄስ በዚያ በኩል ሲያልፍ ለእነዚህ ጠንካራ ሠራተኞች ምን ያህል እንደሚከፍላቸው ከሽማግሌዎቹ አንዱን ጠየቀው። ቄሱ ምንም እንኳ የራሱ ቤተ ክርስቲያን አባላት የሆኑ የተወሰኑ የግንባታ ሠራተኞችን ቢቀጥርም ሥራው እንደተጓተተ ገለጸ። የመንግሥት አዳራሹን እየገነቡ የነበሩትን ሠራተኞች ሊቀጥር ይችል እንደሆነ አሰበ። ሁሉም ምሥክሮች እየሠሩ ያሉት በነፃ እንደሆነ ሲነገረው በጣም ተገርሞ ጉዞውን ቀጠለ።
ከመንግሥት አዳራሹ በጣም ርቀው የሚኖሩ ምሥክሮች በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ከፍተኛ መሥዋዕትነት መክፈል ሊጠይቅባቸው ይችላል። በ1994 የተጠመቀው ክዋን የተባለው ወጣት ይህ ሁኔታ አጋጥሞታል። እውነትን የሰማው ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ ግማሹን ክፍል ባጠናበት በጋቦን ነበር። ከዚያ በኋላ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ተመልሶ ከሞንጎሞ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የትውልድ መንደሩ መኖር ጀመረ። ይህ ጥናቱን ለመቀጠል ችግር ፈጠረበት። ሆኖም ይህ ሁኔታ ተስፋ ቆርጦ ጥናቱን እንዲተው አላደረገውም። በየወሩ በሞንጎሞ ከሚገኙት ሽማግሌዎች አንዱ ከሆነው ከሳንቲያጎ ጋር ለማጥናት ወደዚያ ሥፍራ በብስክሌት ስምንት ሰዓት ያህል ይጓዛል። በሞንጎሞ ለጥቂት ቀናት በሚያደርገው ቆይታ ወቅት ሦስት ወይም አራት ጊዜ አጥንቶ ይመለሳል። በዚህ መንገድ ጥናቱን ጨርሶ ለመጠመቅ በቃ።
ክዋን ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር የሚገናኘው አልፎ አልፎ ብቻ ሆኖ ሳለ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኖ ሊቀጥል የቻለው እንዴት ነው? ከሁሉም በላይ የረዳው የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት መስበኩ ነው። በመንደሩ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ሰብኳል፤ በተጠመቀበት ወቅት 13 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እያስጠና ነበር። ከጥናቶቹ መካከል ስድስቱ በጥምቀቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት በሞንጎሞ ወደተካሄደው የልዩ ስብሰባ ቀን ፕሮግራም አብረውት ሄደዋል። በአሁኑ ጊዜ በአካባቢው ካሉ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ጋር ሆኖ ቋሚ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት የሚመራ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር ወደ 20 ይደርሳል።
የተዘራውን ዘር ያለመታከት ማጠጣት
ፈጣን መንፈሳዊ እድገት የሚያሳዩት ሁሉም አይደሉም። አንዳንድ ጊዜ ዘሩ ፍሬ እስኪያፈራ ድረስ ብዙ ትዕግሥት ሊጠይቅ ይችላል። ይህ በፓካ ሁኔታ ላይ ታይቷል፤ ፓካ ምሥራቹን በመጀመሪያ የሰማችው ኤዲታ የተባለች አቅኚ እህት በ1984 በአንድ የገበያ ቦታ በመሰከረችላት ጊዜ ነበር። ኤዲታ በቀጣዩ ሳምንት እቤቷ ሄዳ ስታነጋግራት ፓካ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማማች። ምንም እንኳ ፓካ ብዙ እድገት ባታሳይም አንዳንድ ጥሩ ባሕርያት እንዳላት ኤዲታ ስለተረዳች ማስጠናቷን ቀጠለች። “በግ መሰል ሰው ነች ብዬ አሰብኩ” ስትል ኤዲታ ገልጻለች፤ “ይሖዋ ልቧን እንዲከፍተው ጸለይኩ።”
ፓካ አንዴ ስትጀምር አንዴ ደግሞ ስታቋርጥ ለአራት ዓመት ተኩል ያህል አጠናች፤ ሆኖም እምብዛም ያደረገችው እድገት አልነበረም። ስለዚህ ለዘላለም መኖር የተባለውን መጽሐፍ አጥንተው ሲጨርሱ ኤዲታ እውነትን በቁም ነገር የመያዝን አስፈላጊነት በግልጽ ነገረቻት። ኤዲታ የፓካን ልብ ለመንካት ባደረገችው ጥረት እንባ አውጥታ እስከ ማልቀስ ደርሳ ነበር።
“ያ ከልብ የመነጨ ምክር በጣም ነካኝ” ስትል ፓካ ወደ ኋላ መለስ ብላ ታስታውሳለች። “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሕይወቴ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን ማድረግ ጀመርኩ። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዘገብኩና በዚያው ዓመት ያልተጠመቅኩ አስፋፊ ሆንኩ። በመጨረሻም ስጠመቅ በሕይወቴ እንደዚያ ቀን ተደስቼ አላውቅም!” ፓካ በአሁኑ ጊዜ ያላት የጋለ መንፈስ ቀደም ሲል ከነበራት የግዴለሽነት ስሜት ፈጽሞ የተለየ ነው። በአሁኑ ጊዜ 13 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እያስጠናች ስትሆን ፈጣን እድገት የማያደርጉትን ጥናቶች በትዕግሥት እንደምትይዛቸው ምንም አያጠራጥርም።
ሰዎች ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ መርዳት
በኢኳቶሪያል ጊኒ ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ መስፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖራቸው ሐቀኞችና መልካም ምግባር ያላቸው ሰዎች ናቸው የሚል ስም አትርፈዋል። በምሥክሮቹ ጠባይ የተደነቀ አንድ ሰው አንድን የቤታ ጉባኤ ሽማግሌ ቀርቦ በማነጋገር እንዲህ ሲል ጠየቀው፦ “ማመራመር የተባለው መጽሐፍ አለህ?b አሁንስ ዓለማዊ ሰው ሆኖ መኖር ሰልችቶኛል። የይሖዋ ምሥክር መሆን እፈልጋለሁ!”
በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር ሆኖ በማላቦ ጉባኤ ውስጥ በጉባኤ አገልጋይነት የሚሠራው አንቶኒዮ ከነበረበት ዓለማዊ ኑሮ በመለወጥ ረገድ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናቱ በፊት ብልሹ የሆነ ሕይወት የነበረው ሰው ነበር። ሰዓት በመጠገን የሚያገኘውን ገንዘብ በአብዛኛው የሚያጠፋው በመጠጥ ነበር፤ በተጨማሪም ሥነ ምግባር የጎደለው ሰው ነበር። ይህን የአኗኗር ዘይቤ እንዲለውጥ የረዳው ምንድን ነው? በ1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 ላይ ጠንከር ባለ አነጋገር የተገለጸው ሐሳብ በጣም ነካው፦ “አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ . . . ወይም ሰካሮች . . . የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የአኗኗር መንገዱን መለወጥ እንዳለበት ተገነዘበ። ይህን ለማድረግ ሲል ጓደኞቹን መምረጥ ጀመረ። (ምሳሌ 13:20) የቀድሞ ጓደኞቹ አብሯቸው ሄዶ መጠጥ እንዲጠጣ ሲጋብዙት ግብዣቸውን አልተቀበለም፤ ከዚህ ይልቅ መሠከረላቸው። ብዙም ሳይቆይ እነሱም እሱን ማስቸገራቸውን አቆሙ።
ይህን ሁሉ ጥረት በማድረጉ ተጠቅሟልን? አንቶኒዮ “የአኗኗር መንገዴን በመለወጤ በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲል ይገልጻል። “ምንም እንኳ አሁን በ60ዎቹ ዓመታት ዕድሜ ላይ የምገኝ ብሆንም ጤንነቴ የተሻለ ሆኗል፤ የቀድሞ ጓደኞቼ ግን ወይ ሞተዋል አሊያም በጤና መታወክ እየተሠቃዩ ነው። አሁን ያሉኝ ጓደኞች እነዚያ ለመጠጥ የሚከፍልላቸውን ጓደኛ የሚፈልጉት ሰዎች ሳይሆኑ እውነተኛ ጓደኞች ናቸው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና አለኝ። በአሁኑ ጊዜ የዘወትር አቅኚ ሆኜ እያገለገልኩ ከመሆኑም በላይ የመጠጥ ችግር ያለበትን አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ እያስጠናሁ ስለሆነ እሱን ለመርዳት የራሴን ተሞክሮ መጠቀም እችላለሁ።”
የአምላክ ባሪያዎች መሆን
ወደ 200 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት በኢኳቶሪያል ጊኒ የባሕር ጠረፍ አካባቢ የነበሩ ሰዎች ታፍሰው በመርከብ ይጫኑና ለባርነት ወደ አሜሪካ ይወሰዱ ነበር። በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች በፈቃደኝነት የአምላክ ባሪያዎች እየሆኑ ነው። ይህ ዓይነቱ ባርነት ከባቢሎናዊ መሠረተ ትምህርቶችና መናፍስታዊ ልማዶች በማላቀቅ እውነተኛ ነፃነት አስገኝቶላቸዋል። በተጨማሪም አርኪና ፍሬያማ ኑሮ መኖር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ አስተምሯቸዋል። ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” ሲል የሰጠው ተስፋ በራሳቸው ሕይወት ላይ ተፈጽሟል።—ዮሐንስ 8:32
በ1995 በተደረገው መታሰቢያ በዓል ላይ 1,937 ሰዎች ተገኝተዋል፤ ይህ በአገሪቱ ውስጥ ካሉት አስፋፊዎች ቁጥር ስድስት ጊዜ እጥፍ ይሆናል ማለት ይቻላል። ይህም ወደፊት ተጨማሪ መንፈሳዊ እድገት እንደሚኖር የሚያሳይ ግሩም ተስፋ ነው። በኢኳቶሪያል ጊኒ የሚገኙ ምሥክሮች ቅንዓት በተሞላበት መንፈስ የእውነትን ዘር መዝራታቸውንና ማጠጣታቸውን ሲቀጥሉ ‘አምላክ እንደሚያሳድገው’ እርግጠኞች ናቸው። (1 ቆሮንቶስ 3:6) በኢኳቶሪያል ጊኒ ውስጥ ለመንፈሳዊ እድገት ተስማሚ ሁኔታ እንዳለ ምንም አያጠራጥርም!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።