ለተጨቆኑ ሰዎች የሚሆን ማጽናኛ
በሕይወት ዘመንህ በሙሉ በአርዕስተ ዜና ላይ በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ የተወሰኑ ቃላትን አስተውለሃልን? ስለ ጦርነት፣ ወንጀል፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ረሃብ፣ ሥቃይና እነዚህን ስለመሳሰሉት ነገሮች ማንበብ ሰልችቶሃልን? ይሁን እንጂ በዜና ዘገባዎች ላይ ሲጠቀስ የማይታይ አንድ ቃል አለ። ሆኖም ይህ ቃል የሰው ልጅ በእጅጉ የሚፈልገውን ነገር የሚገልጽ ነው። ይህም “ማጽናኛ” የሚለው ቃል ነው።
“ማጽናናት” ማለት ለአንድ ሰው “ማበረታቻና ተስፋ መስጠት” እንዲሁም “ሐዘኑን ወይም ችግሩን ማቅለል” ማለት ነው። ዓለም በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ካሳለፈችው ይህ ነው የማይባል ውጣ ውረድ አንፃር ሲታይ ተስፋ የሚሰጥና ሐዘንን የሚያቃልል ነገር በጣም ያስፈልጋል። እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ አንዳንዶቻችን የቀድሞ አባቶቻችን ፈጽሞ ሊሆን ይችላል ብለው ያልገመቱት ዓይነት የተደላደለ ኑሮ እየኖርን ሊሆን ይችላል። ለዚህ ትልቁ ምክንያት የዘመኑ የሳይንስ ዕድገት ነው። ሆኖም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሰው ልጅ መከራ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች በማስወገድ ማጽናኛ አላስገኙልንም። እነዚህ መንስኤዎች ምንድን ናቸው?
ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ጠቢቡ ሰሎሞን ‘ሰው ሰውን የሚገዛው ለጉዳቱ ነው’ ብሎ በተናገረ ጊዜ አንዱን የሥቃይና የመከራ መሠረታዊ መንስኤ ጠቅሷል። (መክብብ 8:9) ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሰው ሰውን ለመግዛት ያለውን ፍላጎት ለመለወጥ አልቻሉም። ይህም በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን በየአገሩ አምባገነናዊ የጭቆና አገዛዝ ከማስከተሉም በላይ በተለያዩ አገሮች መካከል በጣም አሠቃቂ ጦርነቶች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል።
ከ1914 ወዲህ በጦርነት ሳቢያ ከአንድ መቶ ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች አልቀዋል። የእነዚህ ሰዎች ሞት ያስከተለውን ሐዘንና ሥቃይ እስቲ አስበው፤ ማጽናኛ የሚፈልጉ በሐዘን ስሜት የተቆራመዱ በሚልዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች እንዲኖሩ አድርጓል። ጦርነቶች አሠቃቂ ሞት ከማስከተላቸውም ባሻገር ሌሎች መከራዎችንም አምጥተዋል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በአውሮፓ ውስጥ ከ12 ሚልዮን በላይ ስደተኞች ነበሩ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከአንድ ሚልዮን ተኩል በላይ የሚሆኑ ሰዎች በደቡብ ምሥራቅ እስያ ከሚገኙ የጦርነት ቀጣናዎች ሸሽተው ወጥተዋል። በባልካን አገሮች አካባቢ የተካሄዱ ጦርነቶች ከሁለት ሚልዮን በላይ የሆኑ ሰዎች መኖሪያቸውን ለቅቀው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆነዋል፤ ብዙዎቹ ይህን ያደረጉት “ከዘር ማጥፋት ዘመቻ” ለማምለጥ ሲሉ ነው።
ስደተኞች በተለይ ደግሞ ወዴት እንደሚሄዱና ወደፊት እነርሱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው ምን እንደሚገጥማቸው ሳያውቁ መሸከም የቻሉትን ንብረት ብቻ ይዘው ከቀዬአቸው ለመሰደድ የሚገደዱት ሰዎች በእርግጥም ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ሰዎች ከፍተኛ ጭቆና የደረሰባቸው እጅግ አሳዛኝ ተጠቂዎች ናቸው፤ ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል።
የተሻለ ሰላማዊ ሁኔታ ባለባቸው የምድር ክፍሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት ባሪያ አድርጓቸዋል። እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች የተትረፈረፈ ቁሳዊ ሀብት አላቸው። ይሁን እንጂ አብዛኛው ሰው ኑሮውን ለማሸነፍ በየዕለቱ ከፍተኛ ትግል ያደርጋል። ብዙዎች የተሟላ መኖሪያ ቤት ማግኘት ይፈልጋሉ። የሥራ አጦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። አንድ በአፍሪካ እየታተመ የሚወጣ ጋዜጣ “ዓለም ከዚህ ቀደም ታይቶ ወደማያውቅ የሥራ አጥነት ቀውስ ውስጥ እየገባች ነው፤ በ2020 ከ1.3 ቢልዮን በላይ የሚሆኑ ተጨማሪ ሰዎች ሥራ አጥ ይሆናሉ” ሲል ከወዲሁ ተንብዮአል። በእርግጥም የኢኮኖሚው ሁኔታ ያስጨነቃቸው ሰዎች “ማበረታቻና ተስፋ፣” አዎን፣ ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል።
ተስፋ አስቆራጭ የሆኑ ሁኔታዎችን ለመቋቋም አንዳንዶች ዘራፊዎች ይሆናሉ። እርግጥ፣ ይህ የጥቃቱን ሰለባዎች ችግር ውስጥ ከመክተት ሌላ የሚፈይደው ነገር አይኖርም፤ የወንጀል ድርጊቶች ቁጥር መጨመር ደግሞ የጭንቀቱን መጠን ያባብሰዋል። በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ውስጥ የሚታተም ዘ ስታር የተባለ ጋዜጣ “‘በዓለም ላይ ከፍተኛ የግድያ ወንጀል በሚፈጸምባት አገር ውስጥ’ የአንድ ቀን ውሎ” የሚል ርዕሰ ዜና በቅርቡ ይዞ ወጥቶ ነበር። ጽሑፉ በአንድ ቀን ውስጥ በጆሃንስበርግና በአካባቢዋ የተፈጸሙ ድርጊቶችን ዘግቦ ነበር። በዚያ ቀን አራት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ስምንት ሰዎች ደግሞ መኪናዎቻቸው ተጠልፈዋል። በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰዎች በሚኖሩበት ከከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ አካባቢ ቤት ሰብሮ በመግባት አሥራ ሰባት የዘረፋ ወንጀሎች ተፈጽመዋል። ከዚህም በተጨማሪ በታጠቁ ሌቦች የተፈጸሙ በርካታ የዘረፋ ወንጀሎች ነበሩ። ጋዜጣው እንዳለው ፖሊስ ይህን “በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አነስተኛ ወንጀል የተፈጸመበት ቀን” ሲል ገልጾታል። የግድያ ሰለባ የሆኑት ሰዎች ዘመዶች እንዲሁም ቤታቸው ተሰብሮ የተዘረፉና መኪናዎቻቸው የተጠለፉባቸው ሰዎች ምንኛ የመንፈስ ስብራት እንደሚደርስባቸው መረዳት አያዳግትም። ማበረታቻና ተስፋ አዎን፣ ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል።
በአንዳንድ አገሮች ልጆቻቸውን ለሴተኛ አዳሪነት የሚሸጡ ወላጆች አሉ። ጎብኚዎች “ለጾታ ሲባል የሚደረግ ጉብኝት” ለማካሄድ በብዛት የሚጎርፉባት በእስያ ውስጥ የምትገኝ አንዲት አገር ሁለት ሚልዮን ሴተኛ አዳሪዎች እንደሚገኙባት ሪፖርት ተደርጓል። ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ በልጅነታቸው የተሸጡ ወይም ታፍነው የተወሰዱ ናቸው። ከእነዚህ ምስኪን ሰለባዎች የበለጠ ግፍ የደረሰባቸው ሰዎች ይኖራሉን? ታይም የተባለው መጽሔት ስለዚህ አስነዋሪ ንግድ ሲገልጽ በደቡባዊ ምሥራቅ እስያ ያሉ የሴቶች ድርጅቶች በ1991 ስላካሄዱት ኮንፈረንስ ዘግቦ ነበር። በስብሰባው ላይ በተሰጠው ግምታዊ አኃዝ መሠረት “ከ1970ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ 30 ሚልዮን የሚሆኑ ሴቶች ለሴተኛ አዳሪነት ተሽጠዋል።”
እርግጥ፣ ልጆች የጥቃት ሰለባ የሚሆኑት ለሴተኛ አዳሪነት በመሸጥ ብቻ አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ልጆች በራሳቸው ቤት ውስጥ በወላጆቻቸውና በዘመዶቻቸው አካላዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፤ አልፎ ተርፎም ተገደው በጾታ ይነወራሉ። እነዚህ ልጆች የተፈጸመባቸው ግፍ ያስከተለባቸውን የስሜት ጠባሳ ለረጅም ጊዜ ይዘው ሊኖሩ ይችላሉ። እጅግ አሳዛኝ የጭቆና ሰለባዎች እንደመሆናቸው መጠን ማጽናኛ እንደሚያስፈልጋቸው ምንም አያጠራጥርም።
የተፈጸመውን ጭቆና በአንክሮ ያስተዋለ አንድ የጥንት ሰው
በሰው ላይ የሚደርሰው ከፍተኛ ጭቆና ንጉሥ ሰሎሞንን በጣም አሳዝኖት ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔም ተመለስሁ፣ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፤ እነሆም፣ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፣ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም።”—መክብብ 4:1
ጠቢቡ ንጉሥ ከ3,000 ዓመታት በፊት የተጨቆኑ ሰዎች አጽናኝ በጣም በሚያስፈልጋቸው አሳዛኝ ሁኔታ ሥር እንደነበሩ ተገንዝቦ ከነበረ ዛሬ ቢኖርማ ኖሮ ምን ይል ነበር? ያም ሆነ ይህ ሰሎሞን እሱን ጨምሮ ማንኛውም ፍጹም ያልሆነ ሰው የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን ማጽናኛ መስጠት እንደማይችል ተገንዝቦ ነበር። የጨቋኞችን የግፍ ቀንበር ለመስበር አንድ የላቀ ሰው ያስፈልግ ነበር። እንዲህ ዓይነት ሰው ሊኖር ይችላልን?
መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 72 ላይ ሁሉንም ሰው ስለሚያጽናና ታላቅ አጽናኝ ይናገራል። መዝሙሩ የተጻፈው የሰሎሞን አባት በሆነው በንጉሥ ዳዊት ነው። መግቢያው ላይ ያለው ሐሳብ “ስለ ሰሎሞን” ይላል። መዝሙሩ በዕድሜ ገፍቶ የነበረው ንጉሥ ዳዊት ዙፋኑን የሚወርሰውን ሰው አስመልክቶ የጻፈው እንደሆነ ግልጽ ነው። መዝሙሩ እንደሚለው ይህ ሰው ከጭቆና በማላቀቅ ዘላቂ እፎይታን ያመጣል። “በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፣ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው። ከባሕር እስከ ባሕር ድረስ፣ . . . እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይገዛል።”—መዝሙር 72:7, 8
ዳዊት እነዚህን ቃላት ሲጽፍ በአእምሮው የያዘው ልጁን ሰሎሞንን ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም ሰሎሞን በመዝሙሩ ውስጥ በተገለጸው መንገድ የሰውን ዘር ማገልገል የሚያስችል ኃይል እንደሌለው ተገንዝቦ ነበር። የመዝሙሩን ቃላት መፈጸም የቻለው በጥቂቱ ከመሆኑም በላይ ይህን ያደረገው ለእስራኤል ሕዝብ እንጂ ለመላው ምድር አልነበረም። ስለዚህ ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ትንቢታዊ መዝሙር አንድን ከሰሎሞን የበለጠ ሰው የሚያመለክት እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ይህ ሰው ማን ነው? ከኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ማንም ሊሆን አይችልም።
አንድ መልአክ የኢየሱስን መወለድ ሲያበስር “ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል” ብሏል። (ሉቃስ 1:32) በተጨማሪም ኢየሱስ ራሱን “ከሰሎሞን የሚበልጥ” በማለት ጠርቷል። (ሉቃስ 11:31) ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ በአባቱ ቀኝ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ የመዝሙር 72 ቃላትን መፈጸም በሚችልበት ቦታ ማለትም በሰማይ ይገኛል። በተጨማሪም የሰብዓዊ ጨቋኞችን የጭቆና ቀንበር መስበር የሚችልበትን ኃይልና ሥልጣን ከአምላክ ተቀብሏል። (መዝሙር 2:7-9፤ ዳንኤል 2:44) ስለዚህ የመዝሙር 72ን ቃላት የሚፈጽመው ኢየሱስ ነው።
ጭቆና በቅርቡ ያከትማል
ይህ ምን ማለት ነው? በቅርቡ ከማንኛውም ዓይነት ሰብዓዊ ጭቆና ነፃነት ይገኛል ማለት ነው። ከዚህ ቀደም ታይቶ በማያውቅ ሁኔታ በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን የደረሰው መከራና ጭቆና ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረው “የዚህ የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ” ምልክት አንዱ ክፍል ነው። (ማቴዎስ 24:3 አዓት) ከተነበያቸው ሌሎች ነገሮች አንዱ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሣል” ይላል። (ማቴዎስ 24:7) ይህ የትንቢቱ ገጽታ የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በ1914 ሲፈነዳ ፍጻሜውን ማግኘት ጀምሯል። ኢየሱስ አክሎም “ከዓመፃም ብዛት የተነሣ የብዙ ሰዎች ፍቅር ትቀዘቅዛለች” ብሏል። (ማቴዎስ 24:12) ሕገ ወጥነትና የፍቅር መጥፋት ክፉና ጨቋኝ ትውልድ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ የምድር ንጉሥ ሆኖ እጁን ጣልቃ የሚያገባበት ጊዜ ቀርቧል ማለት ነው። (ማቴዎስ 24:32-34) በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እምነት ላላቸውና የሰውን ዘር እንዲያጽናና በአምላክ እንደተሾመ አድርገው ለሚመለከቱት የተጨቆኑ ሰዎች ይህ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በክርስቶስ ኢየሱስ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙትን አንዳንድ ተጨማሪ የመዝሙር 72 ቃላት እንመልከት፦ “ወደ እርሱ የሚጮኹትን ድኾች ነፃ ያወጣል፤ ችግረኞችንና የተናቁትን ሰዎች ይታደጋል። ለድኾችና ለደካሞች ይራራል፤ በችግር ላይ ያሉትን ሰዎች ከሞት ያድናል። የእነርሱ ሕይወት በእርሱ ዘንድ ውድ ስለሆነ፣ ከጭቆናና ከዐመፅ ይታደጋቸዋል።” (መዝሙር 72:12-14፤ የ1980 ትርጉም) በዚህ መንገድ በአምላክ የተሾመው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉም ሰው ከጭቆና ቀንበር እንዲላቀቅ ያደርጋል። ማንኛውም ዓይነት የግፍ ሥራ እንዲያከትም የማድረግ ኃይል አለው።
አንድ ሰው ‘ይህ በጣም የሚያስደስት ነው፤ ግን በጊዜያችንስ? በአሁኑ ጊዜ እየተሠቃዩ ያሉት ሰዎች ምን ማጽናኛ አላቸው?’ ብሎ ሊጠይቅ ይችላል። አሁንም ቢሆን ለተጨቆኑት ሰዎች የሚሆን ማጽናኛ አለ። በዚህ መጽሔት ውስጥ ከዚህ ቀጥሎ ያሉት ሁለት ርዕሶች በአሁኑ ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከእውነተኛው አምላክ ከይሖዋና ከውድ ልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የቅርብ ዝምድና በመኮትኮት እንዴት ማጽናኛ እያገኙ እንዳሉ ይገልጻሉ። እንዲህ ዓይነቱ ዝምድና በእነዚህ የጭቆና ዘመናት ሊያጽናናን ከመቻሉም በላይ አንድን ሰው ከጭቆና ነፃ የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት ሊያስገኝለት ይችላል። ኢየሱስ ለአምላክ ሲጸልይ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” ብሏል።—ዮሐንስ 17:3
[በገጽ 4, 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ አንዱ ሌላውን አይጨቁንም