“ሁላችንም አንድ ወገን ነን”
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ጭፍን ሃይማኖታዊ ጥላቻና ዘረኝነት በመላው ዓለም ተስፋፍቷል። የጎሣ ልዩነቶች የእርስ በርስ ፍጅቶችን፣ ማሠቃየትንና ሌሎች አሳፋሪ የሆኑ አረመኔያዊ ድርጊቶች እንዲቀጣጠሉ አድርገዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ዘገባ መሠረት ሰብዓዊ መብቶች በመጣሳቸው በ1994 በመላው ዓለም ከ23 ሚልዮን በላይ የሆኑ ሰዎች የትውልድ አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል።
በሩዋንዳ ብቻ 500,000 የሚያህሉ ሰዎች የተጨፈጨፉ ሲሆን በቱትሲዎችና በሁቱዎች መካከል ብጥብጥ ከተቀሰቀሰ በኋላ ከ2,000,000 በላይ የሆኑ ሌሎች ሰዎች ለስደተኝነት ተዳርገዋል። ለ ስዋር የተባለ አንድ የቤልጅየም ጋዜጣ “በተለይ የይሖዋ ምሥክሮች የጦር መሣሪያ አንይዝም በማለታቸው ስደት ደርሶባቸዋል” በማለት ዘግቧል። የይሖዋ ምሥክሮች በጦርነቶች አይካፈሉም። ሆኖም በመቶ የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በዓመፅ ተገድለዋል። ይህ “ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል” በማለት ኢየሱስ የተናገረውን ቃል ያስታውሰናል።—ዮሐንስ 15:19
አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ማለትም እዤን ነታባና፣ ባለቤቱና ሁለት ልጆቻቸው በዋና ከተማዋ በኪጋሊ ውስጥ ይኖሩ ነበር። እዤን ስለ ክርስቲያናዊ ገለልተኛነት ለጎረቤቶቹ ሲያስረዳ ሞቃት የአየር ፀባይ ስለሚስማማው ቡገንቪሊያ ስለ ተባለው ረጅም ሀረግ ብዙውን ጊዜ ይናገር ነበር።—ማቴዎስ 22:21
እዤን እንዲህ በማለት ያስረዳ ነበር፦ “እዚህ ኪጋሊ ውስጥ ቡገንቪሊያ ቀያይ፣ ሐምራዊና አንዳንድ ጊዜም ነጫጭ አበቦች ያፈራል። ሆኖም ሁሉም አንድ ወገን ናቸው። ሰዎችም እንዲሁ ናቸው። ምንም እንኳ በዘር፣ በቆዳ ቀለም ወይም በጎሣ የምንለያይ ብንሆንም ሁላችንም አንድ ወገን ነን፤ ከአንድ የሰው ዘር ቤተሰብ የተገኘን ነን።”
የሚያሳዝነው ምንም እንኳ ሰላማውያን የሆኑና የገለልተኛነት አቋም የያዙ ቢሆንም የንታባና ቤተሰብ አባላት ደም በተጠማ አንድ የሰዎች ቡድን ተገደሉ። ሆኖም የሞቱት በታማኝነት ነው። ይሖዋ አምላክ እንደዚህ ላሉት ሰዎች የገባላቸውን ቃል እንደሚፈጽምና ከሞት ተነሥተው ከወገናዊነት የመነጨ ጥላቻ የማይኖርበት ዓለም እንደሚወርሱ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። (ሥራ 24:15) በዚያን ጊዜ የንታባና ቤተሰብ አባላት ከሌሎች ጋር ሆነው “በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11