ለይሖዋ የምንሰጠው ለምንድን ነው?
ፀሐይ ሰራፕታ በምትባለው ትንሿ የሲዶናውያን ከተማ ላይ ገና ብርሃንዋን ስትፈነጥቅ አንዲት መበለት እንጨት ለመልቀም ጎንበስ ቀና ማለት ጀመረች። ትንሽ የሚቀመስ ነገር ለማዘጋጀት እሳት ማንደድ ነበረባት፤ ይህ ምናልባት እሷና ትንሽ ልጅዋ ለመጨረሻ ጊዜ የሚበሉት እርጋፊ ምግብ ሊሆን ይችላል። ለረዥም ጊዜ በቆየው የድርቅና የረሃብ ዘመን ራስዋንና ወንድ ልጅዋን በሕይወት ለማቆየት ስትታገል ነበር። አሁን ግን በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። በረሃብ በመሠቃየት ላይ ናቸው።
አንድ ሰው ወደ እነሱ መጣ። ስሙ ኤልያስ ነው፤ መበለቲቱ ወዲያውኑ የይሖዋ ነቢይ እንደሆነ አወቀች። ይሖዋ ስለሚባለው አምላክ የሰማችው ነገር ያለ ይመስላል። ይሖዋ በአገሯ በሲዶና ውስጥ ጭካኔና ርኩሰት የተሞላበት አምልኮ ከሚያቀርቡለት ከበኣል የተለየ ነው። ስለዚህ ኤልያስ የሚጠጣ ውኃ ሲለምናት እሱን ለመርዳት ፈቃደኛ ነበረች። ምናልባት እንዲህ ማድረጓ የይሖዋን ሞገስ እንደሚያስገኝላት አስባ ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 10:41, 42) ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ኤልያስ ጥቂት ምግብ ጨምራ እንድታመጣለት ለመናት። ከልጅዋ ጋር አንዴ ለመጨረሻ የሚቀምሱት ምግብ ብቻ እንዳላት ገለጸችለት። ሆኖም ኤልያስ ድርቁ እስኪያልፍ ድረስ ይሖዋ በተአምር ምግብ እንደሚሰጣት በማረጋገጥ መለመኑን ቀጠለ። እሷስ ምን አደረገች? መጽሐፍ ቅዱስ “እርስዋም ሄዳ እንደ ኤልያስ ቃል አደረገች” ይላል። (1 ነገሥት 17:10-15) ይህ ቀላል አነጋገር አንድ ትልቅ እምነት የታየበት ተግባር ይገልጻል፤ ሴትዮዋ ያሳየችው እምነት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳ ከአንድ ሺ ዓመት ከሚያህል ጊዜ በኋላ ይህችን መበለት አወድሷታል!—ሉቃስ 4:25, 26
ቢሆንም ይሖዋ ከአንዲት ድሀ ሴት ይህን ያህል መጠየቁ እንግዳ ነገር ሊመስል ይችላል። በተለይ አንድ በጣም ታዋቂ የነበረ ሰው ያቀረበውን ጸሎት ስንመለከት ነገሩ እንግዳ ይሆንብናል። ንጉሥ ዳዊት ልጁ ሰሎሞን ለሚሠራው ቤተ መቅደስ እንዲጠቀምበት መዋጮዎች ሲያሰባስብ ከፍተኛ ልግስና እንዲያደርግ ሕዝቡን አነሣስቷል። በዘመናዊ ገንዘብ ሲሰላ የተዋጣው ስጦታ በብዙ ቢልዮን ዶላር የሚገመት ነው! ሆኖም ዳዊት ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “ሁሉ ከአንተ ዘንድ ነውና፣ ከእጅህም የተቀበልነውን ሰጥተንሃልና ይህን ያህል ችለን ልናቀርብልህ እኔ ማን ነኝ? ሕዝቤስ ማን ነው?” ብሎ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 29:14) ዳዊት እንዳለው ማንኛውም ነገር የይሖዋ ነው። ስለዚህ ንጹሑን አምልኮ ለማራመድ በምንሰጥበት ጊዜ የእሱ የሆነውን መልሰን ለእሱ መስጠታችን ነው። (መዝሙር 50:10) ታዲያ ቀድሞውኑ ይሖዋ እንድንሰጠው የሚፈልገው ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ይነሣል።
የእውነተኛ አምልኮ አንዱ ዐብይ ክፍል
ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ የሚሆነው ይሖዋ ከጥንት ጀምሮ መስጠትን የንጹሕ አምልኮ አንዱ ዐብይ ክፍል እንዲሆን ማድረጉ ነው። ታማኝ የነበረው አቤል ከመንጋው መካከል ውድ የሆኑትን ለይሖዋ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ኢዮብ ያሉት ዕብራውያን አባቶች ተመሳሳይ መሥዋዕቶች አቅርበዋል።—ዘፍጥረት 4:4፤ 8:20፤ 12:7፤ 26:25፤ 31:54፤ ኢዮብ 1:5
የሙሴ ሕግ ለይሖዋ የሚሰጡትን መዋጮዎች ከማጽደቁም በላይ እነዚህን መዋጮዎች የሚቆጣጠሩ ደንቦች አውጥቷል። ለምሳሌ ያህል ሁሉም እስራኤላውያን አሥራት እንዲያወጡ ወይም ምድሪቱ ከምታፈራውና ከብቶቻቸው ከሚወልዱት አንድ አሥረኛውን እንዲሰጡ ታዘው ነበር። (ዘኁልቁ 18:25-28) ሌሎች መዋጮዎች እንደዚህ የተወሰኑ አልነበሩም። ለምሳሌ ያህል እያንዳንዱ እስራኤላዊ ከመንጋውና ካመረተው በኵራት እንዲሰጥ ይፈለግበት ነበር። (ዘጸአት 22:29, 30፤ 23:19) ሆኖም እያንዳንዱ ግለሰብ ምርጡን እስከ ሰጠ ድረስ ከበኵራቱ ምን ያህሉን እንደሚሰጥ ራሱ እንዲወስን ሕጉ ይፈቅድለት ነበር። በተጨማሪም ሙሉ በሙሉ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የምስጋና መሥዋዕትና የስእለት መሥዋዕት ማቅረብ እንደሚቻል ሕጉ ይገልጽ ነበር። (ዘሌዋውያን 7:15, 16) ይሖዋ በባረካቸው መጠን እንዲሰጡት ሕዝቡን አበረታቷቸዋል። (ዘዳግም 16:17) የመገናኛ ድንኳንና የኋለኛው ቤተ መቅደስ ሲሠራ እያንዳንዱ ሰው ልቡ እንደገፋፋው ሰጥቷል። (ዘጸአት 35:21፤ 1 ዜና መዋዕል 29:9) እንዲህ ዓይነቶቹ በፈቃደኛነት የሚደረጉ መዋጮዎች ይሖዋን በይበልጥ ያስደስቱት እንደ ነበር አያጠራጥርም!
‘በክርስቶስ ሕግ’ ሥር ማንኛውም ስጦታ በፈቃደኛነት የሚቀርብ ነው። (ገላትያ 6:2፤ 2 ቆሮንቶስ 9:7) ይህ ማለት ግን የኢየሱስ ተከታዮች መስጠታቸውን አቁመዋል ወይም ደግሞ አነስተኛ ስጦታዎች ይሰጣሉ ማለት አይደለም። ሐቁ ከዚህ የተለየ ነው! ኢየሱስና ሐዋርያቱ በእስራኤል ውስጥ በሚሰብኩበት ወቅት ሴቶች እነሱን ተከትለው በገንዘባቸው ያገለግሏቸው ነበር። (ሉቃስ 8:1-3) በተመሳሳይም ሐዋርያው ጳውሎስ የሚስዮናዊነት ሥራውን ለማካሄድ የሚረዱ ስጦታዎችን ይቀበል ነበር፤ እሱ ራሱ ደግሞ አንዳንድ ጉባኤዎችን ሌሎች ሰዎች ሲቸገሩ በገንዘብ እንዲረዷቸው አበረታቷቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 8:14፤ ፊልጵስዩስ 1:3-5) በኢየሩሳሌም የነበረው የአስተዳደር አካል የተዋጡት ነገሮች ለችግረኞች በትክክል መታደላቸውን እንዲቆጣጠሩ ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎችን ሾሞ ነበር። (ሥራ 6:2-4) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የጥንት ክርስቲያኖች በእነዚህ መንገዶች ንጹሕ አምልኮን መደገፍን እንደ መብት አድርገው ቆጥረውት ነበር።
ያም ሆኖ ግን ይሖዋ መስጠትን የአምልኮው ክፍል ያደረገው ለምንድን ነው? ብለን እንጠይቅ ይሆናል። እነዚህን አራት ምክንያቶች ተመልከት።
የምንሰጥበት ምክንያት
በመጀመሪያ ደረጃ ይሖዋ መስጠትን የእውነተኛ አምልኮ ክፍል ያደረገው እንዲህ ማድረጋችን ለእኛ ስለሚጠቅመን ነው። ለአምላክ ጥሩነት ያለንን አድናቆት ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል አንድ ልጅ አንድ ነገር ገዝቶ ወይም ሠርቶ ለወላጁ ስጦታ ሲሰጥ ወላጁ ደስ የሚለው ለምንድን ነው? ስጦታው ወላጁ በምንም መንገድ ሊያቃልለው የማይችለውን ከባድ ችግር የሚያስወግድ ስለሆነ ነውን? ምናልባት ላይሆን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ወላጁ የሚደሰተው ልጁ የአድናቆትና የለጋስነት መንፈስ በመኮትኮቱ ነው። ይሖዋ እንድንሰጥ የሚያበረታታን በተመሳሳይ ምክንያት ሲሆን እንዲህ ስናደርግ ይደሰታል። ለእኛ ያሳየውን ወሰን የሌለው ደግነትና ልግስና እንደምናደንቅ የምናረጋግጠው በዚህ መንገድ ነው። ‘የማናቸውም በጎ ስጦታና ፍጹም በረከት’ ሰጪ ስለሆነ መቼም ቢሆን እሱን የምናመሰግንበት ምክንያት አናጣም። (ያዕቆብ 1:17) ከሁሉም በላይ ደግሞ ይሖዋ እኛ ለዘላለም መኖር እንድንችል ሲል እንዲሞት በመፍቀድ ተወዳጅ ልጁን ሰጥቶናል። (ዮሐንስ 3:16) እሱን የቱንም ያህል ብናመሰግነው በቂ ሊሆን ይችላልን?
በሁለተኛ ደረጃ የመስጠት ልማድ ካለን በዚህ በጣም አስፈላጊ በሆነ ባሕርይ ረገድ ይሖዋንና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን መምሰል እንማራለን። የይሖዋ ሰጪነትና ለጋስነት ማለቂያ የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም” ይሰጣል ይላል። (ሥራ 17:25) ለምንተነፍሰው አየር፣ ለምንመገበው ምግብ፣ በሕይወታችን ለምናገኘው ደስታና እርካታ ሁሉ ልናመሰግነው ይገባል። (ሥራ 14:17) ኢየሱስም እንደ አባቱ የልግስና መንፈስ አሳይቷል። ራሱን ሳይቆጥብ ሰጥቷል። ኢየሱስ ተአምራት በሚፈጽምበት ወቅት እሱ አንድ የሚያጣው ነገር እንደ ነበረ ታውቃለህን? የታመሙ ሰዎችን በሚፈውስበት ወቅት ‘ኃይል ከእርሱ ይወጣ’ እንደ ነበር ቅዱሳን ጽሑፎች ይናገራሉ። (ሉቃስ 6:19፤ 8:45, 46) ኢየሱስ በጣም ለጋስ ከመሆኑ የተነሣ ነፍሱን ማለትም ሕይወቱን እንኳ ሳይቀር ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል።—ኢሳይያስ 53:12
ስለዚህ ጊዜያችንን፣ ኃይላችንን ወይም ንብረቶቻችንን ስንሰጥ ይሖዋን እንመስለዋለን እንዲሁም ልቡን ደስ እናሰኛለን። (ምሳሌ 27:11፤ ኤፌሶን 5:1 የ1980 ትርጉም) በተጨማሪም ለሰብዓዊ አኗኗር ፍጹም አርአያ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ እንከተላለን።—1 ጴጥሮስ 2:21
በሦስተኛ ደረጃ በመስጠታችን በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንዲሟሉ እናደርጋለን። እርግጥ ይሖዋ ቢፈልግ ኖሮ በእኛ ፈንታ ድንጋዮች ቃሉን እንዲሰብኩ ማድረግ ይችል እንደ ነበረ ሁሉ ያለ እኛ እርዳታ የመንግሥቱን ፍላጎቶች በቀላሉ ሊያሟላ ይችላል። (ሉቃስ 19:40) ይሁን እንጂ እነዚህን መብቶች በመስጠት እኛን ለማክበር መርጧል። ስለዚህ የመንግሥቱን ጥቅሞች ለማራመድ ያሉንን ነገሮች ስንሰጥ በዚህ ምድር ላይ ከሚካሄዱት ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆነው ሥራ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንዳደረግን ስለምናውቅ ከፍተኛ እርካታ ይሰማናል።—ማቴዎስ 24:14
ዓለም አቀፉን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ለማካሄድ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። በ1995 የአገልግሎት ዓመት ማኅበሩ ልዩ አቅኚዎችን፣ ሚስዮናውያንንና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን በመስክ አገልግሎት ሥራቸው ለመደገፍ ብቻ ወደ 60 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ብር ወጪ አድርጓል። ሆኖም በዓለም ዙሪያ ላሉት ቅርንጫፍ ቢሮዎችና የማተሚያ ፋብሪካዎች ግንባታና ለሥራው ማካሄጃ ከወጣው ወጪ ጋር ሲነጻጸር ይህ በጣም አነስተኛ ነው። ሆኖም ይህ ሁሉ ሊከናወን የቻለው በፈቃደኝነት በሚደረጉ መዋጮዎች አማካኝነት ነው!
የይሖዋ ሕዝቦች እኔ ሀብታም እስካልሆንኩ ድረስ ሸክሙን ሌሎች ይሸከሙት አይሉም። እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ ይህን የአምልኮታችንን ገጽታ እንድናጣ ሊያደርገን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመቄዶንያ የሚኖሩት ክርስቲያኖች ‘በጣም ደህይተው’ እንደ ነበር ገልጿል። ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች የመስጠት መብት እንዲያገኙ ለምነው ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስ እንደመሠከረው የሰጡት ‘ከዓቅማቸው በላይ’ ነበር!—2 ቆሮንቶስ 8:1-4
በአራተኛ ደረጃ ይሖዋ መስጠት የእውነተኛ አምልኮ ክፍል እንዲሆን ያደረገው መስጠት ደስተኞች እንድንሆን ስለሚረዳን ነው። ኢየሱስ ራሱ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” አዓት] ነው” ብሏል። (ሥራ 20:35) ይሖዋ የሠራን በዚህ መንገድ ነው። የቱንም ያህል ብንሰጠውም እንኳ ለእሱ ካለን ልባዊ አድናቆት ጋር የሚመጣጠን ነገር እንዳልሠራን የሚሰማን በዚህ ምክንያት ነው። ደስ የሚለው ግን እሱ እኛ መስጠት ከምንችለው በላይ አይጠብቅብንም። በደስታ የዓቅማችንን ያህል ስንሰጠው እንደሚደሰት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን!—2 ቆሮንቶስ 8:12፤ 9:7
የለጋስነት መንፈስ ከማሳየት የሚገኙ በረከቶች
ቀደም ሲል ወደ ጠቀስነው ምሳሌ ስንመለስ የሰራፕታዋ መበለት ኤልያስ የሚያስፈልገውን ምግብ ሌላ ሰው ሊሰጠው ይችላል ብላ አስባ ነበር እንበል። እንዲህ አስባ ቢሆን ኖሮ እንዴት ያለ በረከት ያመልጣት ነበር!
የለጋስነት መንፈስ የሚያሳዩትን ይሖዋ እንደሚባርካቸው ምንም አያጠያይቅም። (ምሳሌ 11:25) የሰራፕታዋ መበለት የመጨረሻ ምግቤ ነው ብላ ያሰበችውን በመስጠቷ አልተጎዳችም። ይሖዋ በተአምር ወሮታዋን ከፍሏታል። ኤልያስ ቃል እንደገባላት ድርቁ እስኪያልፍ ድረስ የዱቄትና የዘይት ዕቃዋ ባዶ አልሆኑም። ይሁን እንጂ ከዚህ የበለጠ ሽልማት አግኝታለች። ልጅዋ ታሞ ሲሞት የእግዚአብሔር ሰው የነበረው ኤልያስ አስነሥቶላታል። ይህም መንፈሳዊነቷን በጣም አጠናክሮት መሆን አለበት!—1 ነገሥት 17:16-24
በዛሬው ጊዜ በተአምራት እንድንባረክ አንጠብቅም። (1 ቆሮንቶስ 13:8) ይሁን እንጂ ይሖዋ በሙሉ ነፍሳቸው የሚያገለግሉትን እንደሚረዳቸው ቃል ገብቷል። (ማቴዎስ 6:33) ስለዚህ ይሖዋ እንደሚንከባከበን ተማምነን በልግስና በመስጠት ረገድ የሰራፕታዋን መበለት ልንመስል እንችላለን። በተጨማሪም ታላላቅ መንፈሳዊ በረከቶችን አግኝተን ልንደሰት እንችላለን። መስጠት አልፎ አልፎና በቅድሚያ ሳይታሰብበት የሚደረግ ከመሆን ይልቅ የዘወትሩ ልማዳችን ክፍል ከሆነ ዓይናችን ቀላል እንዲሆንና በመንግሥቱ ፍላጎቶች ላይ እንዲያተኩር ኢየሱስ የሰጠውን ምክር እንድንሠራበት ያስችለናል። (ሉቃስ 11:34፤ ከ1 ቆሮንቶስ 16:1, 2 ጋር አወዳድር።) እንዲሁም የሥራ ባልደረቦቻቸው በመሆን ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋር በይበልጥ እንደተቀራረብን እንዲሰማን ያደርጋል። (1 ቆሮንቶስ 3:9) በተጨማሪም በመላው ዓለም የሚገኙ የይሖዋ አምላኪዎች ተለይተው የሚታወቁበትን የለጋስነትና የመስጠት መንፈስ እንዲበዛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች ለመንግሥቱ ሥራ እርዳታ የሚያደርጉባቸው መንገዶች
ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረግ መዋጮ
ብዙዎች “ለማኅበሩ ዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩትን የተወሰነ የገንዘብ መጠን ይመድባሉ ወይም ወጪ ያደርጋሉ። ጉባኤዎች ይህን ገንዘብ በየወሩ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወዳለው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአካባቢው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ።
በፈቃደኛነት የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎች በቀጥታ Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Hieghts, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገርህ ወደሚገኝ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም በእርዳታ መስጠት ይቻላል። የተላከው ነገር ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ አብሮ መላክ ይኖርበታል።
ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት
አንድ ሰው ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሰጠውን ገንዘብ ሊጠቀምበት በሚፈልግበት ጊዜ ሊመለስለት የሚያስችል ዝግጅት በማድረግ እስኪሞት ድረስ ማኅበሩ በአደራ መልክ እንዲይዘው ሊሰጥ ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እባክህ ከላይ በተገለጸው አድራሻ Treasurer’s Office ብለህ ጻፍ።
በእቅድ የሚደረግ ስጦታ
ለማኅበሩ በቀጥታ ስጦታ ከመለገስና ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥት አገልግሎት ለመደጎም መስጠት የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ። ከእነዚህም አንዳንዶቹ፦
ኢንሹራንስ፦ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአንድ የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ሲደረግ ለማኅበሩ ማስታወቅ ይገባል።
የባንክ ሒሳብ፦ የአገሩ ባንክ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል። ማንኛውም እንዲህ ዓይነት ዝግጅት መደረጉን ለማኅበሩ ማስታወቅ ይገባል።
አክሲዮኖችና ቦንዶች፦ አክሲዮኖችና ቦንዶች በይፋ ስጦታነትም ሆነ ገቢው ለሰጪው በተከታታይ እንዲመለስለት ዝግጅት ተደርጎ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በእርዳታ መስጠት ይቻላል።
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች፦ ሊሸጡ የሚችሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በይፋ ስጦታነት ወይም ሰጪው በሕይወት እስካለ ድረስ በንብረቱ በመተዳደር እንዲቀጥል መብቱን በማስጠበቅ ለማኅበሩ በእርዳታ መስጠት ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማኅበሩ ከማስተላለፉ አስቀድሞ ከማኅበሩ ጋር ግንኙነት ማድረግ ይኖርበታል።
ኑዛዜዎችና አደራዎች፦ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተፈጻሚነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ የሃይማኖት ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት። የኑዛዜው ወይም ንብረት በአደራ የተሰጠበት ስምምነት ቅጂ ለማኅበሩ ሊላክ ይገባል።
ከእነዚህ በእቅድ የሚደረጉ ስጦታዎች መካከል በአንዱ ለመጠቀም የሚፈልጉ ከታች በተዘረዘረው አድራሻ ወይም በአገራቸው ላለው የማኅበሩ ቢሮ Planned Giving Desk ብለው ሊጽፉ ይችላሉ። በእቅድ የሚደረግ ስጦታ ዴስክ ከእነዚህ ዝግጅቶች ጋር የተያያዙ ሰነዶች አንድ አንድ ቅጂ ሊደርሰው ይገባል።
ማኅበሩ በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የተባለ ብሮሹር በእንግሊዝኛ ቋንቋ አዘጋጅቷል። ለማኅበሩ ልዩ ስጦታ ለመስጠት ወይም በሚሞቱበት ጊዜ ውርስ ለመተው እያቀዱ ያሉ በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ሰዎች ይህን ሐሳብ ጠቃሚ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ። በተለይም አንዳንድ የቤተሰብ ግብ ለማከናወን ወይም ውርሱ የሚያስከፍለውን ቀረጥ በሕጋዊ መንገድ ለማስቀነስ በሚፈልጉበት ጊዜ ይህ ሐሳብ ሊረዳቸው ይችላል። በጽሑፍ ወይም በስልክ ጥያቄ በማቅረብ ብሮሹሩን ማግኘት ይቻላል።
PLANNED GIVING DESK
Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
100 Watchtower Drive, Patterson, New York 12563-9204
Telephone: (914) 878-7000