ጾም ጊዜ ያለፈበት ነገር ነውን?
ምሩዱላቤን የተባሉ አንዲት የ78 ዓመት ሕንዳዊት ባለጠጋ “ከአሥራዎቹ ዕድሜዬ ጀምሬ ሰኞ ሰኞ እጾማለሁ” ይላሉ። ጾም የአምልኳቸው ክፍል ሆኖ የቆየ ሲሆን ይህን የሚያደርጉት ትዳራቸው እንዲሠምር፣ ልጆቻቸው ጤናማ እንዲሆኑና ባለቤታቸው ደህና እንዲሆኑላቸው ሲሉ ነው። በአሁኑ ወቅት መበለት የሆኑት እኚህ ሴት ለራሳቸው ጥሩ ጤናና ለልጆቻቸው ብልጽግና በመመኘት ሰኞ ሰኞ መጾማቸውን ቀጥለዋል። እንደ እርሳቸው ሁሉ በሂንዱ እምነት ውስጥ ያሉት አብዛኞቹ ሴቶች ዘወትር መጾምን የሕይወታቸው ክፍል አድርገውታል።
በሕንድ ውስጥ ከሙምቤይ (ቦንቤ) ወጣ ብሎ በሚገኝ አካባቢ የሚኖር መካከለኛ ዕድሜ ያለው ፕራካሽ የተባለ ነጋዴ በየዓመቱ በሳቨን (ሽራቫን) ወር ሰኞ ሰኞ እንደሚጾም ይናገራል። ይህ ወር በሂንዱ እምነት ተከታዮች ዘንድ ልዩ ሃይማኖታዊ ትርጉም ያለው ወር ነው። ፕራካሽ እንዲህ ይላል፦ “መጾም የጀመርኩት በሃይማኖታዊ ምክንያት ቢሆንም ለጤናም ጥሩ ሆኖ ስላገኘሁት እንድገፋበት ተጨማሪ ማበረታቻ ሆኖልኛል። ሳቨን የሚመጣው ወደ ክረምቱ መገባደጃ ላይ ስለሆነ ሰውነቴ በዝናቡ ወቅት ከሚመጡት በሽታዎች ራሱን እንዲያጸዳ አጋጣሚ ይሰጠዋል።”
አንዳንዶች መጾም አንድን ሰው በአካል፣ በአእምሮና በመንፈሳዊ ሁኔታ ይረዳዋል ብለው ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል ግሮሊያ ኢንተርናሽናል ኢንሳይክሎፔድያ እንዲህ ይላል፦ “በቅርቡ የተደረጉ ሳይንሳዊ ምርምሮች ጾም ለጤና ጠቃሚ እንደሆነና በጥንቃቄ ከተደረገም አእምሮአችን ይበልጥ ንቁ እንዲሆን ሊያደርግ እንደሚችል ይጠቁማሉ።” የግሪኩ ፈላስፋ ፕላቶ ለአሥርና ከዚያም ለሚበልጡ ቀናት ይጾም እንደነበርና የሒሳብ ሊቅ የነበረውም ፓይታጎረስ ተማሪዎቹን ከማስተማሩ በፊት እንዲጾሙ ያደርግ እንደነበር ይነገራል።
በአንዳንዶች ዘንድ ጾም ማለት ለተወሰነ ጊዜ ጨርሶ ከምግብና ከውኃ መራቅ ማለት ሲሆን ሌሎች ደግሞ በሚጾሙበት ወቅት የሚጠጡ ነገሮችን ይወስዳሉ። ብዙዎች በቀን ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ምግብ ሳይበሉ መቆየትን ወይም ደግሞ ከተወሰኑ ዓይነት ምግቦች መራቅን እንደ ጾም ይመለከቱታል። ይሁን እንጂ ለረጅም ጊዜ የሚቆይና ገደብ ያልተበጀለት ጾም አደገኛ ሊሆን ይችላል። ጋዜጠኛው ፓሩል ሼዝ እንደሚሉት ሰውነታችን በውስጡ ያከማቸውን ካርቦሃይድሬት ከጨረሰ በኋላ የጡንቻዎቻችንን ፕሮቲን ወደ ግሉኮስ መቀየር ይጀምራል፤ ከዚያም የሰውነታችንን ስብ ወደ ግሉኮስ መቀየሩን ይያያዘዋል። ስብን ወደ ግሉኮስ መቀየር ደግሞ በሰውነት ውስጥ ኪቶን ቦዲስ የተባሉ መርዝነት ያላቸው ቅመሞች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። እነዚህ ቅመሞች በሰውነታችን ውስጥ እየተከማቹ ሲመጡ ወደ አንጎል ይሄዱና የሰውነታችንን ማዕከላዊ ሥርዓተ ነርቭ ይጎዳሉ። ሼዝ “ጾም አደገኛ የሚሆነው ይኼን ጊዜ ነው” ይላሉ። “ድንግርግር ሊላችሁና ያላችሁበት ሊጠፋችሁ ይባስ ብሎም ከዚህ የከፋ ነገር ሊገጥማችሁ ይችላል። . . . ራስን መሳትና በመጨረሻም ሞት [ሊያስከትል ይችላል]።”
መሣሪያም ሃይማኖታዊ ሥርዓትም ሆኖ አገልግሏል
ጾም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ዓላማዎችን ለማሳካት ኃይለኛ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል። በዚህ መሣሪያ በመጠቀም ረገድ ጉልህ ሥፍራ የያዙት የሕንዱ ሞሃንዳስ ኬ ጋንዲ ናቸው። በመቶ ሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ሰው ስለነበሩ ጾምን በመጠቀም የሂንዱ እምነት ተከታይ በሆነው በብዙሐኑ የሕንድ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድረዋል። ጋንዲ የእርሳቸው ጾም በፋብሪካ ሠራተኞችና የፋብሪካ ባለቤቶች መካከል የተነሣውን የኢንዱስትሪ ውዝግብ በማርገብ በኩል ያስገኘውን ውጤት ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “አንዱን ውጤት ለመጥቀስ ያህል በሁሉም ሰዎች ዘንድ ቀና መንፈስ አሳድሯል። የፋብሪካ ባለቤቶቹ ልብ ተነካ . . . ሦስት ቀናት ብቻ እንደጾምኩ አድማው ቆመ።” የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ የፖለቲካ እስረኛ በነበሩባቸው ዓመታት ወቅት በተደረገው የአምስት ቀናት የረሃብ አድማ ተካፍለው ነበር።
ሆኖም ጾምን ልማዳቸው ካደረጉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የሚጾሙት ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ምክንያት ነው። በሂንዱይዝም እምነት ውስጥ ጾም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው። ፋስት ኤንድ ፌስቲቫል ኦቭ ኢንዲያ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ጨርሶ ጾም የሚዋልባቸው . . . ውኃ እንኳ የማይቀመስባቸው ቀናት አሉ። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ደስታና ብልጽግና እንዲሁም ከኃጢአት መተላለፋቸው ሁሉ ይቅርታ ለማግኘት ብለው . . . በጥብቅ ይጾማሉ።”
በጄይን ሃይማኖት ውስጥም ጾም በሰፊው የተለመደ ነገር ነው። ዘ ሰንዴይ ታይምስ ኦቭ ኢንዲያ ሪቪው እንዲህ በማለት ይዘግባል፦ “በቦምቤ [ሙምቤይ] የሚገኙ አንድ የጄይን ሃይማኖት መኒ [ጠቢብ] በቀን ሁለት ብርጭቆ የፈላ ውኃ ብቻ እየጠጡ 201 ቀናት በመቆየታቸው 33 ኪሎ ግራም ቀንሰዋል።” አንዳንዶችም መዳን ያስገኝልናል ብለው በማመን በጾም ራሳቸውን ለሕልፈተ ሕይወት ዳርገዋል።
የእስልምናን እምነት የሚከተሉ ጎልማሶች ባጠቃላይ በረመዳን ወር የመጾም ግዴታ አለባቸው። በዚያ ወር ፀሐይ ከምትወጣበት ጊዜ አንስቶ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ምንም ዓይነት ምግብ ወይም ውኃ መውሰድ አይፈቀድም። በዚህ ወቅት የታመመ ወይም በጉዞ ላይ ያለ ሰው ቢኖር የጎደሉትን ቀናት በሌላ ወቅት ማካካስ ይኖርበታል። ከበዓለ ትንሣኤ በፊት ያለው የአርባ ቀን የሁዳዴ ጾም በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉት አንዳንዶች የሚጾሙበት ወቅት ሲሆን ብዙ ሃይማኖቶችም እንዲሁ የሚጾሙባቸው የተወሰኑ ቀናት አሏቸው።
በእርግጥም ጾም ዛሬም ቢሆን አልተረሳም። በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚዘወተር ነገር በመሆኑ እንደሚከተለው ብለን ልንጠይቅ እንችላለን፦ አምላክ እንድንጾም አዝዞናልን? ክርስቲያኖች ለመጾም ሊወስኑ የሚችሉባቸው ጊዜያት አሉን? ይህስ ጠቃሚ ሊሆን ይችላልን? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጄይን ሃይማኖት ጾም የነፍስ መዳን የሚገኝበት መንገድ እንደሆነ ያምናል
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሞሃንዳስ ኬ ጋንዲ ጾምን ፖለቲካዊ ወይም ማኅበራዊ ዓላማዎችን ለማሳካት ኃይለኛ መሣሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ በረመዳን ወር መጾም ግዴታ ነው
[ምንጭ]
Garo Nalbandian