የሕክምናውን ዓይነት አውቆ የመስማማት መብት ተረጋገጠ
በቅርቡ በኢጣሊያ ሜሲና የሚገኘው ቀዳሚ ምርመራ ያደረገው ፍርድ ቤት ዳኛ ያሳለፉት ብይን በአዋቂዎች ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ታማሚ የሚያደርገውን የሕክምና ምርጫ ዶክተሮች መቀበል እንደሚኖርባቸው በድጋሚ ያረጋገጠ ነበር። ይህ ውሳኔ የተላለፈው ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር በተያያዘ ጉዳይ ላይ ነበር።
በጥር 1994 አንቶኒኖ ስቴላሪዮ ሌንቲኒ የተባለ አንድ የደም መርጋት ችግር ያለበት (ሄሞፊሊክ) የ64 ዓመት የይሖዋ ምሥክር በቶአርሚና ሜሲና ወደሚገኝ ሆስፒታል በድንገት ይገባል። የአንቶኒዮ ባለቤት ካቴና እርሷም ሆነች ቧላ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናቸው በደም አማካኝነት የሚደረግ ሕክምና እንደማይፈልጉ ለሆስፒታሉ ሠራተኞች አሳወቀች። (ሥራ 15:20, 28, 29) ፍላጎታቸው ተከበረላቸው።
ይሁን እንጂ አንቶኒዮ ወደ ሌላ የጤና ጣቢያ እየተዛወረ እያለ የመተንፈስ ችግር ይገጥመውና ለሕይወቱ የሚያሰጋ ሁኔታ ላይ ይወድቃል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሞተ። ካቴና በከባድ ሐዘን ውስጥ የወደቀች ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው የትንሣኤ ተስፋ ትልቅ መጽናኛ ሆኗታል። (ሥራ 24:15) ይግረምሽ ብሎ ደግሞ የሕግ ባለ ሥልጣናቱ በመገናኛ ብዙሐን ከተላለፈው የተሳሳተ ዜና በመነሣት ሳይሆን አይቀርም፣ ዶክተሮች አስፈላጊ እንደሆነ ያመኑበትን ሕክምና ለመቀበል አሻፈረኝ ብላ ባሏ እንዲሞት አድርጋለች የሚል ክስ መሠረቱባት።
ከአንድ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ሐምሌ 11, 1995 ካቴና ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልፈጸመች ተረጋግጦ ነጻ ተለቀቀች። እንዲያውም የሕክምና ባለሙያዎቹ የሰጡት የምሥክርነት ቃል እንደሚጠቁመው የታማሚው ሁኔታ ሲመረመር በወቅቱ ምንም ዓይነት የሕክምና እርዳታ ቢሰጠው ሕይወቱን ለማትረፍ አይቻልም ነበር።
ሆኖም የዳኛው ውሳኔ ዋነኛውን አከራካሪ ጉዳይ የሚጠቁም ነበር። ታማሚው ወይም እርሱን የሚወክሉት ግለሰቦች የማይፈልጉትን ሕክምና ሠራተኞቹ ጣልቃ ገብተው መስጠት አለባቸው የሚለውን ሐሳብ ፍርድ ቤቱ ለመቀበል እንደሚቸግረው ተናግረዋል። በመቀጠልም ዳኛው በኢጣሊያ ውስጥ የሚሠራበት በሕክምና ባለሙያዎች ላይ የተጣለው የሞራል ግዴታ ደንብም ቢሆን “ምንም ዓይነት የሕክምና ጣልቃ ገብነት ከመደረጉ በፊት ግለሰቡ ስለሚሰጠው ሕክምና የሚያውቅና የሚስማማበትም መሆኑን የማረጋገጡን አስፈላጊነት” አስፍሯል። በመሆኑም ካቴና “ባለቤቷ እንዲህ ዓይነት ቀዶ ሕክምና እንዲደረግለት ላለመፍቀድ መብት አላት” ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ውሳኔ በአዋቂዎች ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ሰው ከገዛ ፈቃዱ ወይም ፈቃዷ ውጭ የሆነ የሕክምና ዓይነት ላለመቀበል መብት እንዳለው በድጋሚ የሚያረጋግጥ ሆኗል።