ይህ ተወዳዳሪ የማይገኝለት አጋጣሚ አያምልጥህ!
ፒተር የመጽሐፍ ቅዱስ የመዳን መልእክት ትኩረቱን የሳበው በሕክምና ትምህርት ብዙ ገፍቶ ሳለ ነበር። ተመርቆ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ በዶክተርነት በሚሠራበት ጊዜ አለቆቹ ኒውሮሰርጀን ለመሆን እንዲያጠና ከመጎትጎት አልቦዘኑም ነበር። ብዙ አዳዲስ ዶክተሮች ይህን አጋጣሚ ለመጠቀም ዓይናቸውን አያሹም።
ሆኖም ፒተርa በዚህ አጋጣሚ ላለመጠቀም ወሰነ። ለምን? ጉጉትና ውስጣዊ ፍላጎት ስላልነበረው ነውን? አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ፒተር የቀረበለትን ግብዣ በጥንቃቄ አስቦበት ነበር። ራሱን የወሰነና የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ በኋላ ፍላጎቱ በተለያዩ የክርስቲያናዊ አገልግሎት ዘርፎች የተቻለውን ያህል ሰፊ ጊዜ ማሳለፍ ነበር። የኒውሮሰርጀን ባለሙያ ከሆነ ግን ሙያው አብዛኛውን ጊዜውንና ጉልበቱን እንደሚያጠፋበት አሰበ። በዚህ ልዩ አጋጣሚ አለመጠቀሙ ሞኝነት ነበር ወይስ ብልህነት?
አንዳንዶች የፒተር ውሳኔ ሞኝነት ሊመስላቸው ይችላል። ይሁን እንጂ እርሱ እንደ ኤፌሶን 5:15, 16 ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ግምት ውስጥ አስገብቶ ነበር። እዚህ ጥቅስ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ጓደኞቹን እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል፦ “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።”
“ዘመኑን” የሚለውን ቃል ልብ በል። ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአብዛኛው አንድ የተለየ ገጽታ ያለውን ወይም ለአንድ ዓይነት ሥራ ተስማሚ የሆነን ወቅት ወይም ክፍለ ጊዜ ለማመልከት ከሚሠራበት የግሪክኛ ቃል የተተረጎመ ነው። እዚህ ላይ ጳውሎስ ክርስቲያኖች በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች ጊዜ እንዲመድቡ ጠበቅ አድርጎ መክሯቸዋል። ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ፈትነው ማወቅ’ እንዳለባቸው አያጠያይቅም። (ፊልጵስዩስ 1:10 አዓት) ይህ የትኞቹ ነገሮች መቅደም እንዳለባቸው የመወሰን ጉዳይ ነው።
ታዲያ በጊዜያችን መፈጸም ያለበት መለኮታዊ ዓላማ ምንድን ነው? አምላክ እርሱን የሚያፈቅሩ ሰዎች ምን እንዲያደርጉ ይፈልግባቸዋል? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ያለንበት ጊዜ ‘የፍጻሜ ዘመን’ ወይም ‘የመጨረሻ ቀን’ እንደሆነ በግልጽ ያሳያሉ። (ዳንኤል 12:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1) ክርስቶስ ኢየሱስ በዚህ በእኛ ዘመን ከሁሉ የበለጠ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው አንገብጋቢ ነገር ምን እንደሆነ በማያሻማ መንገድ ገልጿል። የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት ‘ለአሕዛብ ሁሉ ምሥክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል’ በማለት በግልጽ ተናግሯል። መጨረሻው የሚመጣው ከዚህ በኋላ ይሆናል።—ማቴዎስ 24:3, 14
ስለዚህ የመንግሥቱን ምሥራች ለመስበክና ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ማንኛውንም አጋጣሚ መጠቀም ይኖርብናል። (ማቴዎስ 28:19, 20) እነዚህ ሥራዎች ወደፊት የማይደገሙ በመሆናቸው በዚህ ሕይወት አድን ሥራ ውስጥ በሙሉ ኃይላችን የምንረባረብበት አጋጣሚ ይህ ብቻ ነው። “የተወደደው ሰዓት አሁን ነው።” አዎን፣ “የመዳን ቀን አሁን ነው።”—2 ቆሮንቶስ 6:2
ጥበብ ያለበት ውሳኔ ማድረግ
በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ወጣቱ ፒተር ስለሚያደርገው ውሳኔ አውጥቶ አውርዶ ያሉትን አማራጮች በሚገባ አመዛዝኗል። ኒውሮሰርጀን ለመሆን ማጥናቱ ስህተት እንደማይሆንበት ተገንዝቦ ነበር። ይሁን እንጂ ለእርሱ ይበልጥ አስፈላጊ የነበረው ነገር ምንድን ነው? ከሥራው አጣዳፊነት አንጻር ሲታይ ለእርሱ ይበልጥ አንገብጋቢ የነበረው ነገር በክርስቲያናዊ አገልግሎት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ነበር። በተጨማሪም ሌሎች ኃላፊነቶችም ነበሩበት። ባለ ትዳር ስለ ነበር በሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ የተሠማራችውን ሚስቱን መደገፍ ነበረበት። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ከዚህም ሌላ ፒተር ከትምህርቱ ጋር በተያያዘ የነበረበትን ብድር መክፈል ይጠብቀዋል። ታዲያ ምን ለማድረግ ወሰነ?
ፒተር ራዲዮሎጂ ለማጥናትና በአልትራሳውንድ የምርመራ ሙያ ለመሥራት ወሰነ። ይህ በተለመደው የሥራ ሰዓት ብቻ መሥራትን የሚጠይቅ ሥራ ነበር። ከዚህም ሌላ ሥልጠናውን የሚወስደው በመደበኛው የሥራ ሰዓት ነበር። አዎን፣ አንዳንዶች ይህን እንደ ዝቅተኛ ሥራ አድርገው ይመለከቱት ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ሥራው ለመንፈሳዊ ነገሮች ብዙ ጊዜ ለመመደብ የሚያስችለው ነበር።
ፒተር እዚህ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ የገፋፋው ሌላም ነገር አለ። በጉዳዩ ላይ ከዚህ የተለየ ውሳኔ የሚያደርጉ ሌሎች ክርስቲያኖችን መተቸት ባያስፈልግም በዓለማዊ ጉዳዮች ከልክ በላይ መጠላለፍ ለአንድ ክርስቲያን አደገኛ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። መንፈሳዊ ኃላፊነቶቹን ቸል እንዲል ሊያደርገው ይችላል። ይህን የሚያሳይ አንድ ሌላ ምሳሌ እንመልከት። ይህኛውም ምሳሌ ቢሆን ከሥራ ጋር የተያያዘ ነው።
አንድ በሙያው የተካነ አርቲስ የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪ ሆኖ ያገለግል ነበር። የስዕል ሥራዎቹን በመሸጥ ራሱን ያስተዳድር ነበር። ምንም እንኳ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያውለው ይበልጥ አስፈላጊ ለሆነው ክርስቲያናዊ አገለግሎት ቢሆንም ጥሩ ኑሮ ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ የአርቲስትነት ሥራውን ይበልጥ የማዳበሩ ምኞት በውስጡ እያደገ መጣ። በስዕል ሥራውና በኪነ ጥበቡ ዓለም በይበልጥ በመጠመዱ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቱን አቋረጠ፣ በመጨረሻም የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ጨርሶ አቆመ። ከዚያም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ተግባሮች ውስጥ በመግባቱ ከክርስቲያን ጉባኤ ተወገደ።—1 ቆሮንቶስ 5:11-13
ያለንበት ወቅት ልዩ ነው
በዛሬው ጊዜ ይሖዋን እንደሚያገለግሉት ሕዝቦቹ እኛም የታመንን ሆነን ለመገኘት እንደምንፈልግ ምንም አያጠራጥርም። የምንኖረው በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በጣም ልዩ በሆነ ወቅት ላይ እንደሆነ እናውቃለን። አምላክን ማገልገላችንን ለመቀጠልና ዛሬ ያሉትን ሁኔታዎች በተሳካ ሁኔታ ለመቋቋም እንድንችል የተለያዩ ማስተካከያዎችን ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። ይህንን የመከር ወቅት ከደረሰበት ገበሬ ጋር ልናወዳድረው እንችላለን። ይህ ወቅት በእርሻ ላይ የተሠማሩ ሠራተኞች ከወትሮው በተለየ ትጋት እንዲሠሩና በቀን ብዙ ሰዓታት በሥራ እንዲያሳልፉ የሚጠይቅ ልዩ የሥራ እንቅስቃሴ የሚያደርግበት ጊዜ ነው። ለምን? ምክንያቱም መከሩ በተወሰነ ወቅት ተሰብስቦ ማለቅ ስለሚኖርበት ነው።
ይህ ክፉ ሥርዓት ሊጠፋ የቀረው ጊዜ በጣም አጭር ነው። አንድ እውነተኛ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የኢየሱስን ምሳሌ ለመኮረጅና ፈለጉን ለመከተል ከፍተኛ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልገው ዛሬ ነው። ኢየሱስ በምድር ያሳለፈው ሕይወቱ ለእርሱ ይበልጥ አንገብጋቢ የነበረው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነበር። “ቀን ሳለ የላከኝን ሥራ ላደርግ ይገባኛል፤ ማንም ሊሠራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች” ብሎ ነበር። (ዮሐንስ 9:4) ኢየሱስ ሌሊት ትመጣለች ሲል መከራ የሚቀበልበትንና በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የሚሞትበትን ጊዜ ማመልከቱ ነበር፤ በዚህ ወቅት ምድራዊ አገልግሎት ስለሚያበቃ ሰማያዊ አባቱ የሰጠውን ሥራ መሥራት አይችልም።
ኢየሱስ በሦስት ዓመት ተኩል አገልግሎቱ ወቅት የተወሰነውን ጊዜውን ተዓምር በመፈጸምና የታመሙትን በመፈወስ እንዳሳለፈ አይካድም። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው የመንግሥቱን መልእክት በማወጅና በሐሰት ሃይማኖት ‘ለታሰሩት ሰዎች መፈታትን በመስበክ’ ነበር። (ሉቃስ 4:18፤ ማቴዎስ 4:17) ኢየሱስ በትጋት ያገለገለ ከመሆኑም በላይ ደቀ መዛሙርቱ እርሱ በጣለው መሠረት ላይ መገንባትና በስብከቱ ሥራ ውጤታማ በሆነ መንገድ ወደፊት መግፋት እንዲችሉ ጊዜውን እነርሱን ለማሠልጠን ተጠቅሞበታል። ኢየሱስ የመንግሥቱን ዓላማ ለማራመድ ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ የተጠቀመ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱም እንዲሁ እንዲያደርጉ ፈልጎ ነበር።—ማቴዎስ 5:14-16፤ ዮሐንስ 8:12
በዚህ ዘመን የምንኖረው ተከታዮቹም ልክ እንደ ኢየሱስ ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ በይሖዋ አምላክ ዓይን ማየት ይኖርብናል። ይህ የነገሮች ሥርዓት ሊጠፋ የቀረው ጊዜ አጭር ነው፤ አምላክ በምሕረቱ ተገፋፍቶ ሁሉም ሰዎች የመዳን አጋጣሚ እንዲያገኙ ይፈልጋል። (2 ጴጥሮስ 3:9) ታዲያ የይሖዋን ፈቃድ በማስቀደም ለሌሎች ጉዳዮቻችን ሁለተኛ ቦታ መስጠታችን ጥበብ አይሆንምን? (ማቴዎስ 6:25-33) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በተለይ ደግሞ እንደ አሁኑ ባለው ልዩ ወቅት ላይ በሌሎች ዘንድ በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ ተደርገው ለሚታዩት ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ አነስተኛውን ቦታ መስጠታችን ተገቢ ነው።
ከመካከላችን በሕይወቱ ውስጥ የአምላክን ፈቃድ በማስቀደሙ የሚጸጸት ይኖራልን? ፈጽሞ አይኖርም፤ ምክንያቱም ክርስቲያኖች የሚከተሉት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ ጎዳና በእጅጉ የሚክስ ነው። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንም እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።”—ማርቆስ 10:29, 30
ጊዜያቸውን ይሖዋን ለማወደስና የመንግሥቱን መልእክት ለማወጅ የሚያውሉ ሰዎች የሚያገኙትን በረከት ማንም በገንዘብ ሊተምነው አይችልም። በጣም ብዙ በረከቶችን ያገኛሉ! ይህም እውነተኛ ወዳጆችን፣ መለኮታዊውን ፈቃድ ከመፈጸም የሚገኘውን እርካታ፣ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘትን እና የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋን ይጨምራል። (ራእይ 21:3, 4) ሰዎችን በመንፈሳዊ መርዳትና ምሥክሮቹ በመሆን ለይሖዋ ቅዱስ ስም ክብር ማምጣት እንዴት ያለ በረከት ነው! ‘ዘመኑን መዋጀት’ በእውነትም የጥበብና መልሶ የሚክስ ጎዳና መሆኑ ፈጽሞ የሚያጠያይቅ አይደለም። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የአምላክን መንግሥት በማወጁ ሥራ መካፈል ያለብን ዛሬ ነው። ይህ ተወዳዳሪ የማይገኝለት አጋጣሚ እንዳያመልጥህ ትጠቀምበታለህን? በዚህ ውሳኔህስ ትቀጥላለህን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሙ በሌላ ተተክቷል።