ይሖዋ መጠጊያ ሆኖልኛል
ፐነሎፒ ማክሪስ እንደተናገረችው
“ይህን ባልሽን ተይው፤ ወንድሞችሽ ሌላ የተሻለ ባል ያገኙልሻል” ስትል እናቴ አጥብቃ ተማጸነችኝ። የምትወደኝ እናቴ ትዳሬን እንዳፈርስ የፈለገችው ለምንድን ነው? እንዲህ ያናደዳት ምንድን ነው?
ሳሞስ ተብላ በምትጠራው የግሪክ ደሴት አምቤሎስ በሚባል አንድ ትንሽ መንደር ውስጥ በ1897 ተወለድኩ። ቤተሰባችን አጥባቂ የግሪክ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ነበር። አባቴ የሞተው እኔ ከመወለዴ ጥቂት ቀደም ብሎ ነው። አስከፊ የሆነውን የድህነት ኑሮ ለመግፋት እናቴ፣ ሦስት ወንድሞቼና እኔ ሌት ተቀን መሥራት ነበረብን።
አንደኛው የዓለም ጦርነት በ1914 ሲፈነዳ ሁለቱ ታላላቅ ወንድሞቼ ለወታደርነት እንዲመዘገቡ ታዘዙ። እነሱም ከዚህ ለመሸሽ ሲሉ እኔንና አንደኛውን ወንድሜን ከእናታችን ጋር ትተውን በስደት ወደ አሜሪካ ሄዱ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1920 ዲሚትሪ የሚባል በመንደራችን የሚኖር አንድ ወጣት አስተማሪ አገባሁ።
ጠቃሚ የሆነ ጥየቃ
አግብቼ ብዙ ሳይቆይ የእናቴ ወንድም ከአሜሪካ ሊጠይቀን መጣ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ ቻርልስ ቴዝ ራስል በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተደረገ ጥናት (የእንግሊዝኛ) በሚል ርዕስ ከጻፋቸው መጽሐፎች መካከል አንዱን ጥራዝ ይዞ መጥቶ ነበር። ይህ መጽሐፍ በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በመባል የሚታወቁት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያሳተሙት መጽሐፍ ነበር።
ዲሚትሪ መጽሐፉን ሲገልጥ ከልጅነቱ ጀምሮ ሲከነክነው ስለነበረው “ሰው ሲሞት ምን ይሆናል?” ስለሚለው ጥያቄ የሚናገር ርዕሰ ጉዳይ ተመለከተ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረበት ወቅት ስለዚሁ ጉዳይ አንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ የሃይማኖት ምሁር ጠይቆ ምንም የሚያረካ መልስ አላገኘም። በመጽሐፉ ላይ የቀረበው ግልጽና ምክንያታዊ የሆነ ማብራሪያ ዲሚትሪን በጣም ስላስደሰተው የግሪክ ወንዶች ብዙውን ጊዜ ተሰባስበው ወደሚጫወቱበት በመንደሩ ውስጥ ወደሚገኘው ቡና ቤት በቀጥታ ሄደ። እዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማራቸውን ነገሮች ነገራቸው።
ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የወሰድነው አቋም
በ1920ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ግሪክ ሌላ ጦርነት ውስጥ ነበረች። ዲሚትሪ በግዳጅ ለወታደርነት ተመልምሎ በትንሿ እስያ ወደሚገኘው የቱርክ ግዛት ተላከ። ከዚያም ቆስሎ ወደ ቤት ተመለሰ። ዲሚትሪ ካገገመ በኋላ በትንሿ እስያ ወደምትገኘው ስሚርና (በአሁኑ ጊዜ ኢዝሚር ወደምትባለው የቱርክ ከተማ) አብሬው ሄድኩ። በ1922 ጦርነቱ በድንገት ሲያቆም አካባቢውን ጥለን መሸሽ ነበረብን። ወዲያው በአንዲት ሰባራ ጀልባ ተሳፍረን ወደ ሳሞስ ጠፍተን ሄድን። ስለ አምላክ ያለን እውቀት ገና ጥቂት ቢሆንም ልክ እቤት እንደደረስን ተንበርክከን አመሰገንነው።
ብዙም ሳይቆይ ዲሚትሪ የደሴቲቱ ዋና ከተማ በሆነችው በቬቲ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት እንዲያስተምር ተመደበ። ዲሚትሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚያዘጋጅዋቸውን ጽሑፎች ማንበቡን ቀጠለ። በአንድ ዝናባማ ምሽት ከካዮስ ደሴት የመጡ ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እቤታችን መጥተው አነጋገሩን። እነዚህ ሰዎች ኮልፖርተርስ (በዚያን ጊዜ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የሚጠሩበት ስም) ሆነው ለማገልገል ከአሜሪካ ወደ አገራቸው ተመልሰው ነበር። የዚያን ቀን እቤታችን አሳደርናቸውና ስለ አምላክ ዓላማዎች ብዙ ነገር ነገሩን።
ከዚያም ዲሚትሪ እንዲህ አለኝ፦ “ፔነሎፒ፣ እውነት ይህ መሆኑንና ይህን መከተል እንዳለብኝ እገነዘባለሁ። ይህ ደግሞ ግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እየሄድኩ መዘመሬንና ከተማሪዎች ጋር ቤተ ክርስቲያን መሄድን ጨርሶ ማቆም አለብኝ ማለት ነው።” ምንም እንኳ ስለ ይሖዋ ያለን እውቀት ውስን ቢሆንም እሱን ለማገልገል ያለን ፍላጎት ከፍተኛ ነበር። ስለሆነም “እኔ እንቅፋት አልሆንብህም፤ ቀጥልበት” ስል መለስኩለት።
“አዎ፣ ግን ይህን እየተከተልን እንዳለን ከታወቀ እኔ ከሥራ እባረራለሁ” በማለት ስጋቱን ገለጸልኝ።
“ምንም አትጨነቅ፤ ሰዎች ሁሉ የሚተዳደሩት በአስተማሪነት ነው እንዴ? እኛ ገና ወጣቶችና ጠንካሮች ነን፤ በአምላክ እርዳታ ሌላ ሥራ ማግኘት እንችላለን” አልኩት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ኮልፖርተር ሆኖ ወደ ሳሞስ እንደመጣ ሰማን። የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር እዳይሰጥ ፖሊስ ፈቃድ እንደከለከለው ስንሰማ እሱን ፍለጋ ሄድን። አንድ ሱቅ ውስጥ ከሁለት የግሪክ ኦርቶዶክስ የሃይማኖት ምሁራን ጋር ሲነጋገር አገኘነው። የሃይማኖት ምሁራኑ ስለ እምነታቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻላቸው አፍረው ወዲያው ሄዱ። ባለቤቴ በኮልፖርተሩ እውቀት በጣም ስለተደነቀ “መጽሐፍ ቅዱስን እንዲህ በቀላሉ ልታብራራ የቻልከው እንዴት ነው?” ሲል ጠየቀው።
“መጽሐፍ ቅዱስን በዘዴ ስለምናጠና ነው” ሲል መለሰ። ቦርሳውን ከፍቶ የአምላክ በገና የተባለውን የማጥኛ መጽሐፍ ካወጣ በኋላ ይህ መጽሐፍ ለእንዲህ ዓይነቱ ጥናት እንዴት እንደሚያገለግል አሳየን። ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት ስለነበረን ባለቤቴ፣ እኔ፣ ኮልፖርተሩና ሌሎች ሁለት ሰዎች ሆነን ከባለ ሱቁ ጋር ወደ መኖሪያ ቤቱ ሄድን። ኮልፖርተሩ የአምላክ በገና የተባለውን መጽሐፍ ለእያንዳንዳችን ከሰጠን በኋላ ወዲያው ማጥናት ጀመርን። ጥናታችንን እኩለ ሌሊት እስኪያልፍ ድረስ ቀጠልን፤ ከዚያም ሊነጋጋ ሲል የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚዘምሯቸውን መዝሙሮች መለማመድ ጀመርን።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ መጽሐፍ ቅዱስን በቀን ውስጥ ለበርካታ ሰዓታት ማጥናት ጀመርኩ። ውጭ አገር ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን በየጊዜው ይልኩልን ነበር። ራሴን ሳልቆጥብ ፈቃዱን ለማድረግ በመሳል ጥር 1926 በጸሎት ራሴን ለአምላክ ወሰንኩ። ቀጥሎ ባለው የበጋ ወቅት እኔና ባለቤቴ ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን በውኃ ጥምቀት አሳየን። ስለምንማራቸው ነገሮች ለሌሎች ለመናገር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረን፤ ስለዚህ ተስፋ የያዘ መልእክት በተባለው ትራክት አማካኝነት ከበር ወደ በር ማገልገል ጀመርን።
ከባድ ተቃውሞ መቋቋም
አንድ ቀን አንዲት ወጣት ሴት በአንድ አነስተኛ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የጸሎት ቤት በሚከናወን የቅዳሴ ሥነ ሥርዓት ላይ እንድገኝ ጋበዘችኝ። “እኔ አምላክን በዚህ መንገድ ማምለክ ትቻለሁ። ልክ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው በመንፈስና በእውነት ነው የማመልከው” በማለት አስረዳኋት። (ዮሐንስ 4:23, 24) በዚህ በጣም በመገረሟ ስለ እኔ ብቻ ሳይሆን ስለ ባለቤቴ ጭምር የሰማችውን ነገር በአካባቢው በሙሉ ነዛች።
ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ይቃወመን ጀመር። እቤታችንም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ ከሆኑ ሰዎች ጋር ስብሰባ በምናደርግበት ቦታ ፈጽሞ ሰላም ነሱን። በኦርቶዶክስ ቀሳውስት ቀስቃሽነት ብዙ ሰዎች ስብሰባ ከምናደርግበት ቤት ውጭ እየተሰበሰቡ ድንጋይ ይወረውሩብን እንዲሁም ይሰድቡን ጀመር።
ተስፋ የያዘ መልእክት የተባለውን ትራክት ስናሰራጭ ልጆች ተሰብስበው “የሺው ዓመት አማኞች” እያሉ ይጮሁና ሌሎች መጥፎ መጥፎ ስድቦች ይሰድቡን ጀመር። ባለቤቴንም የሥራ ጓደኞቹ አስቸገሩት። በ1926 መገባደጃ ላይ ለአስተማሪነት ብቁ አይደለም በሚል ተከሶ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ 15 ቀን እንዲታሰር ተፈረደበት።
እናቴ ይህን ስትሰማ ነበር ባሌን እንድተወው የመከረችኝ። “እማማ ምን ያህል እንደምወድሽና እንደማከብርሽ ታውቂያለሽ። ነገር ግን እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን እንዳናመልክ እንቅፋት የምትሆኝብን ከሆነ በዚህ አልስማማም” ስል መለስኩላት። ያልጠበቀችው መልስ ስለሆነ በጣም አዝና ወደ ቤቷ ተመለሰች።
በ1927 በአቴንስ ውስጥ አንድ ትልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስብሰባ ተካሄደ፤ እኛም በዚህ ስብሰባ ላይ እንድንገኝ ይሖዋ መንገዱን ከፈተልን። ከብዙ የእምነት ጓደኞቻችን ጋር በመሰብሰባችን በጣም ከመደሰታችንም በላይ በመንፈሳዊ ተበረታታን። ወደ ሳሞስ ተመልሰን ለዓለም ገዢዎች የምሥክርነት ቃል (የእንግሊዝኛ) የተባለውን ትራክት በከተሞችና ገጠር መንደሮች 5,000 ቅጂዎችን አሰራጨን።
በዚሁ ጊዜ ገደማ ዲሚትሪ ከአስተማሪነት ሥራው ተባረረ፤ በእኛ ላይ እንዲሁ መሠረተ ቢስ የሆነ ጥላቻ ስላለ ሌላ ሥራ ማግኘት የማይቻል ነገር ነበር። ይሁንና እኔ ልብስ መስፋት ስለምችል፣ ዲሚትሪም ጥሩ ቀለም ቀቢ ስለነበረ ለመተዳደሪያ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ችለን ነበር። በ1928 ባለቤቴና በሳሞስ የሚገኙ ሌሎች አራት ክርስቲያን ወንድሞች ምሥራቹን ስለ ሰበኩ ሁለት ወር እንዲታሰሩ ተፈረደባቸው። ያልታሰርኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እኔ ብቻ ስለነበርኩ እስር ቤት ስንቅ አመላልስላቸው ነበር።
ከባድ ከሆኑ የጤና እክሎች ጋር መታገል
አንድ ወቅት ቱበርኩላር ስፖንዲላይትስ የሚባል የነቀርሳ በሽታ ያዘኝ። ይህ በሽታ ደግሞ በዚያን ጊዜ አይታወቅም ነበር። የምግብ ፍላጎቴ ከመጥፋቱም በላይ የማያቋርጥ ትኩሳት ነበረኝ። የሚደረግልኝ ሕክምና ከአንገቴ እስከ ታፋዬ ድረስ በጀሶ ተሸፍኖ መቆየትን የሚጨምር ነበር። ሕክምናውን እንድቀጥል ለማድረግ የሚያስችለውን ገንዘብ ለማግኘት ባለቤቴ መሬት ቆርጦ ሸጠ። ጭንቀት ስለያዘኝ ብርታት እንዲሰጠኝ ዘወትር ወደ አምላክ እጸልይ ነበር።
ሊጠይቁኝ የሚመጡ ዘመዶች ሁሉ የተቃውሞ እሳት የሚያራግቡ ነበሩ። እናቴ ደግሞ ይህ ሁሉ ችግር እየደረሰባችሁ ያለው ሃይማኖታችሁን ስለ ለወጣችሁ ነው አለች። ወዲያ ወዲህ መገላበጥ ስለማልችል እዚያው የተኛሁበት ሆኜ ለመጽናት የሚያስችለኝን ትዕግሥትና ድፍረት እንዲሰጠኝ የሰማዩ አባታችንን ስማጸነው ትራሴ በእንባ ራሰ።
አልጋዬ አጠገብ ባለው ጠረጴዛ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም ሊጠይቁኝ ለሚመጡ ሰዎች የምሰጣቸው ቡክሌቶችና ትራክቶች አስቀምጥ ነበር። ትንሹ ጉባኤያችን ስብሰባዎቹን የሚያደርገው እኛ ቤት መሆኑ ትልቅ በረከት ነበር። ዘወትር መንፈሳዊ ማበረታቻ ማግኘት ችያለሁ። በአቴንስ የሚገኝ አንድ ሐኪም ላደረገልኝ ሕክምና ገንዘብ ለመክፈል ሌላ መሬት መሸጥ ነበረብን።
ከዚያ ምንም ሳይቆይ ተጓዥ የበላይ ተምልካቹ ጎበኘን። እኔ በዚህ ሁኔታ ላይ መሆኔንና ዲሚትሪ ደግሞ ሥራ እንደሌለው ሲያይ በጣም አዘነ። ሌዝቦስ ደሴት ላይ በሚትሊን ከተማ እንድንኖር ዝግጅት በማድረግ በደግነት ረዳን። በ1934 ወደዚያ ሄድን፤ ዲሚትሪም ሥራ ማግኘት ቻለ። በተጨማሪም የሚያስታምሙኝ ግሩም የሆኑ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች አገኘን። ከአምስት ዓመት ሕክምና በኋላ ሙሉ በሙሉ ዳንኩ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ማለትም በ1946 ቱበርኩላር ፔሪቶናይትስ የሚባል ሌላ የነቀርሳ በሽታ ያዘኝና በድጋሚ በጠና ታመምኩ። በኃይለኛ ትኩሳትና የሕመም ስሜት እየተሰቃየሁ ለአምስት ወር አልጋ ላይ ዋልኩ። ሆኖም እንደ በፊቱ ሁሉ ሊጠይቁኝ ለሚመጡ ሰዎች ስለ ይሖዋ መናገሬን በፍጹም አላቆምኩም። ከጊዜ በኋላ ጤንነቴ ተመለሰልኝ።
ተቃውሞ ቢኖርም አቅኚ መሆን
ከጦርነቱ በፊት በነበሩት ዓመታት በግሪክ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ፋታ የሌለው ተቃውሞ ይደርስባቸው ነበር። ከቤት ወደ ቤት እያገለገልን ሳለን ብዙ ጊዜ ተይዘን ታስረናል። ባለቤቴ በጠቅላላው ወደ አንድ ዓመት ገደማ በእስር ቤት አሳልፏል። ብዙውን ጊዜ ወደ አገልግሎት ስንወጣ ተይዘን ፖሊስ ጣቢያ እናድራለን ብለን በመጠበቅ ተዘጋጅተን እንወጣ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ ፈጽሞ አልተወንም። ለመጽናት የሚረዳንን ድፍረትና ብርታት ሁልጊዜ ይሰጠን ነበር።
በ1940ዎቹ ውስጥ በኢንፎርማንት (አሁን የመንግሥት አገልግሎታችን በሚባለው) ላይ የእረፍት ጊዜ አቅኚነትን አስመልክቶ ስለተደረገው ዝግጅት አነበብኩ። በአገልግሎት በወር 75 ሰዓት ማሳለፍ በሚጠይቀው በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ መካፈል እችል እንደሆነ ለመሞከር ወሰንኩ። ከዚያም ተመላልሶ መጠየቅ የማደርግላቸውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምመራላቸው ሰዎች ቁጥር ጨመረ፤ ለተወሰነ ጊዜ በየሳምንቱ 17 ጥናቶች እመራ ነበር። በተጨማሪም በሚትሊን የንግድ አካባቢ የመጽሔት ደንበኞችን ለማግኘት ችያለሁ፤ በየጊዜው 300 የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎችን በየሱቆች፣ በየቢሮዎችና በባንክ ቤቶች አደርስ ነበር።
በ1964 አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ጉባኤያችንን ሲጎበኝ “እህት ፐነሎፒ በአገልግሎትሽ ምን ያህል እንደተሳካልሽ ከአስፋፊ ካርድሽ ላይ ለማየት ችያለሁ። የዘወትር አቅኚነት ማመልከቻ ለምን አትሞይም?” አለኝ። ለሰጠኝ ማበረታቻ ዘወትር አመሰግነዋለሁ፤ ከሠላሳ ለሚበልጡ ዓመታት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፍያለሁ።
አስደሳች ተሞክሮ
በሚትሊን የግሪክ ስደተኞች ይኖሩበት የነበረ ላንጋዳ የሚባል ብዙ ሕዝብ የሰፈረበት መንደር አለ። ከዚህ በፊት የአክራሪዎች ተቃውሞ ስለገጠመን እዚህ አካባቢ ከቤት ወደ ቤት አንሄድም ነበር። ሆኖም ባለቤቴ እስር ቤት በነበረበት ጊዜ እየተመላለስኩ ስጠይቀው የግድ በዚህ መንደር መሀል አቋርጬ ነበር የማልፈው። ዝናብ በበዛበት አንድ ቀን አንዲት ሴት ባለቤቴ ለምን እንደታሰረ ልትጠይቀኝ ወደ ቤቷ እንድገባ ጋበዘችኝ። ባለቤቴ የታሰረው የአምላክን መንግሥት ምሥራች ስለ ሰበከ እንደሆነና ክርስቶስ የተለያየ መከራ እንደደረሰበት ሁሉ እሱም ተመሳሳይ ነገር እየደረሰበት እንዳለ ገለጽኩላት።
ከጊዜ በኋላ ሌላ ሴት ወደ ቤቷ ጎራ እንድል ዝግጅት አደረገች። ቤቷ ስደርስ ሌሎች 12 ሴቶች ጋብዛ ጠበቀችኝ። ተቃውሞ ሊኖር ይችላል ብዬ ስላሰብኩ የመጣውን ነገር ለመጋፈጥ እንድችል ጥበብና ድፍረት እንዲሰጠኝ ወደ አምላክ ጸለይኩ። ሴቶቹ ብዙ ጥያቄዎች ነበሯቸው፤ አንዳንዶቹ የተቃውሞ ሐሳቦችን አነሱ። ያም ሆነ ይህ እኔ ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ መልሶችን ሰጠኋቸው። ልሄድ ስነሳ የቤቱ ባለቤት የሆነችው ሴት ሌላ ቀን ተመልሼ እንድመጣ ጠየቀችኝ። ግብዣዋን በደስታ ተቀበልኩ። በሚቀጥለው ቀን እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ እዚያ ቤት ስንደርስ ሴቶቹ ተሰብስበው ሲጠብቁን አገኘን።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይታችን በቋሚነት የቀጠለ ሲሆን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ሊገኙ ችለዋል። ከሴቶቹ መካከል ብዙዎች በትክክለኛው እውቀት እድገት ከማድረጋቸውም በላይ ቤተሰቦቻቸውም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል። ይህ ቡድን በሚትሊን ለተቋቋመው አዲስ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ እንደ መሠረት ሆኗል።
ይሖዋ ብዙ ጥሩ ነገር አድርጎልኛል
ይሖዋ እኔና ባለቤቴ እሱን ለማገልገል ያደረግነውን ጥረት ባርኮታል። በ1920ዎቹ አካባቢ በጣት ይቆጠሩ የነበሩት በሳሞስ የሚገኙ ምሥክሮች 130 የሚያክሉ አስፋፊዎች ያሉባቸው ሁለት ጉባኤዎችና አንድ ቡድን እስከመሆን ለማደግ በቅተዋል። እንዲሁም በሊዝቦስ ደሴት አራት ጉባኤዎችና አምስት ቡድኖች ያሉ ሲሆን እነዚህም ወደ 430 የሚጠጉ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎችን ያቀፉ ናቸው። ባለቤቴ በ1977 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ የአምላክን መንግሥት በቅንዓት አውጅዋል። እኛ እውነትን እንዲያውቁ የረዳናቸው በዚህ አገልግሎት አሁንም በቅንዓት እየተሳተፉ መሆናቸውን ማየት እንዴት ያለ መብት ነው! ከልጆቻቸው፣ ከልጅ ልጆቻቸውና ከልጅ ልጅ ልጆቻቸው ጋር ይሖዋን በአንድነት የሚያመልክ ታላቅ ሕዝብ ሆነዋል!
ከ70 ለሚበልጡ ዓመታት በክርስቲያናዊ አገልግሎት የተጓዝኩበት ጎዳና ቀላል አልነበረም። ቢሆንም ይሖዋ ተወዳዳሪ የማይገኝለት መጠጊያ ሆኖልኛል። እድሜዬ እየገፋ ጤንነቴ ከዕለት ወደ ዕለት እያሽቆለቆለ ከመሄዱ የተነሳ የአልጋ ቁራኛ ስለሆንኩ በስብከቱ ሥራ ላከናውን የምችለው በጣም ውስን ነው። ሆኖም ልክ እንደ መዝሙራዊው እኔም ይሖዋ “አንተ መከታዬና መጠጊያዬ ነህ፤ አንተ አምላኬ ስለሆንህ በአንተ እታመናለሁ” ለማለት እችላለሁ።—መዝሙር 91:2 የ1980 ትርጉም
(እኅት ማክሪስ ይህ ተሞክሮ በመዘጋጀት ላይ እያለ ሞታለች። ሰማያዊ ተስፋ ነበራት።)
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1955 ከባለቤቷ ጋር
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እኅት ማክሪስ ጥር 1997 መቶ ዓመት ይሞላት ነበር