የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 1/1 ገጽ 26-29
  • መጥፎ የሆነውን ነገር እንጸየፍ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጥፎ የሆነውን ነገር እንጸየፍ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የጉባኤውን ንጽሕና መጠበቅ
  • የማይቀሩ መጥፎ ውጤቶች
  • ራሱን ለአምላክ የወሰነ ክርስቲያን ኃጢአት ሲሠራ
  • ሕፃን በጾታ ያስነወረ ግለሰብስ?
  • ድክመትን፣ ክፋትንና ንስሐን ለይቶ ማወቅ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ይሖዋ በብዙ ምሕረት ይቅር ይላል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ምንጊዜም የይሖዋን ተግሣጽ ተቀበል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • በመንፈስ ቅዱስ ላይ ኃጢአት ሠርተሃል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 1/1 ገጽ 26-29

መጥፎ የሆነውን ነገር እንጸየፍ

ይሖዋ ቅዱስ አምላክ ነው። በጥንት ዘመን ‘የእስራኤል ቅዱስ’ የነበረ በመሆኑ እስራኤላውያን ንጹሕና ነቀፋ የሌለባቸው እንዲሆኑ ይፈልግ ነበር። (መዝሙር 89:​18) የተመረጡትን ሕዝቦቹን “እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ” ብሏቸዋል። (ዘሌዋውያን 11:​45) ‘ወደ እግዚአብሔር ተራራ ለመውጣት’ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው “እጆቹ የነጹ፣ ልቡም ንጹሕ” መሆን አለበት። (መዝሙር 24:​3, 4) ይህ ማለት ከኃጢአት ድርጊቶች መታቀብ ማለት ብቻ አይደለም። ‘መጥፎ የሆነውን ነገር መጥላት’ ማለት ነው።​— ምሳሌ 8:​13

የእስራኤል ሕዝብ መጥፎ ድርጊቶችን አውቀው ከእነሱ ለመራቅ እንዲችሉ ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ ዝርዝር ሕጎችን ሰጥቷቸዋል። (ሮሜ 7:​7, 12) እነዚህ ሕጎች ሥነ ምግባርን በተመለከተ የተሰጡ ጥብቅ መመሪያዎችን የሚጨምሩ ነበሩ። ምንዝር፣ ግብረ ሰዶም፣ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚደረግ የጾታ ግንኙነትና ከእንስሳት ጋር ግንኙነት ማድረግ ሰዎችን በመንፈሳዊ የሚበክሉ የረከሱ ተግባራት እንደሆኑ ተገልጾ ነበር። (ዘሌዋውያን 18:​23፤ 20:​10-17) በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ወራዳ ተግባሮች ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ሰዎች ከእስራኤል ሕዝብ መካከል እንዲጠፉ ይደረግ ነበር።

የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ‘የአምላክ እስራኤል’ ከሆነም በኋላ በእነሱ ላይ ተመሳሳይ የሥነ ምግባር ደረጃዎች ተጥሎባቸዋል። (ገላትያ 6:​16) ክርስቲያኖችም ‘መጥፎ የሆነውን ነገር መጸየፍ’ ያስፈልጋቸዋል። (ሮሜ 12:​9) ይሖዋ “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” በማለት ለእስራኤላውያን የተናገራቸው ቃላት በእነሱም ላይ ይሠራሉ። (1 ጴጥሮስ 1:​15, 16) እንደ ዝሙት፣ ምንዝር፣ ግብረ ሰዶም፣ ከእንስሳት ጋር መገናኘትና በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚደረግ የጾታ ግንኙነት የመሳሰሉት የረከሱ ተግባራት የክርስቲያን ጉባኤን እንዲበክሉ አይፈቀድላቸውም። በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች መካፈላቸውን የሚቀጥሉ ሰዎች በአምላክ መንግሥት ውስጥ ቦታ አይኖራቸውም። (ሮሜ 1:​26, 27፤ 2:​22፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10፤ ዕብራውያን 13:​4) በእነዚህ ‘መጨረሻ ቀናት’ “በሌሎች በጎች” ላይም ተመሳሳይ የሆኑ የሥነ ምግባር ደረጃዎች ይሠራሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1፤ ዮሐንስ 10:​16) በዚህም ምክንያት ቅቡዓን ክርስቲያኖችና ሌሎች በጎች በይሖዋ ምሥክርነታቸው የአምላካቸውን ስም መሸከም የሚችሉ ንጹሕና ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሕዝቦች ሊሆኑ ችለዋል።​— ኢሳይያስ 43:​10

የጉባኤውን ንጽሕና መጠበቅ

ከዚህ በተቃራኒ ዓለም ማንኛውንም ዓይነት የሥነ ምግባር ብልግና በቸልታ ይመለከታል። ምንም እንኳ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከዚህ የተለዩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ይሖዋን በማገልገል ላይ የሚገኙ ብዙ ሰዎች በአንድ ወቅት በዓለም ውስጥ እንደነበሩ መዘንጋት የለብንም። ቅዱስ የሆነውን አምላካችንን ከማወቃቸው በፊት የውዳቂው ሥጋቸውን ምኞትና ቅዠት የማይፈጽሙበት ምንም ምክንያት እንደሌለ ተሰምቷቸው “በወራዳ ሥነ ምግባር ውስጥ ተዘፍቀው” የነበሩ ብዙዎች አሉ። (1 ጴጥሮስ 4:​4 አዓት) ሐዋርያው ጳውሎስ ወራዳ የሆኑት አሕዛብ የሚፈጽሟቸውን የረከሱ ተግባራት ከገለጸ በኋላ “ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደ እነዚህ ነበራችሁ” ብሎ ነበር። ሆኖም ከዚያ ቀጥሎ “ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል” ብሏል።​— 1 ቆሮንቶስ 6:​11

ይህ እንዴት የሚያጽናና አነጋገር ነው! አንድ ግለሰብ በቀድሞ ሕይወቱ ምንም ዓይነት ድርጊት ቢፈጽም ስለ ክርስቶስ የሚገልጸው ክብራማ ምሥራች ልቡን ሲነካው ይለወጣል። በተማራቸው ነገሮች ላይ እምነት ካሳደረ በኋላ ራሱን ለይሖዋ አምላክ ይወስናል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በንጹሕ ሥነ ምግባር ስለሚመላለስ በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋም ይኖረዋል። (ዕብራውያን 9:​14) ቀደም ሲል የፈጸማቸው ኃጢአቶች ይቅር ይባሉለታል፤ ስለዚህ ‘በፊቱ ያለውን ለመያዝ ሊዘረጋ’ ይችላል።a​— ፊልጵስዩስ 3:​13, 14፤ ሮሜ 4:​7, 8

ይሖዋ ነፍስ ግድያና ምንዝር የፈጸመውንና በኋላም ንስሐ የገባውን ዳዊትን ይቅር ብሎታል፤ አጸያፊ የጣዖት አምልኮ የፈጸመውንና ብዙ ደም ያፈሰሰውን ምናሴንም ቢሆን ንስሐ ከገባ በኋላ ይቅር ብሎታል። (2 ሳሙኤል 12:​9, 13፤ 2 ዜና መዋዕል 33:​2-6, 10-13) እኛም ንስሐ ከገባንና በቅንነትና በትሕትና ወደ እሱ ከቀረብን ይሖዋ ይቅር ሊለን ዝግጁ በመሆኑ አመስጋኞች ልንሆን እንችላለን። ሆኖም ይሖዋ ዳዊትንና ምናሴን ይቅር ቢላቸውም እንኳ እነዚህ ሁለት ሰዎችና እስራኤላውያን ኃጢአታቸው ካስከተለባቸው መጥፎ ውጤት የትም ሊያመልጡ አልቻሉም። (2 ሳሙኤል 12:​11, 12፤ ኤርምያስ 15:​3-5) በተመሳሳይም ምንም እንኳ ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር የሚላቸው ቢሆንም የፈጸሟቸው ድርጊቶች የሚያስከትሉባቸው የማይቀሩ ውጤቶች ሊኖሩ ይችላሉ።

የማይቀሩ መጥፎ ውጤቶች

ለምሳሌ ያህል አንድ በመጥፎ ሥነ ምግባር የሚኖር ሰው ኤድስ ከያዘው በኋላ እውነትን ይቀበልና በሕይወቱ ውስጥ ለውጥ አድርጎ ራሱን ወስኖ ወደ መጠመቅ ደረጃ ሊደርስ ይችላል። አሁን ከአምላክ ጋር ዝምድና የመሠረተ በመንፈሳዊ ንጹሕ የሆነ ግለሰብ ሲሆን ስለ መጪው ጊዜም አስደናቂ ተስፋ አለው፤ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ኤድስ አለበት። ከጊዜ በኋላ በበሽታው ምክንያት ሊሞት ይችላል፤ ነገሩ በጣም አሳዛኝ ቢሆንም ቀደም ሲል የነበረው አኗኗር ያስከተለበት ሊያመልጠው የማይችለው መጥፎ ውጤት ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ቀደም ሲል የፈጸሙት ከባድ የሥነ ምግባር ብልግና በሌሎች መንገዶች ጭምር ሊጎዳቸው ይችላል። እነዚህ ክርስቲያኖች ከተጠመቁ በኋላ ለብዙ ዓመታት ምናልባትም በዚህ ሥርዓት ቀሪ ጊዜያት ሁሉ ቀደም ሲል ወደ ነበራቸው የአኗኗር ዘይቤ እንዲመለሱ ሥጋቸው የሚያመጣባቸውን ግፊቶች መዋጋት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ብዙዎች በአምላክ መንፈስ እርዳታ በውጊያው አሸናፊዎች ሆነዋል። ይሁን እንጂ ያለማቋረጥ መጋደል ያስፈልጋቸዋል።​— ገላትያ 5:​16, 17

እንደነዚህ ዓይነቶቹ ግለሰቦች በውስጣቸው የሚሰማቸውን ኃይለኛ ግፊት እስከ ተቆጣጠሩ ድረስ ኃጢአት አይሠሩም። ይሁን እንጂ ወንዶች ከሆኑ ኃይለኛ የሆኑ ሥጋዊ ግፊቶችን ገና እየተዋጉ ስላሉ በጉባኤው ውስጥ አንድ ኃላፊነት ‘ላለመያዝ’ በጥበብ ሊወስኑ ይችላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:​1) ለምን? ጉባኤው በሽማግሌዎች ላይ የሚጥልባቸው አደራ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው። (ኢሳይያስ 32:​1, 2፤ ዕብራውያን 13:​17) ሽማግሌዎች ብዙ የግል ጉዳዮች እንደሚያጋጥሟቸውና ጥንቃቄ የሚጠይቁ ሁኔታዎችን መያዝ እንደሚያስፈልጋቸው ይገነዘባሉ። ንጹሕ ካልሆኑ ሥጋዊ ምኞቶች ጋር ያለማቋረጥ የሚታገል ሰው እንዲህ ዓይነቱን የኃላፊነት ቦታ ቢይዝ ፍቅራዊና የጥበብ እርምጃ ካለመሆኑም ሌላ ምክንያታዊ አይደለም።​— ምሳሌ 14:​16፤ ዮሐንስ 15:​12, 13፤ ሮሜ 12:​1

ከመጠመቁ በፊት ሕፃን በጾታ ያስነወረ ግለሰብ ድርጊቱ ሌላ መጥፎ ውጤት ሊያስከትልበት ይችላል። እውነትን ሲያውቅ ንስሐ ገብቶ ከኃጢአቱ ይመለሳል፤ በዚህ መንገድ እንዲህ ዓይነቱ ከባድ ኃጢአት በጉባኤው ውስጥ ሰርጎ እንዲገባ አያደርግም። ከዚህ በኋላ ጥሩ እድገት አድርጎ መጥፎ ግፊቶቹን ሙሉ በሙሉ ሊቋቋም ይችላል፤ እንዲያውም በጉባኤው ውስጥ ወደ አንድ የኃላፊነት ቦታ ለመድረስ ‘ይጣጣር’ ይሆናል። ሆኖም ቀደም ሲል ልጅ በማስነወሩ ያተረፈው መጥፎ ስም ከኅብረተሰቡ አእምሮ ፈጽሞ ያልተፋቀ ከሆነስ? “የማይነቀፍ፣ . . . ከክስ ነፃ የሆነ . . . በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል” የሚለውን ብቃት ያሟላልን? (1 ጢሞቴዎስ 3:​1-7, 10፤ ቲቶ 1:​7) በፍጹም አያሟላም። በመሆኑም ለጉባኤ ልዩ መብቶች ብቁ አይሆንም።

ራሱን ለአምላክ የወሰነ ክርስቲያን ኃጢአት ሲሠራ

ይሖዋ እኛ ደካሞች እንደሆንንና ከተጠመቅንም በኋላ እንኳ ኃጢአት ልንሠራ እንደምንችል ያውቃል። ሐዋርያው ዮሐንስ በዘመኑ ለነበሩት ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ልጆቼ ሆይ፣ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፣ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፣ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።” (1 ዮሐንስ 2:​1, 2) አዎን፣ ኃጢአት የሠሩ የተጠመቁ ክርስቲያኖች ከልባቸው ንስሐ ከገቡና ከመጥፎ አካሄዳቸው ከተመለሱ ይሖዋ በኢየሱስ መሥዋዕት አማካኝነት ይቅር ይላቸዋል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ ለዚህ ምሳሌ የሚሆን ነገር ተስተውሏል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ አዲስ ጉባኤ ውስጥ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚደረግ የጾታ ግንኙነት እንደተፈጸመ በመስማቱ ጉዳዩ የሚመለከተው ግለሰብ እንዲወገድ መመሪያ ሰጥቷል። ከጊዜ በኋላ ኃጢአት የሠራው ግለሰብ ንስሐ ስለገባ ጳውሎስ ጉባኤው እንዲመልሰው መክሯል። (1 ቆሮንቶስ 5:​1, 13፤ 2 ቆሮንቶስ 2:​5-9) በዚህ መንገድ የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት ባለው የመፈወስ ኃይልና የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ባስገኘው ታላቅ ዋጋ አማካኝነት ሰውዬው ከኃጢአቱ ነጽቷል። በዛሬው ጊዜም ተመሳሳይ ነገር ሊከሰት ይችላል። ሆኖም ከባድ ኃጢአት የሠራ አንድ የተጠመቀ ክርስቲያን ንስሐ ቢገባና ይሖዋ ይቅር ቢለውም እንኳ ኃጢአቱ በእሱ ላይ የሚያስከትልበት መጥፎ ውጤት ሊኖር ይችላል።​— ምሳሌ 10:​16, 17፤ ገላትያ 6:​7

ለምሳሌ ያህል ራስዋን ለይሖዋ የወሰነች አንዲት ወጣት ዝሙት ከፈጸመች በኋላ በድርጊቷ በጣም ብትጸጸት ቀስ በቀስ በጉባኤው እርዳታ መንፈሳዊ ጤንነቷ እንደገና ሊመለስላት ይችላል። ሆኖም በፈጸመችው የሥነ ምግባር ብልግና ምክንያት ብታረግዝስ? በፈጸመችው ድርጊት ምክንያት ከዚያ በኋላ መላ ሕይወቷ መለወጡ የማይቀር ነው። አንድ ምንዝር የፈጸመ ግለሰብ ንስሐ ሊገባና ላይወገድ ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ንጹሕ የሆነችው የትዳር ጓደኛው እሱን ለመፍታት ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አላት፤ ምናልባት እሱን ልትፈታው ትፈልግ ይሆናል። (ማቴዎስ 19:​9) ሴትየዋ ባልዋን ከፈታችው ሰውዬው በይሖዋ ፊት የኃጢአት ይቅርታ ቢያገኝም እንኳ ቀሪውን ሕይወቱን ኃጢአቱ ያስከተለበትን መጥፎ ውጤት ተሸክሞ ይኖራል።​— 1 ዮሐንስ 1:​9

ሌላ ሴት ለማግባት ሲል ፍቅር በጎደለው ሁኔታ ሚስቱን ስለፈታ ግለሰብስ ምን ለማለት ይቻላል? ምናልባት ከጊዜ በኋላ ንስሐ ገብቶ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሊመለስ ይችል ይሆናል። ከጊዜ ብዛት እድገት አድርጎ “ወደ ጉልምስና ሊደርስ” ይችላል። (ዕብራውያን 6:​1 አዓት) ይሁን እንጂ የመጀመሪያዋ ሚስቱ እስካላገባች ድረስ በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ይዞ ለማገልገል ብቁ አይሆንም። የመጀመሪያ ሚስቱን ለመፍታት የሚያበቃ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት ስላልነበረው “የአንዲት ሚስት ባል” አይደለም።​— 1 ጢሞቴዎስ 3:​2, 12

እነዚህ ምክንያቶች አንድ ክርስቲያን መጥፎ የሆነውን ነገር መጸየፍ እንዳለበት የሚጠቁሙ ከባድ ምክንያቶች አይደሉምን?

ሕፃን በጾታ ያስነወረ ግለሰብስ?

አንድ የተጠመቀ አዋቂ ክርስቲያን አንድን ሕፃን በጾታ ቢያስነውርስ? ኃጢአተኛው በጣም ክፉ ከመሆኑ የተነሣ ይሖዋ ፈጽሞ ይቅር አይለውምን? የግድ ይቅር አይለውም ማለት አይቻልም። ኢየሱስ ‘መንፈስ ቅዱስን የሰደበ’ ኃጢአቱ ይቅር አይባልለትም ብሏል። በተጨማሪም እውነትን ካወቀ በኋላ ሆን ብሎ ኃጢአት እየሠራ ለሚኖር ግለሰብ ስለ ኃጢአቱ የሚቀርብ ምንም መሥዋዕት እንደማይኖር ጳውሎስ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:​10፤ ዕብራውያን 10:​26, 27) ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትኛውም ስፍራ ቢሆን ዘመዱ ሆነም አልሆነም አንድን ሕፃን በጾታ ያስነወረ አዋቂ ክርስቲያን ኃጢአቱ ይቅር አይባልለትም የሚል አይገኝም። ሆኖም ከልቡ ንስሐ ከገባና አካሄዱን ከለወጠ ከኃጢአቱ ንጹሕ ሊሆን ይችላል። ሆኖም አሁንም ቢሆን ቀደም ሲል በውስጡ እንዲያድጉ ካደረጋቸው መጥፎ የሆኑ ሥጋዊ ምኞቶች ጋር መታገል ሊኖርበት ይችላል። (ኤፌሶን 1:​7) በተጨማሪም የትም ሊሸሸው የማይችለው የፈጸመው ድርጊት የሚያስከትልበት መጥፎ ውጤት ሊኖር ይችላል።

ሕፃን ያስነወረው ግለሰብ በሚኖርበት አገር ሕግ መሠረት ሊታሰር ወይም መንግሥት ሌላ ቅጣት ሊቀጣው ይችላል። ጉባኤው ከዚህ ችግር አያድነውም። ከዚህም በላይ ሰውዬው ከዚያን ጊዜ ወዲህ ግምት ውስጥ መግባት የሚኖርበት አንድ ከባድ ድክመት እንዳለበት አሳይቷል። ንስሐ መግባቱን ካሳየ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግ፣ በመስክ አገልግሎት እንዲሳተፍ፣ በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል እንዲያቀርብና በአገልግሎት ስብሰባ ላይ ከመድረክ ማስተማርን የማይጠይቁ ክፍሎች እንዲያቀርብ ማበረታቻ ሊሰጠው ይችላል። ይህ ማለት ግን በጉባኤው ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ይዞ ለማገልገል ብቁ ነው ማለት አይደለም። ለዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች የሚሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው?

በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ሽማግሌ “ራሱን የሚገዛ” መሆን አለበት። (ቲቶ 1:​8) እርግጥ ሁላችንም ብንሆን ራሳችንን ሙሉ በሙሉ መግዛት አንችልም። (ሮሜ 7:​21-25) ይሁን እንጂ አንድን ሕፃን በጾታ ያስነወረ ራሱን ለአምላክ የወሰነ አዋቂ ክርስቲያን ከመጠን በላይ የሆነ ሥጋዊ ድክመት እንዳለበት አሳይቷል። እንዲህ ዓይነቱ አዋቂ ሰው ሌላ ሕፃን በጾታ ሊያስነውር እንደሚችል ከተሞክሮ መረዳት ተችሏል። እርግጥ ሕፃንን በጾታ ያስነወረ እያንዳንዱ ግለሰብ ኃጢአቱን ይደግማል ማለት ባይሆንም ብዙዎች እንዲህ አድርገዋል። በተጨማሪም ማን በድጋሚ ልጆችን በጾታ እንደሚያስነውርና እንደማያስነውር ለማወቅ የሚያስችል ልብን የመመርመር ችሎታ ጉባኤው የለውም። (ኤርምያስ 17:​9) ስለዚህ “በማንም ላይ ፈጥነህ እጆችህን አትጫን፣ በሌሎችም ኃጢአት አትተባበር” የሚለው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር ልጆችን በጾታ ባስነወሩ የተጠመቁ አዋቂ ግለሰቦች ረገድ በይበልጥ የሚሠራ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:​22) ለልጆቻችን ጥበቃ ሲባል ቀደም ሲል አንድን ሕፃን በጾታ እንዳስነወረ የሚታወቅ ግለሰብ በጉባኤው ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ብቁ አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ አቅኚ ሊሆን ወይም በማንኛውም ልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ሊሠማራ አይችልም።​— በዘጸአት 21:​28, 29 ላይ ከሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር አወዳድር።

‘አንዳንድ ሰዎች ሌላ ዓይነት ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ንስሐ ገብተው እንደገና የሠሩትን ኃጢአት ይደግሙ የለምን?’ ብለው አንዳንዶች ይጠይቁ ይሆናል። አዎን፣ ይህ ተከስቷል፤ ሆኖም ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ሌሎች ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ ግለሰብ በሌላ አዋቂ ሰው ላይ ወሲብ ለመፈጸም ቢቃጣ አዋቂው ሰው የእሱን ወይም የእሷን ጥያቄ መቃወም እንደሚችል የታወቀ ነው። ልጆችን ግን በቀላሉ ማታለል፣ ግራ ማጋባት ወይም ማስፈራራት ይቻላል። መጽሐፍ ቅዱስ ልጆች ጥበብ እንደሚጎድላቸው ይናገራል። (ምሳሌ 22:​15፤ 1 ቆሮንቶስ 13:​11) ኢየሱስ ሕፃናትን ምንም ክፋት የማያውቁ የዋሆች መሆናቸውን በመጥቀስ እንደ ምሳሌ አድርጎ ተጠቅሞባቸዋል። (ማቴዎስ 18:​4፤ ሉቃስ 18:​16, 17) ሕፃናት ተንኮል የማያውቁ ቅኖች የሚሆኑበት አንዱ ምክንያት ምንም ተሞክሮ የሌላቸው በመሆናቸው ነው። አብዛኞቹ ልጆች ደግና ሌሎችን ለማስደሰት የሚፈልጉ ስለሆኑ የሚያውቁትና የሚተማመኑበት አንድ አዋቂ የሆነ ግለሰብ በቀላሉ በጾታ ሊያስነውራቸው ይችላል። ስለዚህ ጉባኤው በይሖዋ ፊት ልጆቹን ከአደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት።

ተገቢውን ሥልጠና ያገኙ ልጆች ወላጆቻቸውን፣ አረጋውያንን ወይም ሌሎች አዋቂዎችን መታዘዝና ማክበር ይማራሉ። (ኤፌሶን 6:​1, 2፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​1, 2፤ ዕብራውያን 13:​7) ከእነዚህ አዋቂዎች አንዱ የሕፃኑን ቅንነት አለአግባብ ተጠቅሞ በማታለል ወይም በግድ በእሱ ወይም በእሷ ላይ ወሲብ ቢፈጽምባቸው ይህ ዘግናኝ ድርጊት ምን ጊዜም ከአእምሯቸው የማይጠፋ ይሆናል። በዚህ መንገድ በጾታ የተነወሩ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የደረሰባቸውን የስሜት መቃወስ ለመቋቋም የብዙ ዓመታት ትግል ይጠይቅባቸዋል። ስለዚህ እንዲህ ዓይነቱ ሕፃናትን በጾታ ያስነወረ ግለሰብ በጉባኤ ውስጥ ከባድ ተግሣጽ ከመቀበሉም በላይ አንዳንድ እገዳዎች ይደረጉበታል። አሳሳቢው ነገር እሱ በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት አለመያዙ ሳይሆን የጉባኤው ንጽሕና ነው።​— 1 ቆሮንቶስ 5:​6፤ 2 ጴጥሮስ 3:​14

አንድን ሕፃን ያስነወረ ግለሰብ ከልቡ ንስሐ ከገባ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሥራ ላይ ማዋል የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ይገነዘባል። መጥፎ የሆነውን ነገር ከልቡ መጸየፍን ከተማረ ቀደም ሲል የፈጸመውን ነገር በጣም ይጠላዋል፤ እንዲሁም ኃጢአቱን ላለመድገም ይታገላል። (ምሳሌ 8:​13፤ ሮሜ 12:​9) በተጨማሪም እንደሱ ያለው ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ቅዱስ የሆነውን አምላካችንን ለማምለክና ወደፊት በምድር ላይ ለዘላለም ከሚኖሩት “ቅኖች” መካከል ለመሆን ተስፋ ማድረግ በመቻሉ ይሖዋ ላሳየው ታላቅ ፍቅር አመስጋኝ እንደሚሆን አያጠራጥርም።​— ምሳሌ 2:​21

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የግንቦት 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ እትም “የአንባብያን ጥያቄዎች”ን ተመልከት።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ይሖዋ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችን ይቅር የሚላቸው ቢሆንም እንኳ የፈጸሟቸው ድርጊቶች የሚያስከትሏቸው መጥፎ ውጤቶች ሊኖሩ ይችላሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ