የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች ስብሰባ አደረጉ
“እስከ ዛሬ ድረስ በተገኘንባቸው የአውራጃ ስብሰባዎች ሁሉ ታንጸናል” ሲል በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ተናግሯል። “የአሁኑ ዓመት ግን በቃላት ሊገለጽ አይችልም። በየዕለቱ ከስብሰባው ወደ ቤታችን ስንመለስ የሚቀጥለው ቀን ፕሮግራም ከገመትነው በላይ ይሆናል ብለን እናስብ ነበር። ደግሞም ከገመትነው በላይ ሆኗል!”
“የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከተገኘህ ከዚህ ከፍተኛ አድናቆት ያሳየ ወንድም ሐሳብ ጋር እንደምትስማማ አያጠራጥርም። እያንዳንዱ የስብሰባ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መልእክተኞች በመሆን በሚያከናውኑት ተልእኮ የተለያዩ ገጽታዎች ላይ ያተኮረ ነበር። እስቲ የሦስቱን ቀናት ፕሮግራም እንከልስ።
“ሰላምንም የሚያወራ . . . እጅግ ያማረ ነው”
ይህ የመጀመሪያው ቀን ስብሰባ ጭብጥ ነበር። ጭብጡ በኢሳይያስ 52:7 ላይ የተመሠረተ ነበር። በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ብዙዎች በፈታኝ ሁኔታዎች ሥር ይሖዋን በማገልገል ላይ ናቸው። “ቀናተኛ ከሆኑት የሰላም አዋጅ ነጋሪዎች አፍ መስማት” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር ከእነዚህ የታመኑ ሰዎች መካከል ከአንዳንዶቹ ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶች ይዞ ነበር። የግል ተሞክሯቸውን መስማት በጣም የሚያበረታታ ነበር። በዚህ መንገድ ተሰብሳቢዎቹ ይሖዋ እነሱንም ሊያጠነክራቸው እንደሚችልና አስፈላጊ ከሆነም እነሱን ለመርዳት ሲል “ከወትሮው የበለጠ ኃይል” እንደሚሰጣቸው እርግጠኞች ሆነዋል።— 2 ቆሮንቶስ 4:7
ይሖዋ እንድናሟላ የሚፈልግብን ነገሮች ሸክም አይደሉም። (1 ዮሐንስ 5:3) ይህ በጠዋቱ ፕሮግራም በመጨረሻ ንግግር ላይ በግልጽ ተብራርቷል። በዚህ ንግግር መደምደሚያ ላይ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው ? የተሰኘ ባለ 32 ገጽ ብሮሹር ወጥቷል። ውብ የሆኑ ሥዕሎች ያሉት ይህ አዲስ የማስጠኛ ጽሑፍ ብዙ ሰዎች የአምላክን ዓላማዎች እንዲማሩ በመርዳት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ምንም አያጠራጥርም። በዚህ አዲስ ጽሑፍ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል የሚገልጹ ሐሳቦች በዚህ መጽሔት የመጨረሻ የጥናት ርዕስና በገጽ 16 እና 17 ላይ ይገኛሉ።
“በመልካም ሥራ መጽናት” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር ይሖዋ የሚደርሱብንን ፈተናዎች በሚገባ እንደሚያውቅ የሚገልጽ ነበር። መጽናት ማለት ከአቋም ፍንክች አለማለትና ተስፋ አለመቁረጥ ማለት ነው። ይሖዋ እኛን ለማገዝ ቃሉን፣ መንፈሱንና ድርጅቱን ሰጥቶናል። ምንም እንኳ መስበክ መጽናትን የሚጠይቅ ቢሆንም ስብከት ራሱ እምነታችን ሕያው ሆኖ እንዲቆይ ስለሚያደርግ ለመጽናት ይረዳል። ወደ ሩጫው ማቆሚያ መስመር ስለተጠጋን በእኛ ላይ የሚደርሱት ችግሮች ቅንዓታችንን እንዲቀንሱብን መፍቀድ የለብንም። ምክንያቱም የሚድኑት እስከ መጨረሻው የሚጸኑ ሰዎች ብቻ ናቸው።— ማቴዎስ 24:13
“የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች በመሆን የምናከናውነው የሥራ ድርሻ” በሚል ርዕስ በቀረበው የጭብጡ ቁልፍ ንግግር አይሁዳውያን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ከወጡ በኋላ በ537 ከዘአበ በኢየሩሳሌም ውስጥ ንጹሕ አምልኮ እንደገና ስለ መቋቋሙ የሚያብራራ ነበር። ተናጋሪው ይህ ድርጊት የአምላክ መንግሥት በቅርቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያከናውነውን ነገር የሚጠቁም እንደሆነ ገልጿል። (መዝሙር 72:7፤ ኢሳይያስ 9:7) በአሁኑ ጊዜ የተሰጠን ሥራ ስለ መንግሥቱ የሚገልጸውን ምሥራች መስበክና ከዚህ መልእክት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ነው። ለአምላክና እንደኛው ላሉ ሰዎች ያለን ፍቅር ይህን ሥራ ማከናወናችንን እንድንቀጥል ሊገፋፋን ይገባል።— ሥራ 5:42
በዓርቡ ፕሮግራም ላይ ጎላ ብሎ የተገለጸው “መዝናኛዎች ከያዟቸው ስውር ወጥመዶች ተጠንቀቁ” የሚል ርዕስ ያለው ሲምፖዚየም ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉት ሙዚቃዎች፣ ፊልሞች፣ የቪዲዮ ካሴቶች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የቪዲዮ ጨዋታዎች፣ መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና አስቂኝ ትርኢቶች ብዙውን ጊዜ አጋንንታዊ አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁ ናቸው። ስለዚህ ‘ክፉ የሆነውን ነገር መጸየፍ’ እና ‘ከመልካም ነገር ጋር መጣበቅ’ ያስፈልገናል። (ሮሜ 12:9) አዎን፣ ንጹሕ በሆኑ፣ በጎነት ባለባቸውና በሚያስመሰግኑ ነገሮች ላይ እያተኮርን ወራዳ የሆኑ መዝናኛዎችን እንደ አጸያፊ ነገሮች አድርገን በመመልከት ከእነሱ መሸሽ ይኖርብናል። (ፊልጵስዩስ 4:8) የይሖዋ ድርጅት አዘጋጅቶ የሚያቀርባቸው ጽሑፎችና የምርምር መሣሪያዎች አእምሯችንን በሚያንጹ ሐሳቦች የሚያነቃቁ ከመሆናቸውም በላይ መልካምና ክፉውን ለይተን እንድናውቅ ያሠለጥኑናል። (ዕብራውያን 5:14) አንድ ሰው በሚናወጥ ባሕር ውስጥ ከመስጠም ለመዳን አንድን የሚንሳፈፍ ግንድ የሙጥኝ እንደሚል ሁሉ እኛም በእነዚህ ዝግጅቶች በሚገባ መጠቀም ይኖርብናል።
ከዚያም “ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ አንዳችም ተቀናቃኝ ነገር አትታገሡ” የሚለው ንግግር ቀረበ። በሺህ የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ጥቂት ሲቀራቸው በጾታ ብልግና ተጠምደው ወድቀዋል። ፊንሐስ ንጹሕ አምልኮን የሚቀናቀን አንዳችም ነገር እንዲኖር አልፈቀደም። በክፉ አድራጊዎቹ ላይ ቆራጥነት የተሞላበት እርምጃ ወሰደ፤ በዚህ መንገድ ለይሖዋ ያሳየው ታማኝነት ይሖዋን አስደስቶታል። (ዘኁልቁ 25:1-13) የሰይጣን ዓላማ እያንዳንዳችንን ለአዲሱ ዓለም እንዳንበቃ ማድረግ ነው። ስለዚህ እኛን ለማርከስ የሚያደርጋቸውን ጥረቶች እንደ ፊንሐስ መቃወም ያስፈልገናል። ባለ ትዳርም ሆንን ነጠላ “ከዝሙት መሸሽ” ይኖርብናል።— 1 ቆሮንቶስ 6:18
“የአምላክ ቃል እንዳይበረዝ በታማኝነት መከላከል” የሚለው ንግግር የመጀመሪያው ቀን ስብሰባ መቋጫ ነበር። ብዙ ተርጓሚዎች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ለውጠዋል ወይም ደግሞ ሰርዘዋል። ለምሳሌ ያህል አዲስ ኪዳንና መዝሙራት፤ ሁሉን አቀፍ ትርጉም (The New Testament and Psalms: An Inclusive Version ) የተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጆች የሴቶች መብት ተከራካሪዎችን ተቃውሞ ለማብረድ ሲሉ አምላክን አባት ከማለት ይልቅ አባት-እናት ያሉት ሲሆን ኢየሱስን ደግሞ በወንዴ ጾታ “የሰው ልጅ” ከማለት ይልቅ “ሰብዓዊ” ብለውታል። ከዚህ በተቃራኒ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም ከመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥና የግሪክኛ ጽሑፎች ጋር በጣም የተቀራረበ በመሆኑ በብዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ጉዳዮች ላይ ያለንን አስተሳሰብ ለማስተካከል አገልግሏል። ለምሳሌ ያህል ተናጋሪው እንዲህ ብሎ ነበር:- “በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ ይሠራበት የነበረውን ሥርዓት በመከተል የሽማግሌዎችን አካላት በመሾም ጉባኤዎችን በአዲስ ሁኔታ ለማዋቀር ያስቻለን በአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ውስጥ የሚገኘው ትክክለኛ አተረጓጎም ነበር።” በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱሱን በማንበብና ምክሩን በሥራ ላይ በማዋል ለአምላክ ቃል ያለንን ታማኝነት እናሳያለን። በተጨማሪም ተናጋሪው እንዲህ ብሎ ነበር:- “የአምላክን ቃል በቅንዓት ለሰዎች ስንሰብክና ሌሎችን በምናስተምርበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር ከግል አስተሳሰባችን ጋር እንዲስማማ ለማድረግ ሳናጣምመው ወይም ሳንለጥጠው በጥንቃቄ ስንጠቀምበት የአምላክ ቃል ታማኝ ጠበቆች መሆናችንን እናሳያለን።”
‘የአምላክ ሰላም ከሐሳብ ሁሉ ከፍ ያለ ነው’
የሁለተኛው ቀን ስብሰባ በፊልጵስዩስ 4:7 (አዓት ) ላይ በተመሠረተው ጭብጥ ላይ ያተኮረ ነበር። አብዛኛው ትምህርት አንድ ሰው ለአገልግሎት፣ ለቤተሰብ፣ ራስን ለአምላክ ለመወሰንና ለሌሎች የዕለታዊ ኑሮ ዘርፎች ተገቢ አመለካከት ሊይዝ የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ነበር።
የዕለቱ ጥቅስ ከተብራራ በኋላ “የሰላም ምሥራች የሚያመጡ መልእክተኞች” የሚል ርዕስ ያለው ሲምፖዚየም ቀረበ። መልእክታችን የሰላም መልእክት ስለሆነ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መቅረብ አለበት። (ኤፌሶን 6:15) ዓላማችን በክርክር መርታት ሳይሆን የሰዎችን ልብ ማሳመን ነው። ከይሖዋ ድርጅት የምናገኘው ሥልጠና እና የተቀበልናቸው ጽሑፎች የሰዎችን ልብ ለማሳመን ያስችሉናል። የሰዎች ፍላጎት ማጣት ወይም ግዴለሽነት ተስፋ ሊያስቆርጠን አይገባም። ከዚህ ይልቅ ጥሩ የግል ጥናት፣ በስብሰባ ላይ የመገኘትና በስብከቱ ሥራ የመሳተፍ ልማድ በማዳበር ‘የአቅማችንን ያህል መሥራታችንን’ መቀጠል ይኖርብናል። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) ለሌሎች በተለይም በእምነት ለሚዛመዱን መልካም ማድረግን ችላ ማለት የለብንም። (ገላትያ 6:10) እርግጥ የአቅምን ያህል መሥራት ማለት ከመጠን በላይ በመሥራት ራስን ማድከም ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ሰው የሚችለውንና ሁኔታዎቹ የሚፈቅዱለትን ያህል መሥራቱ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያስገኝለታል።
የአምላክ ሕዝቦች የመንግሥቱን ሥራዎች ለማራመድ ጊዜያቸውን፣ ኃይላቸውንና ሀብታቸውን ይሰጣሉ። “በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ደስተኛ ሰጪ መሆን” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር ብዙ በግ መሰል ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ በሰጡ መጠን ተጨማሪ መገልገያ መሣሪያዎች፣ የመሰብሰቢያ ቦታዎችና የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቁሟል። የምናደርጋቸው መዋጮዎች ድርጅቱ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የስብከት ሥራ ለማከናወን የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ቁሳቁስ እንዲያገኝ ያስችሉታል። በልግስና መስጠት ለይሖዋ ክብር ከማምጣቱም በተጨማሪ ለሰጪው ደስታ ያስገኛል። ስለዚህ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይህን በጣም አስፈላጊ የሆነ የአምልኮታችንን ገጽታ ችላ ማለት የለብንም።— 2 ቆሮንቶስ 8:1-7
የጠዋቱ ፕሮግራም የተጠናቀቀው በየትኛውም የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ የጎላ ስፍራ በሚይዘው የጥምቀት ንግግር ነበር። ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ አዲሶች የኢየሱስን ፈለግ ተከትለው ራሳቸውን ለውኃ ጥምቀት ሲያቀርቡ ማየት ምንኛ ያስደስታል! (ማቴዎስ 3:13-17) ይህን እርምጃ የወሰዱት በሙሉ ከሁሉ የበለጠው ጥበብ ምንጭ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ተምረዋል። በሕይወታቸው ውስጥ እውነተኛ ዓላማ ከመያዛቸውም በላይ ትክክል የሆነውን ነገር እያደረጉ እንዳሉ ማወቃቸው ሰላም አስገኝቶላቸዋል!— መክብብ 12:13
“አስተዋይነት ይጠብቃችሁ” በተባለው ንግግር ላይ ቀጥተኛ የሆነ ምክር ተሰጥቷል። በንግድ ጉዳዮች ረገድ ማስተዋል በጣም አስፈላጊ ነው። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ የግል ንግድ ጉዳዮችን ማካሄድም ሆነ ሌሎች ክርስቲያኖችን የገንዘብ ትርፍ ማግኛ ማድረግ የለብንም። (ከዮሐንስ 2:15, 16 ጋር አወዳድር።) በተጨማሪም ገንዘባችንን በንግድ ሥራ ላይ ስናውል ወይም ለሌሎች ስናበድር ወይም ከሌሎች ስንበደር አስተዋይ መሆን ያስፈልገናል። ተናጋሪው “በጥንቃቄ ጉድለት ሳቢያ አደገኛ በሆኑ የንግድ ሥራዎች ላይ ገንዘባቸውን ያዋሉ ክርስቲያኖች ያወጧቸው የንግድ እቅዶች ሳይሳኩ በመቅረታቸው ምክንያት ከፍተኛ ብስጭት ከማትረፋቸውም በላይ አንዳንዶቹ መንፈሳዊነታቸውን ጭምር አጥተዋል” ብሏል። ምንም እንኳ ክርስቲያኖች አብረው መነገዳቸው ስሕተት ባይሆንም ጥንቃቄ ማድረጋቸው ጥበብ ነው። በተጨማሪም ሁለት ወገኖች የንግድ ስምምነት ሲያደርጉ ውሉ ምን ጊዜም ቢሆን በጽሑፍ ላይ መስፈር ይኖርበታል።
“ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” በሚለው ንግግር ላይ አምላክ ለወንዶችና ለሴቶች ያወጣው የአቋም ደረጃ ተብራርቷል። በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሰዎች ስለ ጾታ ልዩነት የተዛባ አመለካከት ነበራቸው። “ወንድነትን አስገድዶ ከመግዛት፣ ከኃይለኛነት ወይም ከትምክህተኝነት ጋር የሚያመሳስሉ ብዙዎች ናቸው” አለ ተናጋሪው። “በአንዳንድ ባሕሎች አንድ ወንድ በሰው ፊት ወይም ለብቻው ሆኖ እንኳን ቢያለቅስ አሳፋሪና ያልተለመደ ነገር እንደሆነ ይቆጠራል። ዮሐንስ 11:35 ግን ኢየሱስ በሕዝብ መካከል በአልዓዛር መቃብር አጠገብ ቆሞ በነበረበት ጊዜ ‘እንዳለቀሰ’ ይናገራል።” ስለ ሴትስ ምን ለማለት ይቻላል? ብዙውን ጊዜ ሴትነት በአካላዊ ማራኪነት ይለካል። ይሁን እንጂ ተናጋሪው እንዲህ ሲል ጠይቋል:- “አንዲት ሴት ቆንጆ ብትሆንና ነገር ግን አስተዋይነት የጎደላት፣ አሽሟጣጭ፣ ተጨቃጫቂ ወይም እብሪተኛ ብትሆን በእርግጥ ቆንጆና የሴትነት ባሕርይ ያላት ናት ልትባል ትችላለችን?” (ከምሳሌ 11:22፤ 31:26 ጋር አወዳድር።) ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች በንግግራቸው፣ በጠባያቸውና በፀጉር አበጣጠራቸው የመጽሐፍ ቅዱስን የአቋም ደረጃዎች ለማንጸባረቅ ጥረት ያደርጋሉ። ተናጋሪው “የመንፈስ ፍሬዎችን የሚያፈራ ወንድ ማክበር ወይም የመንፈስ ፍሬዎችን የምታፈራ ሴት መውደድ ቀላል ነው” ብሏል።— ገላትያ 5:22, 23
ከዚህ በኋላ “የሰላም አምላክ ይንከባከባችኋል” የሚል ርዕስ ያለው ሲምፖዚየም ቀረበ። ብዙ ክርስቲያኖች የገንዘብ ችግር አለባቸው። ሆኖም ይሖዋ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” የሚል ተስፋ ሰጥቷል። (ዕብራውያን 13:5) አንዳንዶች የኢኮኖሚ ችግሮች ቢኖሩባቸውም ረዳት አቅኚዎች ወይም ዘወትር አቅኚዎች በመሆን በዚህ ተስፋ እንደሚተማመኑ አሳይተዋል። ሌሎች ደግሞ አሁን አቅኚ መሆን ባይችሉም እያንዳንዱን አጋጣሚ ለመመሥከር በመጠቀም የአምላክን መንግሥት ጥቅሞች አስቀድመዋል። (ማቴዎስ 6:33) እንደነዚህ ዓይነቶቹ ጥረቶች ሁሉ የሚያስመሰግኑ ናቸው! የይሖዋ ድርጅት እኛን በአገልግሎት ለመርዳትና ችግሮቻችንን ለመቋቋም እንድንችል ለማገዝ ብዙ ጽሑፎችን አዘጋጅቷል። ለይሖዋ መንፈሳዊ ዝግጅቶች አድናቆት ካሳየን በዚህ በኢኮኖሚ በተቃወሰ ዘመን ሰላም በመስጠት ይባርከናል።— መዝሙር 29:11
“በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ አምላካዊ ሰላም ተከታተሉ” የሚል ርዕስ የነበረው የቀኑ የመጨረሻ ንግግር ከቀረበ በኋላ ተሰብሳቢዎቹ የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ምሥጢር የተባለ አዲስ መጽሐፍ (በእንግሊዝኛ) በማግኘታቸው ተደስተዋል። ተናጋሪው እንዲህ ሲል መከረ:- “በግላችሁም ሆነ ከቤተሰባችሁ ጋር በቡድን ሆናችሁ ይህን መጽሐፍ በትጋት አጥኑ። በውስጡ የሚገኙትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ምክሮች ሥራ ላይ ለማዋል ከልባችሁ ጣሩ። ይህን ብታደርጉ የቤተሰባችሁን ሰላምና ደስታ ከፍ ለማድረግ እንደምትችሉ የተረጋገጠ ነው።”
“በሰላም ማሰርያ . . . አንድነት ለመጠበቅ ትጉ”
በኤፌሶን 4:3 ላይ የተመሠረተው ይህ ጭብጥ ለመጨረሻው የስብሰባ ቀን ተስማሚ ነበር። ከብዙ የዓለም ብሔራት የተውጣጡት የይሖዋ ምሥክሮች ከአምላክ የተማሩ ናቸው። ስለዚህ ሰላምን ይወዳሉ። የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተሉ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ‘በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ’ ጥረት ያደርጋሉ።
በአምላክ ድርጅት ውስጥ የሰፈነው ሰላም “ትክክለኞቹን መልእክተኞች ለይቶ ማወቅ” በሚል ርዕስ በቀረበው ሲምፖዚየም ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ሐሰተኛ ነቢያት ነበሩ። ሆኖም እንደ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤልና ኤርምያስ የመሳሰሉት የአምላክ እውነተኛ ነቢያት የኢየሩሳሌምን ውድቀት፣ በግዞት የሚያሳልፉበትን ዘመንና የአምላክ ሕዝቦች ከጊዜ በኋላ የሚያገኙትን ነፃነት በትክክል ተንብየዋል። ዛሬም ቢሆን ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። በፖለቲካው ዓለምና በሐሰተኛ ሃይማኖት ውስጥ ሐሰተኛ መልእክተኞች በብዛት ይገኛሉ። ሆኖም ይሖዋ ይህን የነገሮች ሥርዓት በተመለከተ ያለውን ዓላማ እንዲያውጁ ምሥክሮቹን አስነሥቷል። በተለይ ከ1919 ጀምሮ የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክን መልእክት ሲያውጁ ቆይተዋል። ከሕዝበ ክርስትና ሐሰተኛ መልእክተኞች ምንኛ የተለዩ ናቸው! ይሖዋ ሥራው ተጠናቋል እስኪል ድረስ ለዚህ ሥራ የበኩላችንን አስተዋጽኦ በትጋት እናድርግ።
“የአምላክን ቃል አዳምጡ፤ ታዘዙም” በሚለው ንግግር ላይ ቅዱሳን ጽሑፎች ከሁሉ የበለጡ የመመሪያ፣ የመጽናናትና የተስፋ ምንጭ እንደሆኑ ተገልጿል። (ኢሳይያስ 30:20, 21፤ ሮሜ 15:4) በዛሬው ጊዜ የሚገኘው ዓለም በሥነ ምግባር እየላሸቀ ነው። ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ ከአምላክ ቃልና ከአምላክ ድርጅት የሚሰጠንን ምክር ማዳመጥ ያስፈልገናል። ይሖዋ ድክመታችንን የሚያውቅ ከመሆኑም በተጨማሪ በቃሉ አማካኝነት እኛን የሚጠቅመንን አካሄድ ግልጽ በሆነ መንገድ አሳውቆናል። ይሖዋ እንደሚረዳን ማወቃችን በልበ ሙሉነት የሚጠይቀንን ነገር ሁሉ በማድረግ ወደፊት ለመግፋት ያስችለናል።
ይህ ንግግር የአድማጮችን አእምሮ ለቀጣዩ ድራማ አዘጋጅቷል። ድራማው “ቲኦክራሲያዊ ዝግጅቶችን ማክበር ያለብን ለምንድን ነው?” የሚል ርዕስ ነበረው። ይህ ድራማ ስለ ጌዴዎን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ መሠረት በማድረግ አንድ ኃይለኛ ትምህርት አስጨብጧል። የአምላክን መመሪያዎች እንጂ የራሳችንን አስተሳሰብ መከተል ወይም አንድን ቲኦክራሲያዊ ምክር ችላ ማለት እንደሌለብን አስተምሮናል።
የሕዝብ ንግግሩ “በመጨረሻ እውነተኛ ሰላም ይገኛል!— ግን ከየት?” የሚል ርዕስ ነበረው። አምላክ እሰጣችኋለሁ ብሎ ቃል የገባልን ሰላም ዓለም ሊገምት ከሚችለው ከማንኛውም ነገር የላቀ ነው። ተናጋሪው “እውነተኛ ሰላም ማለት እያንዳንዱን ቀን በሰላም ማሳለፍ ማለት ነው” ብሏል። “የአምላክን ሰላም ማግኘት ማለት በሽታ፣ ሕመም፣ ሐዘንና ሞት በሌለበት ዓለም ውስጥ መኖር ማለት ነው።” መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ይሽራል” ሲል ይነግረናል። (መዝሙር 46:9) ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ጦርነት ቆስቋሽ የሆነውን ሰይጣን ዲያብሎስን በማጥፋት ነው። (ራእይ 20:1-3) ይህም ቅኖች ‘ምድርን እንዲወርሱና በብዙ ሰላም ደስ እንዲላቸው’ ጥርጊያ መንገድ ይከፍታል።— መዝሙር 37:11
የሳምንቱ የመጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕስ በአጭሩ ከቀረበ በኋላ የአውራጃ ስብሰባው የመጨረሻ ንግግር ቀረበ። “የሰላም መልእክተኞች በመሆን ወደፊት እንግፋ” በሚል ርዕስ የቀረበው ይህ ቀስቃሽ ንግግር የስብከት ሥራችን በዓይነቱ ብቸኛ የሆነና አስቸኳይ መሆኑን የሚያጎላ ነበር። አሁን የምንዝናናበት፣ የምንለግምበት ወይም ቀደም ሲል ወደ ነበሩን የተሳሳቱ አመለካከቶች የምንመለስበት ጊዜ አይደለም። የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ በማግኘት ታጥቀናል፤ የአምላክ መልእክት፣ ቅዱስ መንፈሱ፣ አፍቃሪ የሆነው ቲኦክራሲያዊ ድርጅቱ ያደረገልን ዝግጅቶች አሉን። እንግዲያውስ የይሖዋ ምሥክሮች እንደ መሆናችን መጠን የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች በመሆን ወደፊት መግፋታችንን እንቀጠል!
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]
ለቤተሰቦች የተዘጋጀ ፍቅራዊ ስጦታ
“የአምላካዊ ሰላም መልእክተኞች” በተባለው የአውራጃ ስብሰባ ሁለተኛ ቀን ፕሮግራም ላይ የተገኙ ሁሉ የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ምሥጢር የተባለ አዲስ መጽሐፍ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። ይህ መጽሐፍ አምላክን ለሚወዱ ቤተሰቦች ሁሉ የሚጠቅም ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳብ ይዟል።
በኮነቲከት ዩ ኤስ ኤ ውስጥ የሚገኝ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝሯል:- “ሰኔ 15 የቤተሰብ ደስታ የተባለውን መጽሐፋችንን አገኘን። ሰኔ 16 መጽሐፉን አጋመስኩት። ሰኔ 17 በመጽሐፉ የመጀመሪያ የቤተሰብ ጥናታችንን ያደረግን ሲሆን ይህም በጣም አበረታቶናል! በዚያኑ ቀን መጽሐፉን አንብቤ ጨረስኩ። ይህ ግሩም የሆነ መጽሐፍ ለሚገለገሉበት ሁሉ በጣም ጠቃሚ መሣሪያ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። የመጽሐፉ ግልጽነትና የያዘው ወቅታዊ የሆነ ሐሳብ ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ ‘በተገቢው ጊዜ ምግብ’ እያቀረበ እንዳለና በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሚገባ እንደሚያውቅ ተጨማሪ ማረጋገጫ የሚሆን ነው።”— ማቴዎስ 24:45-47
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች አምላክ ምን እንደሚፈልግ ለማወቅ ይሻሉ