በእስር ቤት ያሉ ሰዎች መንፈሳዊ ነፃነት እንዲያገኙ መርዳት
“በጉጉት ስንጠብቃችሁ ነበር።” “ሰሞኑን ስለ እናንተ መምጣት ሳልም ነበር።” “ዘወትር እየመጣ የሚረዳን ሰው ስለመደባችሁልን በጣም እናመሰግናችኋለን።” “ይሖዋ ለእኛ ለማይገባን ሰዎች ለሰጠን በረከት ሁሉና ለድርጅቱ እንዲሁም ለሚቀርብልን ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ምስጋናችንን መግለጽ እንፈልጋለን።”
ለእነዚህ የምስጋና መግለጫዎች ምክንያት የሆነው ነገር ምንድን ነው? እነዚህ በሜክሲኮ በተለያዩ ወኅኒ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ እስረኞች የተናገሯቸው አንዳንድ የምስጋና ቃላት ናቸው። እነዚህ እስረኞች የይሖዋ ምሥክሮች እነሱን ለመርዳት የሚያደርጉትን ጥረት በጣም ያደንቃሉ፤ ምንም እንኳ እስር ቤት ውስጥ ያሉ ቢሆንም መንፈሳዊ ነፃነት ለማግኘት ችለዋል። በሜክሲኮ ውስጥ 42 ወኅኒ ቤቶች ያሉ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ወኅኒ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ እስረኞችን መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ዘወትር ይጥራሉ። እነዚህ ወኅኒ ቤቶች ሴንትሮ ሪአዳፕታሲዮን ሶሲያል (የጠባይ ማረሚያ ማዕከል) ተብለው ይጠራሉ። ሌላው ቀርቶ ከእነዚህ እስር ቤቶች መካከል በአንዳንዶቹ ውስጥ ዘወትር ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይደረጋሉ፤ በዚህም በጣም ጥሩ ውጤት እየተገኘ ነው። ለምሳሌ በቅርቡ በእነዚህ ቦታዎች በድምሩ 380 የሚያክሉ ተሰብሳቢዎች እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል። በዚሁ ወቅት በአማካይ 350 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመመራት ላይ ነበሩ። ሠላሳ ሰባቱ ለአገልግሎት ብቁ ሲሆኑ 32 ደግሞ ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወስነው በውኃ ተጠምቀዋል።
ሥራው የሚከናወነው እንዴት ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ ቦታዎች የስብከት ሥራቸውን የሚያከናውኑት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ዓላማቸው እስረኞቹ የአኗኗር ለውጥ የሚያደርጉበትንና አምላክን እሱ በሚፈልገው ሁኔታ ማገልገል የሚችሉበትን መንገድ ማስተማር መሆኑን በመግለጽ ወደ እስር ቤቱ ለመግባት የሚያስችላቸውን የጽሑፍ ፈቃድ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣኖች ይጠይቃሉ።
ባለሥልጣኖቹ ፈቃድ ከልክለዋቸው አያውቁም። እነዚህ ባለሥልጣኖች ለእስረኞቹ በመሰጠት ላይ ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ይደግፋሉ። የእስር ቤቶቹ ባለሥልጣኖች የይሖዋ ምሥክሮች የወኅኒ ቤቶቹን የጥበቃ ደንቦች በሚገባ እንደሚያከብሩ ለመገንዘብ ችለዋል። እየተመላለሱ እስረኞቹን በመንፈሳዊ የሚረዱት የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎቻቸውን ለማድረግ ቢሮዎችን፣ የመመገቢያ አዳራሾችንና የተለያዩ ክፍሎችን እንዲጠቀሙ ባለሥልጣኖቹ ፈቅደውላቸዋል። እንዲያውም በደቡባዊ ምሥራቅ ሜክሲኮ የሚገኝ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የተናገረው ቀጥሎ ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው በአንደኛው እስር ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች አነስተኛ የመንግሥት አዳራሽ እንዲሠሩ ተፈቅዶላቸዋል።
“በ1991 መጀመሪያ ላይ በትዋንትፔክ ኦዋዛካ የሚገኘውን እስር ቤት በጎበኘንበት ወቅት በመንፈሳዊ የተራቡ በርካታ ሰዎች አገኘን። ወዲያው 27 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አስጀመርን። እስረኞቹ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበራቸው አምስቱም የጉባኤ ስብሰባዎች እንዲደረጉ ፕሮግራም ወጣ። ለይሖዋ ከፍተኛ ፍቅር የነበረው አንድ እስረኛ ስብሰባዎች የሚደረጉበት አንድ አነስተኛ የመንግሥት አዳራሽ በወኅኒ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ለመሥራት ወሰነ። ወደ ወኅኒ ቤቱ አዛዥ ሄዶ ፈቃድ ጠየቀ፤ የወኅኒ ቤቱ አዛዦች በጣም ተባበሩት። ታኅሣሥ 1992 መጀመሪያ ላይ ስድስት እስረኞች የምሥራቹ አስፋፊዎች ለመሆን ብቁ ሆኑ። በጣም ጥሩ እድገት በመታየቱ እዚያው ወኅኒ ቤቱ ውስጥ የመታሰቢያው በዓል ለማክበር ዝግጅት ተደረገ። ምሳሌያዊዎቹን ቂጣና ወይን ጠጅ ለማስገባት የወኅኒ ቤቱን አዛዥ ፈቃድ ጠየቅን፤ አራት ሰዓት የፈጀ ውይይት ካደረግን በኋላ ተፈቀደልን።
“ሚያዝያ 3, 1993 (የመታሰቢያው በዓል ከመከበሩ ከሦስት ቀን በፊት ማለት ነው) የተወሰኑ እስረኞች ተፈቱ። አስፋፊ ከሆኑት እስረኞች መካከል አንዱ የመልቀቂያ ወረቀት ሲሰጠው የመታሰቢያው በዓል እስኪከበር ድረስ በዚያው በወኅኒ ቤቱ ውስጥ እንዲቆይ ፈቃድ ለማግኘት የወኅኒ ቤቱን አዛዥ ለማነጋገር ፈቃድ ጠየቀ። እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ ያልተለመደ ነገር ስለሆነ የወኅኒ ቤቱን አዛዥ በጣም አስገረመው፤ ሆኖም እስረኛው በዚያው በእስር ቤቱ ውስጥ የመታሰቢያውን በዓል ለማክበር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ስለተገነዘበ ፈቀደለት። በመታሰቢያው በዓል ላይ 53 ሰዎች የተገኙ ሲሆን ፕሮግራሙ ሲጠናቀቅ ሁሉም የደስታ እንባ አንብተዋል። መንፈሳዊ ነፃነት ስላገኙ በዚያ የሚገኘውን ቡድን ‘ፍሪደም ሴሪሶ’ ብለን ሰየምነው።”
የይሖዋ ምሥክሮች በእነዚህ እስር ቤቶች ውስጥ የሚያከናውኑት ሥራ ከፍተኛ አድናቆት ተችሮታል። ከእነዚህ ወኅኒ ቤቶች በአንዱ የሚገኝ አንድ አዛዥ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ እስረኞች ፈጣን የጠባይ መሻሻል እንዲያሳዩ የሚረዳ አንድ ራሱን የቻለ “ሕክምና” መሆኑን በግልጽ መስክሯል።
ውጤታማ የጠባይ ማረሚያ ፕሮግራም
የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ብዙ እስረኞች ሙሉ በሙሉ የባሕርይ ለውጥ እንዲያደርጉ ረድቷል። እስር ቤት የነበሩ ሰዎች ከእስር ቤት ሲፈቱ ተመልሰው በቀድሞ የዓመፅ ድርጊታቸው መሠማራታቸው የተለመደ ነገር ቢሆንም የአምላክ ቃል የያዘውን መልእክት ከልብ የተቀበሉ ሰዎች ግን ሙሉ በሙሉ ለውጥ አድርገዋል። እነዚህ ሰዎች ያደረጉት ለውጥ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል የተናገረውን ያስታውሰናል:- “ሴሰኞች ቢሆኑ . . . ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም። ከእናንተም አንዳንዶቹ እንደነዚህ ነበራችሁ፤ ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥባችኋል፣ ተቀድሳችኋል፣ ጸድቃችኋል።”— 1 ቆሮንቶስ 6:9-11
እስረኞቹ ስሜታቸውን ሲገልጹ መስማት ያደረጉትን ከፍተኛ የባሕርይ ለውጥ ለመገንዘብ ያስችላል። በካምፒቺ ከተማ በካምፒቺ እስር ቤት የሚገኘው ሚገል እንደሚከተለው በማለት ገልጿል:- “ራሴን በ2 ጴጥሮስ 3:13 እና በማቴዎስ 5:5 ላይ የተመዘገበውን ተስፋ በመጠባበቅ ላይ ከሚገኙት ከሌሎች በጎች እንደ አንዱ አድርጌ ለመቁጠር በመቻሌ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል።” በካምፒቺ እስር ቤት በኮቤን የሚገኘው ሆሴ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ገልጿል:- “ምንም እንኳ እስረኛ ብሆንና የፈጸምኩትም ወንጀል ከባድ ሊሆን ቢችልም ይሖዋ መሐሪ እንደሆነና ጸሎቴንና ምልጃዬን እንደሚሰማ አውቃለሁ። የፈጸምኩትን ስህተት ይቅር ሊለኝና ቀሪ ሕይወቴን የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሌሎች በማካፈል እንዳሳልፍ አጋጣሚ ሊሰጠኝ ይችላል። የአምላክ መንግሥት ከያዛቸው ተስፋዎች ተጠቃሚ እንድንሆን ጊዜ መድበው እዚህ ወኅኒ ቤት ድረስ እየመጡ የሚረዱንን ሽማግሌዎቻችንን እናመሰግናቸዋለን። ምንኛ ተባርከናል! አሁን እኔ እስረኛ ነኝ ብዬ መናገር እችላለሁ? በፍጹም፤ ይሖዋ ያስፈልገኝ የነበረውን መንፈሳዊ ነፃነት ሰጥቶኛል።”
ነፍሰ ገዳዮች፣ ሌቦች፣ አስገድደው በፆታ የሚደፍሩ፣ ቤት ንብረት የሚያቃጥሉና ሌሎች ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ሰዎች ትክክለኛ ሕይወት የሚመሩ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው? የአምላክ ቃል ያለው የመለወጥ ኃይልና ከልባቸው ለአምላክ ካደሩ ሰዎች ጋር መሰብሰባቸው መሆኑን እነዚሁ ሰዎች ራሳቸው ተናግረዋል። በሲናሎአ በማዝትላን ወኅኒ ቤት የታሰረው የቲቡርሲዮ ሁኔታ የዚህን የጠባይ ማረሚያ ፕሮግራም ስኬታማነት ያሳያል። በሲናሎአ በኮንኮርድያ ወኅኒ ቤት ታስሮ ሳለ የግልፍተኝነት ችግር ነበረበት። ሚስቱ የይሖዋ ምሥክር ነች፤ በጣም ያንገላታት ነበር፤ እስር ቤት ልትጠይቀው በምትመጣበት ጊዜ እንኳ ሳይቀር ይሰድባት ነበር። እሷ ግን ይህን ሁሉ ችላ እየተመላለሰች መጠየቋን ቀጠለች፤ ከዚያም በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ እንድታመጣለት ጠየቃትና በግሉ ማንበብ ጀመረ።a ከዚያም አንድ ሰው ወኅኒ ቤት እየመጣ እንዲያስጠናው ጠየቀ። መንፈሳዊ እድገት ማድረግ ጀመረ፤ እንዲሁም ከሌሎች ጋር ያለው ግንኙነት እየተሻሻለ መጣ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ወደሚገኝበት ወደ ማዛትላን እስር ቤት ተዛወረ፤ አሁን አስፋፊ ሆኗል። እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “በዚህ ቦታ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመስማት በመቻሌ ከባለቤቴ፣ ከልጆቼና ከእስር ቤት ጓደኞቼ ጋር በመሆን ከፍ ያለ ምስጋናዬን እገልጻለሁ፤ በቅርቡ እንደምፈታና ሁሉንም ትላልቅ ስብሰባዎችና የጉባኤ ስብሰባዎች እንደምካፈል ተስፋ አደርጋለሁ።”
በተጨማሪም በሕይወቱ ውስጥ ለውጦችን ለማድረግ በመቻሉ አመስጋኝ የሆነ ኮንራድ የሚባል እስረኛ አለ። በትዳሩ ውስጥ ከፍተኛ ችግር የነበረበት ሲሆን ሚስቱ ጥላው ሄዳለች። ስለዚህ ዕፅ በመውሰድ ከችግሩ ለመሸሽ ፈለገ። ከጊዜ በኋላ የዕፅ አዘዋዋሪ ሆነ። ከዚያም ማሪዋናና ኮኬይን ጭኖ ሲሄድ ተያዘና ወኅኒ ቤት እንዲገባ ተፈረደበት። በእስር ቤቱ ውስጥ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጠና አንድ ቡድን ነበር፤ እሱም አብሯቸው እንዲያጠና ግብዣ ቀረበለት። እንዲህ በማለት ስሜቱን ይገልጻል:- “ስብሰባዎቹ ይካሄዱበት የነበረው ሥርዓት፣ በጽሑፎች አማካኝነት የሚደረገው ምርምርና ሁሉም ነገር ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑ በጣም ማረከኝ። ወዲያው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጠየቅሁና በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርኩ።” ይህ የሆነው በጥር 1993 ነበር። ኮንራድ አሁን ከእስር ቤት ተፈቶ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እድገት ማድረጉን ቀጥሏል።
ኢስላስ ማሪስ
በሜክሲኮ አራት ደሴቶችን ያቀፈ ኢስላስ ማሪስ በመባል የሚጠራ አንድ በጣም አስፈሪ እስር ቤት አለ። እስረኞቹ በታሰሩባቸው ደሴቶች ውስጥ ወዲያ ወዲህ መዘዋወር ይችላሉ። አንዳንዶች ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እዚያው አብረው ይኖራሉ።
አንድ አነስተኛ ጉባኤ ተቋቁማል። ሦስት ወንድሞች ከማዛትላን በወር አንድ ጊዜ እየሄዱ ስብሰባዎችን በመምራት፣ ጽሑፎችን ይዘውላቸው በመሄድና ማበረታቻ በመስጠት ይረዷቸዋል። አንዳንድ ጊዜም የወረዳ የበላይ ተመልካች እየሄደ ይጎበኛቸዋል። አማካይ ተሰብሳቢዎች ከ20 እስከ 25 ይደርሳሉ። አራት የተጠመቁና ሁለት ያልተጠመቁ አስፋፊዎች አሉ። ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ እንደሚከተለው ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “አንዳንዶች እሁድ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት 17 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ፤ እንዲሁም እስር ቤት የስም ጥሪ በሚደረግበት ጊዜ በዚያ ለመገኘት ከስብሰባ ተጣድፈው ይሄዳሉ፤ በፍጥነት እየተጓዙ እንኳ ተመልሰው እዚያ ለመድረስ ከሁለት ሰዓት በላይ ይፈጅባቸዋል።” እዚህ እስር ቤት ውስጥ እውነትን ካወቁት ወንድሞች አንዱ በቅርቡ እንዲህ ብሏል:- “ከእስር ቤት ቶሎ በተለቀቅሁ ብዬ እጓጓ ነበር፤ አሁን ግን እዚህ እስር ቤት የምሠራው ብዙ ሥራ ስላለኝ ይሖዋ በፈቀደው ጊዜ ልወጣ እችላለሁ።”
ይሖዋን ለማስደሰት በሚጥሩ ቅን ሰዎች ላይ የእውነት ኃይል ሲሠራ በመመልከታችን ተደስተናል። እስር ቤት ውስጥ እውነትን ካጠኑት መካከል ከደርዘን በላይ የሚሆኑት ከእስር ቤት የተለቀቁ ሲሆን ተጠምቀው በአሁኑ ጊዜ የተስተካከለ ሕይወት እየመሩ ነው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ የጉባኤ ሽማግሌዎች ሆነዋል። ልብ የማስተካከልና ሰዎችን በመለወጥ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው ኃይል በሚያስደንቅ ሁኔታ ታይቷል። ባንድ ወቅት መጥፎ ነገር በመፈጸማቸው ታስረው የነበሩ ሰዎች አሁን በአምላክ ቃል ብርሃን መጓዝ ጀምረዋል፤ ኢየሱስ “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” በማለት በሰጠው ተስፋ መሠረት እውነተኛውን ነፃነት በማጣጣም ላይ ይገኛሉ።— ዮሐንስ 8:32፤ መዝሙር 119:105
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙዎች እስር ቤት እያሉ የተማሯቸው ክርስቲያናዊ እውነቶች በጣም ጠቅመዋቸዋል