ዘመኑ በጣም አስከፊ የሆነው ለምንድን ነው?
ጋዜጣ ለማንበብ ወይም በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና ለመመልከት አለዚያም በሬዲዮ የሚተላለፈውን ዜና ለመስማት ቁጭ ስትል አንድ አሳዛኝ ዜና ይኖራል ብለህ መጠበቅህ አይቀርም፤ አይደለም እንዴ? ካሁን ቀደም የተጀመረው ጦርነት ተፋፍሞ እንደቀጠለ፣ ዘግናኝ ወንጀሎች እንደ አሸን ፈልተው እንደሚገኙ ወይም ረሃብ ታዳጊ አገሮችን እያሽመደመደ እንዳለ ስትሰማ ብዙም አይገርምህ ይሆናል።
እነዚህ ነገሮች ከሚፈጸሙበት ቦታ ርቀህ የምትኖር ከሆነ እንዲህ ያሉት ሪፖርቶች እጅግም አያስጨንቁህ ይሆናል። ለነገሩማ እንዲህ ያለው ሥቃይና መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች ሁሉ አዝነን አንችልም። ቢሆንም በግለሰቦች ላይ የሚደርሰውን መከራ በዓይናችን እያየን ምንም አዘኔታ አይሰማኝም ማለት ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። በሌላ አባባል ስለ ጦርነት እያነበቡ ስለ ሞቱት ሰዎች ቁጥር ማሰብና አድናን ስለተባለ ሕፃን ታሪክ ማንበብ ፈጽሞ የተለያየ ነገር ነው፤ አድናን ቤታቸው በቦምብ ሲጋይ እናቱን በሞት ያጣ በቦስኒያ የሚገኝ የዘጠኝ ዓመት ልጅ ነው። ከጥቂት ወራት በኋላ አድናንና አባቱ አብረው ሲሄዱ ከደፈጣ ተዋጊዎች በተተኮሰ ጥይት አባቱ ተገደለ። ጥቂት ሳምንታት እንዳለፉ ደግሞ እህቱ በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ በወደቀ የመድፍ ጥይት በመጎዳቷ ብዙ ደም ፈስሷት ዓይኑ እያየ ሞተች። አድናን ከደረሰበት የስሜት መቃወስ እንዲያገግም የሚረዱት ዶክተሮች ጨርሶ ስሜቱ ሁሉ እንደጠፋና ስለ ምንም ነገር የማወቅ ጉጉት እንኳ እንደሌለው ተናግረዋል። ፍርሃትና ድንገት ፊቱ ድቅን የሚልበት የሚሰቀጥጥ ትውስታ የእንቅልፍ ሰዓቱን አዛብተውበታል፤ ቅዠት የሰላም እንቅልፍ ነስቶታል። የአድናንን ታሪክ ከአኃዛዊ ማስረጃ ጋር ፈጽሞ ማነጻጻር አይቻልም። አድናን አሳሩን የሚያይ ልጅ ነው፤ በደረሰበት ሁኔታ ከልብ ማዘናችን አይቀርም።
በዓለም ውስጥ በሚታዩ ሌሎች ሰቆቃዎችም ረገድ ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። ስለ ረሃብ ማንበብና የረሃብ ሰለባ በመሆኗ ሳቢያ ሆዷ የተነፋና እግሮቿ እንደ ክብሪት እንጨት የሰለሉ በሞት አፋፍ ላይ የምትገኝ የአምስት ዓመት ልጅ ፎቶግራፍ ማየት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለ ወንጅል አኃዛዊ ማስረጃዎችን ማንበብና አንዲት በዕድሜ የገፋች መበለት በጭካኔ ተደብድባ ንብረቷን ሁሉ ከተዘረፈች በኋላ ተገዳ በጾታ እንደተደፈረች መስማት ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። የቤተሰብ ተቋም እየተዳከመ እንዳለ ማንበብና አንዲት እናት ሆን ብላ የገዛ ልጆቿን በረሃብ እንደምታሠቃይና በጭካኔ እንደምታንገላታ ማወቅ ፈጽሞ የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
እንዲህ ስላሉት ነገሮች ማንበብ ይሰቀጥጣል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ምድር አቀፍ መቅሰፍቶች አንዱ እኛ ላይ ሲደርስ ምንኛ ይበልጥ ከባድ ይሆናል! አንድ ክፉ ነገር እኛ ላይ ሲደርስብን በዓለም የዜና ማሠራጫዎች የሚስተጋባው ነገር ይበልጥ ጉልህ ሆኖ ይታየናል። ወንጀል፣ ጦርነት፣ ረሃብና ሕመም የሚያስከትሉት ሰቆቃ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማያውቅ ከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን አምኖ መቀበል በጣም ያስፈራል። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ውስጥ ከሚታዩት ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር መታገል የሚያስከትለው ውጤት በእርግጥም በጣም አስከፊ ሊሆን ይችላል፤ ግራ መጋባት፣ ፍርሃትና የመንፈስ ጭንቀት የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል።
በብዙ ሃይማኖቶች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ዛሬ ሁኔታዎች በጣም አስከፊ የሆኑት ለምንድን ነው? የሰው ልጅ ወዴት እያመራ ይሆን? ለሚሉት የሚያስጨንቁ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ይጥራሉ።
የሚያሳዝነው ግን በዛሬ ጊዜ አርኪ መልስ የሚሰጡ ሃይማኖቶች እምብዛም ናቸው። መጀመሪያ እዚህ መጽሔት ሽፋን ላይ ያለውን ጥያቄ ስትመለከት መልስ ይገኝለት ይሆን የሚል ጥርጣሬ አድሮብህ ሊሆን ይችላል፤ ይህ የሚጠበቅ ነገር ነው። ብዙውን ጊዜ የአክራሪነት አቋም ያላቸው ሃይማኖቶች መጽሐፍ ቅዱስ ያላለውን እንዳለ አድርገው በማቅረብ ስለዚህ ዓለም መጥፊያ ትክክለኛ ቀንና ሰዓት ለማብራራት ይሞክራሉ። (ማቴዎስ 24:36ን ተመልከት።) የዚህ መጽሔት አዘጋጆች ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ መልስ ቢሰጥ የተሻለ እንደሆነ ያምናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መጨረሻው ቀን የሚናገረው ነገር እውነተኛና ምክንያታዊ መሆኑን ስታውቅ ትገረም ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ የሚያብራራው ሁኔታዎቹ ለምን በጣም አስከፊ እንደሆኑ ብቻ አይደለም። የወደፊቱን ጊዜ በሚመለከት በጣም የሚያጽናና ተስፋ ይሰጣል። ይህንን ሁኔታ ለመረዳት የሚቀጥሉትን ርዕሶች እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Jobard/Sipa Press