አይዟችሁ መዳናችሁ ቀርቧል
‘አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ ይላል ይሖዋ።’— ኤርምያስ 1:19
1, 2. ሰብዓዊው ቤተሰብ መዳን የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
መዳን! እንዴት የሚያጽናና ቃል ነው! ዲሊቨረንስ የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ከአደጋ መትረፍ፣ ከመጥፎ ወይም ከአሳዛኝ ሁኔታ መገላገል ማለት ነው። ይህም ወደ ተሻለና ይበልጥ አስደሳች ወደ ሆነ ሁኔታ መግባትን የሚጨምር ነው።
2 ሰብዓዊው ቤተሰብ በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነት መዳን በእጅጉ ያስፈልገዋል! በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ሰዎች በኢኮኖሚያዊ፣ በማኅበራዊ፣ በአካላዊ፣ በአእምሯዊና ስሜታዊ ችግሮች ከመደቆሳቸውም በላይ ተስፋ ቆርጠዋል። አብዛኞቹ ሰዎች አሁን ባለው የዓለም ሁኔታ በጣም ስለሚከፉና ስለሚያዝኑ አንድ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋሉ።— ኢሳይያስ 60:2፤ ማቴዎስ 9:36
“የሚያስጨንቅ ዘመን”
3, 4. በአሁኑ ጊዜ መዳን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
3 ይህ 20ኛው መቶ ዘመን ከየትኛውም ዘመን ይበልጥ ይህ ነው የማይባል ሰቆቃ እየተፈራረቀበት ስለሆነ መዳን በጣም የሚያስፈልግበት ዘመን ሆኗል። ዛሬ ከአንድ ቢልዮን በላይ ሰዎች በአስከፊ ድኽነት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ይህ አኃዝ በየዓመቱ ቢያንስ በ25 ሚልዮን ይጨምራል። የተመጣጠነ ምግብ በማጣት ወይም ከድኽነት ጋር በተያያዙ ሌሎች ችግሮች የተነሳ በየዓመቱ ወደ 13 ሚልዮን የሚጠጉ ማለትም በቀን ከ35, 000 በላይ ልጆች ይሞታሉ! በሚልዮን የሚቆጠሩ ትልልቅ ሰዎችም በተለያዩ በሽታዎች የተነሳ ያለ እድሜያቸው ይሞታሉ።— ሉቃስ 21:11፤ ራእይ 6:8
4 ጦርነቶችና የእርስ በርስ ብጥብጦች ይህ ነው ለማይባል ሰቆቃ መንስዔ ሆነዋል። መንግሥት ያስከተለው እልቂት (Death by Government) የተባለው መጽሐፍ በጦርነት፣ በጎሳዊና ሃይማኖታዊ ግጭት እንዲሁም መንግሥታት በገዛ ዜጎቻቸው ላይ በፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋ “በዚህ መቶ ዘመን ከ203 ሚልዮን በላይ ሰዎች እንደተገደሉ” ይገልጻል። አክሎም እንዲህ ይላል:- “የተገደሉት ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ወደ 360 ሚልዮን ሊጠጋ ይችላል። ይህም ጥቁር ሞት እየተባለ ከሚጠራው ቸነፈር ጋር የሚመሳሰል የሰውን ዘር እየፈጀ ያለ የዘመኑ መቅሰፍት ነው። በእርግጥም የሰውን ዘር እየጨረሰ ላለው ለዚህ ቸነፈር መንስዔ በሽታ የሚያመጡ ረቂቅ ሕዋሳት ሳይሆኑ ሥልጣን ነው።” ሪቻርድ ሃርውድ የተባሉት ደራሲ “ጥንት በባርባራውያን ዘመን የተደረጉት ጦርነቶች ከዚህ ጋር ሲወዳደሩ ምንም ከጦርነት አይቆጠሩም” ሲሉ ተናግረዋል።— ማቴዎስ 24:6, 7፤ ራእይ 6:4
5, 6. ያለንበትን ዘመን አስጨናቂ ያደረገው ምንድን ነው?
5 ዛሬ ካሉት አስጨናቂ ሁኔታዎች በተጨማሪ አሠቃቂ ወንጀሎች፣ የሥነ ምግባር ብልግና እና የቤተሰብ መፈራረስ በእጅጉ እያሻቀቡ ሄደዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ የትምህርት ሚኒስትር ዊልያም ቤነት በ30 ዓመታት ውስጥ የአሜሪካ ሕዝብ 41 በመቶ የጨመረ ሲሆን ወንጀል 560 በመቶ፣ ዲቃላ መውለድ 400 በመቶ፣ ፍቺ 300 በመቶ እንዲሁም በአሥራዎቹ እድሜ የሚገኙ ራሳቸውን የሚገድሉ ወጣቶች ቁጥር 200 በመቶ እንደጨመረ ገልጸዋል። የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ዲዩልዮ ጁንየር “ሰው የሚገድሉ፣ የሚያንገላቱ፣ አስገድደው የሚደፍሩ፣ የሚሰርቁ፣ ቤት ሰብረው ገብተው የሚዘርፉና ከባድ ማኅበራዊ ቀውሶችን የሚፈጥሩ” ቀንደኛ የሆኑ ወጣት ጥፋተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱ ስጋት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል። “እነዚህ ወጣቶች እያዛለሁ፣ እታሰራለሁ ወይም የሕሊና ወቀሳ ይደርስብኛል የሚል ፍርሃት የለባቸውም።” በዚህች አገር ከ15 እስከ 19 እድሜ ላሉ ወጣቶች ሞት ምክንያት በመሆን ረገድ በአሁኑ ጊዜ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የነፍስ ግድያ ነው። እንዲሁም ከአራት ዓመት በታች ያሉ ልጆች በአብዛኛው የሚሞቱት ከበሽታ ይልቅ በሚፈጸምባቸው ግፍ ነው።
6 እንዲህ ዓይነቱ ወንጀልና ዓመፅ በአንድ አገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም። አብዛኞቹ አገሮች ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ ሪፖርት ያደርጋሉ። አንዱ ለዚህ አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው የብዙዎችን ሕይወት የሚያበላሸው ሕገ ወጥ የአደንዛዥ ዕፅ አጠቃቀም መስፋፋት ነው። የአውስትራሊያው ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ጋዜጣ “ዓለም አቀፍ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር በዓለም ላይ ከጦር መሣሪያ ሽያጭ ቀጥሎ ከፍተኛ ትርፍ የሚዛቅበት ንግድ ሆኗል” ሲል ዘግቧል። ሌላው አስተዋጽኦ እያደረገ ያለው ነገር በዓመፅና በሥነ ምግባር ብልግና የተሞላው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ነው። በብዙ አገሮች አንድ ልጅ 18 ዓመት እስኪሞላው ድረስ ቁጥር ስፍር የሌላቸው የዓመፅ ድርጊቶችንና የጾታ ብልግና ሲፈጸም የሚያሳዩ ፊልሞችን በቴሌቪዥን ያያል። ባሕርያችን የሚቀረጸው ዘወትር አእምሯችንን በምንመግበው ነገር ስለሆነ ይህ ሁኔታ የሚያስከትለው የሚበክል ተጽዕኖ ቀላል አይደለም።— ሮሜ 12:2፤ ኤፌሶን 5:3, 4
7. አሁን ያሉትን መጥፎ ሁኔታዎች በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አስቀድሞ የተናገረው እንዴት ነው?
7 ባለንበት መቶ ዘመን ያሉትን ሁኔታዎች አደገኛ አዝማሚያ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት አስቀድሞ ተናግሯል። ዓለም አቀፍ ጦርነት፣ ወረርሽኝ በሽታዎች፣ የምግብ እጥረትና እየጨመረ የሚሄድ ዓመፅ እንደሚኖር ተነግሯል። (ማቴዎስ 24:7-12፤ ሉቃስ 21:10, 11) እንዲሁም በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ የተመዘገበውን ትንቢት ማንበብ ልክ የየዕለቱን ዜና እንደመከታተል ያክል ነው። ያለንበትን ዘመን ‘የመጨረሻ ቀን’ ብሎ ከጠራ በኋላ ሰዎች ‘ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ ከዳተኞች፣ የተፈጥሮ ፍቅር የሌላቸው፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚወዱ’ እንደሚሆኑ ይገልጻል። ዛሬ ዓለማችን በእርግጥም ይህን የሚመስል ነው። ልክ ዊልያም ቤነት እንደተናገሩት “ሥልጣኔ ጨርሶ እንደተበላሸ የሚያሳዩ . . . በጣም ብዙ ምልክቶች አሉ።” እንዲያውም ሥልጣኔ ያከተመለት በአንደኛው የዓለም ጦርነት እንደሆነ ይነገራል።
8. አምላክ በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ ያመጣው ለምን ነበር? በዚያን ዘመን የነበረው ሁኔታ ከዘመናችን ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?
8 ዛሬ ያለው ሁኔታ ‘ምድር በዓመፅ በተሞላችበት’ በኖኅ የጥፋት ውኃ ዘመን ከነበረው ሁኔታ በእጅጉ የከፋ ነው። በዚያ ዘመን የነበሩት ሰዎች ባጠቃላይ ከመጥፎ መንገዳቸው ለመመለስ አሻፈረን ብለው ነበር። ከዚህም የተነሳ አምላክ “ምድር በግፍ ተሞልታለችና፤ እኔም እነሆ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ” ሲል ተናግሯል። የጥፋት ውኃው ያን ዓመፀኛ ዓለም ጠራርጎ አስወግዶታል።— ዘፍጥረት 6:11, 13፤ 7:17-24
ሰዎች ማዳን አይችሉም
9, 10. ደኅንነት ለማግኘት በሰዎች ላይ መመካት የሌለብን ለምንድን ነው?
9 በሰዎች ጥረት ከእነዚህ መጥፎ ሁኔታዎች ልንገላገል እንችላለንን? የአምላክ ቃል እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል:- “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ።” “አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመደው ሰው አይደለም።” (መዝሙር 146:3፤ ኤርምያስ 10:23) የብዙ ሺህ ዓመታት ታሪክ የእነዚህን አባባሎች አውነተኝነት አረጋግጧል። ሰዎች መፍትሄ ያስገኛል ብለው የሚያስቡትን ማንኛውንም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሥርዓት ሞክረው ነበር፤ ሁኔታዎቹ ግን ይበልጥ ተባባሱ። ሰብዓዊ መፍትሄ ቢኖር ኖሮ እስከ ዛሬ ድረስ እውን በሆነ ነበር። ሐቁ ግን ‘ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።’— መክብብ 8:9፤ ምሳሌ 29:2፤ ኤርምያስ 17:5, 6
10 የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ የጸጥታ አማካሪ ዝቢግኒዬቭ ብራዢንስኪ ከጥቂት ዓመታት በፊት እንዲህ ብለው ነበር:- “ዓለም አቀፍ አዝማሚያዎችን ገለልተኛ በሆነ አቋም ብንመረምር ወደ አንድ የማይቀር መደምደሚያ እንደርሳለን፤ ይህም ማለት ማኅበራዊ ብጥብጥ፣ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ቀውስና በአገሮች መካከል የሚነሳ ግጭት ይበልጥ እየተስፋፋ እንደሚሄድ እንገነዘባለን።” አክለውም “የሰው ዘር አስጊ የሆነ ዓለም አቀፍ ሁከት እፊቱ ተጋርጧል” ሲሉ ተናግረዋል። የዓለም ሁኔታዎችን አስመልክቶ የተሰጠው ይህ አስተያየት ዛሬ ይበልጥ ይሠራል። በከኔቲከት ኒው ሃቨን የሚታተመው ሬጂስተር የተባለው ጋዜጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ ያለንበትን ዘመን የዓመፅ መጨመር አስመልክቶ ሲያትት “ሁኔታው ፈጽሞ ከቁጥጥራችን ውጭ የሆነ ይመስላል” ብሏል። ስለ “መጨረሻው ቀን” የሚናገረው ትንቢት “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” ስለሚል እያዘቀጠ የሚሄደው የዓለም ሁኔታ መግቻ የለውም።—2 ጢሞቴዎስ 3:13
11. ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ የሚሄዱት ሁኔታዎች በሰዎች ጥረት ሊስተካከሉ የማይችሉት ለምንድን ነው?
11 ‘የዚህ የነገሮች ሥርዓት አምላክ’ ሰይጣን ስለሆነ ሰዎች እነዚህን ሁኔታዎች ማስተካከል አይችሉም። (2 ቆሮንቶስ 4:4) አዎን፣ ‘ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል።’ (1 ዮሐንስ 5:19፤ በተጨማሪም ዮሐንስ 14:30ን ተመልከት።) መጽሐፍ ቅዱስ ያለንበትን ዘመን አስመልክቶ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” ሲል መናገሩ ትክክል ነው። (ራእይ 12:12) ሰይጣን የእሱ አገዛዝና እሱ የሚቆጣጠረው ዓለም ሊጠፋ እንደተቃረበ ያውቃል፤ ስለዚህ ‘የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ’ በመዞር ላይ ነው።—1 ጴጥሮስ 5:8
መዳን ቀርቧል—ግን ለእነማን?
12. በቅርቡ መዳን የሚያገኙት እነማን ናቸው?
12 በምድር ላይ እየጨመሩ የሚሄዱት ሁኔታዎች መባባስ፣ በእርግጥም ታላቅ መዳን እንደቀረበ የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው! ግን ለእነማን? መዳን የቀረበው የማስጠንቀቂያ ምልክቶችን ልብ ለሚሉትና ተገቢውን እርምጃ ለሚወስዱ ሰዎች ነው። አንደኛ ዮሐንስ 2:17 “ዓለሙም [የሰይጣን የነገሮች ሥርዓት] ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” በማለት መደረግ ያለበትን ነገር ይገልጻል።—ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን፤ በተጨማሪ 2 ጴጥሮስ 3:10-13ን ተመልከት።
13, 14. ኢየሱስ ነቅቶ የመኖርን አስፈላጊነት ያጎላው እን ዴት ነው?
13 ኢየሱስ ዛሬ ያለው ብልሹ ኅብረተሰብ ‘ከዓለም መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ባልሆነውና ከዚያም በኋላ በማይሆነው’ ታላቅ መከራ በቅርቡ ተጠራርጎ እንደሚጠፋ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:21) እንዲህ ሲል ያስጠነቀቀው ለዚህ ነው:- “ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋል። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ . . . እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።”—ሉቃስ 21:34-36
14 ‘በጥንቃቄ የሚመላለሱ’ እና ‘ሁልጊዜ ንቁ’ የሆኑ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ መርምረው ካወቁ በኋላ በሥራ ይተረጉሙታል። (ምሳሌ 2:1-5፤ ሮሜ 12:2) በቅርቡ በሰይጣን ሥርዓት ላይ ከሚመጣው ጥፋት ‘ማምለጥ’ የሚችሉት እነዚህ ሰዎች ናቸው። ደግሞም ከጥፋቱ እንደሚድኑ ሙሉ ትምክኽት ሊኖራቸው ይችላል።— መዝሙር 34:15፤ ምሳሌ 10:28-30
ታላቁ አዳኝ
15, 16. ታላቁ አዳኝ ማን ነው? የጽድቅ ፍርዶች እንደሚፈርድ እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው?
15 የአምላክ አገልጋዮች ከመከራ እንዲገላገሉ ሰይጣንም ሆነ በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም አቀፍ ሥርዓት በአጠቃላይ መወገድ አለበት። ይህ ደግሞ ከሰው በላይ የሆነ ኃያል አዳኝ ሊያከናውነው የሚችል ነገር ነው። ይህ አዳኝ አስደናቂውን አጽናፈ ዓለም የፈጠረው ሁሉን ቻይ ሉዓላዊ ገዢ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። ታላቁ አዳኝ እሱ ነው፤ “እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፣ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም” ብሏል።— ኢሳይያስ 43:11፤ ምሳሌ 18:10
16 ይሖዋ ይህ ነው የማይባል ኃይል፣ ጥበብ፣ ፍትሕና ፍቅር አለው። (መዝሙር 147:5፤ ምሳሌ 2:6፤ ኢሳይያስ 61:8፤ 1 ዮሐንስ 4:8) ስለዚህ ፍርዱን በሚያስፈጽምበት ጊዜ የሚወስደው እርምጃ የጽድቅ እርምጃ እንደሚሆን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። አብርሃም “የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?” ሲል ጠይቋል። (ዘፍጥረት 18:24-33) ጳውሎስ “አምላክ ፍትህን ያዛባልን? እንዲህስ ከቶ አይሁን!” ሲል ተናግሯል። (ሮሜ 9:14 NW ) ዮሐንስ “አዎን፣ ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፣ ፍርዶችህ እውነትና ጽድቅ ናቸው” ሲል ጽፏል።— ራእይ 16:7
17. ቀደም ባሉት ዘመናት የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋ ላይ ሙሉ እምነት እንደነበራቸው ያሳዩት እንዴት ነው?
17 ይሖዋ አድናለሁ ብሎ ቃል ከገባ ያለምንም ጥርጥር ቃሉን ይፈጽማል። ኢያሱ “እግዚአብሔር . . . ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም” ብሏል። (ኢያሱ 21:45) ሰሎሞንም “[አምላክ] ከሰጠው ከመልካም ተስፋ ሁሉ አንድ ቃል አልወደቀም” ሲል ተናግሯል። (1 ነገሥት 8:56) አብርሃም “እግዚአብሔር . . . የሰጠውንም ተስፋ ደግሞ ሊፈጽም እንዲችል አጥብቆ እየተረዳ፣ በእምነት በረታ እንጂ በአለማመን ምክንያት በእግዚአብሔር ተስፋ ቃል አልተጠራጠረም” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ ተናግሯል። ሣራም በተመሳሳይ “ተስፋ የሰጠው [አምላክ] የታመነ እንደ ሆነ” እርግጠኛ ነበረች።— ሮሜ 4:20, 21፤ ዕብራውያን 11:11
18. ዛሬ ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ይሖዋ እንደሚያድናቸው እርግጠኞች የሚሆኑት ለምንድን ነው?
18 ይሖዋ እንደ ሰዎች አይደለም፤ ሙሉ በሙሉ የታመነና ምን ጊዜም ቢሆን ቃሉን የሚጠብቅ ነው። “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ምሎአል:- እንደ ተናገርሁ በእርግጥ ይሆናል፣ እንደ አሰብሁም እንዲሁ ይቆማል።” (ኢሳይያስ 14:24) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ “ጌታ እግዚአብሔር የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፣ በደለኞችንም . . . ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል” በማለት የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን። (2 ጴጥሮስ 2:9) “ከእናንተ ጋር ይዋጋሉ፣ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፣ ይላል እግዚአብሔር” ሲል ከነቢያቱ ለአንዱ የሰጠው ተስፋ የይሖዋን ስሜት የሚያንጸባርቅ ስለሆነ የይሖዋ አገልጋዮች ኃያላን የሆኑ ጠላቶቻቸው እንደሚያጠፏቸው ቢዝቱባቸውም እንኳ አይፈሩም።—ኤርምያስ 1:19፤ መዝሙር 33:18, 19፤ ቲቶ 1:2
ከዚህ ቀደም የተወሰዱ የማዳን እርምጃዎች
19. ይሖዋ ሎጥን ያዳነው እንዴት ነበር? ይህስ ለዘመናችን ምን ጥላነት አለው?
19 ይሖዋ ከዚህ ቀደም የወሰዳቸውን አንዳንድ የማዳን እርምጃዎች መለስ ብለን በመቃኘት ትልቅ ማበረታቻ ልናገኝ እንችላለን። ለምሳሌ ያክል ሎጥ በሰዶምና ገሞራ ክፋት ‘በጣም ተጨንቆ’ ነበር። ሆኖም ይሖዋ የእነዚህን ከተሞች “ጩኸት” ሰማ። ይሖዋ ሎጥና ቤተሰቡ በአስቸኳይ ከዚያ አካባቢ ለቅቀው እንዲወጡ ለማድረግ መልእክተኞች ላከ። ከዚያስ ምን ሆነ? ይሖዋ “ጻድቁን ሎጥን” አድኖ ‘የሰዶምንና ገሞጎራን ከተሞች አመድ እስኪሆኑ ድረስ አቃጠላቸው።’ (2 ጴጥሮስ 2:6-8፤ ዘፍጥረት 18:20, 21) ዛሬም በተመሳሳይ በዚህ ዓለም ላይ በሚፈጸመው ይህ ነው የማይባል ክፋት የተነሳ የሚሰማውን ሰቆቃና ሮሮ ይሖዋ ያስተውላል። ዘመናዊ መልእክተኞቹ አጣዳፊ የሆነውን የምስክርነት ሥራቸውን እሱ የሚፈልገውን ያክል አከናውነው ሲያጠናቅቁ በዚህ ዓለም ላይ እርምጃ በመውሰድ ልክ ሎጥን እንዳዳነው አገልጋዮቹን ያድናቸዋል።— ማቴዎስ 24:14
20. ይሖዋ የጥንቶቹን እስራኤላውያን ከግብፅ እንዴት እንዳዳናቸው ግለጽ።
20 በሚልዮን የሚቆጠሩ የአምላክ ሕዝቦች በጥንቷ ግብፅ ውስጥ በባርነት ሥር ነበሩ። ይሖዋ እነሱን በተመለከተ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ሥቃያቸውንም አውቄአለሁ፤ . . . አድናቸው ዘንድ . . . ወረድሁ።” (ዘጸአት 3:7, 8) ይሁን እንጂ ፈርዖን የአምላክ ሕዝቦች በነፃ እንዲሄዱ ከለቀቀ በኋላ ሐሳቡን ቀየረና ግዙፍ በሆነው ሠራዊቱ አማካኝነት ያሳድዳቸው ጀመር። እስራኤላውያን ቀይ ባሕር ጋር ሲደርሱ ከዚያ በኋላ ምንም ማምለጫ የሌላቸው መስሏቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሙሴ “አትፍሩ፣ . . . ቁሙ፣ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ” ሲል ተናገረ። (ዘጸአት 14:8-14) ይሖዋ ቀይ ባሕርን በመክፈል እስራኤላውያን እንዲያመልጡ አደረገ። የፈርዖን ሠራዊት እንደጋለቡ ተከትለዋቸው ወደ ባሕሩ ገቡ፤ ሆኖም ይሖዋ ኃይሉን ሲጠቀም ‘ባሕሩ ከደናቸው፤ እነሱም እንደ አሸዋ ቁልቁል ሰምጠው ቀሩ።’ ከዚያም ሙሴ እንዲህ ሲል ይሖዋን በመዝሙር አወደሰ:- “በምስጋና የተፈራህ፣ ድንቅንም የምታደርግ፣ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?”— ዘጸአት 15:4-12, 19
21. የይሖዋ ሕዝቦች ከአሞን፣ ከሞዓብና ከሴይር የዳኑት እንዴት ነበር?
21 በአንድ ወቅት ደግሞ እንደ አሞን፣ ሞዓብና ሴይር (ኤዶም) ያሉ ጠላት መንግሥታት የይሖዋን ሕዝቦች ለማጥፋት ዛቱ። ይሖዋ እንዲህ አለ:- “ሰልፉ የእግዚአብሔር ነው እንጂ የእናንተ አይደለምና ከዚህ ታላቅ ወገን የተነሣ አትፍሩ፣ አትደንግጡም። . . . እናንተ በዚህ ሰልፍ የምትዋጉ አይደላችሁም። . . . ዝም ብላችሁ ቁሙ፣ የሚሆነውንም የእግዚአብሔርን መድኃኒት እዩ።” ይሖዋ በጠላት ጦር ሠፈር ግራ መጋባት እንዲፈጠርና እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ በማድረግ ሕዝቦቹን አዳነ።—2 ዜና መዋዕል 20:15-23
22. ይሖዋ እስራኤላውያንን ከአሦራውያን ለማዳን ምን ተዓምራታዊ እርምጃ ወስዷል?
22 የዓለም ኃያል የነበረው የአሦር መንግሥት በእስራኤል ላይ በዘመተበት ጊዜ ንጉሥ ሰናክሬም በቅጥሩ ላይ ላለው ሕዝብ “እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ [ድል ካደረግኋቸው] አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው?” ብሎ በመናገር በይሖዋ ላይ ተዘባበተ። ለአምላክ አገልጋዮች እንዲህ አላቸው:- “ሕዝቅያስም:- እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል . . . ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።” ከዚያ በኋላ ሕዝቅያስ “አምላካችን አቤቱ፣ የምድር መንግሥታት ሁሉ አንተ ብቻ እግዚአብሔር እንደሆንህ ያውቁ ዘንድ ከእጁ አድነን” በማለት አጥብቆ ጸለየ። ይሖዋ 185, 000 የአሦር ወታደሮችን ገደለ፤ የአምላክ አገልጋዮችም ዳኑ። ከዚያም ሰናክሬም የሐሰት አምላኩን እያመለከ ሳለ በልጆቹ ተገደለ።—ኢሳይያስ ምዕራፍ 36 እና 37
23. በዘመናችን የሚፈጸመውን የማዳን እርምጃ በተመለከተ የትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል?
23 ቀደም ባሉት ዘመናት ይሖዋ ሕዝቦቹን በሚያስደንቅ ሁኔታ እንዴት እንዳዳነ ስንመለከት በእርግጥም ድፍረት እንድናገኝ ሊያደርገን ይችላል። ስላለንበት ጊዜስ ምን ለማለት ይቻላል? የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በቅርቡ የእሱን ተዓምራታዊ ማዳን የሚጠይቅ ምን አደገኛ ሁኔታ ይጠብቃቸዋል? እነሱን ለማዳን እስከ አሁን ድረስ የቆየው ለምንድን ነው? “ይህ ሁሉ መሆን በሚጀምርበት ጊዜ ደኅንነታችሁ ቀርቦአልና ቀና ብላችሁ ወደ ላይ ተመልከቱ” በማለት ኢየሱስ የተናገረው ነገር ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ነው? (ሉቃስ 21:28 የ1980 ትርጉም ) ከአሁን ቀደም የሞቱት የአምላክ አገልጋዮች ደኅንነት የሚያገኙት እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ጥያቄዎች ያብራራል።
የክለሳ ጥያቄዎች
◻ መዳን በጣም አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ምንድን ነው?
◻ ለመዳን በሰዎች ላይ መመካት የሌለብን ለምንድን ነው?
◻ በቅርቡ መዳን የሚያገኙት እነማን ናቸው?
◻ በይሖዋ የማዳን ችሎታ ሙሉ በሙሉ ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
◻ ቀደም ባሉት ዘመናት የተከናወኑ የትኞቹ የማዳን እርምጃዎች ድፍረት እንዲኖረን ያደርጉናል?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክኽት ከነበራቸው ሰዎች መካከል አብርሃም አንዱ ነው