ለዓለም አስተማማኝ የምግብ አቅርቦት—እንዴት?
በዋሽንግተን ዲ ሲ የዎርልድዎች ኢንስቲትዩት ፕሬዚዳንት የሆኑት ሌስተር ብራውን “በዚህ መቶ ዘመን በአብዛኛው እንደተመለከትነው የምግብ አቅርቦትን አስተማማኝ ለማድረግ የእኛ ከፍተኛ ጥረት ብቻ በቂ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል። ኒው ሳይንቲስት የተባለው መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ በ1995 መባቻ የዓለም የእህል ምርት ክምችት ከምን ጊዜውም በላይ ቀንሶ ወደ 255 ሚልዮን ቶን ዝቅ ያለ ሲሆን ይህ ደግሞ የዓለምን ሕዝብ ለ48 ቀናት ብቻ መመገብ የሚችል ነው። በቀደሙት ዓመታት የእህል ክምችቱ ዝቅ የሚለው ለ60 ቀናት መመገብ ወደሚችልበት ደረጃ ስለነበረ እንደገና ወደ ነበረበት መመለስ ይቻል ነበር። አሁን ግን ምድር ያጣችውን መልሳ ለማግኘት ባላት አቅም ላይ ወርልድዎች ከፍተኛ ጥርጣሬ አለው።
ለሦስት ዓመታት በቂ ምርት ስላልተሰበሰበና አብዛኞቹ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች እህሉን ለከብቶች ስለሚመግቡ የሚበሉት የሌላቸውን ድሆች ለመመገብ የሚበቃ እህል የለም። ጉዳዩ አፋጣኝ ትኩረት ካልተሰጠው በስተቀር ቢያንስ 70 ከመቶ የሚሆነውን ገቢያቸውን ለምግብ የሚያውሉት አንድ ቢልዮን ሰዎች በረሀብ ሊጠቁ እንደሚችሉ ኒው ሳይንቲስት መጽሔት አስጠንቅቋል።
መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ያሉ የምድር ነዋሪዎች “የምግብ እጥረት” እንደሚያጋጥማቸው አስቀድሞ ተንብዮአል። (ሉቃስ 21:11 NW) ሆኖም አምላክ ችግሩን በግዴለሽነት አይመለከትም። እንዲያውም የእሱ መንግሥት የምድርን ጉዳዮች በሚቆጣጠርበት ጊዜ በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰው መከራ በጣም እንደሚያሳስበው በግልጽ ይታያል። በዚያን ጊዜ ‘ምድር ፍሬዋን ትሰጣለች።’ ‘በምድር ላይ በቂ እህል ይኖራል፤ ተራሮች በሰብል ይሸፈናሉ።’ (መዝሙር 67:6፤ 72:16 የ1980 ትርጉም) ከዚያም ስለ ፈጣሪ የሚናገሩት እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ:- “ምድርን ጎበኘሃት አጠጣሃትም፣ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ . . . ሸለቆዎችም በእህል ተሸፈኑ።”— መዝሙር 65:9, 13
ይህ አስደናቂ ተስፋ ያስደስትሃልን? እንዴት ከዚህ ተስፋ ተካፋይ መሆን እንደምትችል ማወቅ ትፈልጋለህ? እንግዲያው በሚቀጥለው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ቤትህ ሲመጡ ስለዚህ የገነት ተስፋ በይበልጥ እንዲነግሩህ ጠይቃቸው። አንድ ሰው እቤትዎ መጥቶ መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ እንዲያስተምርዎ የሚፈልጉ ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የፖ.ሣ.ቁ 5522፣ አዲስ አበባ ብለው ወይም በገጽ 2 ላይ ካሉት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው ይጻፉ።
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Inset: Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.