ዛሬ የአቋም ጽናት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት ትንሽ ቀደም ብሎ ባርኒ ባርናቶ የተባለ አንድ የአልማዝ ነጋዴ ከደቡብ አፍሪካ ተመልሶ ወደ እንግሊዝ ይመጣል። እንደ ደረሰም አንድ ጋዜጣ ላይ ስለ እርሱ የወጣው ዜና አልዋጥልህ ይለዋል። ስለዚህ “አንዳንድ ነገሮችን አስተካክሎ” ሁለተኛ ጊዜ እንዲያወጣለት ሲል ለጋዜጣው አዘጋጅ በእጅ የተጻፈ ማስታወሻና ጠቀም ያለ ገንዘብ የያዘ ቼክ ይሰጠዋል።
አዘጋጁ ጄ ኬ ጀሮም፣ ባርናቶ የሰጠውን ማስታወሻ ጠቅልሎ ቅርጫት ውስጥ ከጣለ በኋላ ቼኩን ይመልስለታል። ባርናቶ በሁኔታው በመገረም ወዲያውኑ እጥፍ ገንዘብ እንደሚሰጠው ቃል ገባለት። እርሱ ግን ይህንንም ቢሆን አልተቀበለም። “ታዲያ ምን ያህል ነው የምትፈልገው?” ሲል ጠየቀው። ጀሮም “እንዲህ የመሰለ ነገር ለንደን ውስጥ እንደማይሠራ ነገርሁት” በማለት የሆነውን ነገር ያስታውሳል። ለሙያው ያለውን የጸና አቋም ለድርድር ለማቅረብ እንዳልፈለገ የታወቀ ነው።
የአቋም ጽናትን የሚያመለክተው “ኢንቴግሪቲ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ትክክለኛ ምግባር፣ ሐቀኝነት” የሚል ትርጉም ሲሰጠው ቆይቷል። የአቋም ጽናት ያለው ሰው እምነት የሚጣልበት ሰው ይሆናል። ይሁን እንጂ ዛሬ የአቋም ጽናት የማሳየት ችግር ያልዳሰሰው የኅብረተሰብ ክፍል የለም።
የብሪታንያ መገናኛ ብዙሐን ሥነ ምግባራዊ የአቋም ጽናት ማጣትን የሚገልጸውን “ስሊዝ” የሚለውን የእንግሊዝኛ ቃል ለሕዝብ አስተዋውቀዋል። ዚ ኢንዲፐንደንት የተባለው ጋዜጣ እንደገለጸው ከሆነ ስሊዝ የሚለው ቃል “በፍቅረኛ ላይና በመንግሥት መስተዳድሮች ውስጥ ከሚፈጸመው ሸፍጥ አንስቶ በከፍተኛ የውጭ ንግድ ዘርፍ እስከሚታየው የገንዘብ ቅሌት ድረስ” ያለውን ሁሉ ያጠቃልላል። ከዚህ ነፃ የሆነ የኑሮ ዘርፍ የለም።
የሚዋዥቀው የአቋም ጽናት ደረጃ
እርግጥ የአቋም ጽናት ማሳየት ማለት ፍጹም መሆን ማለት አይደለም፤ ይሁን እንጂ ለአንድ ሰው ወሳኝ ባሕርይ ነው። ሀብትን የማጋበስ ምኞት በተጠናወተው ዓለማችን ውስጥ ጽኑ አቋም መያዝ እንደ እንቅፋት እንጂ በጎ ምግባር ተደርጎ ላይታይ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ተማሪዎች የተራቀቁ መሣሪያዎችን በፈተና ወቅት ለማጭበርበር መጠቀማቸው በሰፊው እየተዘወተረ መጥቷል። እነዚህን አዳዲስ መሣሪያዎች በፍተሻ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። አንድ የብሪታንያ ተወላጅ የሆኑ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ከጠቅላላዎቹ የብሪታንያ ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እንደሚያጭበረብሩና ይህ ደግሞ የብሪታንያ ብቻ ችግር እንዳልሆነ ገልጸዋል።
እምነት ሊጣልባቸው የማይችሉ ሰዎች የሚናገሩት ውሸትና የሚፈጽሙት ማጭበርበር በንጹሐን ሰዎች ላይ የሚያስከትለውም ውጤት ሳይጠቀስ አይታለፍም። ለምሳሌ ያህል በ1984 በመርዘኛ ጋዝ ከ2,500 የሚበልጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ሕይወት የተቀጠፈባትንና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች የቆሰሉባትን የሕንድ ከተማ ቦፓልን ተመልከት። ዘ ሰንዴይ ታይምስ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “የአደጋውን ሰለባዎች ለመርዳት የተደረጉት ጥረቶች ማጭበርበር ሞልቶባቸው ነበር። . . . የቀረቡት በሺህ የሚቆጠሩ የሐሰት የይገባኛል ጥያቄዎች፣ የተጭበረበሩ ሰነዶችና፣ የማታለያ ማስረጃዎች እውነተኞቹን ተረጂዎች ለመለየት የተደረጉትን ጥረቶች ውስብስብ አድርገዋቸዋል።” በመሆኑም ከአሥር ዓመታት በኋላ እንኳ ለሰፋሪዎቹ ከተመደበው የ470,000,000 የአሜሪካን ዶላር የጉዳት ካሳ ውስጥ መስጠት የተቻለው 3,500,000 የአሜሪካን ዶላር ብቻ ነው።
ስለ ሃይማኖትስ ምን ማለት ይቻላል? የጸና አቋም በመያዝ ረገድ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? በዚህ ረገድ ሃይማኖቶች የሚገኙበት ሁኔታ ከቀረው ዓለም የተለየ አለመሆኑ ያሳዝናል። ለምሳሌ ያህል የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን የኤመን ካሴይን ሁኔታ ተመልከት። እኚህ ሊቀ ጳጳስ በአሁን ወቅት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ዲቃላ ልጅ እንዳላቸው በቅርቡ አምነዋል። ጋርዲያን የተባለው የብሪታንያ ጋዜጣ እንደጠቆመው ከሆነ ካሴይ የፈጸሙት ነገር “እንግዳ አይደለም።” በተመሳሳይም ሁኔታ ዘ ታይምስ የተባለው መጽሔት እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “ሊቀ ጳጳስ ካሴይ የፈጸሙት አሳፋሪ ተግባር የሚያሳየው የፈጸሙት ስህተት እንግዳ ነገር እንደሆነ ሳይሆን የብሕትውናን መሐላ መጣስ አዲስ ወይም ያልተለመደ ነገር እንዳልሆነ ነው።” በስኮትላንድ የሚታተመው ዘ ግላስጎው ሄራልድ ይህንኑ አስተያየት በመደገፍ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ካሉት የሮማ ካቶሊክ ቀሳውስት መካከል ከተቃራኒ ፆታ ጋር ከሚደረግ ሩካቤ ሥጋም ሆነ ከግብረ ሰዶም የተቆጠቡት 2 በመቶ የሚሆኑት ብቻ እንደሆኑ ገልጿል። ይህ ቁጥር ትክክል ሆነም አልሆነ የካቶሊክ ቀሳውስት ሥነ ምግባርን በተመለከተ ምን ዓይነት ስም እንዳተረፉ ያሳያል።
ከእነዚህ ሁሉ ምሳሌዎች አንጻር አንድ ሰው የጸና የሥነ ምግባር አቋሙን ሳያጎድፍ መኖር ይችላልን? ይህንንስ ማድረግ ያን ያክል ጠቃሚ ነውን? ይህን ማድረግ ምን ይጠይቃል? የሚያስገኘውስ ወሮታ ምንድን ነው?