መጽሐፍ ቅዱስ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መጽሐፍ
በዓለም ላይ በብዛት ከተሸጡት መጻሕፍት መካከል የመጀመሪያውን ደረጃ እንደያዘ ይነገርለታል፤ ደግሞም እውነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከማንኛውም ሌላ መጽሐፍ በበለጠ በብዙዎች ዘንድ ለንባብ የበቃና ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈ መጽሐፍ ነው። እስከዛሬ ድረስ (በሙሉም ይሁን በከፊል) ከ2,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች በአራት ቢልዮን ቅጂ እንደተሠራጨ ይገመታል።
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት ከስርጭቱ ይበልጥ ትኩረት የሚስበው በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት እንደተጻፈ የሚገልጽ መሆኑ ነው። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ “ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት” እንደተጻፈ ገልጿል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 NW) ይህ ምን ማለት ነው? “በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት” የሚለው ሐረግ (በግሪክኛ ቴኦፕኔዎስቶስ) ጥሬ ፍች “አምላክ የተነፈሰበት” ማለት ነው። ከዚህ ጋር ተዛማጅ የሆነው ፕኔውማ የሚለው የግሪክኛ ቃል ትርጉሙ “መንፈስ” ማለት ነው። በመሆኑም በመጨረሻ ቃሉ የሰው ሳይሆን በእርግጥ የአምላክ ነው ለመባል ይበቃ ዘንድ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ጸሐፊዎቹን የተነፈሰባቸው ያክል እየመራ እንዲጽፉ ገፋፍቷቸዋል ማለት ነው። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስን ያጠኑ ብዙ ሰዎች መጽሐፉ እርስ በርሱ ባለው አጠቃላይ ስምምነት፣ በሳይንሳዊ ትክክለኛነቱ፣ በጸሐፊዎቹ ሐቀኝነትና ግልጽነት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፍጻሜያቸውን ባገኙት ትንቢቶቹ በጣም ይደነቃሉ። እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች በሚልዮን የሚቆጠሩ አስተዋይ አንባብያን የመጽሐፉ ምንጭ ከሰው በላይ የሆነ አካል መሆኑን እንዲያምኑ አድርገዋቸዋል።a
ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ሲጻፍ አምላክ ምን ያህል በቅርብ ተከታትሏል? አንዳንዶች አምላክ እያንዳንዱን ቃል እየነገረ አስጽፏቸዋል ይላሉ። ሌሎች ደግሞ እንዲሁ ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መልእክት በመንፈሱ አማካኝነት ገለጸላቸው እንጂ እያንዳንዱን ቃል አልነገራቸውም ይላሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሰዎች ቃሉን እንዲጽፉ አምላክ በመንፈሱ ያነሳሳቸው በአንድ ዓይነት መንገድ ብቻ አይደለም። ምክንያቱም “በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት” ተናግሯል። (ዕብራውያን 1:1 ጋደል አድርገን የጻፍነው እኛ ነን፤ ከ1 ቆሮንቶስ 12:6 ጋር አወዳድር።) በሚቀጥለው ርዕስ አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን በጽሑፍ ላሠፈሩት 40 የሚያክሉ ጸሐፊዎች መልእክቱን ያስተላለፈባቸውን መንገዶች እንመረምራለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በኒው ዮርክ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን (የእንግሊዝኛ) መጽሐፍ ገጽ 53-4 እንዲሁም 98-161 ተመልከት።