በናቫሆ ምድር ለሚኖሩ በግ መሰል ሰዎች የሚሆን የግጦሽ መስክ
በናቫሆ ሕንዶች ቋንቋ ሆዝሆኒ ማለት “ውብ” ማለት ሲሆን የናቫሆ ሰዎች ምድራቸውን በዚህ ቃል ይገልጹታል። ከ1868 ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት አራቱ ግዛቶች ማለትም አሪዞና፣ ኮሎራዶ፣ ኒው ሜክሲኮና ዩቶታ በሚገናኙበት አራት ማዕዘናት ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ አካባቢ ያለውንና በሰሜናዊ ምሥራቅ አሪዞና የሚገኘውን ወደ 62,000 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የተከለለ መሬት ለናቫሆ ሰዎች ሰጥቷል። ሞንዩመንት ቫሊ እየተባለ የሚጠራው ታሪካዊ ሸለቆ በምዕራብ አሜሪካ የነበረውን ኑሮ በሚያሳዩ ፊልሞች ላይ በብዛት ይታይ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የናቫሆ ፓርክ ሆኖ በማገልገል በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ቱሪስቶችን በመሳብ ላይ ይገኛል። በከፍታ ቦታ ላይ ባሉት በረሃማ ሜዳዎች ላይ ተራርቀው የሚገኙ በመቶ ሜትሮች የሚቆጠር ከፍታ ያላቸው ቀያይ የሆኑ አሸዋማ አለቶች በሸለቆው ውስጥ ቆመው ይታያሉ። “በአለቶች መካከል ያለ ቦታ” የሚል ትርጉም ያለው ሸለቆው የተሰየመበት የናቫሆ መጠሪያ ለቦታው ተስማሚ ስያሜ ነው።
በጥቅሉ ሲታይ የናቫሆ ሰዎች በትሕትናቸውና በእንግዳ ተቀባይነታቸው የሚታወቁ ከመሆናቸውም በላይ ከቅርብ ዘመዶቻቸው ጋር የጠበቀ ትስስር ያላቸውና አንድ ላይ የሚኖሩ ናቸው። በዚህ ክልል ውስጥ የሚገኙት 170,000 ነዋሪዎች በአብዛኛው ተራርቀው በመስፈር ባሕላዊ በሆነ መንገድ የሚኖሩ ናቸው። አንዳንዶቹ አሁንም ድረስ በጎች የሚያረቡ ሲሆን ከእንጨት በተሠሩና የአፈር ክዳን ባላቸው ሆጋን ተብለው በሚጠሩ ትንንሽ ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ። የናቫሆ የኪነ ጥበብና የእጅ ሥራዎች በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት አግኝቷል። በተለይ ከበግ ፀጉር የሚሠሩት በቀለም ያሸበረቁና የተለያዩ ጂኦሜትሪያዊና ባሕላዊ ንድፎች ያሉባቸው ስጋጃዎችና ብርድ ልብሶች በጣም የሚደነቁ ናቸው። ተርኮይዝ ተብሎ ከሚጠራው የከበረ ድንጋይና ከሌሎችም ተፈጥሮአዊ ነገሮች የሚሠራው የናቫሆ የብር ጌጣጌጥም በብዙዎች ዘንድ የታወቀ ነው።
ምሥራቹን በናቫሆ ምድር ማሰማት
የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ናቫሆ ምድር ከመጡ ከ30 ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል፤ ወደዚህ ሥፍራ የመጡት እንዲሁ አካባቢውን ለመጎብኘት ብቻ ሳይሆን በዚህ ርቆ በሚገኝ ሥፍራ ለሚኖሩት ሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማሰማት ሲሉ ነው። (ማቴዎስ 24:14) የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑ የዘወትርና ልዩ አቅኚ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት በማገልገል ላይ ናቸው። ብዙዎቹ የመጡት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና በዚህ ክልል የሚኖሩ ምሥክሮች ይበልጥ ሠራተኞች ወደሚያስፈልጉበት ሥፍራ መጥተው እንዲረዱ ላቀረቡላቸው ጥሪ ምላሽ በመስጠት ነው። አንዳንዶቹ በአቅራቢያው ከሚገኙ ጉባኤዎች የመጡ ሲሆኑ የአሜሪካ ተወላጅ የሆኑ ጎሳዎች አባላትን ጨምሮ ሌሎቹ ደግሞ የመጡት ከዩናይትድ ስቴትስ የተለያዩ ክፍሎች ነው።
የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደረጉት እነዚህ ወንዶችና ሴቶች በዚህ ሥፍራ የሚያከናውኑትን አገልግሎት ከሚስዮናዊነት ሥራ ጋር ያመሳስሉታል። ከሚስዮናዊነት ሥራ ጋር ያመሳሰሉት ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ በዚህ አካባቢ የሚነገሩት ቋንቋዎች አስቸጋሪ የሆነ የድምፅ ቃና፣ ይዘትና መግለጫ ያሏቸው በጣም ውስብስብ የሆኑ ቋንቋዎች በመሆናቸው ነው። በተጨማሪም የዚህ ክልል ተወላጆች በጥቅሉ በሃይማኖትና በቤተሰብ አወቃቀር ረገድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ወግና ልማድ አጥብቀው የሚከተሉና በግብርና ሥራ የሚተዳደሩ ናቸው። ከዚህም ሌላ ሕንዳውያን ያልሆኑ ሰዎች በቀላሉ ቤትና ሥራ ማግኘት አይችሉም፤ ይህም በዚህ ሥፍራ ለመኖር ከሌላ ቦታ ለመጡት ሰዎች ችግር ፈጥሮባቸዋል። በመጨረሻም፣ ነጮች ለረጅም ዘመናት በእነዚህ ሰዎች ላይ የፈጸሙት ግፍ ወደዚህ ሥፍራ የሚመጡ ሰዎችን በጥርጣሬ ዓይን እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል።a
በመጀመሪያ ምሥክሮቹ ሙሉ ልብስ አድርገውና ክራባት አስረው ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ የአካባቢው ነዋሪዎች ሞርሞኖች ናቸው የሚል የተሳሳተ አመለካከት አድሮባቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ ብዙዎቹ በራቸውን አይከፍቱላቸውም ነበር። አለባበሳቸውን ለውጠው ተራ የሆነ ልብስ ለብሰው ሲሄዱ ወደ ቤታቸው አስገብተው ብዙውን ጊዜ ለአንድ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ለሚሆን ጊዜ ያወያዩአቸው ጀመር። በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሲያገለግሉ እንደ ቀድሞው ሙሉ ልብስ የሚለብሱና ክራባት የሚያስሩ ቢሆንም ሰዎቹ ለይተው ያውቋቸዋል።
በናቫሆ ክልል የሚኖሩትን ሰዎች ለማግኘት ብዙ መሰናክል ማለፍ ይጠይቃል። ድንጋያማ፣ አሸዋማና ጭቃማ በሆኑ ምንም መንገድ ባልተቀየሰላቸው ቦታዎች ብዙ ኪሎ ሜትሮች በመኪና መጓዝ የተለመደ ነገር ነው። ይህ ደግሞ መኪናዎቹን ይበልጥ እንደሚጎዳቸውና ተሳፋሪዎቹንም እንደሚያንገላታቸው የታወቀ ነው። በተጨማሪም መኪናዎቹ ሊቀረቀሩ ይችላሉ፤ ሆኖም ብዙውን ጊዜ እግረኞች እርዳታ ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው። ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ተመልሶ ለማነጋገር፣ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጠናት ወይም ደግሞ አንድን ሰው ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ለመውሰድ ብዙውን ጊዜ የብዙ ሰዓት የደርሶ መልስ ጉዞ ማድረግ ይጠይቃል። ሆኖም ምሥክሮቹ በፈቃደኝነት ይህን በማከናወን የዚህ ክልል ተወላጆች ለሆኑት ሰዎች ፍቅራቸውን በማሳየት ላይ ናቸው።—ከ1 ተሰሎንቄ 2:8 ጋር አወዳድር።
የናቫሆ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ማድረግ ያስደስታቸዋል። ብዙውን ጊዜ መላው ቤተሰብ ማለትም ልጆች፣ ወላጆችና አያቶች ወደፊት ስለምትመጣዋና የሰው ዘሮች መኖሪያ ስለምትሆነው ገነት የተሰጠውን ተስፋ ለመስማት አንድ ላይ ይሰበሰባሉ። አንድ የናቫሆ ተወላጅ ገነት ምን ዓይነት መልክ ይኖራታል ብሎ እንደሚያስብ ሲጠየቅ “ብዙ በጎች ያሉበት አረንጓዴ መስክ” ብሎ በመመለስ ለሚኖሩበት አካባቢና ለመንጎቻቸው ያላቸውን ፍቅር የሚያንጸባርቅ መልስ ሰጥቷል። ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችም አድናቆት አላቸው፤ አንዳንድ ጊዜ ለመንግሥቱ አገልግሎት ድጋፍ ለመስጠት ለጌጥ የሚያገለግሉ ዶቃዎች፣ ሳሙና፣ በጣሳ የታሸገ ወተትና የመሳሰሉትን ነገሮች አስተዋጽኦ በማድረግ ይህን አድናቆታቸውን ያሳያሉ። አንድ ልዩ አቅኚ በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ 200 የሚጠጉ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ኮንትራት ማስገባት ችሏል፤ ከእነዚህ መካከል ሁለቱን ኮንትራት የገባው በፈረስ ይጓዝ የነበረ ሰው ነው።
“የበጎች ሰፈር” ማቋቋም
የበጋ ወቅት በሚደርስበት ጊዜ የናቫሆ እረኛ መንጋውን/ዋን ወደ አንድ የበጎች ሰፈር ይወስዳቸዋል/ትወስዳቸዋለች። በጎቹ በበጋ እንዲሠፍሩ የሚደረገው አረንጓዴ መስኮችና በቂ ውኃ ባለበት ሥፍራ አቅራቢያ በመሆኑ መንጎቹ እንዲፋፉ ይረዳቸዋል። በምሳሌያዊ አነጋገር አንድ የመንግሥት አዳራሽም መንፈሳዊ የግጦሽ መስክና የእውነት ውኃ ምንጭ የሚገኝበት ቦታ በመሆኑ ከእንዲህ ዓይነቱ ሰፈር ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ወደ መንግሥት አዳራሽ የሚመጡ ሰዎች በመንፈሳዊ ጤናሞችና ጠንካሮች እንዲሆኑ የሚረዳቸውን መንፈሳዊ ምግብ ሊያገኙ ይችላሉ።
ስብሰባዎች ለተወሰነ ጊዜ ያህል ይካሄዱ የነበሩት በአሪዞና ኬይንታ ውስጥ በሚገኝ የአንድ ትምህርት ቤት ክፍል ውስጥ ነበር። ከዚያ በኋላ ነሐሴ 1992 ላይ ከበርካታ ግዛቶች በመጡና ፈቃደኛ ሠራተኞች በሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች እርዳታ በኬይንታ ውስጥ አንድ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ተሠራ። ይህ የመንግሥት አዳራሽና በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የመንግሥት አዳራሾች በዚህ ሥፍራ የሚኖሩት ሰዎች የስብከቱ ሥራ በቋሚነት የሚከናወን መሆኑን እንዲገነዘቡ አድርገዋቸዋል። በዚህ ሰፊ ግዛት ውስጥ አገልግሎት የሚሠጡት ሌሎቹ የመንግሥት አዳራሾች ደግሞ በዚሁ ክልል ውስጥ በሚገኙት በቱባና በቺንሊ ከተሞች ያሉትን፣ በናቫሆ ክልል በሆፒ ጎሳ መሬት ውስጥ በሚገኘው በኪምስ ካንዮን ያለውንና በክልሉ አቅራቢያ በሚገኙ አዋሳኝ ከተሞች ውስጥ ያሉትን ሌሎች የመንግሥት አዳራሾች ያካትታሉ። ታዲያ ይህ ምን ውጤት አስገኝቷል?
ለመንግሥቱ መልእክት የተሰጠ አስደናቂ ምላሽ
በኬይንታ የመንግሥት አዳራሹ ከተሠራ ጊዜ ጀምሮ ወደ አሥራ ሁለት የሚሆኑ የአካባቢው ሰዎች ተጠምቀዋል፤ ይህም ይሖዋ በዚህ የእውነተኛ አምልኮ ቦታ በረከቱን እንዳፈሰሰ የሚያመለክት ነው። አዳራሹ የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ሥፍራ በቋሚነት የሚኖሩ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ ከመሆኑም በላይ በሚሰብኩት የመንግሥቱ ምሥራች ላይ እምነት ይገነባል። በቅርቡ በዚህ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በናቫሆ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ሕዝባዊ ንግግር ተሰጥቷል። አርባ የሚሆኑት የጉባኤው አባላት የወላጅነት ኃላፊነቶችን በተመለከተ የተሰጠውን ንግግር ለመስማት የመጡትን 245 ሰዎች በደስታ ተቀብለዋቸዋል። ስምንት አባላት ያሉት አንድ ቤተሰብ ለስብሰባው ልባዊ አድናቆት በማሳየት ንግግሩ ወደሚሰጥበት ቦታ ለመድረስ ብቻ ሦስት ሰዓት ያህል ተጉዘዋል፤ ወደ መንግሥት አዳራሽ ሲመጡ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር!
ይሖዋ ያዘጋጀው ሌላው ጠቃሚ የሆነ መሳሪያ በምድር ላይ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው በናቫሆ ቋንቋ የተተረጎመው ብሮሹር ነው። ይህን ብሮሹር በጣም ውስብስብ ወደሆነው የናቫሆ ቋንቋ መተርጎም በጣም ከባድ ሥራ ነበር። ተርጓሚዎቹ ይህ ብሮሹር የመንግሥቱን መልእክት በትክክል የሚያስተላልፍ ሆኖ እንዲወጣ ለማድረግ በድምሩ ከ1,000 ሰዓት በላይ አውለዋል። ብሮሹሩ በ1995 ማብቂያ ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ የሚገኙት ምሥክሮች ብዙ ሺህ ቅጂዎች አበርክተዋል፤ ይህም እውነት ፈላጊዎች የሆኑ በርካታ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የመንግሥቱ አስፋፊዎች የናቫሆን ቋንቋ እየተማሩ በሄዱ መጠን ቋንቋው በአገልግሎት ሥራ ላይ ይበልጥ እየተሠራበት በመሄድ ላይ ይገኛል። በዚህ ሥፍራ የሚገኙ ጉባኤዎች የናቫሆን ቋንቋ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ መጠቀም ጀምረዋል። አስፋፊዎቹንም ለማሠልጠን የናቫሆ ቋንቋ ትምህርት በመሰጠት ላይ ነው። ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ክልል የሚካሄዱት ትልልቅ ስብሰባዎችም በናቫሆ ቋንቋ ይተረጎማሉ። ይህ ሁሉ ጥረት በዚህ ክልል የበለጠ አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያስገኝ ጥርጥር የለውም።
በዚህ የሕንዳውያን ክልል ውስጥ ባለው የመንግሥቱ ፍሬ መካከል የናቫሆ ወንድሞቻችን የሚያንጸባርቋቸው የላቁ መንፈሳዊ ባሕርያትም በቸልታ የሚታለፉ አይደሉም። ጂሚና ሳንድራ አምስት ልጆቻቸውን ይዘው በሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በአንድ ጉዞ ብቻ 120 ኪሎ ሜትር እየተጓዙ ሰባት ዓመታት ያህል አሳልፈዋል። ቤተሰቡ ረጅሙን ጉዞ በሚያደርጉበት ወቅት የመንግሥቱን መዝሙሮች በመዘመርና መጽሐፍ ቅዱስን አንድ ላይ በማጥናት ያሳለፏቸው ጊዜያት አስደሳች ትዝታ ጥለውባቸዋል። ወላጆቹ ለእውነት ያላቸው ፍቅርና ቅንዓት ልጆቹ ምሳሌያቸውን ተከትለው ራሳቸውን ለአምላክ በመወሰን የይሖዋ አወዳሾች እንዲሆኑ አነሳስቷቸዋል። በአሁኑ ጊዜ አራቱ የዘወትር አቅኚዎች ሆነው በማገልገል ላይ ሲሆኑ ጂሚ ደግሞ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። በቅርቡ ኤልሲ የምትባለው የጂሚ እህት የናቫሆን ቋንቋ ብቻ ከሚናገሩት ሰዎች መካከል የመጀመሪያዋ ተጠማቂ መሆን በመቻሏ የቤተሰቡ ደስታ እጥፍ ድርብ ሆኗል።
የናቫሆን ክልል ውበት ካላበሱት እንደ ዓምድ ሆነው የቆሙ ትልልቅ አለቶች በተጨማሪ በአካባቢው ያሉት እረኞችና መንጎች በክልሉ ያለውን የተረጋጋ ያገር ቤት ኑሮ ያንጸባርቃሉ። ከብዙ ዘመናት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ ይሖዋን አስመልክቶ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል:- “መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፣ ጠቦቶቹን በክንዱ ሰብስቦ በብብቱ ይሸከማል፣ የሚያጠቡትንም በቀስታ ይመራል።” (ኢሳይያስ 40:11) ይሖዋ በመልካሙ እረኛው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት በናቫሆ ክልል የሚገኙትን የመንግሥቱን ምሥራች መስማትና ዘላለማዊ በረከቱን ማግኘት በሚችሉበት ጎዳና መጓዝ የሚፈልጉትን ሰዎች በሙሉ ወደ መንፈሳዊ የግጦሽ መስኩ እየሰበሰበ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የግንቦት 8, 1948፣ የየካቲት 22, 1952፣ የሰኔ 22, 1954ና የመስከረም 8, 1996 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት እትሞች ተመልከት።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንዲት የናቫሆ እረኛ ምሥራቹን ስትሰማ