በዛሬው ጊዜም በሥነ ምግባር የታነጹ ልጆች ማሳደግ ይቻላልን?
“የምንኖረው የተለያየ ዓይነት ባሕል ባለው፣ ወጥ የሆነ የሥነ ምግባር ደንብ በሌለው በጣም በተወሳሰበ ኅብረተሰብ ውስጥ ነው” በማለት በኦቶዋ ካናዳ የቫንየር የቤተሰብ ተቋም አባል የሆኑት ሮበርት ግሎሶፕ ተናግረዋል። ይህስ ምን ውጤት አስከትሏል? ዘ ቶሮንቶ ስታር በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “በአሥራዎቹ እድሜ የሚያረግዙ፣ ዓመፀኛና በአሥራዎቹ እድሜ ውስጥ ራሳቸውን የሚገድሉ ወጣቶች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል።”
ችግሩ በሰሜን አሜሪካ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በሮድ አይላንድ ዩ ኤስ ኤ በሚገኘው ብራውን ዩኒቨርሲቲ ሴንተር ፎር ሂውማን ዴቨሎፕመንት የተባለው ማዕከል ዲሬክተር የሆኑት ቢል ዴመን በብሪታንያና በሌሎች የአውሮፓ አገሮች እንዲሁም በአውስትራሊያ፣ በእስራኤልና በጃፓን በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት አካሂደዋል። ቤተ ክርስቲያኖች፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ተቋማት ለወጣቶች ይሰጡ የነበረው የምክር አገልግሎት እየቀነሰ መሄዱን ሳይጠቁሙ አላለፉም። ባሕላችን “ልጆች ሊያጎለብቱት የሚገባውን ጠባይና ብቃት ዘንግቷል” የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። “ልጆችን መቅጣት ለጤንነታቸውና ለደህንነታቸው ጎጂ ነው” ብለው የሚያስተምሩትን የወላጅ አማካሪዎች በመጥቀስ ይህ ሐሳብ “ልጆች ስድና ዓመፀኛ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው” በማለት ዴመን ተናግረዋል።
በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የሚያስፈልጋቸው ምንድን ነው? አእምሮንና ልብን የሚያቃና የማያቋርጥ በፍቅር የሚሰጥ ስልጠና ያስፈልጋቸዋል። የተለያዩ ወጣቶች የተለያየ ዓይነት ተግሣጽ ያስፈልጋቸዋል። በፍቅር ተነሳስቶ የሚሰጥ ተግሣጽ አብዛኛውን ጊዜ ምክንያታዊ ሐሳቦችን በማቅረብ በአንደበት ብቻ ሊገለጽ ይችላል። ለዚህም ነው በምሳሌ 8:33 ላይ “ተግሣጽን ስማ” [NW] ተብሎ የተነገረን። አንዳንዶች ግን ‘በቃል ብቻ የማይገሠጹ’ ናቸው። እንደዚህ ዓይነቶቹ ልጆች ላጠፉት ጥፋት ተገቢውን ቅጣት መቀበል ያስፈልጋቸው ይሆናል። (ምሳሌ 17:10፤ 23:13, 14፤ 29:19) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ምክር ሲሰጥ ልጅን ሊያቆስልና አካለ ስንኩል ሊያደርግ በሚችል ሁኔታ በንዴት ገንፍሎ መግረፍን ወይም ክፉኛ መደብደብን ማበረታታቱ አይደለም። (ምሳሌ 16:32) ከዚህ ይልቅ ልጁ ለምን እንደተቀጣና ይህም ለእርሱ ጥቅም እንደሆነ እንዲገባው ያስፈልጋል።—ከዕብራውያን 12:6, 11 ጋር አወዳድር።
እንዲህ ዓይነቱ ጠቃሚና ትክክለኛ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር የቤተሰብ ደስታ የሚገኝበት ምስጢር በተባለው መጽሐፍ ላይ ጎላ ብሎ ተገልጿል።