የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 10/15 ገጽ 24-27
  • በታሂቲ ስለ ገነት የሚነገር ምሥራች

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በታሂቲ ስለ ገነት የሚነገር ምሥራች
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • አነስተኛ ጅምር
  • ሥራው ወደፊት ገፋ
  • በታሂቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቋመ
  • አሁንም ብዙ የሚሠራ አለ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 10/15 ገጽ 24-27

በታሂቲ ስለ ገነት የሚነገር ምሥራች

ታሂቲ! ስሙ እንግዳ የሆነ መስህብ ያለው ይመስላል። እንደ ፖል ጎገ፣ ሮበርት ሉዊስ ስቲቨንሰንና ኸርማን ሜልቪል የመሳሰሉ አርቲስቶችና ደራሲያን የሞቃታማ የደቡብ ባህር ደሴቶች ውበትና የተረጋጋ ሁኔታ የሚያሳዩና የብዙ ሰዎችን ትኩረት የሳቡ የሥዕልና የድርሰት ሥራዎቻቸው ደሴቱን ታዋቂ እንዲሆን አስችለውታል።

ታሂቲ በደቡብ ፓስፊክ በፍሬንች ፖሊኔዥያ ከሚገኙ ከ120 በላይ ከሚሆኑ ደሴቶች መካከል ትልቁ ነው። አብዛኞቹ ሰዎች ይህን በደቡብ ባህር የሚገኝ ደሴት ገነት አድርገው የሚቆጥሩት ቢሆንም በታሂቲ የሚኖሩ ሰዎች በቅርቡ ስለሚመጣ ሌላ ገነት መስማት ያስፈልጋቸዋል። (ሉቃስ 23:​43) በአሁኑ ጊዜ በታሂቲ የሚገኙ 1,918 የይሖዋ ምሥክሮች 220,000 ለሚያክሉ ነዋሪዎች የአምላክ መንግሥት በቅርቡ እውነተኛ ገነታዊ ሁኔታዎችን በታሂቲ ብቻ ሳይሆን በመላው ምድር ላይ እንደሚያመጣ በመናገር ላይ ናቸው።​—⁠ማቴዎስ 24:​14፤ ራእይ 21:​3, 4

ለብዙ ዓመታት በታሂቲ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ በበላይነት ይቆጣጠር የነበረው 3,500 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የፊጂ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ነበር። በመካከሉ የነበረው ሰፊ ርቀት ነገሮችን አስቸጋሪ፣ ዕድገቱንም አዝጋሚ አድርጎት ነበር። በመሆኑም በሚያዝያ 1, 1975 በታሂቲ የቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቋመ፤ ይህ ደግሞ በዚያ ክልል የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነበረ። ይህን ለውጥ ያስከተለው ነገር ምንድን ነው? እንዲሁም በታሂቲ የሚከናወነው የስብከት ሥራ የጀመረው እንዴት ነው?

አነስተኛ ጅምር

በታሂቲ የመንግሥቱ ምሥራች በመጀመሪያ የተሰበከው በ1930ዎቹ ሲሆን ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አክብሮት የነበራቸው ብዙዎቹ የደሴቱ ነዋሪዎች አድናቆት የተሞላበት ምላሽ ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ በመንግሥት እገዳና በሌሎች ገደቦች ምክንያት እስከ 1950ዎቹ መጨረሻ ድረስ በደሴቱ ምንም ምሥክር አልነበረም። በዚያን ጊዜ አንዬስ ሼንክ የተባለች በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር የታሂቲ ተወላጅ ከባሏና ከወንድ ልጅዋ ጋር ወደ ታሂቲ ለመመለስ ወሰነች። ነገሩ እንዴት ሆኖ እንደተፈጸመ እንዲህ ስትል ተናግራለች።

“በ1957 በሎስ አንጀለስ ተደርጎ በነበረው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወንድም ኖር [በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው] በታሂቲ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚፈለጉ ተናግሮ ነበር። በዚያን ጊዜ ከተጠመቅሁ አንድ ዓመት ሆኖኝ የነበረ ሲሆን ጥሪውን ስሰማ ‘ታዲያ ወደ ታሂቲ ለምን አንሄድም’ ስል በድንገት ጮክ ብዬ ተናገርኩ። የቅርብ ወዳጆቻችን የነበሩት የኒልስና የካራኖ ቤተሰቦች የተናገርኩትን ሰምተው ነበር። ከእኛ ጋር አብረው ለመምጣት እንደሚፈልጉ ቢገልጹልንም እኛ ግን በቂ ገንዘብ አልነበረንም። ባለቤቴ ለረዥም ጊዜ ታምሞ የነበረ ሲሆን ወንዱ ልጄ ደግሞ በጣም ትንሽ ነበር። ስለዚህ ተመልሶ መሄዱ አስቸጋሪ ነበር። በጎረቤት ጉባኤዎች ይገኙ የነበሩ ምሥክሮች ግባችንን ሲሰሙ የገንዘብና የቤት ቁሳቁሶች እርዳታ አደረጉልን። ከዚያም በግንቦት 1958 ወደ ታሂቲ ስንሄድ ከሌሎች ቁሳቁሶች በተጨማሪ የያዝናቸው አንሶላዎች 36 ደርሰው ነበር!

“ከደሴቱ ከተለየሁ ከ20 ዓመታት በኋላ ታሂቲ ስንደርስ በጣም ግር ብሎኝ ነበር። መስበክ ብንጀምርም ክርስቲያናዊ ሥራችን በእገዳ ስር ስለነበር ጠንቃቆች መሆን ነበረብን። መጽሔቶቻችንን መደበቅ ስለነበረብን በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ እንጠቀም ነበር። በመጀመሪያ ላይ የምንመሠክረው የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ኮንትራት ላላቸው ሰዎች ብቻ ነበር።

“ክላይድ ኒልና ዴቪድ ካራኖ ከነቤተሰቦቻቸው በ1958 በኒው ዮርክ ከተማ ከተደረገው ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ በኋላ ወደ እኛ መጡ። አንድ ላይ እንሰብክና በወንድሞች ቤት የሚሰጡ ንግግሮችን መጥተው እንዲያዳምጡ ሰዎችን እንጋብዝ ነበር። ቀስ በቀስ ነገሮች በመደራጀታቸው 15 ሰዎች የሚገኙበት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ተጀመረ። ከሦስት ወራት በኋላ የኒልና የካራኖ ቤተሰቦች የጉብኝት ቪዛቸው ጊዜው ስላለቀ አገሩን ለቅቀው መሄድ ነበረባቸው። ስለዚህ ወንድሞች ከመሄዳቸው በፊት ፍላጎት ያላቸውንና ብቁ የሆኑትን እንዲጠመቁ አደረጉ። እኔ የመጀመሪያውን የጥምቀት ንግግር የማስተርጎም መብት ለማግኘት ችዬ ነበር። በዚህ ጊዜ ስምንት የደሴቱ ተወላጆች ራሳቸውን ለይሖዋ በመወሰን ተጠመቁ። ከዚያ በኋላ የኒልና የካራኖ ቤተሰቦች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለሱ።

“የስብከቱ ሥራ ቀጠለ። በትንንሽ ቡድኖች በመደራጀት የምሽት አገልግሎት እናከናውን ነበር። ብዙውን ጊዜ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር የምናደርገው ውይይት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ይዘልቅ ነበር። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የፕሮቴስታንት አገልጋዮች በውይይቱ ላይ ይገኙ ነበር። በ1959 የመጀመሪያው ጉባኤ ተመሠረተ። ከዚያም በ1960 መንግሥት ለይሖዋ ምሥክሮች ማኅበር በይፋ እውቅና በመስጠቱ በጣም ተደሰትን። እነዚያ የቀድሞዎቹ ዓመታት በደስታና ከፍተኛ በሆኑ መንፈሳዊ እድገቶች የተሞሉ ነበሩ። ይሖዋ የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ለመሄድ ያደረግነውን ውሳኔ በእርግጥ ባርኮታል።” እህት ሼንክ አሁን 87 ዓመቷ ሲሆን ባለችበት ጉባኤ ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ትገኛለች።

ሥራው ወደፊት ገፋ

በ1969 ዣክና ፖሌት ኢኖዲ የተባሉ ሁለት ፈረንሳውያን ምሥክሮች በታሂቲ ልዩ አቅኚዎች ሆነው እንዲሠሩ ተመደቡ። ዣክ እንዲህ በማለት ያስታውሳል:- “ታሂቲ ስንደርስ 124 አስፋፊዎች፣ በፓፒኤቲ የሚገኝ አንድ ጉባኤና ባህረ ገብ መሬት በሆነው በቬራኦ ደግሞ ሁለት ልዩ አቅኚዎች ብቻ ነበሩ።” ባህረ ገብ የሆነው መሬት ከታሂቲ ጋር የሚገናኘው በአንድ ልሳነ ምድር አማካኝነት ነው። “ሰላም በምድር ላይ” የሚል ጭብጥ የነበረው ዓለም አቀፍ ስብሰባ የሚካሄድበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። ዣክ ቀጥሎ ሲናገር “የአውራጃ ስብሰባ ሳደራጅ ይህ የመጀመሪያዬ ነበር” ብሏል። “ከውጪ ለሚመጡ እንግዶች በእንግሊዝኛ የሚሰጥ ፕሮግራም፣ የመንግሥቱን መዝሙሮች ለመዘመር እንድንችል አንድ የሙዚቃ ጓድ ማዘጋጀትና ሁለት ድራማዎችን ማጥናት ነበረብን። ይህ ሁሉ ሥራ የተከናወነው በ126 አስፋፊዎች ብቻ ነበር። አብዛኛውን ነገር ያከናወነው ይሖዋ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።” በስብሰባው ላይ 488 ተሰብሳቢዎች በመገኘታቸው የደሴቱ ተወላጆች ፈንድቀው ነበር። ብዙዎቹ ወንድሞች ከሌሎች አገሮች ከመጡ መሰል ምሥክሮች ጋር ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነበር።

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዣክ ኢኖዲ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል ተመደበ። የተለያዩ ደሴቶችን በሚጎበኝበት ጊዜ ብዙ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንዳሉና ኮትኩተው ሊያሳድጓቸው የሚችሉ አስፋፊዎች ግን ጥቂት መሆናቸውን ተገነዘበ። ዣክ እንዲህ ይላል:- “የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ እነዚህ ደሴቶች በመሄድ እንዲያገለግሉ ብዙ ቤተሰቦችን ያበረታታሁት ለዚህ ነበር። ስለዚህ ምሥራቹ ቀስ በቀስ ወደ እነዚህ ተጎራባች ደሴቶች ተሰራጨ።” ወንድም ኢኖዲ ከ1969 እስከ 1974 ድረስ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ያገለገለ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በታሂቲ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ነው።

ለወንድም ኢኖዲ ማበረታቻ ምላሽ ከሰጡት ወንድሞች መካከል በ1958 ከተጠመቁት ስምንት ሰዎች አንዱ የነበረው ኦጉስት ቴማናሄ ይገኝበታል። ስለተከናወነው ነገር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል። “በ1972 የወረዳ የበላይ ተመልካች የነበረው ዣክ ኢኖዲ በሶሳይቲ ደሴቶች ውስጥ ከሚገኙት የሊዋርድ ደሴቶች መካከል አንዱ ወደ ሆነው ወደ ዋሂኔ ሄደን እንድናገለግል ማበረታቻ ሰጠን። በጉባኤ ውስጥ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ክፍል ሌላ አቅርቤ ስለማላውቅ ይህን ኃላፊነት ለመሸከም ብቁ አይደለሁም በማለት አመንትቼ ነበር። ይሁን እንጂ ወንድም ኢኖዲ ‘አይዞህ፣ ይህን ያህል ከባድ አይደለም!’ እያለ ዘወትር ያበረታታኝ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለመሄድ ወሰንን። ስለዚህ በ1973 ያለንን ነገር ሁሉ ሸጥንና ከሦስት ትናንሽ ልጆቻችን ጋር ወደ ዋሂኔ ተጓዝን።

“እዚያ ስንደርስ ሁሉንም ነገር ማለትም የመጠበቂያ ግንብ ጥናት፣ የቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤትና ሌሎች ነገሮችንም መጀመር እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ይህን ማድረግ ቀላል አልነበረም፤ ቢሆንም የይሖዋን ጥበቃና እርዳታ አግኝተናል። በተለያዩ ወቅቶች የምንኖርበት ቤት እንድናገኝ ረድቶናል። አንድ የተቃዋሚዎች ቡድን ምሥክሮቹን ከደሴቱ ለማባረር በሞከረ ጊዜም በአካባቢው የሚገኝ አንድ የፖለቲካ ሰው ከጎናችን በመቆም ተከላክሎልናል። በእርግጥ ይሖዋ በእነዚያ ጊዜያት ሁሉ ጠብቆናል።” አሁን በዋሂኔ ሁለት ጉባኤዎች ይገኛሉ፤ አንዱ 23 አስፋፊዎች ያሉት የፈረንሳይኛ ጉባኤ ሲሆን ሌላው ደግሞ 55 አስፋፊዎች ያሉት በታሂቲ ቋንቋ የሚካሄድ ጉባኤ ነው።

በ1969 ኤለን ማፑ በባህረ ገቡ መሬት በልዩ አቅኚነት እንድታገለግል ተመደበች። ኤለን እንዲህ ትላለች:- “በባህረ ገቡ መሬት ፍላጎት ያሳዩ በርካታ ሰዎች ስለነበሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን አስጀመርኩ።” ብዙም ሳይቆይ በቬራኦ አንድ ትንሽ ጉባኤ የተቋቋመ ቢሆንም ሽማግሌዎች ግን ያስፈልጉ ነበር። በወቅቱ 35 ኪሎ ሜትር ርቆ በፓፓራ የሚኖረው ኮልሶን ዲን እርዳታ ለማበርከት ችሎ ነበር። ወንድም ዲን በዚያን ጊዜ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በቬራኦ ለማገልገል በደንብ መደራጀት ያስፈልገን ነበር። እኔ እሰራ የነበረው ከቬራኦ 70 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው በደሴቱ ሌላኛው ክፍል በፋአአ ነበር። ከሥራ በኋላ በፍጥነት ወደ ቤቴ ተመልሼ ቤተሰቦቼን በመያዝ ወደ ቬራኦ መሄድ ነበረብኝ። ከጊዜ በኋላ በሥራዬ ምክንያት ወደ ፋአአ ለመዛወር ተገደድን። አሁንም በቬራኦ የሚገኘውን ጉባኤ መርዳታችንን መቀጠል እንችል ይሆን? በዚያ የሚገኙትን ወንድሞች ለመርዳት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረን እንደ በፊቱ እየተመላለስን ለመርዳት ወሰንን። ስብሰባ በምናደርግባቸው ምሽቶች መኪና የሌላቸውን ወንድሞች ወደ ቤታቸው ለመውሰድ ብዙ ጊዜ መመላለስ ስለሚኖርብን አብዛኛውን ጊዜ ወደ ቤታችን የምንመለሰው እኩለ ሌሊት ከሆነ በኋላ ነበር። በዚህ ሁኔታ አምስት ዓመታት አሳልፈናል። በአሁኑ ጊዜ በዚህ የደሴቱ ክፍል አራት ጉባኤዎች መኖራቸውን ስናይ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል፤ እንዲሁም በዚያን ጊዜ ያሳለፍናቸው አስደሳች ትዝታዎች አሉን።”

በታሂቲ ቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቋመ

በ1974 በታሂቲ ያሉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ወደ 199 አድጎ ነበር። በቀጣዩ ዓመት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የወቅቱ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ኤን ኤች ኖርና ኤፍ ደብሊው ፍራንዝ፣ ፍሬንች ፖሊኔዥያን በጎበኙበት ጊዜ በዚያ የሚከናወነው የስብከት ሥራ 3,500 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የፊጂ ቅርንጫፍ ቢሮ አመራር ሥር ከሚካሄድ ይልቅ ከዚያው ከታሂቲ በሚሰጥ አመራር ቢካሄድ የተሻለ እንደሚሆን ተገነዘቡ። ስለዚህ በሚያዝያ 1, 1975 በታሂቲ የቅርንጫፍ ቢሮ የተቋቋመ ሲሆን የወረዳ የበላይ ተመልካች የነበረው አለን ዣሜ የቅርንጫፉ የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ።

ወንድም ዣሜ ከሁለት ዓመታት በፊት ይሖዋ ያፈሰሰውን ታላቅ በረከት ለመግለጽ ችሎ ነበር። “ከ1975 ጀምሮ ምዕራብ አውሮፓን የሚያክል ስፋት ባለው ክልላችን ውስጥ ለሚገኙት ለሁሉም ደሴቶችና አጎራባች ለሆኑት ትንንሽ ደሴቶች ምሥራቹን ለማድረስ ትልቅ ጥረት ተደርጓል። ውጤቱም እጅግ የሚያስደስት ነበር። በ1983 የአስፋፊዎች ቁጥር ወደ 538 አድጎ ነበር። በዚያው ዓመት በፔአ ለቅርንጫፍ ቢሮና ለቤቴል ቤት የሚሆን ሕንፃ ተሠራ። በአሁኑ ጊዜ በሶሳይቲ ደሴቶች በ30 ጉባኤዎች ውስጥ ተሰራጭተው የሚገኙ 1,900 አስፋፊዎችን ጨምሮ በኦስትራል ደሴቶች አንድ ጉባኤና አንድ በገለልተኛ ቦታ የሚገኝ ቡድን፣ በማርኬሳስ አንድ ጉባኤና ሁለት በገለልተኛ ቦታ የሚገኙ ቡድኖች እንዲሁም በቱአሞቱና በጋምቢየር ደሴቶች በርከት ያሉ ቡድኖች ይገኛሉ። ወደ ስብሰባዎች የሚመጡ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር ያለማቋረጥ በማደግ ላይ ስለሆነ ብዛት ያላቸው አዳዲስ የመንግሥት አዳራሾች በመገንባት ላይ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ሦስቱ በማርኬሳስ፣ ሰባቱ ደግሞ በታሂቲ ይገኛሉ። ባለፉት 20 ዓመታት በታሂቲ የሚገኘውን መስክ ለማልማት ያደረግነውን ጥረት ይሖዋ በእጅጉ ባርኮታል።”

አሁንም ብዙ የሚሠራ አለ

በፍሬንች ፖሊኔዥያ ከፍተኛ የሆነ እድገት እንደሚኖር ለመመልከት ይቻላል። በመጋቢት 23, 1997 በመላው ፍሬንች ፖሊኔዥያ 5,376 የሚሆኑ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ሞት መታሰቢያን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለማክበር ተሰብስበው ነበር። የእነዚህን ሰዎች መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን በርከት ባሉ የአካባቢው ቋንቋዎች ተዘጋጅተዋል። ከታሂቲ ቋንቋ በተጨማሪ አጎራባች በሆኑት የቱአሞቱ ትንንሽ ደሴቶች በሚነገረው በፖሞቱ ቋንቋ እንዲሁም በሰሜንና በደቡብ ማርኬዚያን ቋንቋዎች ጽሑፎች ተዘጋጅተዋል።

በታሂቲ የሚገኙ የመንግሥቱ አስፋፊዎች የማያቋርጠው እድገትና አስደሳች የሆኑ ተሞክሮዎች የይሖዋን ፍቅርና ትዕግሥት ይበልጥ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ይሖዋ በደቡብ ባህር በሚገኙ ደሴቶች ውስጥ የሚኖሩትን ጨምሮ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:​4) በታሂቲና በሌሎች የፍሬንች ፖሊኔዥያ ደሴቶች ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች “ደሴቶች እኔን በመተማመን ይጠባበቃሉ፣ በክንዴም ይታመናሉ” በሚለው የይሖዋ ተስፋ ላይ ሙሉ እምነት አላቸው።​—⁠ኢሳይያስ 51:​5

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የታሂቲ ቅርንጫፍ በፍሬንች ፖሊኔዥያ የሚካሄደውን ሥራ ይከታተላል

አውስትራሊያ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከግራ ወደ ቀኝ:- አለን ዣሜ፣ ማሪ-አን ዣሜ፣ አንዬስ ሼንክ፣ ፖሌት ኢኖዲ እና ዣክ ኢኖዲ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የታሂቲ ቅርንጫፍ ቢሮ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ