ቅዱስ አገልግሎት የሚያስገኘው ታላቅ በረከት
ሃሪ ብሉር እንደተናገረው
ከዛሬ አንድ መቶ ዓመት ገደማ በፊት አያቴ አጥባቂ የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን አባል ነበር። ቄስ ባይሆንም እንኳ የተከበረ ሰባኪ ከመሆኑም በላይ በሸክላ ሥራ በምትታወቀው የእንግሊዟ ስቶክ ኦን ትሬንት ከተማ ለሚገኙ በርካታ ቤተ ክርስቲያኖች ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን የገንዘብ ችግር አጋጠመው። አባቴ አያቴን ለመርዳት ሲል አንድ ትንሽ ሱቅ ከፈተለት። የሱቁ የንግድ ፈቃድ ቢራ መሸጥም የሚያስችል ነበር፤ ሜቶዲስቶች ይህን ሲያውቁ አያቴን ወዲያው ከቤተ ክርስቲያናቸው አባልነት ሰረዙት።
አባቴ በጣም ስለተናደደ ከእንግዲህ የሃይማኖት ነገር በቃኝ ብሎ እስከ መጨረሻው እርግፍ አድርጎ ተወው። አባቴ ቀደም ሲል ፖሊስ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ግን መጠጥ ቤት ከፍቶ መተዳደር ጀመረ። ስለዚህ ያደግሁት በዚያ የመጠጥ ቤት ሽታና የሲጋራ ጭስ ውስጥ ነው። ሃይማኖት በሕይወቴ ውስጥ ምንም ቦታ አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ በተለያየ ዓይነት የዳማ ጨዋታ የተካንኩ ሆንኩ! ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የነበረኝ እውቀት በጣም አነስተኛ ቢሆንም ቀደም ሲል አያቴ ያሳደረብኝ ተጽዕኖ ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ አክብሮት እንዲኖረኝ አድርጓል።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተማርኩ
በ24 ዓመቴ በ1923 በምሥራቅ ወደሚገኘው ወደ ኖቲንግሃም ተዛወርኩ፤ ከዚያም ከሌስተር ደቡባዊ ምዕራብ 40 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በዌትስቶን መንደር ከምትኖረው ከሜሪ ጋር ለጋብቻ መጠናናት ጀመርኩ። አርተር ሬስት የተባለው አባቷ በአካባቢው በሚገኝ አንድ ቤተ ክርስቲያን ኦርጋን ይጫወት ነበር። በዚያን ጊዜ ግን ከፍተኛ ጉጉትና ፍላጎት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ (ቀደም ሲል የይሖዋ ምሥክሮች ይጠሩበት የነበረ ስም ነው) ነበር። አርተር ስላገኘው አዲስ እምነቱ ሁልጊዜ ይነግረኝ ነበር፤ እኔ ግን ይህን ያህል ፍላጎት አልነበረኝም። ይሁን እንጂ ሐምሌ 13, 1924 እሁድ ከሰዓት በኋላ በአካባቢያችን ወደሚገኘው የባብቲስት ቤተ ክርስቲያን አብሬው በመሄድ በአንድ ታዋቂ የባፕቲስት እምነት ተከታይና የምክር ቤት አባል የቀረበ ንግግር መስማቴ ፍላጎቴን ቀሰቀሰው። “የፓስተር ራስል ትምህርቶች በቅዱሳን ጽሑፎች ብርሃን ሲመረመሩ” በሚል ርዕስ ያቀረበው ንግግር የማወቅ ፍላጎቴን ቀሰቀሰው። በዚያን ጊዜ የያዝኳቸው ማስታወሻዎች አሁንም አሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በእምነታቸው ላይ ስለ ተሰነዘረው ነቀፌታ መልስ ለመስጠት ቢጠይቁም ባፕቲስቶቹ ፈቃደኛ አልሆኑም። በዚህ ስለተበሳጨሁ ይህን የመሰለውን ስብሰባ ለማካሄድ የሚያስችል ሌላ አማራጭ ቦታ ለመፈለግ ተነሳሁ። የተሻለ ሆኖ ያገኘነው አንድ መጋዘን ነበር። ጠርገን፣ የሸረሪት ድሮቹን አንስተን፣ የእህል መውቂያ ማሽኖቹን ወደ አንድ ጥግ በማድረግ ሁሉን ነገር አዘጋጀን። ሰባ ወንበሮችን አሰባሰብን፤ የጥሪ ወረቀቶችንም አሳተምን።
ፍራንክ ፍሪር ንግግሩን ለመስጠት ከሌስተር ሲመጣ ሁሉም መቀመጫዎች ከመሙላታቸውም በላይ ሌሎች 70 ሰዎች ቆመው ነበር! ፍራንክ ከቅዱሳን ጽሑፎች ያቀርብ የነበረው ግልጽ የሆነ ምክንያታዊ ማብራሪያ በስብሰባው ላይ እንደተገኙት እንደ ብዙዎቹ ሌሎች ሰዎች ሁሉ ለእኔም አሳማኝ ነበር። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሌስተር አቅራቢያ በብሌቢ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጉባኤ ፈጣን እድገት አደረገ። በተጨማሪም የእኔንም ሆነ የሜሪን የሕይወት አቅጣጫ የቀየረ ወሳኝ ጊዜ ነበረ። በ1925 ሁለታችንም ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ከተጠመቅን በኋላ ተጋባን።
መንፈሳዊ በረከቶች
በቀጣዩ ዓመት የብሌቢ ጉባኤ የአገልግሎት ዲሬክተር ሆኜ ተሾምኩ። እኔና ሚስቴ የኮልፖልተሮችን ፈለግ በመከተል የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ለመሆን ብንፈልግም የሜሪ ጤንነት ግን ይህን የመሰለውን ብርታት የሚጠይቅ ሥራ ለማከናወን የሚያስችለን እንዳልሆነ ተገነዘብን። ሜሪ በ1987 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ በየጊዜው በጤና መታወክ ብትቸገርም ጥሩ የትዳር ጓደኛና መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በመስጠትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በማስጀመር የተዋጣላት አገልጋይ ነበረች። አብዛኞቹን ምሽቶች የምናሳልፈው በስብሰባዎች ላይ በመገኘት አሊያም በአካባቢያችን ለሚገኙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመናገር ነበር።
ሙያዬ ምህንድስና ሲሆን በአንድ የእንጨት መሰንጠቂያ ማሽን ማምረቻ ድርጅት ውስጥ እሠራ ነበር። ሥራዬ በብሪታንያ እንዲሁም በፈረንሳይ ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት እንድጓዝ ያደርገኝ ስለነበር በአብዛኛው ሜሪ አብራኝ ትጓዝ ነበር። እነዚህ ጉዞዎች ሰፊ ምሥክርነት ለመስጠት አስችለውናል።
ለእድገት መሠረት መጣል
በ1925 በብሌቢ ለምናደርጋቸው ስብሰባዎች የሚያገለግል አንድ ግሩም ቤት ሠራን። ይህን ቤት መሥራታችን እዚያ እየተገናኘን ውጤታማ ምሥክርነት መስጠት የምንችልበትን ዝግጅት ለማድረግ ረድቶናል። ዘወትር እሁድ ጠዋት አውቶቡስ እንከራይና ተበታትነው ወደሚገኙ መንደሮችና ትንንሽ ከተሞች እንሄዳለን። አስፋፊዎች በተለያዩ ቦታዎች እየወረዱ ሲሰብኩ ከቆዩ በኋላ አውቶቡሱ እንደገና እየሰበሰባቸው ይመለስ ነበር። ሞቃት በሆኑት የበጋ ወራት በቅርብ የወጣውን የመጠበቂያ ግንብ እትም በመጠቀም እሁድ አመሻሹ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እናደርግ ነበር። ከዚያ በኋላ በሁለት ሰዓት በሌስተር ገላጣ የገበያ ስፍራ ለሚደረገው የሕዝብ ንግግር እንሰበሰባለን። አንድ ምሽት 200 ሰዎች የተሰጠውን ንግግር አዳመጡ። ይህ እንቅስቃሴ ዛሬ በሌስተርና በአካባቢዋ ለሚገኙ በርካታ ጉባኤዎች መቋቋም መሠረት የጣለ ነበር።
በ1926 በለንደኑ የአሌክሳንድራ ቤተ መንግሥትና በሮያል አልበርት አዳራሽ በዓይነቱ ልዩ የሆነ የአውራጃ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ዲሊቨረንስ የተባለ መጽሐፍ መውጣቱን አስታወቀ። “ለዓለም ገዥዎች የተሰጠ ምሥክርነት” የሚለው ውሳኔና ወንድም ራዘርፎርድ “የዓለም ኃያላን የሚናወጡት ለምንድን ነው? መፍትሔውስ ምንድን ነው?” በሚል ርዕስ የሰጠው ኃይለኛ የሕዝብ ንግግር ሙሉ ቃል በሚቀጥለው ቀን በአንድ እውቅ ጋዜጣ ላይ ታትሞ ወጥቶ ነበር። የቀረበውን ንግግር ከ10,000 የሚበልጡ ሰዎች የሰሙት ሲሆን ከዚያ ቀጥሎ 50,000,000 የሚያክሉ የውሳኔው ቅጂዎች በመላው ዓለም ተሰራጭተዋል። ይህ የአውራጃ ስብሰባ በብሪታንያ የሚካሄደውን የምሥክርነት ሥራ በማፋጠን ረገድ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል።
በጦርነት ጊዜ የተደረገ ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ
በመስከረም 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ። በ1941 ጦርነቱ ክፉኛ ተባብሶ ነበር። የጀርመን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ቀን ከሌት ቦምብ ይጥሉ ስለነበር በመላው አገሪቱ መብራቶች እንዳይበሩ ተከልክሎ ነበር። ከፍተኛ የምግብ እጥረት የነበረ ሲሆን ያለውም ምግብ የሚከፋፈለው በትንሽ በትንሹ ነበር። ባቡርን ጨምሮ የመጓጓዣ አገልግሎት በጣም የተወሰነ ነበር። ፈጽሞ መወጣት የማይቻል የሚመስሉ እነዚህ መሰናክሎች ቢኖሩም ከመስከረም 3-7, 1941 የአምስት ቀን አገር አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ አደረግን።
ሌስተር የእንግሊዝ እምብርት በመሆኗ የሌስተሩ ደ ሞንትፎርት አዳራሽ የአውራጃ ስብሰባውን ለማካሄድ ተመረጠ። በሣንቃ ማምረቻ ድርጅት ውስጥ እሠራ ስለነበር የማስታወቂያ ምልክቶችን በማዘጋጀት እርዳታ ለማበርከት ችያለሁ። በተጨማሪም በአውራጃ ስብሰባው ላይ ለመካፈል ለሚመጡት ሰዎች የመጓጓዣ አገልግሎት እንዲያገኙ ዝግጅቶችን አድርጌያለሁ። ትኬቶችን ቀደም ብለን በመግዛትና ከመደበኛው ዋጋ በላይ በመክፈል የሌስተር ባቡሮች እሁድ እንኳ ሳይቀር እንዲሠሩ አድርገናል።
መጓጓዣ እንደ ልብ ስለማይገኝ ይመጣሉ ብለን የጠበቅናቸው ምሥክሮች ብዛት 3,000 ነበር። ከ10,000 በላይ የሚሆኑ ልዑካን ሊመጡ ማቀዳቸውን ስንሰማ የተሰማንን ስሜት ልትገምቱ ትችላላችሁ! ነገር ግን የት መቆየት ይችሉ ይሆን? የሌስተር ነዋሪዎች በርካታ ወንድሞችን በደግነት በቤታቸው እንዲያርፉ አድርገው ነበር። በተጨማሪም አንድ ሺህ የሚሆኑ ወንድሞች ከአውራጃ ስብሰባው 3 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኝ አንድ ሜዳ ላይ በተተከሉ ድንኳኖች ውስጥ እንዲያርፉ ተደረገ። የጌዴዎን ካምፕ ብለን የጠራነው ይህ ቦታ የኅብረተሰቡን ትኩረት ስቦ ነበር።
ለአውራጃ ስብሰባው የተለያየ ክፍል ለሚያገለግሉና ለስብሰባ የመጣው በርካታ ሕዝብ የሚያርፍባቸው ሰፋፊና ነጫጭ ድንኳኖችን ተከራየን። እነዚህ ድንኳኖች በደማቁ የጨረቃ ብርሃን ምክንያት ለናዚ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ በታወቀ ጊዜ ወዲያውኑ አካባቢውን የሚመስል ቀለም ተቀቡ። ጦርነቱና በተለይም ደግሞ የምሥክሮቹ በጦርነቱ ተሳታፊ አለመሆን ኅብረተሰቡን አሳስቦት ነበር። በጊዜው በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው ገለልተኛ አቋማቸው ምክንያት ታስረው ነበር።—ኢሳይያስ 2:4፤ ዮሐንስ 17:16
ሰንደይ ፒክቶሪያል የተባለው ጋዜጣ በመስከረም 7, 1941 እትሙ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “አብዛኞቹ ወጣቶች የሆኑ 10,000 ሰዎች ለአንድ ሳምንት ያህል አንድ ላይ ተሰብስበው ስለ ጦርነት ሳይሆን ስለ ሃይማኖት ሲወያዩ ማየት የሚያስደንቅ ነገር ነበር። ስለ ጦርነቱ የሚያወሩት አንዳንዴ ብቻ ነበር።
“አባሎቻችሁ በጀርመን ውስጥ ይገኛሉ ወይ? ብዬ ምሥክሮቹን ጠይቄ ነበር። አዎን የሚል መልስ የሰጡኝ ሲሆን ሁሉም (6,000 የሚሆኑት) ለማለት ይቻላል በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ይገኛሉ።”
ጋዜጠኛው እንዲህ ሲል አክሏል:- “አዎን፣ ናዚዎች ጠላቶቻቸው ናቸው። ምሥክሮቹ ግን ትራክቶችን ከመሸጥና ንግግሮችን ከማዳመጥ በስተቀር ምንም ያደረጓቸው ነገር የለም።”
በአጠቃላይ ሲታይ ጋዜጦች አሉታዊ የሆኑ ዘገባዎችን ያቀርቡ የነበረ ሲሆን ተቃዋሚዎችም የአውራጃ ስብሰባችንን ለማደናቀፍ ያልተሳካ ሙከራ አድርገው ነበር። ይሁንና የለንደኑ ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ “ድርጅቱ የተረጋጋ፣ ዝግ ያለና ውጤታማ ነው” በማለት ሳይወድ በግድ ሐቁን አምኖ ተቀብሏል።
በከተማው የሲጋራ እጥረት እንዲከሰት ያደረጋችሁት እናንተ ናችሁ ተብለን ተከሰን ነበር። ይሁን እንጂ ዘ ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ እንዲህ በማለት ማብራሪያ ሰጥቶ ነበር:- “የሌስተር ነዋሪዎችም ሆኑ የሲጋራ ስርጭት ክፍሉ ምሥክሮቹ የሌስተርን ሲጋራ አጭሰው ጨርሰዋል ብለው ሊከሷቸው አይችሉም። እነሱ አያጨሱም።” በተጨማሪም በምሥክሮቹ የተነሳ የከተማው ነዋሪዎች የሚበሉት ምግብ አጥተዋል የሚል ክስ ቢቀርብባቸውም ምሥክሮቹ የራሳቸውን ምግብ ማምጣታቸው በመገለጹ ምክንያት ከክሱ ነፃ ሊሆኑ ችለዋል። እንዲያውም የአውራጃ ስብሰባው ሲያበቃ እያንዳንዳቸው 1.8 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ 150 ዳቦዎች ለሌስተር ሮያል ኢንፈርመሪ በእርዳታ ተሰጥቷል። ይህ እርዳታ የምግብ እጥረት ባየለበት በዚያን ወቅት ከፍተኛ መዋጮ ነበር።
የአውራጃ ስብሰባው በብሪታንያ ለሚገኙ 11,000 ለሚሆኑ ምሥክሮች ሰፊ የሆነ መንፈሳዊ ማነቃቂያ አቅርቧል። በስብሰባው ላይ 12,000 የሚሆኑ ሰዎች በመገኘታቸው ተደስተው ነበር! ልዑካኑ በሌስተር ታይቶ የማይታወቅ የመንገድ ላይ ምሥክርነት በመስጠት በደስታ ከመካፈላቸውም በላይ ከከተማው ርቀው ወደሚገኙ መንደሮች በመሄድ በሸክላ ማጫዎቻዎች የሚቀርቡ ንግግሮች አሰምተዋል።
የአውራጃ ስብሰባው ቁልፍ ንግግሮች የነበሩት ከአንድ ወር በፊት በሴይንት ሉዊስ ሚዙውሪ ዩ ኤስ ኤ በተደረገው የአምስት ቀን የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ በቀረቡበት ጊዜ በክር የተቀዱ ነበሩ። ወንድም ራዘርፎርድ “የንጉሡ ልጆች” በሚል ርዕስ የሰጠው ንግግር የክር ቅጂ በአውራጃ ስብሰባው ላይ ከተሰሙት አስደሳች ንግግሮች ዋነኛው ነበር። በሴይንት ሉዊስ የወጣው ልጆች (የእንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ቅጂዎች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የማይቻል ስለነበር ከጊዜ በኋላ መጽሐፉ ለየት ባለ ጥራዝ እዚያው በብሪታንያ ውስጥ ታትሟል። በአውራጃ ስብሰባው ላይ የተገኙ ልጆች በሙሉ የመጽሐፉ አንድ ቅጂ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
በሌስተር የተደረገ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዓመታዊ ስብሰባ
ከጦርነቱ በኋላ በብሪታንያ የነበረው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እድገት ከፍተኛ ነበር! በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በሌስተር የነበረው የጉባኤዎች ቁጥር አሥር ደርሶ ነበር። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበርን የ1983 ዓመታዊ ስብሰባ በሌስተር ለማድረግ መወሰኑ ተነገረን። የሌስተር ከተማ የበላይ ተመልካች እንደመሆኔ መጠን ዝግጅቶችን በማድረጉና የደ ሞንትፎርት አዳራሽን እንደገና በመከራየቱ ሥራ ወዲያውኑ ተጠመድኩ።
በብሩክሊን ከሚገኘው የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት አሥራ ሦስት የሚሆኑ የአስተዳደር አካል አባላት በስብሰባው ላይ ለመገኘት መጥተው ነበር። በዚህ ወቅት 3,671 የሚሆኑ ከዓለም ዙሪያ የመጡና አብዛኞቹ ለበርካታ ዓመታት ምሥክሮች የነበሩ ወንድሞች አዳራሹን ሞሉት። 1,500 የሚሆኑ ተጨማሪ ሰዎች በቅርብ ከሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ በመሆን ፕሮግራሙን ተከታትለዋል።
በዚህ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ሊቀ መንበር የነበረው በጦርነቱ ወቅት በሌስተር የአውራጃ ስብሰባ ስናደርግ በለንደን የሚገኘውን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ በበላይነት ይቆጣጠር የነበረው አልበርት ዲ ሽሮደር ነበር። በ1941 የተካሄደውን የአውራጃ ስብሰባ በማስታወስ ወንድም ሽሮደር “ዛሬ እዚህ ከተገኛችሁት መካከል በዚያ ስብሰባ ላይ የነበራችሁት ስንቶቻችሁ ናችሁ?” ብሎ ጠየቀ። ከተሰብሳቢዎቹ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እጆቻቸውን አነሱ። “በታማኝነት ከጸናችሁት ከእናንተ ጋር እንደገና ለመገናኘት መቻል እንዴት የሚያስደስት ነው!” ሲል በአድናቆት ተናገረ። በእርግጥም የማይረሳ ተሞክሮ ነበር።
በ98 ዓመት ዕድሜዬ በጉባኤያችን ውስጥ በጸሐፊነት እያገለገልሁ ሲሆን ምንም እንኳ ተቀምጬ ቢሆንም የሕዝብ ንግግር መስጠቴን ቀጥያለሁ። በ1987 ሜሪ ከሞተች በኋላ፣ እኔና ሜሪ ለብዙ ዓመታት እናውቃት ከነበረች ባሏ ከሞተባት ከቤቲና ጋር ተጋባን። በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ በጥሩ ሁኔታ ስለምትንከባከበኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ። በየጊዜው የሜሪ ጤንነት መታወክና አሁን ደግሞ የዕድሜዬ መግፋት ጫና ያስከተለብኝ ቢሆንም ቅዱስ አገልግሎት የበዛልን መሆናችን ምንጊዜም ታላቅ በረከት እንደሚያስገኝ ልገነዘብ ችያለሁ።—1 ቆሮንቶስ 15:58
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1920ዎቹ በአገልግሎት ለመካፈል በዝግጅት ላይ እያለን
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሌስተር የተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ገጽታዎች