በወርቅ ጉትቻ ማጌጥ
ከወርቅ የተሠራ ጌጥ ባለው ዋጋና ውበት ምክንያት ከፍ ያለ ግምት ይሰጠው የነበረው ከጥንት ዘመን ጀምሮ ነው። ዮሴፍ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ በተሾመበት ጊዜ ፈርዖን የወርቅ ሐብል ሰጥቶታል። (ዘፍጥረት 41:42) ርብቃም ባሁኑ ተመን 1,400 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ አፍንጫ ላይ የሚንጠለጠል አንድ የወርቅ ቀለበትና ሁለት የወርቅ አምባር ተሰጥቷት ነበር። (ዘፍጥረት 24:22) እነዚህን ውድ ስጦታዎች በአመስጋኝነት እንደተቀበሏቸውና ደስ ብሏቸው እንዳጌጡባቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍም ሆነ ርብቃ ካደረጉት ጌጥ እጅግ የበለጠ ዋጋ ስላለው ምሳሌያዊ ጌጥ ይናገራል። ምሳሌ 25:12 “የምትሰማን ጆሮ የሚዘልፍ ጠቢብ ሰው እንደ ወርቅ ጉትቻ እንደሚያንጸባርቅም ዕንቁ እንዲሁ ነው” በማለት ይገልጻል። አንድ ሰው የሚሰጠው ምክር ከራሱ ያመነጨውን ሐሳብ ሳይሆን በአምላክ ቃል ላይ ተመስርቶ ከሆነ በእርግጥ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ስጦታ ሰጥቷል ለማለት ይቻላል። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ምክር የሚመነጨው ከራሱ ከይሖዋ ስለሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይነግረናል:- “ልጄ ሆይ፣ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፣ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር። እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥጻልና፣ አባት የሚወደውን ልጁን እንደሚገሥጽ።” (ምሳሌ 3:11, 12) ምክር የተሰጠው ሰው ምክሩን በትሕትና ተቀብሎ በሥራ ላይ ሲያውለው በወርቅ ጉትቻ ራሱን ያስጌጠ ያህል ይቆጠራል። ጉዳዩ በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ጋር ተመሳሳይ ነው:- “ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ፣ በወርቅና በብር ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና።”—ምሳሌ 3:13, 14