“የአንድ ጣት መጽሐፍ ቅዱስ”
ጆሴቭ ሼረሽቭስኪ በበሽታ ምክንያት ሽባ ስለሆነ በአንድ ጣት ብቻ በመጠቀም በጽህፈት መሳሪያ ማሽን ይጽፍ ነበር። በዚህ ሁኔታ ስር ቢሆንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ቻይንኛ ለመተርጎም የነበረውን ዓላማ አሳክቷል። ይህ ቋንቋ ደግሞ ለመልመድ በጣም አስቸጋሪ ከሆኑት ቋንቋዎች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል።
ሼረሽቭስኪ በትውልድ አይሁዳዊ ቢሆንም ካደገ በኋላ የክርስትናን እምነት መርምሮ ተቀብሏል። በኋላም በቻይና ሚስዮናዊ በመሆን አገልግሏል። በዚያም ከ1866 ጀምሮ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን የመጀመሪያ ዓመታት ድረስ በብዙ የትርጉም ሥራዎች ተካፍሏል። ሼረሽቭስኪ አይሁዳዊ ስለነበር በእሱ ዘመን ከነበሩት ሊቃውንት በበለጠ ዕብራይስጥ ያውቅ ነበር። ስለሆነም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሙሉ የመተርጎም ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። ከዚህ አድካሚ ሥራው በኋላ ግን ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ከነማጣቀሻው በቻይንኛ ለማዘጋጀት ችሏል።
ጆሴፍ ሼረሽቭስኪ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ እንደመሆኑ መጠን የመጽሐፍ ቅዱስን ወደ ተራው ሕዝብ ቋንቋ መተርጎም አጥብቆ የሚደግፍ ሰው ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ሥራ ማከናወን ለእሱ ቀላል አልነበረም። በቻይንኛ ለተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ያበረከተው አስተዋጽኦ ልዩ ግምት የሚሰጠው ነው። ዘ ቡክ ኦቭ ኤ ታውዘንድ ታንግስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “መጽሐፍ ቅዱሱ ብዙ ነገሮችን ያካተተ ከመሆኑም በላይ የትርጉም ሥራውን በማዘጋጀት ረገድ የነበሩት ችግሮች እንዲህ የዋዛ አይደሉም።”
ሼረሽቭስኪ እጆቹ ሽባ ከሆኑም በኋላ እንኳ ሥራውን በበለጠ እያሻሻለ ሄዷል። እጆቹ እንደወትሮው ስለማይታዘዙለት በጽህፈት መሳሪያ ማሽን መጻፍ ትልቅ ጥረት የሚጠይቅበት ነበር። በመሆኑም የትርጉም ሥራውን የአንድ ጣት መጽሐፍ ቅዱስ በማለት ሰይሞታል። ሼረሽቭስኪ የአካል ጉዳተኛነቱ ሳይበግረው መጽሐፍ ቅዱስን ተርጎሞ ለማዘጋጀት 25 ዓመት ሙሉ በጽናት መቀጠል አስፈልጎታል። ሼረሽቭስኪ ተስፋ ሳይቆርጥ በመቀጠሉ የአምላክ ቃል ከሁሉም ቋንቋዎች ይበልጥ ብዙ ሕዝብ በሚጠቀምበት በቻይንኛ እንዲነበብ ለማስቻል የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሁለቱም ሥዕሎች:- Courtesy of American Bible Society Archives