ከከተማ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ጠፍ እስከሆነው ጮቄ ምድር ድረስ ወደ ሰዎች መሄድ
ዝናብና በረዶው፣ ቀበሮውና አንበሳው እንዲሁም አስጊ የሆነው አካባቢ አይበግራቸውም። በሚያስገርም ፍጥነት የተንጣለለውን ሜዳና ጭልጥ ያሉትን ሸለቆዎች አቋርጠው እንዲሁም ሞገደኛ ወንዞችን ተሻግረው ከ3,000 ኪሎ ሜትር ሽምጥ ግልቢያ በኋላ አስቸኳይ የሆኑ መልእክቶችን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ምዕራብ ጠረፍ ያደርሳሉ። እነዚህ እነማን ናቸው?
እነዚህ ደፋር የሆኑ የፖኒ ኤክስፕረስ ወጣት ጋላቢዎች ናቸው።a በእነዚህ ወጣቶች ውስጥ ይህን የመሰለ የቁርጠኝነት መንፈስ እንዲቀጣጠል ያደረገው ነገር ምንድን ነው? ምናልባት መልእክቱን ማድረስ ያለው ተፈታታኝ ሁኔታ፣ ሥራው እንደ ጀብዱ መታየቱና በመጨረሻ የሚያስገኘው እርካታ ሊሆን ይችላል። የሚያስገርመው እያንዳንዱ ጋላቢ ከኮርቻው ጋር በተሠራው ኮሮጆ ውስጥ ከሚያደርሰው መልእክት ጋር መጽሐፍ ቅዱስም ይዞ ይሄድ ነበር።
በካናዳ የሚገኙት ከ113,000 የሚበልጡ ለአምላክ ያደሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችም ከአንድ መቶ ዓመት ከሚበልጥ ጊዜ በኋላ ተመሳሳይ ቁርጠኝነት፣ ቅንዓትና ለሥራቸው ያላቸውን ፍቅር አንጸባርቀዋል። ለሥራ ያንቀሳቀሳቸው ነገር ምንድን ነው? ለአምላክና ለጎረቤቶቻቸው ያላቸው ፍቅር የመንግሥቱን መልእክት በጽሑፍም ሆነ በቃል እንዲያሠራጩ ያነሳሳቸዋል። ይህ ሕይወት ሰጪ መልእክት እነዚያ ፈረሰኛ መልእክተኞች ከሚያደርሱት ከማንኛውም ፈጣን መልእክት ይበልጥ አጣዳፊ ነው። አዎን፣ ይህ መልእክት ጋላቢዎቹ በኮሮጆዎቻቸው ይዘውት በሚጓዙት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሠፈረውና ክቡር የሆነው የአምላክ መንግሥት መልእክት ነው።—ምሳሌ 2:21, 22፤ ኢሳይያስ 2:2-4፤ 61:2፤ ማቴዎስ 22:37-39፤ 24:14
ለይሖዋና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር ለሥራ ያንቀሳቅሳቸዋል
የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ስለ አምላክ መንግሥት መወያየት ያስደስታቸዋል። በከተማ ውስጥ ባሉ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ውስጥ፣ ራቅ ብለው በሚገኙ የጮቄ ምድር መንደሮች (tundra communities)፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎች፣ በመንገድ ላይ እንዲሁም በሌሎች ሕዝብ በሚበዛባቸው ሥፍራዎችና በስልክ ከሰዎች ጋር ሲነጋገሩ ታገኛቸዋለህ። እንደዚህ በተለያዩ ዘዴዎች የሚጠቀሙት ለምንድን ነው?
ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችና የሕዝብ ብዛት በሰዎች አኗኗር ላይ ካመጡት ለውጥ የተነሣ ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት ይበልጥ አስቸጋሪ ሆኗል። አብዛኛውን ጊዜ ባልና ሚስት የቤተሰባቸውን መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶች ለማሟላት ሲሉ ሁለቱም ተቀጥረው ይሠራሉ። ብዙውን ጊዜም ይህን የሚያደርጉት መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸውን ችላ ብለው ነው። እንዲህ በመሰለው ውጥረትና ሩጫ በበዛበት ሁኔታ ውስጥ የሚያጽናና የተስፋ መልእክት ማግኘታቸው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መልእክት ለማድረስ ፈቃደኞች ናቸው። ማስተዋልና ደግነት በተላበሰ መንገድ ምሥራቹን ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ማራኪና አስደሳች አድርገው ለማቅረብ የሚያስችሏቸውን አጋጣሚዎች ይፈልጋሉ።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
በሌሎች ቋንቋዎች:- ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘ሄደው ሰዎችን ደቀ መዛሙርት’ እንዲያደርጉ ሲያዝዝ ይህን የተስፋ መልእክት ሁሉንም ዓይነት ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች ለማድረስ በራሳቸው አነሳሽነትና በቁርጠኝነት የመሥራቱን ጉዳይ ለእነርሱ ትቶላቸዋል። (ማቴዎስ 28:19) ካናዳ እንደ ብዙዎቹ አገሮች ሁሉ የተለያዩ ባሕሎችንና ቋንቋዎችን የምታስተናግድ አገር ስትሆን ብዙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችም አዳዲስ ቋንቋዎችን በመማር ራሳቸውን ከሁኔታው ጋር አስማምተዋል።
ለምሳሌ ያህል በኤድመንተን አልቤርታ የሚገኙና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉ አንድ ባልና ሚስት በከተማቸው ውስጥ ያሉትን በማንዳሪን ቻይንኛ ቋንቋ የሚጠቀሙ ሰዎችን የመርዳቱን አስፈላጊነት አስተዋሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ባልና ሚስት በመጀመሪያ ቋንቋውን መማር ነበረባቸው። ስለዚህ የማንዳሪን ቋንቋ ወደሚናገር አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሄዱ። እርሱ ቋንቋውን ሊያስተምራቸው እነርሱ ደግሞ በተራቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያስተምሩት ተስማማ። እንዴት ያለ ጥሩ አጋጣሚ ነበር! በ24 ወራት ውስጥ እነዚህ ለአምላክ ያደሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በማንደሪን ቋንቋ ለማስተማር ብቁ ሆኑ። አስተማሪያቸው የሆነው ተማሪያቸውም በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ለክርስቲያናዊ ጥምቀት ዝግጁ ሆነ።
በሌሎች ከተሞችም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በፍቅር ተነሣስተው የፖላንድን፣ የሩሲያን፣ የቬትናምንና የመሳሰሉትን ቋንቋዎች በመማራቸው ተመሳሳይ ተሞክሮዎች ተገኝተዋል።
በመንገድ ላይ:- ባለፈው መቶ ዘመን የነበሩት የፖኒ ኤክስፕረስ ጋላቢዎች ብቻቸውን ይጓዙ እንደነበር ሁሉ አንዳንድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችም በብሪታንያ ኮሎምቢያ መሃል ለመሃል ብቻቸውን ይጓዛሉ። አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በደን የተሸፈኑ ቦታዎችን አቆራርጠው ወደ እንጨት መሰንጠቂያ ቦታዎች የሚያመሩ ከባድ መኪናዎችን በማሽከርከር ነው። ይህም ከሌሎች የከባድ መኪና ሹፌሮች ጋር በራዲዮ መልእክት የማያቋርጥ ግንኙነት እያደረጉ ስለ መኪኖች ዝውውርና በመንገዱ ላይ ስላጋጠማቸው ችግር መወያየትን ይጠይቃል።
እነዚህ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ራዲዮዎቻቸውን ከዚህ በተለየ መንገድ መጠቀም የሚችሉበትን መንገድ ቀየሱ። ወቅታዊ ጉዳዮችን በማንሳት በራዲዮ ውይይት ይከፍታሉ። ከዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተስማሚ ጥቅስ ይጠቅሳሉ። አንዱ የከባድ መኪና ሾፌር መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙታን ተስፋ የሚናገረውን ነገር ሲሰማ ልቡ ተነካ። (ዮሐንስ 5:28, 29፤ ሥራ 24:15) በአውራ ጎዳና ላይ በተከሰተ አደጋ ምክንያት አንድ ሾፌር ጓደኛው በመሞቱ በጣም ተረብሾ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት ፈቃደኛ ሆኖ ዛሬ አብረውት ለሚሠሩና ለወዳጆቹ ምሥራቹን ሲያውጅ ይታያል። ከዚህም በላይ የሞተው ጓደኛው ሚስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመጀመሯ ተደስቷል። ሕይወት ሰጪ የሆነውን የእውነት መልእክት እንግዳ በሆነ መንገድ መናገር ያስገኘው እንዴት ያለ የሚክስ ውጤት ነው!
በአየር:- ቀናተኛ የሆኑት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ክቡር የሆነውን የእውነት መልእክት ለማድረስ በትንናሽ አውሮፕላኖች ‘ወደተለያዩ መንደሮች ገብተዋል።’ (ማቴዎስ 10:11, 12) ከጥቂት ጊዜ በፊት የምሥራቹን ለማወጅ ባላቸው ቅንዓት የተነሣሱ ወንድሞችና እህቶች በራሳቸው ወጭ በሁለት አውሮፕላኖች ሆነው በተንጣለለው የጮቄ ምድር ጠፍ መሬት ላይ ተበታትነው ወደሚገኙት ሰዎች በረሩ። አውሮፕላኖቹ እያንዳንዳቸው 3,000 ኪሎ ሜትር ያክል ርቀት ተጉዘው በ14 የተለያዩ ቦታዎች ያረፉ ሲሆን ወደ አርክቲክ ክልል ለመግባት የቀራቸው 250 ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር። እነዚህ የማይታክቱ አዋጅ ነጋሪዎች ለሰባት ሙሉ ቀናት ሥራቸውን በመቀጠል በጣም ተራርቀው የሚገኙ ሰዎችን ለማዳረስ ችለዋል።
ጥረታቸው የሚክስ ነበርን? የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚያመጣውን አዎንታዊ ውጤት እስቲ አስበው። ወደዚያ የተጓዙት አገልጋዮች ይሖዋ በቅርቡ ምድርን ገነት ለማድረግ ስላለው ዓላማ በመግለጽ የግድ አስፈላጊ የሆነውን የሰዎቹን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት ችለዋል። (ማቴዎስ 5:3 NW) መልእክቱን ተሸክመው ወደ ስፍራው የሄዱት ሰዎች ከተመለሱም በኋላ ቢሆን የአካባቢው ሰዎች ለረጅም ጊዜ ሊያነቧቸው የሚችሉ 542 መጽሐፍ ቅዱሶችንና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ መጻሕፍት እንዲሁም 3,000 መጽሔቶች አግኝተው ነበር።—ከሥራ 12:24 ጋር አወዳድር።
በስልክ:- በከተማዎች ውስጥ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግባቸው ሕንጻዎች ውስጥ የሚኖሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። ያም ሆኖ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በቅንዓትና በብልሃት ሥራቸውን መሥራታቸውን ቀጥለዋል። እነዚህ ሰዎች ወዳሉበት ሊሄዱ የሚችሉት እንዴት ነው? ሰዎችን ፊት ለፊት አግኝቶ ማነጋገሩ የሚመረጥ ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ በሕንጻው መግቢያ ላይ ያለውን መነጋገሪያ በጥሩ መንገድ መጠቀም ተችሏል። ይህን ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ደግሞ ስልክ በመደወል ሥራውን ለጣቶቻቸው ይተዉታል።
አንድ ቀን ጠዋት አንዲት በዕድሜ የገፋች ሴት ስልኳን አነሳች። አጭርና ትህትና የተሞላበት ሰላምታ ከቀረበላት በኋላ ሰዎች በጎዳናዎች ላይ በምሽት ያለ ስጋት መጓዝ የሚችሉበት ጊዜ ሊመጣ ይችላል ብላ ታስብ እንደሆነ ጥያቄ ቀረበላት። ወደፊት ብዙ ሰላም እንደሚኖር የሚያረጋግጡ ጥቅሶች ተነበቡላት። (መዝሙር 37:10, 11፤ ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) በአምላክ ተስፋዎች ላይ እምነት ሊኖረን የሚችለው ለምን እንደሆነ በቀጣዩ ሳምንት በተመሳሳይ ጊዜ በስልክ ለመወያየት ፈቃደኛ ሆነች። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲረዳ ከተዘጋጀ መጽሐፍ ላይ አንቀጾች እየተነበቡና ተገቢዎቹ ጥያቄዎች እየተጠየቁ አንድ ወር ለሚያክል ጊዜ በስልክ መጽሐፍ ቅዱስ ካጠኑ በኋላ ሴትዬዋ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በየሳምንቱ የተለያየ ርዕስ ይዘው መቅረባቸውን አደነቀች። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲረዳ ተብሎ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ለማስተዋወቅና የራሷን ቅጂ እንድትወስድ ለመጋበዝ ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነበር። ከዚያ በኋላ በአካል ለመገናኘት የሚያስችላቸውን ዝግጅት አደረጉ። በእርግጥም የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች ያላቸውን ፍቅር አሳይተዋል። ሰዎችም ይሖዋ ከእነዚህ ክርስቲያን ሰባኪዎች ጋር እንዳለ በመገንዘብ ምላሽ እየሰጡ ነው።—ከ1 ቆሮንቶስ 14:25 ጋር አወዳድር።
በጽሑፎች አማካኝነት:- ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች በሚበዙባት በኩቤክ ግዛት የሚገኙት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችም ሰዎች ወዳሉበት ቦታ ሁሉ እየሄዱ ነው። አንድ ተጓዥ አገልጋይ ያስተዋለውን ነገር እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ቤተ ክርስቲያን በምትሰነዝረው ከባድ ተቃውሞ ምክንያት ወንድሞች ለዓመታት ምንም ዕድገት እንደሌለ አድርገው ሲያስቡ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ወንድሞች ሳይታክቱ በመሥራታቸውና ወደ ሰዎች ደጋግመው እየሄዱ በመናገራቸው ጥቂቶች ብቻ የሚያነቡት እምብዛም የማይታወቅ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ወደ አብዛኞቹ ቤቶች ገብቷል።”
የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ ከኩቤክ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ሰዎች አዳዲስ ወንጌላውያን ሲሆኑ ማየት እጅግ የሚያስደስት ነው። የአንድ ዶክተር ሁኔታ ይህንን የሚያሳይ ነው። ሚስቱ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ስለሆነች ብዙ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋ ትነግረው ነበር። ንቁ የሆነ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ደም ሕይወትህን ሊያድን የሚችለው እንዴት ነው? የተባለው ብሮሹር በሚጠናበት የጉባኤ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ጋበዘው። ወደ ስብሳባው ከመምጣቱም በላይ ተሳትፎም አደረገ። የውይይቱ ትምህርት ሰጪነትና መንፈሳዊ ጥልቀት ልቡን ስለነካው በግሉ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማ። ዛሬ እርሱም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ሆኗል።
መጽሔቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ሰዎችን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በመሳብ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። አንድን ሰው ወደ እውነት የሚስበው የትኛው ርዕስ እንደሆነ አናውቅም። አንዲት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ለጎረቤቷ አንድ የንቁ! መጽሔት ታበረክትላታለች። ሴትየዋ መልእክቱን ለመስማት አትፈልግም ነበር፤ ይሁን እንጂ ስለ ነፍሳት ማወቅ ያስደስታታል። በኅዳር 22, 1992 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ ያለው “የቻጋስ በሽታ—የሞት ደጅ” በሚለው ርዕስ ሥር ያለው ስዕል ቀልቧን ሳበው። ባነበበችው ነገር ስለተደነቀች ተጨማሪ መጽሔቶችን ጠየቀች። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላት፤ በስድስት ወር ውስጥ ለሌሎች መመሥከር ጀመረች።
ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው ቦታዎች:- የካናዳ ሕግ እንደ አውሮፕላን ማረፊያ ባሉት ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎችም የመናገር ነፃነት ይሰጣል። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በሃሊፋክስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በጥበብ ወደ ተጓዦቹ ቀረብ ብለው ለጉዞ እስኪንቀሳቀሱ ድረስ ባለው ጊዜ ያነጋግሯቸዋል። ውይይቱን ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ለማዞር ወቅታዊ የሆኑ መሪ ጥያቄዎችን ይጠቀማሉ። በኪስ የሚያዝ መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች ጽሑፎችን ይዘው ስለሚሄዱ መንፈሳዊ ፍላጎት ያለው ሰው ሲያገኙ ምላሽ መስጠት ይችላሉ። በዚህ መንገድ የመንግሥቱን መልእክት ከሰሙት ሰዎች መካከል የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች፣ ሳይንቲስቶች፣ ጠበቆች፣ አብራሪዎች፣ ቄሶች፣ ፖሊሶች፣ የታክሲ ሾፌሮች፣ መሐንዲሶች፣ አስተማሪዎች፣ የጦር መኮንኖች እንዲሁም ከሌሎች አገሮች የመጡ የፖለቲካ ሰዎች ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች በልባቸው ተሸክመውት የሄዱት የእውነት ዘር ርቆ በሚገኘው መኖሪያቸው ፍሬ አፍርቷል።—ቆላስይስ 1:6
አንድ ቀን ማለዳ አንድ ሰው በአውሮፕላን ማረፊያው እያለ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ደረሰው። ከዚያም በለሆሳስ ድምፅ “ወይኔ፣ የይሖዋ ምሥክሮችን እንኳ ማለቴ አልነበረም!” አለ። እንዲህ ያለው ለምን ነበር? ሰውዬው አጥባቂ ሙስሊም ነው። በአውሮፕላን ማረፊያው ውስጥ በሚገኘው የጸሎት ቤት አምላክ ጥበቡን እንዲሰጠውና ማስተዋልንና እውነትን እንዲገልጥለት ሲማጸን ቆይቶ መምጣቱ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የጸሎቱ ቅጽበታዊ መልስ ሆነው መገኘታቸው አስገረመው።
በእርግጥም በካናዳ የሚገኙት ደፋር የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ምንም ነገር ቢሆን ክቡር የሆነውን የአምላክ መንግሥት መልእክት ከማቅረብ እንዲገታቸው አልፈቀዱም። የባዕድ አገር ቋንቋዎች፣ ወጣ ገባ የሆኑ አቧራማ መንገዶች፣ ርቀው የሚገኙ አካባቢዎችም ሆኑ በከተማ ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግባቸው መኖሪያ ሕንጻዎች ወደኋላ እንዲሉ አላደረጓቸውም። እውነትን ለሚፈልጉ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የአምላክን መንግሥት ለማዳረስ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። መሰል ሠራተኞች ከተሰለፉበት ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበራቸው ጋር አንድ ላይ ሆነው ኢየሱስ ‘ሂዱና ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ’ ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ያለ ምንም ራስ ወዳድነት ይፈጽማሉ።—ማቴዎስ 28:19
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ፖኒ ኤክስፕረስ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ1860 እስከ 1861 ድረስ ባሉት 18 ወራት ውስጥ ብቻ የተሠራበት የፖስታ አገልግሎት ነበር።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ውጤታማ የሆኑ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በስልክ ይጠቀማሉ
አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ:- “ጤና ይስጥልኝ። [ስማቸውን ጠቅሰው] እባላለሁ። ሰላም ሊገኝ ስለሚችልበት መንገድ በእናንተ ሕንጻ ላይ ካሉት ሰዎች ጋር እየተነጋገርኩ ነበር። በዓለም ዙሪያ ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ ይመጣል ብለው አስበው ያውቃሉ? [መልስ እንዲሰጥ ይፈቅዱለታል።] ጥናት እያካሄድኩ ወይም የሽያጭ ዓላማ ኖሮኝ እንዳልሆነ ልገልጽልዎት እፈልጋለሁ። ከዚህ ይልቅ ቅዱሳን ጽሑፎች አምላክ በእርግጥ ሰላም እንደሚያመጣ የሚናገሩትን ሐሳብ ለሰዎች እያካፈልኩ ነው።” ከዚያ በኋላ አጭር ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት በማድረግ ሊቀጥሉ ይችሉ ይሆናል።
ሌሎች ደግሞ እንዲህ ይላሉ:- “እንደምን አመሹ። [ስማቸውን ጠቅሰው] እባላለሁ። በአካባቢዎ የምገኝ ፈቃደኛ ሠራተኛ ነኝ። እርስዎ በሚኖሩበት ሕንጻ ላይ የሚገኙትን ሰዎች አስተያየት እየጠየቅሁ ነበር። ብዙዎች በአካባቢያችን የሚፈጸሙት የዓመፅ ድርጊቶችና ወንጀሎች እየጨመሩ በመሄዳቸው ስለ ግል ደህንነታቸው ያስባሉ። ይህ ጉዳይ እርስዎንስ ያሳስብዎታል? [መልስ እንዲሰጥ ይፈቅዱለታል።] መላው ዓለም ያለ ስጋት የሚኖርበት ቦታ የሚሆንበት ጊዜ የሚመጣ ይመስልዎታል?” መልስ እንዲሰጥ ይፈቅዱለትና ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይታቸውን ይቀጥላሉ።