የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 6/15 ገጽ 9-11
  • በጣም ልዩ የሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በጣም ልዩ የሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ለጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ መዘጋጀት
  • አስደሳች የሆነ ወቅት
  • አድካሚ ጉዞ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 6/15 ገጽ 9-11

በጣም ልዩ የሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት

በሰሜናዊ ሞዛምቢክ ውብ በሆኑ ተራራዎች የተከበበ ለምለም ሸለቆ ይገኛል። የፊንጎኢ መንደር የሚገኘው በዚህ ቦታ ነው። ማታ የሚታየው ጥርት ያለ የበጋ ሰማይ በከዋክብት አሸብርቋል። ከዚህም በተጨማሪ ጨረቃ የምትፈነጥቀው ደማቅ ብርሃን የመንደሩ ሰዎች የሚኖሩባቸውን የሳር ቤቶች አድምቋቸዋል። በዚህ ማራኪ ሁኔታ ነበር ልዩ የሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት የተካሄደው።

በዚህ ልዩ በሆነ አጋጣሚ ላይ ለመገኘት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሰዓታት አንዳንዶቹም ለቀናት በእግር ተጉዘዋል። አንዳንዶች ወደዚህ ቦታ የመጡት ጅቦች፣ አንበሶችና ዝሆኖች የሚኖሩበትን አደገኛ አካባቢዎች አቋርጠው ነው። አብዛኞቹ መንገደኞች ከያዟቸው ሻንጣዎች በተጨማሪ ዶሮዎች፣ ፍየሎችና አታክልት ይዘዋል። ወደ መንደሩ ከደረሱ በኋላ አብዛኛውን ጊዜ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወደሚጠቀሙበት ገላጣ ሜዳ አመሩ። ምንም እንኳ ጉዞው አድካሚ ቢሆንም ደስተኞች ነበሩ። ፊታቸው ላይ የሚታየው ፈገግታ ቀጥሎ የሚከናወነውን ሥርዓት በጉጉት እንደሚጠባበቁ ያሳያል።

ተጋቢዎቹ እነማን ናቸው? አንድ ወይም ሁለት ጥንዶች ሳይሆኑ ብዙ ናቸው! እነዚህ ተጋቢዎች በስሜት ተነሳስተው የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በኅብረት የሚፈጽሙ ሰዎች አይደሉም። ከዚህ ይልቅ የሚኖሩት ገጠር ውስጥ በመሆኑ ቀደም ሲል ጋብቻቸውን በማዘጋጃ ቤት ማስመዝገብ ያልቻሉ አሁን ግን በትክክለኛ ዝንባሌና ግፊት ይህን ለማድረግ የተነሳሱ ባልና ሚስቶች ናቸው። እነዚህ ባልና ሚስቶች በሙሉ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠኑ ጋብቻን አስመልክቶ ያሉትን መለኮታዊ የአቋም ደረጃዎች ተገነዘቡ። ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስ የሚወለድበት ጊዜ ሲደርስ ታውጆ የነበረውን የመመዝገብ ግዴታ አሟልተው እንደነበረ ሁሉ እነዚህም ሰዎች የጋብቻ መስራች የሆነውን ፈጣሪያቸውን ለማስደሰት ሲሉ የአገሩ ሕግ በሚያዘው መሰረት ጋብቻቸውን ማከናወን እንደሚኖርባቸው ተምረዋል።​—⁠ሉቃስ 2:​1-5

ለጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ መዘጋጀት

በሞዛምቢክ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ወሰነ። በመ​ጀመሪያ ሕጉ ምን የአሠራር ቅደም ተከተሎችን እንደሚጠይቅ ለማወቅ በአገሪቱ ዋና ከተማ በማፑቱ የሚገኙትን የፍትሕና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን አነጋገረ። ቀጥሎም በቴተ ወረዳ ዋና ከተማ ውስጥ ያሉት ሚስዮናውያን ዝግጅቶቹን በይበልጥ ለማቀናጀት በአካባቢው ካሉት ባለሥልጣኖች ጋር ተገናኙ። ሚስዮናውያኑና ከማዘጋጃ ቤት የተላኩት ባለሥልጣኖች ወደ ፊንጎኢ የሚጓዙበት ቀን ተቀጠረ። በዚህ መካከል ቅርንጫፍ ቢሮው ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ጉባኤዎች በሙሉ ጠቃሚ የሆነ መመሪያ የያዘ ስለ ጉዳዩ የሚያብራራ ደብዳቤ ላከ። ምሥክሮቹም ሆኑ የአካባቢው ባለሥልጣኖች ይህን ልዩ አጋጣሚ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር።

እሁድ፣ ግንቦት 18, 1997 ሦስት ሚስዮናውያንና የመንግሥት ባለሥልጣኖቹ ፊንጎኢ ደረሱ። የአካባቢው ባለሥልጣኖች ከአስተዳደር ሕንፃው አጠገብ ለመንግሥት ባለሥልጣኖቹ ምቹ የሆነ ማረፊያ አዘጋጅተው ነበር። ሆኖም ጉዳዩን ለማስፈጸም የተላኩት ባለሥልጣኖች የይሖዋ ምሥክሮች ባሳዩት እንግዳ ተቀባይነት በጣም ስለተደነቁ ጊዜያዊ በሆኑ ጎጆዎች ውስጥ ከሚስዮናውያኑ ጋር መቀመጥ መረጡ። ምግብ ከሚያዘጋጁት አንዱ በአካባቢው ባለ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ እንደሆነና ለጋብቻው ሥነ ሥርዓቱ በሚደረገው ዝግጅት በጣም ዝቅተኛ የሚባሉትን ሥራዎች ለመሥራት ፈቃደኛ ከሆኑት መካከል አንዱ ደግሞ ተጓዥ የበላይ ተመልካች መሆኑን ሲያውቁ በጣም ተደነቁ። ከዚህም በተጨማሪ ሚስዮናውያኑ በደስታ ያላንዳች ማጉረምረም በአንዲት ተራ ጎጆ ውስጥ የሚቀመጡና በጣሳ ውኃ እየቀዱ ገላቸውን የሚታጠቡ መሆናቸውን አስተውለዋል። ከፍተኛ የአስተዳደግ ልዩነት ባላቸው ሰዎች መሃል ይህን የመሰለ ጠንካራ አንድነት ከዚህ በፊት በጭራሽ አይተው አያውቁም። ሆኖም ከሁሉም በላይ ያስደነቃቸው ነገር ከአገሪቱ ሕግና ከአምላክ ዝግጅት ጋር ተስማምተው ለመኖር ሲሉ ከፍተኛ መሥዋዕቶችን በመክፈል ያሳዩት እምነት ነበር።

አስደሳች የሆነ ወቅት

ተጋቢዎቹ በቦታው እንደደረሱ መጀመሪያ ያደረጉት ነገር የልደት የምሥክር ወረቀት መቀበል ነው። ከማዘጋጃ ቤት ተወክለው ለመጡት ሰዎች በየተራ የግል ማስረጃዎቻቸውን ለማቅረብ ሁሉም በትዕግሥት ተሰልፈው መጠበቅ ነበረባቸው። ፎቶግራፍ ለመነሳት እንደገና ሌላ ሰልፍ የያዙ ሲሆን ይህን ከጨረሱ በኋላ መታወቂያ ካርዳቸውን ለማግኘት ወደሚመለከታቸው ባለሥልጣኞች ሄዱ። ከዚያም በጣም የጓጉለት የጋብቻ ምሥክር ወረቀት እንዲዘጋጅላቸው ከመዘጋጃ ቤት ተወክለው ወደመጡት መዝጋቢዎች ተመልሰው ሄዱ። ከዚህ ቀጥሎ በድምፅ ማጉያው ስማቸው እስኪጠራ ድረስ በትዕግሥት ቆመው ጠበቁ። የጋብቻ የምሥክር ወረቀት አሰጣጡ ስሜት ቀስቃሽ ትዕይንት ነበር። እያንዳንዱ ተጋቢ የጋብቻ የምሥክር ወረቀታቸውን ከተቀበሉ በኋላ ልክ እንደ ዋንጫ ወደ ላይ ከፍ አድርገው ሲይዙት የሚታየው ደስታ ልዩ ነበር።

ይህ ሁሉ የተከናወነው እንደ እሳት በሚጠብስ የፀሐይ ሙቀት ውስጥ ነበር። ሆኖም የፀሐዩ ሙቀትም ሆነ አቧራው በወቅቱ የነበረውን ደስታ አልቀነሰውም።

የወንዶቹ አለባበስ በጣም የሚያምር ሲሆን አብዛኞቹ ክራቫት አስረው ኮት አድርገዋል። ሴቶቹ ደግሞ የአገር ልብሳቸውን የለበሱ ሲሆን ይህም ካፑላና የተባለ ደማቅ ቀለም ያለው ረዥም ጨርቅ ማገልደም ይጨምራል። አንዳንዶቹ በዚሁ ጨርቅ ልጆቻቸውን አዝለዋል።

ምንም እንኳ ሥራው የተከናወነው ያለ አንዳች እንቅፋት ቢሆንም ብዙ ተጋቢዎች ስለነበሩ በአንድ ቀን ለማጠናቀቅ አልተቻለም። ቀኑ እየመሸ ቢሄድም የጋብቻ የምሥክር ወረቀቱን የሚሰጡት ሰዎች ለተጋቢዎቹ አገልግሎት መስጠታቸውን ቀጠሉ። እዚህ ለመገኘት ከፍተኛ መሥዋዕት ከፍለው የመጡት “ወንድሞቻችን” ቆመው እየጠበቁ ትተናቸው አንሄድም አሉ። ይህ ያሳዩት የትብብርና የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የማይረሳ ነው።

ቀኑ ሲመሽ ኃይለኛ ብርድ ጀመረ። ጥቂቶች በጎጆዎች ውስጥ ማደሪያ ያገኙ ሲሆን አብዛኞቹ ባልና ሚስት ግን ሜዳ ላይ እሳት አንድደው ከብበው ይሞቁ ነበር። ይህ ሁኔታ የወቅቱን አስደሳችነት አልቀነሰውም። ከሚንጣጣው የእሳት ድምፅ ይበልጥ ጎልቶ የሚሰማው የሳቅ እና አራት ቡድን ሆነው እየተቀባበሉ የሚዘምሩት መዝሙር ነበር። አብዛኞቹ የተቀበሏቸውን ሰነዶች በእጃቸው ይዘው የጉዟቸውን ገጠመኝ ይጫወታሉ።

አንዳንዶቹ ይዘው የመጡትን ዶሮዎች፣ ፍየሎችና አታክልት በመሸጥ ጋብቻቸውን ለማስመዝገብ የወጣውን ወጪ ለመሸፈን በማለዳ ወደ ገበያ ሄዱ። እንስሳቱን በጣም ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ በመሸጥ አብዛኞቹ በእርግጥ እንስሳቱን “መሥዋዕት” አድርገዋል። ድኻ ለሆኑ ሰዎች ፍየል ብርቅና ውድ ንብረት ነው። ሆኖም ይህን መሥዋዕት በማድረግ ለመጋባትና ፈጣሪያቸውን ለማስደሰት ፈቃደኞች ነበሩ።

አድካሚ ጉዞ

አንዳንዶቹ ተጋቢዎች በዚያ ለመገኘት ረጅም ርቀት በእግራቸው ተጉዘዋል። ሻምቦኮ እና ሚስታቸው ሀኩሌራ ያደረጉት ይሄንኑ ነው። በሁለተኛው ቀን ምሽት እግራቸውን እሳት እያሞቁ ገጠመኛቸውን ያወሩ ነበር። ምንም እንኳ ሻምቦኮ የ77 ዓመት አዛውንትና አንድ ዓይናቸው ጨርሶ የማያይላቸው ሌላኛው ደግሞ የደከመ ቢሆንም የ52 ዓመት ጋብቻቸውን ሕጋዊ ለማድረግ ስለቆረጡ ከሌሎቹ የጉባኤው አባሎች ጋር በመሆን ለሦስት ቀናት በባዶ እግራቸው ተጉዘዋል።

ኦንሴልሙ ኬምቦ የ72 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ ከኔርኢ ጋር ለ50 ዓመታት ያህል ኖረዋል። ከጉዞው ከጥቂት ቀናት በፊት እርሻቸው ውስጥ እየኮተኮቱ ሳሉ ትልቅ እሾኽ እግራቸውን ክፉኛ ወጋቸው። ለሕክምና በአቅራቢያው ወዳለ ሆስፒታል በአፋጣኝ ተወስደው ነበር። ሆኖም ሕመሙ በጣም ቢያሰቃያቸውም እንኳ እያነከሱ በእግር ወደ ፊንጎኢ ለመጓዝ ወሰኑ። ጉዞው ሦስት ቀን ፈጀ። ኦንሴልሙ የጋብቻ የምሥክር ወረቀቱን በእጃቸው ካስገቡ በኋላ ደስታቸውን መቆጣጠር አልቻሉም።

ሌላው ትኩረት የሚስበው አዲስ ተጋቢ ደግሞ ቀድሞ ብዙ ሚስቶች የነበሩት ኢቨንዝ ሲኖይያ ነበር። የአምላክን ቃል እውነት በተማረ ጊዜ ከመጀመሪያ ሚስቱ ጋር ጋብቻውን ሕጋዊ ለማድረግ ወሰነ። እሷ ግን አልፈልግም ብላ ትታው ወደ ሌላ ወንድ ሄደች። መጽሐፍ ቅዱስን ታጠና የነበረችው ሁለተኛው ሚስቱ እሱን ለማግባት ተስማማች። ሁለቱም አንበሶችና ሌሎች የዱር አራዊት የሚኖሩበትን አደገኛ የሆነ አካባቢ አቋርጠው በእግራቸው ተጉዘዋል። እነሱም ከሦስት ቀን ጉዞ በኋላ ጋብቻቸውን ሕጋዊ ማድረግ በመቻላቸው ተደስተዋል።

ሚስዮናውያኑና ከመንግሥት ተወክለው የመጡት ባለሥልጣኖች ቦታው ከደረሱ ከአምስት ቀን በኋላ አርብ ዕለት ሥራው ተጠናቀቀ። በውጤቱም 468 የመታወቂያ ካርድና 374 የልደት የምሥክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን 233 የጋብቻ የምሥክር ወረቀት ተሰጥቷል! ከፍተኛ ደስታ የሰፈነበት ሁኔታ ነበር። ምንም እንኳ ቢደክማቸውም ጉዳዩ ሊደከምለት የሚገባ መሆኑን ሁሉም ተስማምተውበታል። ይህ አጋጣሚ በጉዳዩ ተሳታፊ በነበሩት ሰዎች አእምሮና ልብ ውስጥ የማይጠፋ ትዝታ ትቶ እንዳለፈ ምንም ጥርጥር የለውም። በእርግጥም በጣም ልዩ የሆነ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ነበር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ