የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 7/1 ገጽ 26-29
  • በፈረንሳይ የተፈጸመ የማይረሳ ክንውን

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • በፈረንሳይ የተፈጸመ የማይረሳ ክንውን
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ይሖዋ ሥራውን ባርኳል
  • የማይረሳ ስብሰባ
  • “በበረሃ ውስጥ ያለ ገነት”
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 7/1 ገጽ 26-29

በፈረንሳይ የተፈጸመ የማይረሳ ክንውን

“ከተማችን የጅሆቫዎች እንድትሆን አንፈልግም!” የሚሉ መፈክሮች በመላ ከተማዋ ተለጥፈዋል። አንድ የተቃዋሚዎች ቡድን “የጅሆቫዎችን የግንባታ ሥራ ለማክሸፍ አንድ ላይ እንነሳ” በማለት በጥብቅ አሳስቦ ነበር። ያላንዳች ማጋነን፣ በጋዜጦች ላይ የሰፈሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ርዕሶች ጉዳዩን ለሕዝብ አቅርበዋል። መንግሥት ሥራውን እንዲያግድ በርካታ የአቤቱታ ደብዳቤዎች ቀርበዋል፤ ስለ ግንባታ ሥራው የሚገልጹ ከግማሽ ሚልዮን በላይ ትራክቶች በከተማው ያሉትን የፖስታ ሣጥኖች አጥለቅልቀዋል። በሰሜን ምዕራብ ፈረንሳይ የምትገኘውን ሰላማዊ የሆነችውን የሉቪዬን ከተማ ፀጥታ ያናጋው የግንባታ ሥራ ምን ነበር? የይሖዋ ምሥክሮች ለመሥራት ያቀዱት አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮና የመኖሪያ ሕንፃ ግንባታ ነው።

ይሖዋ ሥራውን ባርኳል

የይሖዋ ምሥክሮች በፈረንሳይ ውስጥ መንቀሳቀስ የጀመሩት ከ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ አንስቶ ነው። በ1905 የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች መጋዘን በደቡባዊ ፈረንሳይ በምትገኘው በቦቬን ተቋቋመ። ከዚህም በተጨማሪ ከ1919 አንስቶ አንድ አነስተኛ ቢሮ ፓሪስ ውስጥ ሥራ ጀምሮ ነበር። በ1930 በፓሪስ ቅርንጫፍ ቢሮ በይፋ የተከፈተ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ በዚያ የሚያገለግሉት ሠራተኞች ከፓሪስ በስተሰሜን በኦንጊዬሌበ በሚገኘው የቤቴል መኖሪያ መኖር ጀመሩ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የቤቴል ቤተሰብ እንደገና ወደ ፓሪስ ተመለሰ። ከዚያም በ1959 ቅርንጫፍ ቢሮው በዋና ከተማው ምዕራባዊ ጫፍ በቡሎኝ ቢላንኩር ወደሚገኘው ባለ አምስት ፎቅ ሕንፃ ተዛወረ።

የመንግሥቱ ስብከት ሥራ እየሰፋ በመሄዱ በ1973 የኅትመትና የጽሑፍ መላኪያ ክፍሉ ከፓሪስ በስተምዕራብ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ወደ ሉቪዬ የተዛወረ ሲሆን የተቀሩት ቢሮዎች ግን እዚያው በቡሎኝ ቢላንኩር መሥራታቸውን ቀጠሉ። ምንም እንኳ በ1978 እና በ1985 በሉቪዬ ተጨማሪ ሕንፃዎች ቢገነቡም በፈረንሳይ ውስጥ ከነበረው የአስፋፊዎች ቁጥር ጭማሪ አኳያ በቂ አልነበሩም። ስለዚህ ተጨማሪ ሕንፃዎች ለመገንባትና መላው የቤቴል ቤተሰብ አንድ ላይ እንዲኖር ለማድረግ ተወሰነ። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው ከሉቪዬ ነዋሪዎች መካከል ይህን የግንባታ ሥራ የተቃወሙ ነበሩ። ይህን የመሰለ ተቃውሞ ቢኖርም ከማተሚያ ሕንፃው አንድ ኪሎ ሜትር ከግማሽ ርቀት ላይ ግንባታውን ለማካሄድ የሚያስችል ቦታ ተገኘ። ስድስት ዓመት የፈጀ ከባድ ሥራ ከተካሄደ በኋላ ለ23 ዓመት በተለያየ ቦታ ይሠሩ የነበሩት የቤቴል ቤተሰብ አባላት በሙሉ ከነሐሴ 1996 አንስቶ በሉቪዬ አንድ ላይ ሆነው መሥራት ጀመሩ።

በመሆኑም ቅዳሜ፣ ኅዳር 15, 1997 ሦስት መቶ የሚሆኑትን የፈረንሳይ የቤቴል ቤተሰብ አባላትንና ከሌሎች 42 ቅርንጫፍ ቢሮዎች የመጡ 329 ልዑካንን ጨምሮ በዚህ ክንውን እጅግ የተደሰቱ 1,187 ሰዎች፣ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ሎይድ ባሪ ሕንፃዎቹን ለአምላክ አገልግሎት ለመወሰን የሚሰጠውን ንግግር ለማዳመጥ ተሰበሰቡ። ሆኖም ይህ ፕሮግራም የሚከናወነው በመላው ፈረንሳይ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ጥላቻ በገነነበትና በመገናኛ ብዙሃን ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ስም የማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ላይ በመሆኑ በፈረንሳይ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ባጠቃላይ ይህን ድል ማክበር እንዲችሉ ለማድረግ ታቀደ። በዚህ ምክንያት እሁድ፣ ኅዳር 16 “በክርስቶስ ፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ” በሚል ጭብጥ አንድ ልዩ ስብሰባ ከፓሪስ በስተሰሜን በሚገኘው በቪልፐንት የኤግዚቢሽን ማዕከል ተዘጋጀ። በቤልጂየምና በስዊዘርላንድ የሚገኙ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ምሥክሮችንና በብሪታንያ፣ በጀርመን፣ በሉክሰምበርግና በኔዘርላንድስ የሚገኙ በፈረንሳይኛ የሚካሄዱ ጉባኤዎችን ጨምሮ በፈረንሳይ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ባጠቃላይ ተጋበዙ።

የማይረሳ ስብሰባ

ለስብሰባው ዝግጅት ማድረግ የተጀመረው ከስድስት ወራት በፊት ነበር። ከዚያም ሕንፃዎቹ ለአምላክ አገልግሎት የሚወሰኑበት ሥነ ሥርዓት ከመካሄዱ ከሁለት ሳምንታት በፊት በፈረንሳይ ያሉ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ዋና ዋና መንገዶችንና የነዳጅ አቅርቦቶችን ዘጉ። ወንበሮችና ሌሎች መሳሪያዎች ለስብሰባው በሰዓቱ ይደርሱ ይሆን? የመንገዶቹ መዘጋት ወንድሞችን ለስብሰባው ከመምጣት ያግዳቸው ይሆን? በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የሥራ ማቆም አድማው ማብቃቱና መንገዶቹ ለመኪናዎች እንቅስቃሴ እንደገና መከፈታቸው ሁሉንም እፎይ ያሰኘ ነበር። ሕንፃዎቹ ለአምላክ አገልግሎት ከሚወሰኑበት የሳምንቱ መጨረሻ ቀኖች በፊት ባለው ዓርብ ምሽት ላይ 38 የጭነት መኪናዎች ለፕሮግራሙ ወደተከራዩት ሁለት ሰፋፊ አዳራሾች 84,000 ወንበሮች አጋዙ። ከ800 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ወንበሮቹን ለመደርደር፣ መድረኩን ለማዘጋጀትና የድምፅ መሳሪያውንና ዘጠኝ ትላልቅ የምስል ማሰራጫ ቪዲዮዎችን ለመትከል እስከ ቅዳሜ ጠዋት ሦስት ሰዓት ተኩል ድረስ ሌሊቱን ሙሉ ሲሠሩ አደሩ።

እሁድ ማለዳ በ12 ሰዓት በሮቹ ተከፈቱና ተሰብሳቢዎቹ መጉረፍ ጀመሩ። በድምሩ 17 የሚሆኑ በኮንትራት የተያዙ ባቡሮች ከ13,000 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮችን ወደ ዋናው ከተማ አደረሱ። መንገደኞቹን ለመቀበልና በቡድን በቡድን በመሆን ወደ ስብሰባው ቦታ ለማድረስ የከተማዋ ነዋሪዎች የሆኑ ከሁለት መቶ የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች በባቡር ጣቢያዎቹ ተገኝተው ነበር። አንዲት እህት ይህ ፍቅራዊ ዝግጅት “የመረጋጋትና የደህንነት ስሜት” እንዲሰማን አድርጓል ስትል ተናግራለች።

ሌሎች ደግሞ ወደ ፓሪስ የመጡት በአውሮፕላን ወይም በመኪና ነው። ሆኖም አብዛኞቹ የመጡት በ953 አውቶቡሶች ሲሆን በፓሪስ አካባቢ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ የሕዝብ ማመላለሻዎችን በመጠቀም ወደ ኤግዚቢሽን ማዕከሉ ደረሱ። አብዛኞቹ ሌሊቱን በሙሉ ሲጓዙ ቢያድሩም ወይም ከቤት የወጡት በጣም ማልደው ቢሆንም በዚህ ስብሰባ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸው ደስታ በግልጽ ይታይ ነበር። ከበርካታ ዓመታት በኋላ የተገናኙ ጓደኛሞች ሞቅ ያለ ሰላምታ ሲለዋወጡና ሲተቃቀፉ ይታዩ ነበር። በደስታ የሚፍለቀለቁት ተሰብሳቢዎች የለበሷቸው ደማቅ ባሕላዊ ልብሶቻቸው ዓለም አቀፋዊ ገጽታ አላብሰዋቸዋል። ያላንዳች ጥርጥር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ነገር እየተካሄደ ነበር።

ፕሮግራሙ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ላይ ሲጀምር ወንበሮቹ በሙሉ ሞልተዋል። ሆኖም በየደቂቃው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይመጡ ነበር። አንድ ሰው በየትኛውም አቅጣጫ ቢዞር ዓይኑ የሚያርፈው ፈገግታ በተላበሱ ፊቶች ላይ ነው። በሺህዎች የሚቆጠሩ ቆመዋል ወይም ከሲሚንቶ የተሠራው ወለል ላይ ተቀምጠዋል። ብዙ ወጣቶች የስብሰባው ጭብጥ ያዘለውን መንፈስ በማንጸባረቅና በፍቅር በመነሳሳት አረጋውያን መቀመጫ እንዲያገኙ ብለው ወንበራቸውን ለቅቀዋል። “ከዚህ በፊት ለማናውቃቸው ነገር ግን ውድ ለሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መቀመጫዎቻችንን በመልቀቃችን እጅግ ተደስተን ነበር!” በማለት አንድ ባልና ሚስት ጽፈዋል። ብዙዎች የራስን ጥቅም የመሠዋት መልካም ባሕርይ አሳይተዋል:- “ዓርብ ዕለት ሌሊቱን በሙሉ ወንበሮቹን በመደርደር ያሳለፍን ቢሆንም ፕሮግራሙ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ግን አልተቀመጥንም። ሆኖም እቦታው መገኘታችን ብቻ እንኳ ይሖዋን እጅግ እንድናመሰግነው አድርጎናል።”

ምንም እንኳ ልዑካኑ ቢደክማቸውና ቢጎሳቆሉም ከሌሎች አገሮች የቀረቡትን ሪፖርቶች እንዲሁም የሎይድ ባሪንና እንደ እሱው የአስተዳደር አካል አባል የሆነውን የዳንኤል ሲድሊክን ንግግሮች ያዳመጡት በተመስጦ ነበር። ወንድም ባሪ “ይሖዋ ኃይል ይሰጣል” የሚለውን ርዕስ ያብራራ ሲሆን የተለያዩ ዓይነት መከራዎች ቢኖሩም ይሖዋ ሕዝቦቹ እየጨመሩ እንዲሄዱ በማድረግ እንዴት እንደባረካቸው ግልጽ በሆነ መንገድ ጎላ አድርጎ ተናግሯል። የወንድም ሲድሊክ ንግግር ጭብጥ “ይሖዋ አምላኩ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!” የሚል ነበር። ሁለቱም ንግግሮች በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በፈረንሳይ ውስጥ እየደረሰባቸው ካለው ተቃውሞ አንጻር በጣም ወቅታዊ ነበሩ። ወንድም ሲድሊክ እውነተኛ ደስታ ውጫዊ በሆኑ ነገሮች ላይ የተመካ አለመሆኑንና ከዚህ ይልቅ ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድናና ለሕይወት ባለን አመለካከት ላይ የተመካ መሆኑን ገልጿል። አድማጮቹን “ደስተኞች ናችሁን?” ብሎ ሲጠይቅ በምላሹ አዳራሹ በከፍተኛ ጭብጨባ አስተጋባ።

“ደስታዋን አጥታ” የነበረች አንዲት እህት ከስብሰባው በኋላ እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ደስታ ላገኘው የምችለው ነገር መሆኑን ወዲያውኑ ተገነዘብኩ። ደስታ ለማግኘት የጣርኩት በተሳሳተ አቅጣጫ ነበር፤ ይሖዋ በዚህ ንግግር አማካኝነት ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገኝ አስገንዝቦኛል።” አንድ ሌላ ወንድም እንዲህ ሲል ገልጿል:- “አሁን የይሖዋን ልብ ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብኝ። በውስጤ ያለውን የደስታ ስሜት ምንም ነገር እንዲያሳጣኝ አልፈቅድም።”

ስብሰባው ወደ ማብቂያው ሲቃረብ የስብሰባው ሊቀመንበር የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር 95,888 መሆኑን የገለጸው በከፍተኛ የደስታ ስሜት ነበር። በፈረንሳይ የይሖዋ ምሥክሮች ታሪክ ውስጥ ይህ ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር ነበር!

አብዛኛዎቹ የመደምደሚያውን መዝሙር የደስታ ዕንባ እያነቡ ከዘመሩና ጸሎት ከተጸለየ በኋላ ወንድሞች ወደየመጡበት ቦታ የተመለሱት ደስታና ሐዘን በተቀላቀለበት ስሜት ነበር። በስብሰባው ላይ የተንጸባረቀው ሞቅ ያለ የወዳጅነት መንፈስ የብዙዎችን ትኩረት ስቧል። የአውቶቡስ አሽከርካሪዎቹ ልዑካኑ ስላሳዩት መልካም ባሕርይ በርካታ ገንቢ ሐሳቦችን ሰጥተዋል። አንዳችም ዓይነት የመኪና መጨናነቅ ሳይፈጠር ባጠቃላይ 953 አውቶቡሶች በሁለት ሰዓት ጊዜ ውስጥ የኤግዚቢሽን ማዕከሉን ለቀው መውጣት እንዲችሉ በተደረገው የተቀናጀ አሠራርም ተገርመው ነበር! የባቡርና የሕዝብ ማመላለሻ ሠራተኞቹም ልዑካኑ ያሳዩትን ባሕርይ በጣም አድንቀዋል። በዚህም የተነሳ ብዙ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን ጥሩ ምሥክርነትም ተሰጥቷል።

“በበረሃ ውስጥ ያለ ገነት”

ሐዋርያው ጳውሎስ መሰል ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ . . . እርስ በርሳችን እንመካከር . . . ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብራውያን 10:​24, 25) በእርግጥም ይህ ልዩ ስብሰባ ለሁሉም ትልቅ ማበረታቻ ሆኖላቸዋል፤ አንዲት እህት እንደገለጸችው “በበረሃ ውስጥ ያለ ገነት” ነበር። “ወደየቤታችን የተመለስነው ኃይል አግኝተን፣ ተበረታትተን፣ ተጠናክረንና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በይሖዋ አገልግሎት ለመደሰት ቆርጠን ነበር” ሲሉ ከቶጎ ቅርንጫፍ ቢሮ መጥተው የነበሩ ወንድሞች ጽፈዋል። “አዝነው የነበሩት ወደ ቤታቸው የተመለሱት ተደስተው ነው” በማለት አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ተናግሯል። ሌላው ደግሞ “ወንድሞች ተነቃቅተውና ተበረታትተው ነበር” ሲል ገልጿል። አንድ ባልና ሚስት “ስብሰባው ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከይሖዋ ድርጅት ጋር በጣም እንደተቀራረብን ሆኖ እንዲሰማን አድርጎናል” ብለው ለመጻፍ ተገፋፍተዋል።

መዝሙራዊው “እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና [“ተደላድለው ይቆማሉ፣” NW]፤ አቤቱ፣ በማኅበር አመሰግንሃለሁ” ሲል ገልጿል። (መዝሙር 26:​12) እንደዚህ የመሰሉ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች፣ ችግሮች እያሉብንም በመንፈሳዊ ተደላድለን እንድንቆም ያስችሉናል። አንዲት እህት “ማንኛውም ዓይነት መከራ ቢደርስብን እነዚህ በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ወቅቶች ልባችን ውስጥ በደንብ ስለተቀረጹ ምንጊዜም ያጽናኑናል” ስትል ይህን አባባል የሚያጠናክር ሐሳብ ተናግራለች። በተመሳሳይም አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የአዲሱ ሥርዓት ቅምሻ የሆነው የዚህ ስብሰባ ትዝታ አስቸጋሪ ጊዜያት ሲከሰቱ ችግሮቹን እንድንቋቋም ይረዳናል።”

መዝሙር 96:​7 “የአሕዛብ ወገኖች፣ ለእግዚአብሔር አምጡ፣ ክብርንና ምስጋናን ለእግዚአብሔር አምጡ” በማለት ያሳስበናል። በፈረንሳይ ውስጥ ለአምላክ የተወሰኑት አዳዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች የይሖዋ ድል ሲታወስ እንዲኖር እንደሚያደርጉ ምንም ጥርጥር የለውም። በይሖዋ ኃይል ባይሆን ኖሮ ያን በመሰለ ኃይለኛና ሰፊ ተቃውሞ መካከል የግንባታ ሥራውን ማጠናቀቅ አዳጋች ነበር። በፈረንሳይ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ‘በክርስቶስ ፍቅር ለመኖር’ እና ‘ብርሃናቸው እንዲበራ ለማድረግ’ ቆርጠዋል። (ዮሐንስ 15:​9፤ ማቴዎስ 5:​16) የሚከተሉት የመዝሙራዊው ቃላት ሕንፃዎቹ ለአምላክ በተወሰኑበት ፕሮግራም ላይ የተገኙትን ሰዎች ሁሉ ስሜት በቀጥታ ይገልጻሉ:- “ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፣ ለዓይናችንም ድንቅ ናት።”​—⁠መዝሙር 118:​23

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዳንኤል ሲድሊክ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሎይድ ባሪ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቪልፐንት የኤግዚቢሽን ማዕከል በተካሄደው ልዩ ፕሮግራም ላይ 95,888 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል

[በገጽ 28 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ከተሰብሳቢዎቹ መካከል በሺህ የሚቆጠሩት ንግግሮቹን ያዳመጡት ቆመው ወይም ወለል ላይ ተቀምጠው ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ