ማርያም የሞተችው በአለፍጽምና ምክንያት ነውን?
ቫቲካን የምታሳትመው ለኦሰርቫቶሬ ሮማኖ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው የካቶሊክ እምነት የማርያምን እርገት በተመለከተ የምታስተምረው መሠረተ ትምህርት እንዲህ ይላል:- “ንጽሕት ድንግል ከማንኛውም የአዳማዊ ኃጢአት ጉድፍ ነፃ ስለሆነች ምድራዊ ሕይወቷን እንደጨረሰች ሥጋዋም ሆነ ነፍሷ ወደ ሰማያዊው ክብር ተወስዷል።” ይህ ትምህርት አንዳንድ የካቶሊክ ሃይማኖት ምሁራን ማርያም “ሞትን ሳትቀምስ ከምድራዊው ሕይወት ወደ ሰማያዊው ክብር ተነጥቃለች” ብለው እንዲናገሩ ገፋፍቷቸዋል በማለት ጋዜጣው ያትታል።a
በቅርቡ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በዚህ ጉዳይ ላይ ለየት ያለ መግለጫ ሰጥተዋል። ሰኔ 25, 1997 በቫቲካን በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንዲህ ብለዋል:- “አዲስ ኪዳን ስለ ማርያም የአሟሟት ሁኔታ የሚሰጠን ምንም ፍንጭ የለም። ይህ ጉዳይ አለመጠቀሱ ደግሞ አንድ ሰው ስለ አሟሟቷ ሊነገር የሚገባ አዲስ ክስተት አለመኖሩንና አዳማዊ ሞት መሞቷን እንዲያምን ያስገድደዋል። . . . ማርያም በአለፍጽምና ምክንያት አልሞተችም የሚለው አባባል ድጋፍ ያለው አይመስልም።”
ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ የሰጡት መግለጫ ማርያም ከአዳማዊ ኃጢአት ነፃ ነበረች የሚለው የቤተ ክርስቲያን ቀኖና የያዘውን የጎላ ስህተት ያጋልጣል። የኢየሱስ እናት ማርያም “ከማንኛውም የአዳማዊ ኃጢአት ጉድፍ ነፃ” ከነበረች ኃጢአተኛ ከነበረው አዳም በውርስ በሚተላለፈው የኃጢአት ውጤት ማለትም “በአለፍጽምና ምክንያት” እንዴት ልትሞት ትችላለች? (ሮሜ 5:12) ይህ እርስ በርሱ የሚጋጭ ሃይማኖታዊ ትምህርት ሊፈጠር የቻለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስን እናት አስመልክቶ በያዘችው የተዛባ አመለካከት ምክንያት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መከፋፈልና ግራ መጋባት መፈጠሩ ምንም አያስገርምም።
መጽሐፍ ቅዱስ ማርያም ትሁት፣ ታማኝና ለአምላክ ያደረች መሆንዋን ቢገልጽም እነዚህን ባሕርያት “በተፀነሰችበት ጊዜ ከማንኛውም ኃጢአት ንጹሕ” ከመሆንዋ ጋር አያይዞ አይገልጻቸውም። (ሉቃስ 1:38፤ ሥራ 1:13, 14) መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል” ሲል በግልጽ ይናገራል። (ሮሜ 3:23) አዎን፣ ማርያም እንደተቀረው የሰው ዘር ሁሉ ኃጢአትና አለፍጽምና ወርሳለች። በመሆኑም ባለፍጽምና ምክንያት አለመሞትዋን የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም።—ከ1 ዮሐንስ 1:8-10 ጋር አወዳድር።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በየካቲት 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 26-9 ላይ “የማርያም ፍልሰታ በአምላክ የተገለጠ ቀኖና ነውን?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።