ትክክልና ስህተት የሆነውን መለየት ትችላለህ?
“ወደ 25 በሚጠጉ ሰዎች ላይ ለተፈጸመው ግድያ ሙሉ በሙሉ ተጠያቂው እኔ ነኝ። . . . ሌት ተቀን በዓይነ ሕሊናዬ ይመጡብኛል። ያቃዠኛል። . . . የትም ቦታ ብሄድ የገደልኳቸውን ሰዎች የሚያስታውሱኝ ሰዎች አያለሁ። ዛሬ፣ ልክ በአሁኑ ወቅት የተፈጸመ ያክል ሆኖ በደንብ ይታየኛል። . . . ለፈጸምኩት ነገር ለራሴ ይቅርታ ማድረግ አልችልም።”—ቪ ኤስ
“እዚያ ሄጄ ጠላቶችን የደመሰስኩት ታዝዤ ነው። . . . ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን እንደምገድል አድርጌ አላሰብኩም። . . . ድርጊቱን ታዝዤ እንደፈጸምኩት ሆኖ ነው የተሰማኝ። ዛሬም ቢሆን ስሜቴ ያው ነው። የተሰጠኝን ግዳጅ ፈጽሜአለሁ፤ እንዲህ በማድረጌም ምንም ዓይነት የጸጸት ስሜት አይሰማኝም።”—ደብልዩ ሲ
መጋቢት 16, 1968 ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ሰዎች ከጊዜ በኋላ አስከፊ የጦርነት ወንጀል ተብሎ በሚታወቀው ድርጊት ተካፍለዋል። ከሌሎች ወታደሮች ጋር ሆነው ወደ አንዲት የቬትናም መንደር ገቡና ሴቶችን፣ ልጆችንና አረጋውያንን ጨምሮ በመቶ የሚቆጠሩ ሲቪሎችን ደም አፈሰሱ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሁለት ወታደሮች የሰጡትን ተቃራኒ የሆነ አስተያየት ልብ በሉ። የመጀመሪያው ወታደር ያደረገው ነገር በጣም አስጨንቆታል። ሁለተኛው ደግሞ ይህን ድርጊት ለመፈጸም ያበቃው በቂ ምክንያት እንዳለው ሆኖ ተሰምቶታል። ሁለት ሰዎች ለፈጸሙት አንድ ዓይነት ተግባር እንዴት የተለያየ አመለካከት ሊይዙ ይችላሉ?
መልሱ ከሕሊና ጋር የተያያዘ ነው። ሕሊና ራሳችንን በሃቀኝነት ተመልክተን ባደረግነውና ለማድረግ ባሰብነው ነገር ላይ ፍርድ እንድንሰጥ የሚያደርገን አምላክ የሰጠን ችሎታ ነው። ሕሊና ትክክልና ስህተት የሆኑ ነገሮችን ለይተን እንድናውቅ የሚረዳን ውስጣዊ ስሜት ነው።
አንዳንድ ሰዎች ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ “ሕሊናህ የሚልህን አድርግ” የሚለውን ብሂል ይከተላሉ። የሚያሳዝነው ግን ሕሊና ሁልጊዜ እምነት ሊጣልበት የሚችል አለመሆኑ ነው። እንዲያውም ብዙዎች በጣም አሠቃቂና ዘግናኝ የሆኑ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እያዩና አልፎ ተርፎም ራሳቸው እየፈጸሙ ሕሊናቸው ቅንጣት ታክል እንኳ አይቆረቁራቸውም። (ዮሐንስ 16:2፤ ሥራ 8:1) እንግሊዛዊው ደራሲ ሳሙኤል በትለር ሕሊና “ሊያዳምጡት ፈቃደኛ ላልሆኑ ሰዎች መናገሩን ያቆማል” በማለት በአንድ ወቅት ተናግረዋል።
ሕሊናህን ልታምነው ትችላለህ? ቀጣዩ ርዕስ እንደሚያሳየው መልሱ በአብዛኛው የተመካው ሕሊናህ ምን ያህል በሚገባ ሰልጥኗል በሚለው ላይ ነው።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Upper war scene: U.S. Signal Corps photo