እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብ የነበራቸው ሰዎች ሲለወጡ
በፖላንድ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በ1989 እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት በመቆጠር ሕጋዊ እውቅና አገኙ። በክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸው ምክንያት ታስረው የነበሩ ምሥክሮች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለማወቅ ጉጉት የነበራቸውን እስረኞች እዚያው እስር ቤት ትተው ቀስ በቀስ ከእስር ይለቀቁ ጀመር። የይሖዋ ምሥክሮች እንዲህ ባለ አንድ እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ እንደ ድንጋይ የጠነከረ ልብ ያላቸውን እስረኞች በአምላክ ቃል ኃይል እንዲለወጡ ለመርዳት ያደረጉትን ጥረት የሚገልጽ አንድ ዘገባ ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል።
በደቡባዊ ምዕራብ ፖላንድ በምትገኘው 12,000 ነዋሪዎች ባሏት ቮዉፍ በምትባል ከተማ አንዳንድ በጣም አደገኛ የአገሪቱ ወንጀለኞች የሚታሰሩበት 200 ዓመት ዕድሜ ያለው አንድ ወህኒ ቤት አለ። የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸው ይፋዊ እውቅና ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ በእዚህ ወህኒ ቤት ውስጥ ለሚገኙ እስረኞች የመንግሥቱን ምሥራች ለማድረስ በከፍተኛ ቅንዓት የተቻላቸውን ሁሉ ሲጥሩ ቆይተዋል።
ለዚህ መንገድ የጠረገው የፍትህ ሚኒስቴር በየካቲት 1990 በፖላንድ ለሚገኙ የወህኒ ቤት ኃላፊዎች በሙሉ የላከው አንድ ደብዳቤ ነው። ደብዳቤው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎችን ለመውሰድ ወይም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘት በሚፈልግ ማንኛውም እስረኛ ላይ የወህኒ ቤት ኃላፊዎች “ችግር እንዳይፈጥሩበት” የሚያሳስብ ነበር። ከምሥክሮቹ መካከል አንዳንዶቹ በቮዉፍ ወህኒ ቤት ረጅም ዓመታት ያሳለፉ ስለሆኑ በዚያ ከሚገኙት በርካታ የቆዩ ወንጀለኞች ጋር ይተዋወቃሉ። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የእስረኞቹን እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብ እንዲያለሰልሰው በማድረግ ይሖዋ ጥረታቸውን እንደሚባርክላቸው ይተማመኑ ነበር።
ሥራውን መጀመር
አርባ ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በቭሮትስላቭ ከተማ የሚኖረው የቮዉፍን ወህኒ ቤት እንዲጎበኝ የተፈቀደለት ወንድም ቼስዋፍ “ሥራውን መጀመር ቀላል አልነበረም” ሲል ተናግሯል። “የእኛ ‘ሃይማኖታዊ ስብከት’ ለእስረኞቹ ጠቃሚ መሆኑን የወህኒ ቤቱን ባለ ሥልጣናት ለማሳመን በተደጋጋሚ ጊዜያት ረጅም ሰዓታት የፈጁ ውይይቶችን ማድረግ አስፈልጓል።”
“አንድ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን” ጉዳዩን ለማወሳሰብ ስለፈለገ ብቻ “ወንጀለኞቹ ሃይማኖታዊ ስብከቱን ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት እንደ ሰበብ አድርገው ይጠቀሙበታል በማለት ድርቅ አለ።” ይሁን እንጂ የወህኒ ቤቱ ባለ ሥልጣናት አደገኛ ወንጀለኛ የነበሩ ሦስት እስረኞች በ1991 ሲጠመቁ በተመለከቱ ጊዜ አመለካከታቸው ተለወጠ። ከዚያ በኋላ የተሻለ የትብብር መንፈስ ማሳየት ጀመሩ።
ቼስዋፍ “ሥራችንን የጀመርነው ለእስረኞቹ፣ እነርሱን ለመጠየቅ ወደ እስር ቤቱ ለሚመጡት ቤተሰቦቻቸውና ለወህኒ ቤቱ ሠራተኞች በመመሥከር ነው” ሲል ተናግሯል። “ከዚያም እስረኞች ከታሰሩበት ከአንዱ ሕንፃ ወደ ሌላው እየሄድን ምሥራቹን መስበክ እንደምንችል ያልጠበቅነው ፈቃድ ተሰጠን። በመጨረሻም ፍላጎት ያለው አንድ ሰው እንዳገኘን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምንመራበትና ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን የምናደርግበት አንድ አነስተኛ ክፍል ተሰጠን።” አዎን፣ ይሖዋ እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብ ያላቸውን እስረኞች ምሥራቹን የሚሰሙበትን መንገድ ከፈተ።
ውጤታማ የሆነ የማስተማር መርሃ ግብር
ብዙም ሳይቆይ ያቺ ትንሽ ክፍል በጣም ጠበበች። የተጠመቁ እስረኞችና ከውጪ የሚመጡ ወንድሞች በስብከቱ ሥራ ይካፈሉ ስለነበር 50 የሚሆኑ እስረኞች በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ። “ከሦስት ለሚበልጡ ዓመታት ስብሰባችንን እናከናውን የነበረው እዚሁ ነበር። እስረኞቹም በየሳምንቱ በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው ይገኙ ነበር” በማለት በአካባቢው ካሉት ሽማግሌዎች አንዱ ተናግሯል። በዚህም የተነሳ ግንቦት 1995 ሰፋ ባለ ክፍል እንዲሰበሰቡ ተፈቀደላቸው።
ኃላፊነት የተሰጣቸው ወንድሞች በእስር ቤቱ ውስጥ በሚደረገው ስብሰባ ላይ እነማን መገኘት እንደሚችሉ የሚወስኑት እንዴት ነው? “ለእውነት ልባዊ ፍላጎት ያላቸው እስረኞች እነማን እንደሆኑ የሚገልጽ የስም ዝርዝር የያዘ መዝገብ አለን” በማለት ወንድም ቼስዋፍ እና ወንድም ዝዳሽዋፍ ተናግረዋል። “አንድ እስረኛ መሻሻል የማያደርግና ያለ በቂ ምክንያት ከስብሰባ የሚቀር ከሆነ ይህ ሁኔታው ለዚህ ዝግጅት አድናቆት እንደጎደለው የሚያሳይ በመሆኑ ከመዝገቡ ውስጥ ስሙን እንሰርዝና ለእስር ቤቱ ዋና ተቆጣጣሪ ጉዳዩን እናሳውቃለን።”
ወንድሞች እስረኞቹን መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስጠኑበት ጊዜ ለስብሰባ እንዴት መዘጋጀት እንደሚችሉና ጽሑፎቻችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉም ያስተምሯቸዋል። ስለዚህ እስረኞቹ ወደ ስብሰባ የሚመጡት በሚገባ ተዘጋጅተው ስለሆነ ነፃነት ተሰምቷቸው ይሳተፋሉ። በስብሰባ ላይ የሚያንጽ ሐሳብ ይሰጣሉ፣ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ጥሩ አድርገው ይጠቀሙበታል፤ ብዙውን ጊዜም ሲመልሱ ‘ይህንን ወይም ያንን ማድረግ እንዳለብኝ ተገንዝቤአለሁ’ የሚል ሐሳብ በመስጠት ምክሩ በእነሱ ላይ የሚሠራበትን መንገድ ይገልጻሉ።
በቮዉፍ እስር ቤት በጠቅላላው ለ20 እስረኞች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመራላቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱን የሚያስጠኗቸው ሦስት አስፋፊ የሆኑ እስረኞች ናቸው” በማለት የጉባኤው ጸሐፊ ይናገራል። እነዚህ አስፋፊዎች እስረኞች ከታሰሩበት ከአንዱ ሕንፃ ወደ ሌላው በመሄድና በእስር ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ አየር ለመቀበል ወጣ በሚሉባቸው ሰዓታት ላይ በመስበክ ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል ከመስከረም 1993 እስከ ሰኔ 1994 ባሉት በአሥር ወር ጊዜ ውስጥ 235 መጻሕፍት፣ 300 የሚጠጉ ብሮሹሮችና 1,700 መጽሔቶች አሰራጭተዋል። በቅርቡም ሁለት የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣናት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
አስደሳች የሆኑ ልዩ ስብሰባዎች
ከጊዜ በኋላ በእስር ቤቱ እየተሰጠ ባለው የትምህርት መርሃ ግብር ውስጥ ሌላ ተጨማሪ ነገር ማለትም ልዩ ስብሰባዎችም ታከሉበት። በእስር ቤቱ ስፖርት ማዕከል ውስጥ በሚደረገው የወረዳ ስብሰባና ለአንድ ቀን በሚደረገው የልዩ ስብሰባ ፕሮግራም ላይ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሌሎች ብቃት ያላቸው ወንድሞች ይገኙ ነበር። የመጀመሪያው የልዩ ስብሰባ ፕሮግራም ጥቅምት 1993 ተደረገ። ሃምሳ እስረኞች በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን “ሴቶችንና ትንንሽ ልጆችን ጨምሮ መላው ቤተሰብ ከቭሮትስላቭ መጥቶ ነበር” በማለት ስዎቮ ፖልስኪ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል። በስብሰባው ላይ በድምሩ 139 ሰዎች ተገኝተዋል። የስብሰባው የምሳ ሰዓት እረፍት እህቶች ያዘጋጁትን ምግብ ለመመገብና ክርስቲያናዊ ጭውውት ለማድረግ አጋጣሚ ከፍቶ ነበር።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሰባት ልዩ ስብሰባዎች የተደረጉ ሲሆን በእስር ቤቱ ያሉት እስረኞች ብቻ ሳይሆኑ ከውጭ የመጡትም ከስብሰባዎቹ ተጠቅመዋል። አንዲት እህት፣ ቀደም ሲል በቮዉፍ እስር ቤት የነበረ አሁን ግን ከእስር ተለቅቆ በከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው ስታነጋግር መጀመሪያ ላይ የጥርጣሬ ስሜት አሳይቶ ነበር። ይሁን እንጂ አንድ እስረኛ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ ሲነገረው “ያ ነፍሰ ገዳይ የይሖዋ ምሥክር ሆነ?” በማለት ጮኸ። በዚህም የተነሳ ሰውዬው መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ፈቃደኛ ሆነ።
አስደናቂ የሆነ የባሕርይ ለውጥ ታየ
ይህ መጠነ ሰፊ የማስተማር መርሃ ግብር በእርግጥ እንደ ድንጋይ የጠጠረውን የእስረኞች ልብ አለስልሶት ይሆን? እስቲ ራሳቸው ታሪካቸውን ሲናገሩ እንስማቸው።
“ወላጆቼ የተዉኝ ገና ትንሽ ልጅ እያለሁ ስለነበረ ጥቁር ይሁኑ ቀይ ፈጽሞ አላውቃቸውም፤ በዚህም የተነሳ የወላጅ ፍቅር ሳላገኝ ማደጌ በእጅጉ ጎድቶኛል” በማለት ዝድዚሳቭ ሳይሸሽግ ተናገረ። “በወንጀል ድርጊት መካፈል የጀመርኩት ገና በለጋ ዕድሜዬ ሲሆን በመጨረሻም የነፍስ ግድያ ወንጀል ፈጸምኩ። ይሰማኝ የነበረው የጥፋተኝነት ስሜት ራሴን የመግደል ሐሳብ እንዲያድርብኝ አድርጓል፤ እውነተኛ ተስፋ ለማግኘት በጣም እጓጓ ነበር። ከዚያም በ1987 የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት አገኘሁ። መጽሔቱ ላይ ስለ ትንሣኤና ስለ ዘላለም ሕይወት ተስፋ አነበብኩ። አሁንም ተስፋ እንዳለ ስለተገነዘብኩ ራሴን የማጥፋት ሐሳቤን ከአእምሮዬ አወጣሁና መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። አሁን ከይሖዋ እና ከወንድሞች የፍቅርን ትርጉም ተምሬአለሁ።” ቀደም ሲል ነፍስ አጥፍቶ የነበረው ይህ ሰው በእስር ቤት ውስጥ እያለ ከ1993 አንስቶ የጉባኤ አገልጋይና ረዳት አቅኚ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ሲሆን ባለፈው ዓመት ደግሞ የዘወትር አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀምሯል።
በሌላው በኩል ደግሞ ቶማሽ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመረው ያለ ምንም ማንገራገር ነበር። “ይሁን እንጂ ማጥናት የጀመርኩት በቅን ልብ ተነሳስቼ አልነበረም” ሲል በግልጽ ተናግሯል። “አጠና የነበረው የይሖዋ ምሥክሮችን እምነት ለሌሎች በማብራራት ጉራዬን ለመንዛት ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በቁም ነገር አልያዝኩትም ነበር። አንድ ቀን አስተሳሰቤን አስተካከልኩና ወደ አንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ ሄድኩ። የተጠመቁ እስረኞች ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ። ያገኘሁትን እውቀት ለጉራ ከመጠቀም ይልቅ እንደ ድንጋይ የጠጠረውን ልቤን ማለስለስና አስተሳሰቤን መለወጥ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።” ቶማሽ አዲሱን ክርስቲያናዊ ሰው መልበስ ጀመረ። (ኤፌሶን 4:22–24) ዛሬ ራሱን ለአምላክ ወስኖና ተጠምቆ ከአንዱ ሕንፃ ወደ ሌላው እየሄደ ለእስረኞች የሚሰብክ ደስተኛ ሰው ነው።
የቀድሞ ጓደኞች የሚያሳድሯቸው ተጽእኖዎች
በእስር ቤት እያሉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተማሩት እስረኞች የቀድሞ የእስር ቤት ጓደኞቻቸውና የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣናት ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድሩባቸው ጀመር። ጥቃት ከሚደርስባቸው መካከል አንዱ ሲናገር “ያለ ማቋረጥ ነቀፋና ዛቻ ይደርስብኝ ነበር። ሆኖም የወንድሞችን የማበረታቻ ቃላት ፈጽሞ አልረሳም። ‘ሳታቋርጥ ወደ ይሖዋ ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስህን አንብብ፣ ውስጣዊ ሰላምም ታገኛለህ’ እያሉ ይነግሩኝ ነበር። ይህ አባባላቸው በእርግጥም ረድቶኛል።”
“አብረውኝ የታሰሩት እስረኞች ይሰነዝሩብኝ የነበረው ቅስም የሚሰብር ስድብ እንዲህ ነው ብዬ ልገልጸው የምችለው አልነበረም” በማለት ሪሻርድ የተባለ አንድ የተጠመቀ ወንድም ተናግሯል። ‘ወደ ስብሰባህ መሄድ ትችላለህ፣ ሆኖም የተለየህና የተሻልክ ሆነህ ለመታየት እንዳትሞክር፣ ገባህ?’ በማለት ያስጠነቅቁኝ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሕይወቴ ላይ ተግባራዊ በማድረጌና በመለወጤ ሥቃይ መቀበል ነበረብኝ። አልጋዬን ይገለብጡብኝ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቼን ይበታትኑብኝ እንዲሁም የምተኛበትን አካባቢ ምስቅልቅል ያደርጉብኝ ነበር። ራሴን መቆጣጠር እንድችል ጥንካሬ እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ እጸልይና ጸጥ ብዬ ሁሉንም ነገር ማስተካከል እጀምራለሁ። ከጊዜ በኋላ ተጽእኖው ሁሉ ቆመ።”
ሌሎች የተጠመቁ እስረኞች እንዲህ በማለት ተናግረዋል:- “አብረውን ያሉት እስረኞች እኛ ይሖዋን ለማገልገል ከወሰድነው አቋም ፈጽሞ ዝንፍ እንደማንል ሲመለከቱ የሚሰነዝሩት ጥቃት መልኩን ለወጠ። ‘ከአሁን በኋላ መጠጣት፣ ማጨስ ወይም መዋሸት እንደማትችሉ አስታውሱ’ ብለው እንደሚናገሩ የምንጠብቀው ነገር ነበር። እንዲህ የመሰለው ተጽእኖ አንድ ሰው ማንኛውንም ዓይነት መጥፎ ጠባይ ወይም ሱስ ወዲያው እንዲያስወግድና በሥጋው ላይ አንዲጨክን ያደርገዋል። በተጨማሪም የመንፈስ ፍሬዎችን እንዲያፈራ ይረዳዋል።”—ገላትያ 5:22, 23
ለአምላክ ብቻ የተወሰነ አገልጋይ መሆን
የወህኒ ቤቱን ባለ ሥልጣን በማስፈቀድ በ1991 የጸደይ ወር ላይ የመጀመሪያው የጥምቀት ሥነ ሥርዓት በስፖርት ማዕከሉ ውስጥ ተከናወነ። ዝድዚሳቭ ደስተኛ የጥምቀት እጩ ነበር። በሥነ ሥርዓቱ ላይ አሥራ ሁለት እስረኞች የተገኙ ሲሆን ከውጭ ደግሞ 21 ወንድሞችና እህቶች መጥተው ነበር። ስብሰባው ለሌሎቹ እስረኞች አበረታች ነበር። በርካታ እስረኞች ፈጣን የሆነ እድገት በማድረግ ከመካከላቸው ሁለቱ በዚያው ዓመት ጥቂት ቆየት ብለው ተጠምቀዋል። ከሁለት ዓመት በኋላ በ1993 ሁለት የጥምቀት ሥነ ሥርዓቶች ተደርገው ሰባት ተጨማሪ እስረኞች ለይሖዋ ያደረጉትን ውሳኔ በውኃ ጥምቀት አሳይተዋል!
በታኅሣሥ የተደረገውን የጥምቀት ሥነ ሥርዓት በማስመልከት ቭዬኮርድ ቭሮጽዋቭያ የተባለ በአካባቢው የሚታተም ዕለታዊ ጋዜጣ እንዲህ በማለት ዘግቧል:- “በርካታ ሰዎች ወደ ስፖርት ማዕከሉ ይጎርፉ የነበረ ሲሆን እርስ በርስ ይጨባበጡና ሰላምታ ይሰጣጡ ነበር። በመካከላቸው አንድም ባይተዋር አልነበረም። በአስተሳሰብ፣ በአኗኗርና አንድ አምላክ የሆነውን ይሖዋን በማገልገል የተባበረ አንድ ትልቅ ቤተሰብ መሥርተዋል።” ይህ “አንድ ትልቅ ቤተሰብ” በዚያን ጊዜ 50 ወንጀለኞችን ጨምሮ 135 ሰዎችን ያቀፈ ነበር። እስቲ አንዳንዶቹ የሚሉትን እንስማ።
በሰኔ የተጠመቀው የርዚ እንዲህ በማለት ይተርካል:- “ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር ትውውቅ የነበረኝ ከዓመታት በፊት ቢሆንም በዚያን ጊዜ ልቤ እንደ ድንጋይ የጠጠረ ነበር። ማጭበርበር፣ ከመጀመሪያዋ ሚስቴ መፋታት፣ ከክሪስቲና ጋር ተገቢ ያልሆነ ቅርርብ መፍጠር፣ ዲቃላ መውለድና በተደጋጋሚ ጊዜ መታሰር፤ ሕይወቴ ይህን የሚመስል ነበር።” ደንዳና ልብ የነበራቸው ሌሎች እስረኞች እዛው እስር ቤት እያሉ የይሖዋ ምሥክር ሲሆኑ ሲመለከት ‘እኔስ ጥሩ ሰው የማልሆነው ለምንድን ነው?’ እያለ ራሱን መጠየቅ ጀመረ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት ጠየቀና ወደ ስብሰባዎች መምጣት ጀመረ። ይሁን እንጂ እውነተኛ ለውጥ ያደረገው አንድ አቃቤ ሕግ ክሪስቲና ከሦስት ዓመት በፊት የይሖዋ ምሥክር መሆኗን በነገረው ጊዜ ነበር። የርዚ “ፈጽሞ ያላሰብኩት ነገር ነበር!” በማለት ተናግሯል። “‘እኔስ? ምን እያደረኩ ነው?’ እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ። በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከፈለግኩ አኗኗሬን ማስተካከል እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።” በመጨረሻም ከክርስቲና እና የ11 ዓመት ሴት ልጃቸው ከሆነችው ከማርዜን ጋር አስደሳች በሆነ መንገድ በእስር ቤት ተገናኙ። ብዙም ሳይቆዩ ጋብቻቸውን ሕጋዊ አደረጉ። የርዚ ከእስር ቤት ገና ያልተለቀቀና የመለቀቁም ተስፋ ያልተጨበጠ ቢሆንም እንኳ በቅርቡ በራሱ ጥረት የምልክት ቋንቋ ተምሮ መስማት የተሳናቸውን መርዳት ችሏል።
ሚሮስዋፍ ገና የአንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ በወንጀል ድርጊት ውስጥ ተዘፍቆ ነበር። ጓደኞቹ በሚያደርጉት ነገር በጣም ይደሰት ስለነበር እርሱም ብዙም ሳይቆይ ተመሳሳይ የሆነ ድርጊት መፈጸም ጀመረ። የዘረፋቸውና የደበደባቸው ሰዎች ቁጥር በርካታ ነበር። በመጨረሻም ወደ ወህኒ ቤት ወረደ። “ከታሰርኩ በኋላ እርዳታ ለማግኘት ወደ አንድ ቄስ ሄድኩ” በማለት ሚሮስዋፍ ይናገራል። “ይሁን እንጂ ተስፋዬ ሁሉ ተሟጦ አልቆ ነበር። ስለዚህም መርዝ ጠጥቼ ራሴን ለማጥፋት ወሰንኩ።” ሕይወቱን ለማጥፋት ወስኖ በነበረበት ዕለት ወደ ሌላ የእስር ቤት ሕንፃ ተዛወረ። እዛም ስለ ሕይወት ዓላማ የሚናገር አንድ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ አገኘ። “በመጽሔቱ ላይ የሰፈረው ቀላልና ግልጽ የሆነ ትምህርት በትክክል ለእኔ የሚያስፈልገኝ ነበር” በማለት አክሎ ይናገራል። “አሁን የመኖር ፍላጎቴ ተቀሰቀሰ! ስለዚህ ወደ ይሖዋ ጸለይኩና መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኑኝ ምሥክሮቹን እንዲልክልኝ ጠየቅኩት።” በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ፈጣን እድገት አደረገና በ1991 ተጠመቀ። አሁን በእስር ቤቱ በሚገኙት ሕንፃዎች እየተዘዋወረ የመስበክ ፈቃድ አግኝቶ በእስር ቤቱ ውስጥ ረዳት አቅኚ ሆኖ ያገለግላል።
እስከ አሁን ድረስ በድምሩ 15 እስረኞች ተጠምቀዋል። በሁሉም ላይ የተበየነው ፍርድ በድምሩ 260 የሚያክል ዓመት ይደርሳል። አንዳንዶቹ በአመክሮ ከእስር ቤት ተለቅቀዋል። 25 ዓመት እንዲታሰር የተፈረደበት አንድ እስረኛ 10 ዓመት ተቀንሶለታል። እንዲሁም እስር ቤት እያሉ ፍላጎት ያሳዩ በርካታ እስረኞች ከእስር ቤት ከተለቀቁ በኋላ ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። በተጨማሪም ለጥምቀት እየተዘጋጁ ያሉ አራት ተጨማሪ እስረኞች አሉ።
የእስር ቤት ባለ ሥልጣናት ምስጋናቸውን ገልጸዋል
አንድ የእስር ቤቱ ሪፖርት “እስረኞቹ የሚያሳዩት የጠባይ ለውጥ በሌሎች ዘንድ ግልጽ ሆኖ የሚታይ ነበር” በማለት ይገልጻል። “ብዙዎቹ ማጨስ አቁመዋል፤ እንዲሁም የታሰሩበትን ሕንፃ ንጹሕ አድርገው ይይዛሉ። እንዲህ ዓይነቱ የምግባር ለውጥ በብዙዎቹ እስረኞች ዘንድ በሚገባ የሚታወቅ ነው።”
ዝክ ቫርሻቬ የተባለው ጋዜጣ “ሃይማኖታቸውን የለወጡት እስረኞች ጠባይ እንደ ታረመና በእስር ቤቱ ዘበኞች ላይ ምንም ዓይነት ችግር እንደማይፈጥሩ” የቮዉፍ እስር ቤት አስተዳዳሪዎች ገልጸዋል። ይኸው ጋዜጣ ሃተታውን ሲቀጥል የተበየነባቸውን ፍርድ ከመጨረሳቸው በፊት የተለቀቁት እስረኞች ውጪ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደተደባለቁና እንደገና ወደ ወንጀል ድርጊታቸው እንዳልተመለሱ ዘግቧል።
የወኅኒ ቤቱ አስተዳዳሪ ምን አስተያየት ሰጠ? “የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ወህኒ ቤት የሚያከናውኑት ሥራ በጣም ተፈላጊና ጠቃሚ ነው” ብለዋል። የወህኒ ቤቱ አስተዳዳሪ “እስረኞቹ [ከምሥክሮቹ ጋር] መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናታቸውን ሲገፉበት ምግባራቸውና አቋማቸው ይለወጥና በሕይወታቸው ውስጥ መመሪያ የሚሆናቸውን አዲስ ኃይል ያገኛሉ። በጣም ዘዴኞችና ጨዋዎች ናቸው። ታታሪ ሠራተኞችና ችግር የማይፈጥሩ ናቸው” በማለት ተናግሯል። ባለ ሥልጣናት የሚሰጡት እንዲህ ያለው ገንቢ ሐሳብ በቮዉፍ ወህኒ ቤት ካሉት እስረኞች ጋር ተባብረው የሚሠሩትን ምሥክሮች በደስታ እንዲፈነድቁ አድርጓቸዋል።
ወደ እስር ቤቱ የሚሄዱት ምሥክሮች ኢየሱስ “የራሴን በጎች አውቃለሁ የራሴም በጎች ያውቁኛል፤ . . . ድምፄንም ይሰማሉ፣ አንድም መንጋ ይሆናሉ እረኛውም አንድ” በማለት የተናገራቸውን ቃላት ጠንቅቀው ያውቃሉ። (ዮሐንስ 10:14, 16) መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ በግ መሰል የሆኑ ሰዎችን ለመሰብሰብ የእስር ቤት ቅጥሮች እንኳን አያግዱትም። በቮዉፍ የሚኖሩ ምሥክሮች በዚህ አስደሳች አገልግሎት የመካፈል መብት በማግኘታቸው በጣም ደስተኞች ናቸው። እንዲሁም መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ይሖዋ ልባቸው እንደ ድንጋይ የጠጠረ ተጨማሪ ሰዎች ለመንግሥቱ ምሥራች ምላሽ እንዲሰጡ በማድረግ መባረኩን እንዲቀጥል ይመኛሉ።—ማቴዎስ 24:14
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
“እንደ ሕፃን የሚያደርገው አዋቂ”
“ብዙውን ጊዜ አንድ እስረኛ ለተወሰነ ጊዜ በእስር ቤት ከቆየ በኋላ በነፃነት ወይም በራስ ፈቃድ የመኖር ትርጉሙ ይጠፋዋል” በማለት በቮዉፍ ወህኒ ቤት የሚሠሩ ምሥክሮች ይናገራሉ። “ያለብን መሠረታዊ ችግር ከወህኒ ቤት የተለቀቀው ሰው ‘እንደ ሕፃን ልጅ’ ስለሚያደርገው እንዴት ራሱን ችሎ መኖር እንዳለበት አያውቅም። ጉባኤው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ብቻ የማይወሰነው ለዚህ ነው። ከኅብረተሰቡ ጋር እንዲቀላቀል ማድረግ እንዲሁም ሊገጥሙት ከሚችሉ አዳዲስ አደጋዎችና ፈተናዎች ራሱን እንዲጠብቅ ማስጠንቀቅ አለብን። እንደ ሕፃን እጁን ይዘን መምራት ባይኖርብንም አዲስ ሕይወት እንዲጀምር የመርዳት ግዴታ ግን አለብን።”