አንድ ምሁር የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ የተጻፈበትን ጊዜ አስተካከሉ
በፓፒረስ የተዘጋጁ ጥንታዊ ጽሑፎች ላይ ጥናት የሚያካሂዱት ጀርመናዊው ባለሙያ ካርስተን ፒተር ቴዲ እንዳሉት ከሆነ የማቴዎስ ወንጌል ክፍል የሆኑ ሦስት የፓፒረስ ቁርጥራጮች (የማግደለን ፓፒረስ ተብለው ይጠራሉ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለመጻፋቸው ጠንካራ ማስረጃ አለ።
ቴዲ የፓፒረስ ቁርጥራጮቹን (የማቴዎስ ምዕራፍ 26ን ክፍሎች የያዙ ናቸው) ግብጽ ውስጥ ከተገኘ ጥንታዊ ደብዳቤ ጋር ካነጻጸሩ በኋላ ይህ የግብጽ ሰነድ “በአጠቃላይ ገጽታውም ሆነ በእያንዳንዱ ፊደል ቅርጽና አጣጣል ከማግደለን ፓፒረስ ጋር ፍጹም ተመሳሳይ” እንደሆነ ገልጸዋል። ቴዲና ረዳት አዘጋጅ የሆኑት ማቲው ዳንኮን አይዊትነስ ቱ ጂሰስ—አሜዚንግ ኒው ማንስክሪፕት ኤቪደንስ አባውት ዚ ኦሪጂን ኦቭ ዘ ጎስፕልስ (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፋቸው ላይ በሁለቱ ሰነዶች መካከል ያለው ተመሳሳይነት ተቀራራቢ በሆነ ጊዜ ውስጥ መጻፋቸውን ያሳያል ብለው ደምድመዋል። መቼ? ይህ ደብዳቤ የተጻፈው “‘በገዥው በኔሮ 12ኛ ዓመት፣ ኤፒፍ 30’ ላይ ሲሆን በአሁኑ የቀን አቆጣጠር መሠረት ደግሞ ሐምሌ 24, 66 [እዘአ]” ነው።
“ይህ የቀን ቀመር ትክክል ከሆነ፣ የማቴዎስ ወንጌል ጥንታዊ ጽሑፍ የተጻፈበትን ጊዜ ደብዳቤው ከተጻፈበት መቶ ዘመን ጋር ስለሚያገናኘው ከፍተኛ ትርጉም ይኖረዋል” ሲሉ ፕሮፌሰር ፊሊፕ ደብልዩ ከምፈርት ቲንደል ቡሌቲን ላይ በወጣ ጽሑፍ ውስጥ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከዚህም በተጨማሪ የማግደለን ፓፒረስን እስካሁን ከተገኙት የወንጌል ቁርጥራጮች ረጅም ዕድሜ ያለው ያደርገዋል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የማግደለን ፓፒረስን ትክክለኛ መጠን ለማሳየት የቀረበ
[ምንጭ]
By permission of the President and Fellows of Magdalen College, Oxford