የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 12/15 ገጽ 26-29
  • የታካሚዎችን ምርጫ የሚያስከብር ውሳኔ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የታካሚዎችን ምርጫ የሚያስከብር ውሳኔ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሕዝባዊ ሥርዓትና ግብረ ገብነት
  • ያልተጠበቀ ማበረታቻ
  • ውሳኔው
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 12/15 ገጽ 26-29

የታካሚዎችን ምርጫ የሚያስከብር ውሳኔ

በአጽናፈ ዓለም ውስጥ የሁሉ የበላይ የሆነው አካል በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ ማድረግን ከማንም በላይ ይደግፋል። ይህ ከሁሉ በላይ የሆነው አካል ፈጣሪያችን ነው። ሰው የሚያስፈልገውን ነገር በሙሉ ጠንቅቆ የሚያውቀው ፈጣሪ በጥበብ ለመመላለስ የሚያስችል ትምህርት፣ ማስጠንቀቂያና መመሪያ አትረፍርፎ ይሰጣል። ያም ሆኖ የማሰብ ችሎታ ላላቸው ፍጥረቶቹ የሰጣቸውን የመምረጥ ነፃነት አይጋፋም። ነቢዩ ሙሴ እንደሚከተለው በማለት የአምላክን አመለካከት አንጸባርቋል:- “በፊታችሁ ሕይወትንና ሞትን በረከትንና መርገምን እንዳስቀመጥሁ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በአንተ ላይ አስመሰክራለሁ፤ እንግዲህ አንተና ዘርህ በሕይወት ትኖሩ ዘንድ ሕይወትን ምረጥ።”​—⁠ዘዳግም 30:​19

ይህ መሠረታዊ ሥርዓት በሕክምናውም ዘርፍ ይሠራል። በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ምርጫ ወይም በበቂ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ የማድረግ ጽንሰ ሐሳብ እምብዛም ባልተለመደባቸው እንደ ጃፓን በመሳሰሉ አገሮች ቀስ በቀስ ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል። ዶክተር ሚሺታሮ ናካሙራ በበቂ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ ሲባል “ታካሚው የሚደረግለትን የሕክምና ዓይነት የመምረጥ መብቱን ሳይጋፋ በቀላልና በሚገባ ቋንቋ በሽታውን፣ ያለውን የመዳን አጋጣሚ፣ የሕክምናውን ዘዴና ሊያስከትል የሚችለውን የጎንዮሽ ጉዳት ዶክተሩ ለታካሚው ያብራራለታል ማለት እንደሆነ” ገልጸዋል።​—⁠ጃፓን ሜዲካል ጆርናል

ለበርካታ ዓመታት በጃፓን የሚገኙ ዶክተሮች ታካሚዎችን በዚህ መንገድ የማከሙን አካሄድ ላለመከተል በርካታ ምክንያቶችን ሲደረድሩ ቆይተዋል። ፍርድ ቤቶችም በሕክምናው አካሄድ የመመራት ዝንባሌ ይታይባቸው ነበር። ስለሆነም በየካቲት 9, 1998 የቶኪዮው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋና ዳኛ የሆኑት ታኬኦ ኢናባ በሚገባ አውቆ ምርጫ የማድረግን መብት የሚያስከብር ውሳኔ ማሳለፋቸው ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ነበር። ይህ ውሳኔ ምን ነበር? ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት እንዲደርስ ያደረገውስ ምን ነበር?

በሐምሌ 1992 የይሖዋ ምሥክር የሆነችው የ63 ዓመቷ ሚሳኤ ታኬዳ በቶኪዮ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ሳይንስ ሆስፒታል ተቋም ውስጥ ለመታከም ትገባለች። በጉበቷ ላይ ለሕይወቷ አስጊ የሆነ ቂመኛ እበጥ እንዳለባት በመታወቁ የቀዶ ሕክምና ማድረግ ነበረባት። ደምን አለአግባብ መጠቀም የሚከለክለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ለመታዘዝ ካላት ልባዊ ፍላጎት በመነሳት ደምን የማይጨምር ሕክምና ለመውሰድ እንደምትፈልግ ለዶክተሮቹ በግልጽ ትነግራቸዋለች። (ዘፍጥረት 9:​3, 4፤ ሥራ 15:​29) ዶክተሮቹም ሆኑ ሆስፒታሉ በውሳኔዋ ምክንያት ከሚደርስባት ማንኛውም ነገር ነፃ መሆናቸውን የሚገልጽ ከተጠያቂነት ነፃ የሚያደርግ ሰነድ ተቀበሉ። ውሳኔዋንም እንደሚያከብሩ አረጋገጡላት።

ይሁን እንጂ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ሚሳኤ ከተሰጣት ማደንዘዣ ገና ሳትነቃ በሚገባ የተገለጸውን ፍላጎቷን በቀጥታ በመጣስ ደም ተሰጣት። አንድ የሆስፒታል ሠራተኛ ጉዳዩን ለአንድ የጋዜጣ ዘጋቢ በድብቅ በተናገረ ጊዜ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ደም የመስጠቱን ምስጢር በድብቅ ለመያዝ የተደረገው ጥረት ገሃድ ወጣ። ለመገመት እንደምትችሉት ይህች ቅን ክርስቲያን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ደም የተሰጣት መሆኑን ስትሰማ እጅግ አዘነች። የሕክምና ሠራተኞቹ ቃላቸውን እንደሚጠብቁና ጽኑ ሃይማኖታዊ አቋሟን እንደሚያከብሩላት ተማምና ነበር። በዶክተርና በታካሚ መካከል ያለውን ግንኙነት በከባድ ሁኔታ የሚጥሰው ይህ ድርጊት ባደረሰባት ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ምክንያትና ሌሎችን ተመሳሳይ ከሆነ የሕክምና በደል ለመታደግ የሚያስችል መሠረት ለመጣል ተስፋ በማድረግ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰደችው።

ሕዝባዊ ሥርዓትና ግብረ ገብነት

የቶኪዮ አውራጃ ፍርድ ቤት ሦስት ዳኞች ጉዳዩን ካዳመጡ በኋላ በበቂ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ የማድረግን መብት በመቃወም ለዶክተሮቹ ፈረዱ። መጋቢት 12, 1997 ባሳለፉት ውሳኔያቸው ላይ ያለ ምንም ደም ሕክምና ለመውሰድ የሚደረግ ስምምነት ውድቅ መሆኑን ገልጸዋል። አንድ ዶክተር አደገኛ ሁኔታ ቢከሰት እንኳ ደም ላለመስጠት የሚደረግ ልዩ ስምምነት ውስጥ መግባቱ ኮጆ ራዮዞኩa ወይም ማኅበራዊ የአቋም ደረጃዎችን መጣስ ይሆንበታል የሚል ምክንያት አቀረቡ። የአንድ ዶክተር ዋነኛ ግዴታ የተሻለ ነው የሚለውን የሕክምና ዘዴ ተጠቅሞ ሕይወትን ማዳን ስለሆነ የታካሚው ሃይማኖታዊ እምነት ምንም ይሁን ምን እንዲህ ያለው ስምምነት ቀድሞውኑም ቢሆን የተሳሳተ ነው የሚል አመለካከት ነበራቸው። አንድ ታካሚ ለመውሰድ ስለሚፈልገው ሕክምና አስቀድሞ ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ ቢያቀርብም በመጨረሻው ግምገማ ላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የአንድ ሐኪም ሙያዊ አመለካከት ሊሆን ይገባል የሚል ውሳኔ አስተላለፉ።

ከዚህም በላይ አንድ ሐኪም ሊደረግ ስለ ታቀደው የቀዶ ሕክምና መሠረታዊ ሂደት፣ ውጤትና አደጋ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቢጠበቅበትም ከላይ ከተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ በሆኑ ምክንያቶች “ደም ለመጠቀም ማሰቡን ወይም አለማሰቡን ከመናገር ሊታቀብ ይችላል” በማለት ዳኞቹ ገልጸዋል። የሰጡት ፍርድ እንዲህ የሚል ነበር:- “ከሳሽ በማንኛውም ሁኔታ ሥር ደም መውሰድ የማትፈልግ መሆኗን ተከሳሾቹ ዶክተሮች ቢረዱም ፍላጎቷን የሚያከብሩ መስለው በመቅረብ አጠያያቂ የሆነውን የቀዶ ሕክምና እንድትቀበል ማድረጋቸው ሕገ ወጥ ወይም ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ነው ሊባል አይችልም።” ሐኪሞቹ ከዚህ የተለየ እርምጃ ቢወስዱ ኖሮ ታካሚዋ የቀዶ ሕክምናውን ላለማድረግ ልትወስንና ሆስፒታሉን ትታ ልትሄድ ትችላለች የሚል አመለካከት ነበራቸው።

የፍርድ ቤቱ ብይን በበቂ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ የማድረግ መብትን የሚደግፉ ሰዎችን ያስደነገጠና ቅር ያሰኘ ነበር። በሲቪል ሕግ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ፕሮፌሰር ታኩኦ ያማዳ በታኬዳ ጉዳይ ላይ የተላለፈውን ብይንና በበቂ መረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ የማድረግ መብት በጃፓን ያለውን ትርጉም አስመልክተው ሲያብራሩ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ይህ ውሳኔ የሚያስተላልፈው ሐሳብ ይጽና ከተባለ ደም ለመውሰድ እምቢ ማለትና አውቆ የመስማማት መብት ሕጋዊ ደንብ በነፋስ ሊጠፋ እንደተቃረበ ጭል ጭል የሚል የሻማ ብርሃን ይሆናል።” (የሕግ መጽሔት ሆጋኩ ካዮሺትሱ) “አድብቶ ጥቃት ከመሰንዘር ጋር የሚመሳሰል በሌሎች ላይ ጨርሶ እምነት የሚያሳጣ ተግባር ነው” ሲሉ ከበድ ያሉ ቃላትን በመጠቀም በታኬዳ ላይ የተፈጸመውን ድርጊት ክፉኛ ኮንነውታል። ፕሮፌሰር ያማዳ እንዲህ ዓይነቱ በሌሎች ላይ እምነት የሚያሳጣ ድርጊት “ፈጽሞ እንዲኖር መፍቀድ” አይገባም ሲሉ አክለው ተናግረዋል።

ሚሳኤ በተፈጥሮዋ ትንሽ ዓይነ አፋርነት ስላለባት ስለ ጉዳይዋ የልቧን ለመናገር ተቸግራ ነበር። ሆኖም የደም ቅድስናን በሚመለከት ለይሖዋ ስምና ለጽድቅ መስፈርቶቹ ጥብቅና በመቆም ረገድ የድርሻዋን እንደምታበረክት በመገንዘብ የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ ወሰነች። ለሕግ ጠበቃዋ እንዲህ ስትል ጻፈች:- “እኔ ትቢያ፣ ከትቢያም ያነስኩ ነኝ። እንደ እኔ ያለው ምንም ችሎታ የሌለው ሰው ለምን እንደተመረጠ ይገርመኛል። ይሁንና ይሖዋ የሚናገረውን ለማድረግ እስከጣርኩ ድረስ ድንጋዮች እንኳ እንዲናገሩ ማድረግ የሚችለው አምላክ ኃይል ይሰጠኛል።” (ማቴዎስ 10:​18፤ ሉቃስ 19:​40) የፍርድ ጉዳዩ በተሰማበት ዕለት በምሥክርነት መስጫው ቦታ ላይ ሆና ቁርጥ ቁርጥ በሚል ድምፅ የተፈጸመባት የክህደት ድርጊት ያስከተለባትን የስሜት ጉዳት ገለጸች። “የተፈጸመብኝ በደል ተገድዶ በጾታ የመደፈር ያክል መጥፎ ስሜት አሳድሮብኛል።” የሰጠችው የምሥክርነት ቃል በፍርድ ቤቱ ውስጥ የነበሩትን ብዙዎቹን አስለቅሷል።

ያልተጠበቀ ማበረታቻ

የአውራጃ ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ ምክንያት ጉዳዩ ወዲያውኑ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ቀረበ። ሐምሌ 1997 ጉዳዩ በከፍተኛ ፍርድ ቤት በተሰማበት የመጀመሪያ ዕለት ግርጥት ያለችው ሆኖም ቆራጥ አቋም የነበራት ሚሳኤ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆና በዚያ ተገኝታ ነበር። ካንሰሩ ያገረሸባት ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜም እየተዳከመች በመሄድ ላይ ነበረች። ዋናው ዳኛ ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ ፍርድ ቤቱ ሊከተለው ስላሰበው አቅጣጫ ግልጽ ማብራሪያ በሰጡ ጊዜ ሚሳኤ እጅግ ተበረታታች። የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ አንድ ሐኪም የታካሚውን ፍላጎት የሚያሟላ መስሎ ከቀረበ በኋላ በድብቅ ሌላ ነገር በማድረግ የታካሚውን ፍላጎት የመጋፋት መብት አለው በሚለው የአውራጃ ፍርድ ቤቱ ሐሳብ እንደማይስማማ ዳኛው በግልጽ አስቀመጡ። ዋናው ዳኛ “ሺራሺሙ ቤካራዙ፣ ዮራሺሙ ቤሺ”b ማለትም “በሽተኞችን ምንም ሳትነግራቸው በሐኪም ላይ ብቻ እንዲመኩ” አድርጋቸው በሚለው መመሪያ ፍርድ ቤቱ እንደማይስማማ ገለጹ። ከጊዜ በኋላ ሚሳኤ እንዲህ ብላለች:- “ከአውራጃ ፍርድ ቤቱ ሙሉ በሙሉ የተለየ በሆነው በዳኛው ምክንያታዊ ሐሳብ በጣም ተደስቻለሁ። ወደ ይሖዋ ስጸልይ የነበረውም እንዲህ እንዲያደርግ ነበር።”

በሚቀጥለው ወር የሚወዷት ቤተሰቦቿና ከልብ የምታምንበትን ነገር በተረዱላትና ባከበሩላት የሌላ ሆስፒታል የሕክምና አባላት በተገኙበት ሚሳኤ አረፈች። ወንድ ልጅዋ ማሳሚ እና ሌሎች የቤተሰብ አባላት በመሞቷ እጅግ ቢያዝኑም ጉዳዩን ከእሷ ፍላጎት ጋር በሚስማማ መንገድ ዳር ለማድረስ ቆርጠው ተነሥተው ነበር።

ውሳኔው

በመጨረሻ በየካቲት 9, 1998 የከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስቱ ዳኞች የአውራጃው ፍርድ ቤቱን ውሳኔ የሚሽር ፍርድ ሰጡ። ትንሿ የፍርድ ቤቱ ክፍል በጋዜጠኞች፣ በምሁራንና ጉዳዩን ከመጀመሪያ ጀምሮ ይከታተሉ በነበሩ ሌሎች ሰዎች ተሞልታ ነበር። የታወቁ ጋዜጦችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለ ውሳኔው ዘግበዋል። አንዳንዶቹ ርዕሶች እንዲህ ይሉ ነበር:- “ፍርድ ቤት:- በሽተኞች አልታከምም ማለት ይችላሉ”፤ “ከፍተኛ ፍርድ ቤት:- ደም መስጠት መብት መጋፋት ነው”፤ “አስገድዶ ደም የሰጠ ዶክተር በፍርድ ቤት ተረታ”፤ እንዲሁም “የይሖዋ ምሥክር ደም ስለተሰጣት ካሣ ተቀበለች።”

በውሳኔው ላይ የቀረበው ሐሳብ ትክክልና ከሚጠበቀው በላይ ተስማሚ ነበር። ዘ ዴይሊ ዮሚውሪ የተባለው ጋዜጣ እንደሚከተለው ሲል ዘግቧል:- “ሐኪሞች ታካሚው የማይፈልጋቸውን የሕክምና ዓይነቶች ማከናወናቸው ተገቢ አይደለም በማለት ዳኛ ታኬኦ ኢናባ ተናግረዋል።” በተጨማሪም “[ደም] የሰጧት ሐኪሞች የምትፈልገውን የሕክምና ዓይነት የመምረጥ መብቷን ተጋፍተዋል” ሲል በግልጽ አትቷል።

አሳሂ ሺምቡን የተባለው ጋዜጣ እንዳመለከተው በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለቱም ወገኖች ለሕይወት አስጊ የሆነ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ ደምን ላለመጠቀም መስማማታቸውን የሚገልጽ ውል መኖሩን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ እንደሌለ ፍርድ ቤቱ ቢያምንም ዳኞቹ እንዲህ ባለው ውል ሕጋዊነት ላይ ከአውራጃው ፍርድ ቤት ጋር እንደማይስማሙ ገልጸዋል:- “በማንኛውም ሁኔታ ሥር ደም መሰጠት የሌለበት መሆኑን በግልጽ የሚያስቀምጥ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ወገኖች መካከል የተደረገ ስምምነት ካለ ይህ ፍርድ ቤት ስምምነቱን ሕዝባዊ ሥርዓትን የሚጥስና ሕጋዊነት የሌለው አድርጎ የሚመለከትበት ምክንያት የለውም።” ከዚህም በላይ ጋዜጣው “እያንዳንዱ ሰው የሚሞትበት የተወሰነ ቀን ያለው ሲሆን ወደዚህ ሞት የሚደረገው ሂደት በእያንዳንዱ ግለሰብ ሊወሰን ይችላል” የሚለውን የዳኞቹን አመለካከት አንጸባርቋል።

የይሖዋ ምሥክሮች በጉዳዩ ላይ ምርምር አካሂደዋል፤ ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት መንገድ እንደመረጡም ያምናሉ። ይህ ደግሞ ደምን በደም ሥር መውሰድ የሚያስከትላቸውን የታወቁ አደጋዎች መከላከልንና ከዚህ ይልቅ በብዙ አገሮች በስፋት የሚሠራባቸውንና ከአምላክ ሕግ ጋር የሚስማሙትን ደም አልባ ዝግጅቶች መቀበልን ይጨምራል። (ሥራ 21:​25) አንድ የታወቁ ጃፓናዊ የሕገ መንግሥት ፕሮፌሰር እንዳመለከቱት “እንደ እውነቱ ከሆነ በጥያቄ ላይ ያለውን ሕክምና [ደምን በደም ሥር መውሰድ] አለመቀበል ‘እንዴት መሞት’ እንዳለብን የሚደረግ ምርጫ ከመሆን ይልቅ እንዴት መኖር እንዳለብን የሚደረግ ምርጫ ነው” በማለት ተናግረዋል።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ሐኪሞች ያላቸው ሕጋዊ መብት አንዳንዶች እንደሚያስቡት ሰፊ አለመሆኑን እንዲያስተውሉ ሊያደርጋቸው ይገባል። እንዲሁም በጣም ብዙ የሆኑ ሆስፒታሎች የሥነ ምግባር ደንቦችን እንዲያወጡ ሊያደርጋቸው ይገባል። ይህ የፍርድ ቤት ብያኔ በአጠቃላይ ተቀባይነት ያገኘና የሚወስዱትን የሕክምና ዓይነት የመምረጥ መብት የተነፈጉትን ታካሚዎች የሚያበረታታ ቢሆንም ውሳኔው ተቀባይነት ያገኘው በሁሉም ወገኖች አይደለም። በመንግሥት የሚመራው ሆስፒታልና ሦስቱ ሐኪሞች ጉዳዩን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለዋል። ስለዚህ የጃፓኑ የመጨረሻው ከፍተኛ ፍርድ ቤትም እንደ አጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ የታካሚዎችን መብት የሚደግፍ መሆን አለመሆኑን ለማየት መጠበቅ አለብን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ሕጋዊ ትርጉም የሌለውና የሕግ ባለ ሥልጣኑ እንዲተረጉመውና ተግባራዊ እንዲያደርገው የተተወ ሐሳብ።

b ይህ በቶኩጋዋ ዘመን የነበሩ ከበርቴዎች የበታቾቻቸውን እንዴት አድርገው መግዛት እንዳለባቸው የሚገልጽ ደንብ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ