ማስጠንቀቂያውን ሰምተህ እርምጃ ትወስዳለህን?
ግንቦት 19, 1997 አንድ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ባንግላዴሽ ውስጥ የቺታጎንግን አውራጃ መታ። በካክስ በዛር ከተማ ላይ በሰዓት ወደ 250 ኪሎ ሜትር በሚጠጋ ፍጥነት የሚጓዝ ነፋስ ተመዝግቦ ነበር። በገጠር አካባቢዎች የነበሩ የሳር ክዳን ጎጆዎች ቀድሞ የነበሩበትን ቦታ ከሚጠቁም ትንሽ የጭቃ ምልክት በስተቀር ድምጥማጣቸው ጠፍቷል። ዛፎችና የስልክ እንጨቶች ከሥራቸው ተመንግለዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ልክ እንደ ክብሪት እንጨት ስብርብር ብለዋል። በቮራር ካውጅ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ ዜና በአውሎ ነፋሱ ሳቢያ 105 ሰዎች መሞታቸውን ዘግቧል።
የአየር ትንበያ አገልግሎት ከ36 ሰዓታት ገደማ በፊት በአውሎ ነፋሱ ሊጠቁ የሚችሉትን አካባቢዎች በዜና ማሰራጫዎች አሳውቆ ነበር። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአርማታ በተሠሩ የአውሎ ነፋስ መከለያዎች ውስጥ ገብተው በመጠለላቸው ብዙ ሕይወት ሊተርፍ እንደቻለ ምንም ጥርጥር የለውም።
የይሖዋ ምሥክሮች ከአንድ መቶ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ከማንኛውም አውሎ ነፋስ ይበልጥ እጅግ አውዳሚ የሆነ ጥፋት በመምጣት ላይ እንዳለ የሚገልጽ ዜና ሲያሰራጩ ቆይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጥፋት “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን” ሲል ይጠራዋል። (ኢዩኤል 2:31) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ትንቢታዊ የማስጠንቀቂያ መልእክቶች በመቀበል ከቁጣው ለመትረፍ እንችል ይሆናል።—ሶፎንያስ 2:2, 3
የይሖዋ ምሥክሮች ጥፋት የሚያውጁ ነቢያት አይደሉም። እነርሱ የሚያውጁት ተስፋ የያዘ መልእክት ነው። በቅርቡ ምድርን ከማንኛውም የክፋት ድርጊት ስለሚያጸዳው የአምላክ መንግሥት ሰዎች እንዲማሩ ለመርዳት ይፈልጋሉ። የአምላክ ቃል፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም፤ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:10, 11
[በገጽ 32 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
WHO/League of Red Cross