በአምላክ የሕይወት መንገድ ለመሄድ የቆረጠ ሕዝብ
“የአምላክ የሕይወት መንገድ” የአውራጃ ስብሰባ አምላክን ማገልገል ለሚፈልጉ ሁሉ ያበረከተው ነገር እንዲህ በቀላሉ የሚገመት አይደለም! አንዲት ልዑክ ስለ ስብሰባው ስትናገር “ግሩም የሆነ ትምህርት፣ ማበረታቻና እውቀት ያገኘንበት ወቅት ነበር” ብላለች።
አንድ ሌላ ልዑክ ደግሞ “የምንደሰትባቸው፣ የምናሰላስልባቸውና በአእምሮአችን ይዘናቸው የምንሄዳቸው በርካታ ነገሮች ነበሩ” በማለት ተናግሯል። እስቲ አሁን ደግሞ ፕሮግራሙን አንድ በአንድ እንመርምር።
ኢየሱስ ክርስቶስ—መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነው
ይህ የስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ጭብጥ ነበር። (ዮሐንስ 14:6) የመጀመሪያው ንግግር በስብሰባው ላይ የተገኘንበትን ዓላማ ማለትም ከሁሉም የተሻለ የሕይወት መንገድ ስለሆነው ስለ አምላክ የሕይወት መንገድ ተጨማሪ ትምህርት ለማግኘት መሆኑን ገልጾ ነበር። ይሖዋ በእሱ መንገዶች እንዴት መጓዝ እንደሚቻል ለሕዝቦቹ ያስተምራል። ይህንንም የሚያደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (ማቴዎስ 24:45-47፤ ሉቃስ 4:1፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) ከአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ መማር ምንኛ ታላቅ መብት ነው!
የጭብጡ ቁልፍ ንግግር ከዕለቱ ጭብጥ ጋር በመስማማት “የክርስቶስ ቤዛ—የአምላክ የመዳን መንገድ” የሚል ነበር። ከአምላክ የሕይወት መንገድ ጋር ለመስማማት ኢየሱስ ክርስቶስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ የሚጫወተውን ሚና ማወቁ እጅግ አስፈላጊ ነው። ተናጋሪው እንዲህ ብሎ ነበር:- “የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ባይኖር ማንም ሰው፣ ምንም ዓይነት እምነት ወይም ምግባር ቢኖረው፣ ከአምላክ የዘላለም ሕይወት ሊያገኝ አይችልም።” ከዚያም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” የሚለውን በዮሐንስ 3:16 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ጠቀሰ። በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ማመን ስለ እውነት ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ይጠይቃል። ከዚህም በተጨማሪ ሕይወትን ለይሖዋ መወሰንንና ይህንንም በውኃ ጥምቀት ማሳየትን እንዲሁም ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወው ምሳሌ ጋር ተስማምቶ መኖርን ይጠይቃል።—1 ጴጥሮስ 2:21
የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የጀመረው “የፍቅር መንገድ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” የሚል ርዕስ ባለው ንግግር ነበር። ይህ ንግግር ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 13:4-8 ላይ ስለ ፍቅር በዝርዝር ያሰፈረውን ስሜት ቀስቃሽ ጥቅስ ቁጥር በቁጥር የሚያብራራ ነበር። ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የክርስትና መለያ ገጽታ እንደሆነና አምላክንና ጎረቤትን መውደድ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አምልኮ ለማቅረብ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ አድማጮችን አሳስቧል።
ከዚያም “ወላጆች—በልጆቻችሁ አእምሮ ውስጥ የአምላክን መንገድ ቅረጹ” የሚል ርዕስ ያለው ባለ ሦስት ክፍል ሲምፖዚየም ቀረበ። ወላጆች የአምላክን ቃል በማንበብና በማጥናት ጥሩ ምሳሌ በመተው ልጆቻቸው አምላክን እንዲያገለግሉ መርዳት ይችላሉ። ዘወትር የቤተሰብ ጥናት በማድረግና ጥናቱም የቤተሰቡን ፍላጎት እንዲያሟላ እንደሁኔታው በመለዋወጥ እውነትን በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ሊቀርጹ ይችላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ልጆች በጉባኤ እንቅስቃሴዎችና በመስክ አገልግሎት እንዲካፈሉ መርዳትም በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ልጆች ማሳደግ ተፈታታኝ ቢሆንም እንዲህ ማድረጉ ግን ከፍተኛ በረከት ያስገኛል።
ከዚህ ሲምፖዚየም ቀጥሎ “ይሖዋ ክብራማ ለሆነ አገልግሎት እንዲጠቀምባችሁ ፍቀዱለት” የሚል ንግግር ቀረበ። አንድ ሸክላ ሠሪ ለአንድ የሸክላ ዕቃ ቅርጽ እንደሚያወጣ ሁሉ አምላክም እርሱን ለማገልገል ፈቃደኞች የሆኑትን ሁሉ ይቀርጻቸዋል። (ሮሜ 9:20, 21) ይህንንም የሚያደርገው በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት ምክር በመስጠት ነው። ራሳችንን የምናቀርብ፣ አጋጣሚዎች ሲገኙ ቶሎ ምላሽ የምንሰጥና ይሖዋ እርምጃችንን እንዲመራልን የምንፈቅድ ከሆነ ችሎታችንን ሙሉ በሙሉ እንድንጠቀምበት ይረዳናል።
“በሚስዮናውያን መስክ ያለው የአገልግሎት እንቅስቃሴ” የሚለው ስሜት የሚቀሰቅስ ክፍል ቀጥሎ ቀረበ። በአሁኑ ጊዜ በምድር ዙሪያ በሚገኙ 148 አገሮች ሚስዮናዊ የሚባሉ 2,390 ክርስቲያን አገልጋዮች አሉ። እጅግ ድንቅ የሆነ የታማኝነትና የቅንዓት ምሳሌ ያሳዩ ሲሆን ውጭ አገር በሚገኙ መስኮች እንዲያገለግሉ መብት ማግኘታቸውን በታላቅ አድናቆት ይመለከቱታል። ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በተደረገባቸው ቦታዎች ይህ ክፍል በቀረበበት ወቅት ሚስዮናውያን በሚስዮናዊ ሕይወታቸው ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎችና ደስታዎች ተናግረዋል።
የመጀመሪያው ቀን የመደምደሚያ ንግግር “ከሞት በኋላ ሕይወት አለ?” የሚል ርዕስ ነበረው። ይህ ጥያቄ የሰውን ልጅ ለብዙ ሺህ ዓመታት ግራ ሲያጋባ ቆይቷል። በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ይህን ርዕሰ ጉዳይ ሲያወጡና ሲያወርዱ ኖረዋል። ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡት መልሶች በርካታ ናቸው። መልሶቹ እንደ መልስ ሰጪዎቹ ባሕልና ሃይማኖት የሚለያዩ ናቸው። ሆኖም ሰዎች እውነትን ማወቅ ይኖርባቸዋል።
በመሆኑም ተናጋሪው ስንሞት ምን እንሆናለን? የሚል ርዕስ ያለው በሥዕል የተዋበ ባለ 32 ገጽ ብሮሹር መውጣቱን አስታወቀ። ይህ ብሮሹር ነፍስ አትሞትም የሚለውን ትምህርት ሥረ መሠረት የሚገልጽ ከመሆኑም በላይ ጽንሰ ሐሳቡ በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአብዛኞቹ ሃይማኖቶች ዋነኛ ትምህርት ሊሆን የቻለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል። ብሮሹሩ ግልጽና አሳማኝ በሆነ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ፣ ስለ ሞትና ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት የሚናገረውን ያብራራል። ከዚህም በተጨማሪ ብሮሹሩ የወደፊቱ ጊዜ ለሙታንና በሕይወት ላሉት ምን ተስፋ እንደያዘላቸው ይገልጻል። በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ እውነትን ለተጠሙ ሰዎች ይህ ጽሑፍ ምንኛ በረከት ነው!
እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ
ለሁለተኛው የስብሰባ ቀን ይህ ጭብጥ ምንኛ ተስማሚ ነበር! (ኤፌሶን 5:15) የጠዋቱ ፕሮግራም በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ላይ ያተኮረ ነበር። በዕለት ጥቅሱ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ “ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ እንዲጓዙ ሰዎችን መርዳት” በሚለው ንግግር ፕሮግራሙ ቀጠለ። ይህን አጣዳፊ ሥራ ለማከናወን ይሆናል የሚል አመለካከት መያዝና እውነትን ለሌሎች ማካፈል መብትም ግዴታም መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች የአምላክን ቃል ለመቀበል አሻፈረን ብለው ነበር። ይሁን እንጂ ተቃውሞ እያለም እንኳ ‘ለዘላለም ሕይወት ዝንባሌ የነበራቸውና አማኝ የሆኑ’ ሰዎች ነበሩ። (ሥራ 13:48, 50፤ 14:1-5) ዛሬም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መቀበል ባይፈልጉም ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎችን መፈለጋችንን እንቀጥላለን።—ማቴዎስ 10:11-13
ቀጣዩ ንግግር ሰዎችን አግኝቶ የሕይወት መልእክት እንዲደርሳቸው ማድረግ ያለውን ተፈታታኝ ሁኔታ የሚያብራራ ነበር። ሰዎችን እቤታቸው ማግኘቱ አስቸጋሪ እየሆነ ስለመጣ በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎችን አግኝተን የመንግሥቱን መልእክት ለመንገር ጥበበኞችና ዘዴኞች መሆን ይኖርብናል። በብዙ አገሮች የሚኖሩ የምሥራቹ አስፋፊዎች በስልክና በንግድ አካባቢዎች በመስበክ ጥሩ ውጤቶችን አግኝተዋል። እንዲህ በማድረጋቸውም በሌላ መንገድ ሊያገኟቸው የማይችሏቸውን ሰዎች አግኝተው ለማነጋገር ችለዋል።
“ደቀ መዛሙርት የሚሆኑ ሰዎች ክርስቶስ ያዘዘውን ሁሉ እንዲጠብቁ ማስተማር” የሚለው ንግግር በአገልግሎታችን ጥሩ ችሎታ የማዳበርን አስፈላጊነት የሚያብራራ ነበር። ከሌሎች ስንማርና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ የምናገኛቸውን ግሩም ማሰልጠኛዎች በሥራ ላይ ስናውል የማስተማር ችሎታችን ይዳብራል። የማስተማር ችሎታችንን እያዳበርን በሄድን መጠን ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲማሩ ለመርዳት በምናከናውነው ሥራ ተጨማሪ ደስታና እርካታ እናገኛለን።
የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ የተጠናቀቀው ራስን ወስኖ መጠመቅ ያለውን ትርጉም በሚገልጽ ንግግር ነበር። ተናጋሪው ጎላ አድርጎ ከገለጻቸው ነጥቦች መካከል አንዱ በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ ከተማመንና ፈቃዱን ለመፈጸም ከልብ ከተጣጣርን እርሱ ይባርከናል እንዲሁም ይደግፈናል የሚል ነው። ጠቢቡ ሰው “በመንገድህ ሁሉ እርሱን [አምላክን] እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 3:6) የስብሰባው ጉልህ ክፍል የነበረው አስደሳች የጥምቀት ሥነ ሥርዓትም ብዙዎች በአምላክ የሕይወት መንገድ መጓዝ እንደጀመሩ የሚያሳይ ነበር።
ከምሳ ሰዓቱ ዕረፍት በኋላ የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም “የዘላለም ሕይወትን ተስፋ በማድረግ ማገልገል” በሚል ንግግር ጀመረ። አምላክ በምድር ላይ ለዘላለም የሚያገለግሉት ታዛዥ ሰዎች እንዲኖሩት የነበረው ዓላማ ፍጻሜውን ያገኛል። ስለዚህ አስተሳሰባችንን፣ እቅዳችንንና ተስፋችንን ይሖዋን ለዘላለም በማገልገል ላይ እንዲያተኩር ማድረጉ ምንኛ ተገቢ ነው! ‘የይሖዋን ቀን’ በአእምሯችን አቅርበን መመልከት የምንፈልግ ብንሆንም ዋነኛው ግባችን ግን ዘላለም ማገልገል እንደሆነ ማስታወሳችን እጅግ አስፈላጊ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:12) ኢየሱስ የአምላክን የቅጣት ፍርድ የሚያስፈጽምበትን ትክክለኛ ጊዜ አለማወቃችን ሁልጊዜ ንቁ ሆነን እንድንመላለስ ያደርገናል፤ እንዲሁም ይሖዋን የምናገለግለው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ውስጣዊ ግፊት መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል አጋጣሚ በየዕለቱ ይሰጠናል።
ቀጥለው የቀረቡት ሁለት ንግግሮች ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን የጻፈውን ደብዳቤ 4ኛ ምዕራፍ የሚመረምሩ ነበሩ። ከተብራሩት ነገሮች መካከል በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው “የወንዶች ስጦታ” በማግኘት የተባረክን መሆናችንን የሚገልጽ ነበር። እነዚህ ሽማግሌዎች ለመንፈሳዊ ጥቅማችን ሲሉ ምክርና መመሪያ ይሰጡናል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የጳውሎስ ደብዳቤ ክርስቲያኖች “አዲሱን ሰው” እንዲለብሱ የሚያበረታታም ነበር። (ኤፌሶን 4:8, 24) አምላካዊ ባሕርይ እንደ ርኅራኄ፣ ደግነት፣ ትህትና፣ ትዕግሥትና ፍቅር የመሰሉ ባሕርያትን የሚያጠቃልል ነው።—ቆላስይስ 3:12-14
እንዴት እንደምንመላለስ መጠንቀቃችን ከዓለም እድፍ ራሳችንን መጠበቅንም የሚጨምር ነው። ቀጣዩ ንግግር በዚህ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር። በመዝናኛ ምርጫ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮችና በቁሳዊ ፍላጎት ረገድ ሚዛንን መጠበቁ አስፈላጊ ነው። ከዓለም እድፍ ራስን ስለመጠበቅ የሚናገረውን በያዕቆብ 1:27 ላይ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ በማዋል በአምላክ ፊት ንጹህ አቋምና ንጹሕ ሕሊና ይኖረናል። በተጨማሪም ዓላማ ያለው ሕይወት ይዘን እንድንመላለስ ይረዳናል እንዲሁም ሰላም፣ መንፈሳዊ ብልጽግናና ግሩም ባልንጀሮች በማግኘት እንባረካለን።
ከዚያም “ወጣቶች—የአምላክን መንገድ ተከተሉ” የሚል ርዕስ ያለው ሦስት ክፍል ያለው ሲምፖዚየም ቀጥሎ ቀረበ። አምላክ እንደሚወዳቸውና ንጹሑን አምልኮ ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚያደንቅ በማወቅ ወጣቶች እርሱን በታማኝነት ለማገልገል የማስተዋል ችሎታቸውን ማዳበር ይኖርባቸዋል። የማስተዋል ችሎታ የሚዳብርበት አንደኛው መንገድ የአምላክን ቃል በየዕለቱ በማንበብና በማሰላሰል ነው። ይህን ካደረግን የይሖዋን መንገዶች ለማወቅ እንችላለን። (መዝሙር 119:9-11) ከዚህም በተጨማሪ የማስተዋል ችሎታ ወላጆች፣ ሽማግሌዎችና ማኅበሩ የሚያወጣቸው ጽሑፎች የሚሰጡትን የበሰለ ምክር በመቀበል ይዳብራል። ወጣቶች በማስተዋል ችሎታቸው በትክክለኛው መንገድ በመጠቀም በቁሳዊ ሀብት፣ ርኩስ በሆኑ ንግግሮችና ከአምላክ የራቀው ዓለም በሚታወቅበት መዝናኛ እንዳይጠመዱ ይከላከላሉ። የአምላክን የሕይወት መንገድ በመከተል ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን እውነተኛ ስኬት ላይ ሊደርሱ ይችላሉ።
የዕለቱ የመጨረሻ ንግግር “የፈጣሪ ባሕርያትና መንገዶቹ” የሚል ነበር። በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጣሪን የማያውቁ መሆናቸውን ከገለጸ በኋላ ተናጋሪው እንዲህ አለ:- “የሕይወትን እውነተኛ ትርጉም ማወቅ የሚቻለው ግላዊ ሕልውና ያለውን ፈጣሪ አምላካችንን በማወቅ፣ ባሕርያቱን በመገንዘብና ከመንገዶቹ ጋር ተስማምቶ በመኖር ነው። . . . ሰዎች ፈጣሪን እንዲቀበሉና ከእርሱ ጋር በተያያዘ የሕይወትን ትርጉም እንዲያገኙ ለመርዳት ልትጠቀሙባቸው የምትችሏቸው ዓላማችንን የሚመለከቱ ሐቆች አሉ።” ከዚያም ተናጋሪው ጠቢብና አፍቃሪ የሆነ ፈጣሪ መኖሩን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ጠቀሰ። ንግግሩ ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? የሚል መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) መውጣቱን በማብሰር ተደመደመ።
“መንገዱ ይህች ናት። በእርሷም ሂድ”
ይህ የስብሰባው ሦስተኛ ቀን ጭብጥ ነበር። (ኢሳይያስ 30:21) ፕሮግራሙ የጀመረው ሕዝቅኤል ባየው የቤተ መቅደስ ራእይ ላይ በሚያተኩሩ ስሜት ቀስቃሽ በሆኑ ሦስት ንግግሮች ባሉት ሲምፖዚየም ነበር። ይህ ራእይ በጊዜያችን ስላለው ንጹሕ አምልኮ የሚያብራራ በመሆኑ ዛሬ ለሚኖሩት የአምላክ ሕዝቦች ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። የራእዩ ቁልፍ ትርጉም የሚከተለው ነው:- ታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያደረገውን ዝግጅት የሚያመለክት ነው። ራእዩ የያዘው የተለያዩ ገጽታዎች እየተብራሩ ሲሄዱ አድማጮች አፍቃሪ የሆኑት ቅቡዓን ቀሪዎችና ወደፊት የአለቃው ክፍል አባላት የሚሆኑት የሚያከናውኑትን ሥራ በመደገፍ ረገድ እያደረጉ ያለውን እንቅስቃሴ እንዲያስቡ አደረጋቸው።
ረፋዱ ላይ ጥንታዊ ልብስ የለበሱ ተዋንያን የተካፈሉበት አስደሳች የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ቀረበ። ድራማው “ቤተሰቦች—በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሕይወታችሁ መንገድ ይሁን!” የሚል ርዕስ ነበረው። ድራማው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ወድቀው ለመስገድ ፈቃደኛ ያልሆኑት ሦስቱ ዕብራውያን ያሳዩትን እምነትና ድፍረት የሚገልጽ ነበር። የድራማው ዋነኛ ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስ በጥንታዊ ታሪክ የተሞላ ተራ መጽሐፍ አለመሆኑን ብቻ ሳይሆን በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ወጣቶችንና አዋቂ ሰዎችን በትክክል የሚጠቅም ምክር የያዘ መጽሐፍ መሆኑን ማሳየት ነበር።
የከሰዓት በኋላው ክፍለ ጊዜ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ብቸኛ መንገድ” የሚለው የሕዝብ ንግግር የሚቀርብበት ወቅት ነበር። የሰው ዘር ለኃጢአትና ለሞት የተዳረገበትን ታሪክ ከጠቀሰ በኋላ ተናጋሪው የሚከተለውን ስሜት ቀስቃሽ ቃላት በመናገር ንግግሩን ደመደመ። “የዛሬው ቀን ስብሰባ ጭብጥ የተመሠረተበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ኢሳይያስ ምዕራፍ 30 ቁጥር 21 ነው። ‘ወደ ቀኝም ወደ ግራም ፈቀቅ ብትል ጆሮችህ በኋላህ:- መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ የሚለውን ቃል ይሰማሉ’ ይላል። ይህን ቃል የምንሰማው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በማዳመጥና ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ አምላክ በቃሉና በዘመናዊ ክርስቲያን ድርጅቱ በኩል የሚሰጠንን መመሪያ በመከተል ነው። በእርግጥም ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሰው መንገድ ይህ ብቻ ነው።”
የሳምንቱ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ርዕሰ ትምህርት ፍሬ ሐሳቦች ከቀረቡ በኋላ “በይሖዋ መንገድ መጓዛችሁን ቀጥሉ” በሚል ርዕስ የመደምደሚያው ንግግር ቀረበ። በፕሮግራሙ ውስጥ የቀረቡትን ዋና ዋና ነጥቦች በአጭሩ ከለሰ። ከዚያም ተናጋሪው በአምላክ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግን የሚገልጽ የአቋም መግለጫ አቀረበ።
የአቋም መግለጫው በእነዚህ ስሜት ቀስቃሽ ቃላት ተደመደመ። “ይህንን የአቋም መግለጫ ያወጣነው ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን፣ ምክሮችንና ማሳሰቢያዎችን ተከትሎ መኖር በዛሬው ጊዜ የተሻለ ሕይወት ለመምራትና ወደፊትም እውነተኛውን ሕይወት አጥብቀን ለመያዝ እንችል ዘንድ መልካም መሠረት እንደሚጥልልን አጥብቀን ስለምናምን ነው። ከሁሉም በላይ ይህን የአቋም መግለጫ ያወጣነው አምላካችንን ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ ሐሳባችንና ኃይላችን ስለምንወድ ነው!” ሁሉም ተሰብሳቢዎች በሚያስተጋባ ድምፅ አዎን! በማለት ከአቋም መግለጫው ጋር የሚስማሙ መሆናቸውን አረጋገጡ።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን?
በዚህ ርዕስ የወጣው አዲስ መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ይሖዋ የተባለ ፈጣሪ መኖሩን የሚያረጋግጥ አሳማኝ ማስረጃ ያቀርባል እንዲሁም ስለ ባሕርያቱ ማብራሪያ ይሰጣል። መጽሐፉ የተዘጋጀው በተለይ ከፍተኛ ዓለማዊ ትምህርት ላላቸውና በአምላክ ለማያምኑ ሰዎች ነው። ከዚህም በተጨማሪ ይህ 192 ገጽ ያለው መጽሐፍ በአምላክ የሚያምኑ ግለሰቦችን እምነት ይበልጥ በማሳደግ ለባሕርያቱና ለመንገዶቹ አድናቆት ይገነባላቸዋል።
ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? የተባለው መጽሐፍ አንባቢዎቹ በአምላክ ያምናሉ በሚል ሐሳብ ላይ ተመርኩዞ ሐሳብ አይሰጥም። ከዚያ ይልቅ የቅርብ ጊዜ ሳይንሳዊ ግኝቶችና ጽንሰ ሐሳቦች የአምላክን መኖር እንዴት እንደሚያረጋግጡ ያብራራል። በመጽሐፉ ውስጥ ከተካተቱት ርዕሶች መካከል “ሕይወትህ ትርጉም ያለው ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?፣” “አጽናፈ ዓለማችን የተገኘው እንዴት ነው?—አከራካሪው ጉዳይ፣” “አፈጣጠርህ ምን ያህል ልዩ ነው!” የሚሉት ይገኙበታል። ሌሎች ምዕራፎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ምንጭ አለው ብለን በእርግጠኝነት ማመን የምንችለው ለምን እንደሆነ ማብራሪያ ይሰጣሉ። ከዚህም በተጨማሪ አዲሱ መጽሐፍ የፈጣሪን ባሕርይና መንገዶች የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስን ይዘት ጠቅለል አድርጎ ያቀርባል። መጽሐፉ አምላክ ሥቃይና መከራን ለምን እንደፈቀደ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነም ማብራሪያ ይሰጣል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ብዙ ሰዎች ተጠምቀዋል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ኤ ዲ ሽሮደር አዲስ ብሮሹር መውጣቱን ሲያስታውቅ
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ስሜት ቀስቃሽ የነበረው ድራማ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን አበረታቷል