በዓረማዊ መሠረት ላይ መገንባት
በኢጣሊያ ሮም ጎብኚዎች ከሚያዩዋቸው በርካታ አስደናቂ ታሪካዊ ሕንፃዎች አንዱ ፓንቲየን ነው። ይህ የሮማውያን የስነ ሕንፃ (architecture) ውጤት የሆነው ታላቅ ቅርስ በዚያ ከሚገኙት በአመዛኙ ጥንት የነበራቸውን ይዘት ጠብቀው ከቆዩ ጥቂት ሕንፃዎች መካከል አንዱ ነው። የሕንፃው ግንባታ በ27 ከዘአበ ገደማ በአግሪጳ ተጀምሮ በ120 እዘአ አካባቢ በሃድሪያን ተጠናቀቀ። የሕንፃው አንድ አስደናቂ ገጽታ 43 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ግዙፍ ጉልላት ሲሆን ከዚህ የሚበልጥ ስፋት ያለው ጉልላት የተሠራው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቻ ነው። ፓንቲየን ከስረ መሠረቱ የአረማውያን ቤተ መቅደስ ሲሆን መሠረታዊው የግሪክኛ ቃል “የአማልክት ሁሉ መነሐሪያ” የሚል ትርጉም አለው። በዛሬው ጊዜ ሕንፃው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደሆነ ተደርጎ ይታያል። ይህን የመሰለ አስገራሚ ለውጥ ሊካሄድ የቻለው እንዴት ነው?
በ609 እዘአ ሊቀ ጳጳስ ቦኒፌስ አራተኛ ለረጅም ጊዜ ተዘግቶ የቆየውን ይህን ቤተ መቅደስ “የክርስቲያኖች” ቤተ ክርስቲያን በማድረግ እንደገና መርቀው ከፈቱት። በዚህ ጊዜ የሳንታ ማሪያ ሮቱንዳ ቤተ ክርስቲያን የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር። በ1900 ላ ቺቪልታ ካቶሊካ በተባለው የኢጣሊያ ጀስዊት መጽሔት ላይ ታትሞ የወጣ አንድ ርዕስ እንደዘገበው ቦኒፌስ በዚህ ቤተ መቅደስ ለመጠቀም የተነሳሱበት ዓብይ ዓላማ “በክርስትናው መስክ ሰማዕት ለሆኑት በሙሉ በሌላ አባባል ለጻድቃን ባጠቃላይ፣ በአንደኛ ደረጃ ደግሞ ለድንግል ወላዲተ አምላክ ውዳሴ ማቅረቢያ” ሆኖ እንዲያገለግል ነበር። ዛሬ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለፓንቲየን የሰጠቻቸው ሳንታ ማሪያ አድ ማርቴሬስ ወይም ሌላው ደግሞ ሳንታ ማሪያ ሮቱንዳ የሚሉት ስያሜዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነውን ዓላማ ያንጸባርቃሉ።—ከሥራ 14:8-15 ጋር አወዳድር።
ይኸው ጽሑፍ ፓንቲየንን ለታቀደለት አዲስ ዓላማ ምቹ ለማድረግ “ብዙ ማስተካከያ ማድረግ አላስፈለገም” በማለት አትቷል። “ቦኒፌስ ያደረጉት ነገር ቢኖር አረማዊ ቤተ መቅደሶችን ለክርስትና አምልኮ መገልገያነት በመቀየር ረገድ ሊቅ እና አርአያ የሚሆኑት ቀደምታቸው ታላቁ ቅዱስ ግሪጎሪ [ሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪ አንደኛ] አስቀድመው የደነገጓቸውን ያልተንዛዙና የመቻቻል መንፈስ የሚንጸባረቅባቸውን መመሪያዎች መከተል ነበር።” እነዚህ መመሪያዎች ምን ነበሩ?
በ601 እዘአ ግሪጎሪ፣ አረማዊ ወደሆነችው ብሪታንያ ለሚያቀናው ሚስዮናዊ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ይህን መመሪያ አስተላልፈው ነበር:- “በተጠቀሰችው አገር ውስጥ የሚገኙትን የጣዖት ማምለኪያ ቤተ መቅደሶች ማፍረስ የለባችሁም፤ ከዚህ ይልቅ በውስጣቸው የሚገኙትን ጣዖታት ብቻ ደምስሱ . . . ቤተ መቅደሶቹ በጥሩ ሁኔታ የሚገኙ ከሆነ በውስጣቸው የሚካሄደው ለአጋንንት የሚቀርብ አምልኮ አብቅቶ ለእውነተኛው አምላክ አገልግሎት መዋላቸው አስፈላጊ ነው።” የግሪጎሪ ዕቅድ፣ አረማውያን የቀድሞ ቤተ መቅደሶቻቸው አለመርከሳቸውን ሲመለከቱ አዘውትረው ወደዚያ መሄዳቸውን ለመቀጠል ይገፋፉ ይሆናል የሚል ነበር። አረማውያን “ለአጋንንት መሥዋዕት አድርገው ብዙ ኮርማዎችን ያርዱ” የነበረ ቢሆንም “ካሁን በኋላ ግን እንስሳትን መሥዋዕት የሚያደርጉት ለአጋንንት ሳይሆን ለአምላክ ውዳሴ በማቅረብ ለራሳቸው ለመብልነት ለመጠቀም እንደሚሆን” ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ ሊቀ ጳጳሱ ጽፈዋል።
የሮማ ካቶሊክ፣ በቀድሞዎቹ ቤተ መቅደሶች አቅራቢያ ለጻድቃን “ክርስቲያኖች” መታሰቢያነት ቤተ ክርስቲያኖችን በመሥራትም አረማዊ አምልኮን “ተቀናቅናለች።” ጥንታዊ በዓላት ተቀባይነት አግኝተው “ክርስቲያናዊ” ትርጉም ተሰጥቷቸዋል። ላ ቺቪልታ ካቶሊካ በዘገበው መሠረት ጉዳዩን ስንገልጸው:- “የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ይከተሏቸው የነበሩ አንዳንድ ባሕሎችና ሃይማኖታዊ በዓላት ከአንዳንድ ዓረማዊ ልማዶችና ዘይቤዎች ጋር የቅርብ ትስስር እንዳላቸው ባሁኑ ጊዜ በሁሉም ሃይማኖታዊ ምሁራን ዘንድ የታወቀ ሆኗል። እነዚህ ልማዶች በሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ይሰጣቸው ነበር፤ በጥንታዊው ዓለም ማኅበራዊም ሆነ የግል ሕይወት ውስጥ ሥር የሰደዱና ሊነጠሉ የማይችሉ ባሕሎች ነበሩ። ደግና አስተዋይ የሆነችው እናት ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ልማዶችና ባሕሎች ማስወገድ አለብኝ የሚል አቋም አልያዘችም፤ ከዚህ ይልቅ ክርስቲያናዊ ገጽታ በመስጠትና አዲስ ወደሆነ የቅድስና ደረጃና ሕይወት ከፍ በማድረግ ተራውም ሕዝብ ሆነ የተማረው አንዳች ተቃውሞ ሳያሰማ በቁጥጥሯ ስር ለማዋል ኃይለኛ ሆኖም ለዘብ ያለ ዘዴ ተጠቅማ በእነርሱ ላይ ተንሰራፋች።”
የገና በዓል በሰፊው የሚታወቅና ለአብነት ሊጠቀስ የሚችል ከዓረማውያን የተወረሰ በዓል ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። እንደ እውነቱ ከሆነ ታኅሣሥ 25 የጥንት ሮማውያን ዲኢስ ናታሊስ ሶሊስ ኢንቪክቲ ማለትም “የማትበገረዋን ፀሐይ የልደት ቀን” የሚያከብሩበት ዕለት ነበር።
ቤተ ክርስቲያን የዓረማውያንን ልብ ለመማረክ ከነበራት ምኞት የተነሳ እውነትን አጥብቃ ሳትይዝ ቀርታለች። ቤተ ክርስቲያኒቱ አረማዊ እምነቶችና ልማዶች የመቀበልና የማዋሃድ ተግባርዋን “በምዕመናኑ ዘንድ ተወዳጅ” ስለሆኑ ነው በሚል አሳብባለች። በውጤቱ የተገኘው ከእውነተኛው የክርስትና ትምህርት ፍጹም የራቀ፣ ቅይጥና ከሃዲ ቤተ ክርስቲያን ነበር። ከላይ ባየነው መሠረት “ለአማልክት ሁሉ” የቆመው የቀድሞው የሮማ ቤተ መቅደስ ማለትም ፓንቲየን ለማርያምና “ለጻድቃን” በሙሉ የቆመ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሆኑ ላያስገርም ይችላል።
ይሁን እንጂ አንድ ቤተ መቅደስ የቆመለትን ዓላማ ወይም የአንድን በዓል ስም መቀየሩ ‘ለአጋንንት የሚቀርበውን አምልኮ ለእውነተኛው አምላክ ወደሚቀርብ አገልግሎት’ ለመቀየር በቂ እንዳልሆነ ግልጽ መሆን አለበት። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስም ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው?” ሲል ጠይቋል። “ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ:- እኔም እቀበላችኋለሁ፣ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል።”—2 ቆሮንቶስ 6:16-18