ራሺ ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳደረ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ
በዕብራይስጥ ቋንቋ ለመታተም የመጀመሪያ ከሆኑት መጻሕፍት ውስጥ አንዱ የትኛው ነበር? የፔንታቱች (አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት) ማብራሪያ የያዘ መጽሐፍ ነው። የታተመው በኢጣሊያ፣ ሬጂዮ ካላብሪያ በ1475 ነበር። ጸሐፊው ማን ነበር? ራሺ የተባለ ሰው ነበር።
አንድ የማብራሪያ ጽሑፍ ይህን ያህል ከፍተኛ ክብር የተቸረው ለምንድን ነው? ኢዝራ ሸረሸቪስኪ ራሺ—ዘ ማን ኤንድ ሂዝ ዎርልድ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት የራሺ ማብራሪያ “በአይሁዳውያን መኖሪያ ቤቶች ውስጥና አይሁዳውያን ለጥናት በሚጠቀሙባቸው ቤቶች ውስጥ ዋነኛ የመማሪያ መጽሐፍ ሆነ። ከአይሁዳውያን ጽሑፎች ውስጥ የዚህን ያህል ላቅ ያለ ግምት የተሰጠው መጽሐፍ የለም። . . . ራሺ ስለ ፔንታቱች ከጻፈው ማብራሪያ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ከ200 በላይ የሚሆኑ ጽሑፎች ይገኛሉ።”
የራሺ ማብራሪያ ተጽእኖ ያሳደረው በአይሁዳውያን ላይ ብቻ ነበርን? ብዙዎች አያስተውሉት እንጂ ራሺ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የሰጠው ማብራሪያ ለብዙ ዘመናት በመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ላይ ተጽእኖ ሲያሳድር ኖሯል። ይሁን እንጂ ራሺ ማን ነው? ይህን ያህል ተጽእኖ ሊያሳድር የቻለውስ እንዴት ነው?
ራሺ ማን ነበር?
ራሺ በፈረንሳይ፣ ትሮይ በ1040 ተወለደ።a በወጣትነት እድሜው በራይንላንድ በሚገኘው በዎርምስ እና ሜይንዝ የአይሁድ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች ገብቶ ተምሯል። በዚያም በአውሮፓ ከሚገኙት እጅግ ታዋቂ የአይሁድ ምሁራን መካከል አንዳንዶቹ አስተምረውታል። ወደ 25 ዓመት ዕድሜው ሲጠጋ የግል ሁኔታዎቹ ወደ ትሮይ እንዲመለስ አስገደዱት። ቀድሞውንም ቢሆን በሃይማኖት ሊቅነቱ እውቅና አግኝቶ የነበረው ራሺ ብዙም ሳይቆይ በአካባቢው የሚገኘው የአይሁድ ማኅበረሰብ ሃይማኖታዊ መሪ ሆነ፤ የራሱንም የሃይማኖት ትምህርት ቤት አቋቋመ። ከጊዜ በኋላ እንዲያውም ይህ አዲስ የአይሁዳውያን የጥናት ማዕከል በጀርመን ከሚገኙት የራሺ አስተማሪዎች ይልቅ ይበልጥ እውቅና አገኘ።
በዚያን ጊዜ በፈረንሳይ ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች ክርስቲያን ነን ከሚሉት ጎረቤቶቻቸው ጋር አንጻራዊ የሆነ ሰላምና ስምምነት ስለነበራቸው ራሺ ምሁራዊ ጥናቱን ለማካሄድ ሰፊ ነፃነት አግኝቶ ነበር። ሆኖም ራሺ ተገልሎ የሚኖር ምሁር አልነበረም። ምንም እንኳ ራሺ የተከበረ አስተማሪና የአካዳሚው መሪ ቢሆንም ራሱን ያስተዳድር የነበረው ወይን በመጥመቅ ነበር። ብዙሃኑ ከተሰማራበት ከዚህ ሥራ ጋር የነበረው የቀረበ ትውውቅ መካከለኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው አይሁዳውያን ጋር እንዲገናኝ ያስቻለው ሲሆን ያሉበትን ሁኔታ እንዲገነዘብና እንዲያዝንላቸው ረድቶታል። በተጨማሪም የትሮይስ አቀማመጥ ራሺ ጥልቅ ማስተዋል እንዲያገኝ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከተማዋ ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ በሚካሄድባቸው መንገዶች ላይ የምትገኝ በመሆኗ የብዙ ድብልቅ ሕዝብ መኖሪያ ማዕከል ሆና ታገለግል ነበር። ይህ ደግሞ ራሺ ከብዙ ብሔራት ልማድና ወግ ጋር በሚገባ እንዲተዋወቅ አስችሎታል።
ማብራሪያ ለምን አስፈለገ?
አይሁዳውያን የመጽሐፉ ሰዎች በመባል ይታወቁ ነበር። ይሁን እንጂ “መጽሐፉ” የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘው በዕብራይስጥ ቋንቋ ሲሆን “ሰዎች” የተባሉት ደግሞ አሁን የሚናገሩት አረብኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ስፓንኛና ሌሎች በርካታ ቋንቋዎችን ነው። አብዛኞቹ አይሁዶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ዕብራይስጥ የሚማሩ ቢሆንም አብዛኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት በግልጽ አይረዷቸውም ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ለብዙ ዘመናት ተንሰራፍቶ የኖረው በረቢዎች የሚመራው የአይሁድ እምነት ሕዝቡ የመጽሐፍ ቅዱሱን ጥቅስ ቀጥተኛ ፍቺ ለማወቅ እንዳይመረምር አድርጎታል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላትንና ጥቅሶችን የያዙ ምሳሌዎችና አፈ ታሪኮች እንደ አሸን ፈሉ። እንደነዚህ ያሉት አብዛኛዎቹ ማብራሪያዎችና ታሪኮች ጠቅለል ባለ መልኩ ሚድራሽ ተብለው በሚጠሩ ግዙፍ ጥራዞች ላይ ተመዝግበው ነበር።b
ረቢ ሳሙኤል ቤን ሜዪር (ራሽባም) የተባለው የራሺ የልጅ ልጅም የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር ነበር። ዘፍጥረት 37:2ን በሚመለከት በሰጠው ማብራሪያ ላይ እንዲህ ብሏል:- “. . . [ከራሺ በፊት] የነበሩት ቀደምት ተንታኞች እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው ወዳሉት የስብከት ሥራ (ዴራሾት) ቢያዘነብሉም የመጽሐፍ ቅዱሱን ጥቅስ ቀጥተኛ ትርጉም ለማግኘት ጠልቆ የመቆፈር ልማድ [ግን] አልነበራቸውም።” ዶክተር ኤ ኮኸን (ሶንሲኖ ቡክስ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው ጽሑፍ ዋና አዘጋጅ) በዚሁ ሐሳብ ላይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “እርግጥ ረቢዎች ከፔሻት ወይም ግልጽ ከሆነው የጥቅሱ ትርጉም ጋር የሚቃረን አተረጓጎም እንዳይገባ የሚከለክል ደንብ ቢያወጡም በተግባር ሲታይ ግን ለደንቡ እምብዛም አይጨነቁም ነበር።” እንዲህ ባለ ሃይማኖታዊ አካባቢ ተራው አይሁዳዊ የመጽሐፍ ቅዱሱን ጥቅስ ለመረዳት ስለማይችል አንዳንድ የማብራሪያ መሣሪያዎችን ለማግኘት ይፈልግ ነበር።
የራሺ ግብና ዘዴዎች
የራሺ የዕድሜ ልክ ግብ ሁሉም አይሁዶች የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጥቅስ እንዲረዱ ማድረግ ነበር። ይህን ውጥን ከዳር ለማድረስ ለአንባቢው ያስቸግራሉ ባላቸው የተወሰኑ ቃላትና ጥቅሶች ላይ የተሰጡ ማብራሪያዎችን የያዙ ማስታወሻዎችን መሰብሰብ ጀመረ። የራሺ ማስታወሻዎች አስተማሪዎቹ የሰጧቸውን ማብራሪያዎችና እርሱ ራሱ ስለ ረቢዎች ሥነ ጽሑፍ የነበረውን ሰፊ እውቀት አጣምረው የያዙ ናቸው። ራሺ በቋንቋ ጥናት ረገድ አሉ የሚባሉትን የመረጃ ምንጮች በሙሉ ተመልክቷል። የማሶሪያውያን አመልካችና አናባቢ ምልክቶች የጥቅሱን ሐሳብ በመረዳት ረገድ ያሳደሩትን ተጽእኖ ትኩረት ሰጥቶ አጥንቷል። የአንድን ቃል ትርጉም ለማብራራት በፔንታቱች ላይ የሰጠው ማብራሪያ አብዛኛውን ጊዜ የአረማይኩን ትርጉም (ታርገም ኦቭ ኦንኬሎስ) ይጠቅስ ነበር። ራሺ መስተዋድዶችን፣ መስተፃምሮችን፣ የግሥ ትርጉሞችንና ሌሎች የሰዋሰውና የቃላት አገባብ ለማብራራት የሚያስችሉትን ቀደም ሲል ያልተሠራባቸውን መንገዶች በሚመረምርበት ጊዜ ሐሳቡን ለማስተካከል የማያንገራግርና ብልህ መሆኑን አሳይቷል። እንዲህ ያሉት ማብራሪያዎች የዕብራይስጥ ቋንቋን የቃላት አገባብና ሰዋሰው ለመረዳት የሚያስችል ጠቃሚ የሆነ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በረቢዎች በሚመራው የአይሁድ እምነት ዘንድ ጎልቶ ከሚታየው አሠራር በተቃራኒ ራሺ ሁልጊዜ የአንድን ጥቅስ ቀላልና ቀጥተኛ ትርጉም ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ይፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ በአይሁዳውያን ዘንድ በደንብ የሚታወቀው ሰፊው የሚድራሺያውያን ሥነ ጽሑፍ በቸልታ የሚታለፍ አይደለም። የራሺ ማብራሪያ አንዱ ልዩ ገጽታ አብዛኛውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱሱን ጥቅስ ቀጥተኛ ትርጉም እንዳይታወቅ ካደረጉት ከእነዚሁ የሚድራሺያውያን ጽሑፎች ጋር የሚዛመድበት መንገድ ነው።
ራሺ ዘፍጥረት 3:8ን በተመለከተ በሰጠው ማብራሪያ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ጠቢባኖቻችን በቤሬሺት ራባህ እና በሌሎች የሚድራሺያውያን መድብሎች ላይ ግሩም በሆነ መንገድ ያዘጋጁአቸው ብዙ የአጋዳc ሚድራሺም አሉ። ይሁን እንጂ እኔን ይበልጥ የሚያሳስበኝ የጥቅሱ ቀጥተኛ ትርጉም (ፔሻት) እና እንዲህ ባለ አጋዶት አማካኝነት ቅዱስ ጽሑፋዊውን ታሪክ እንደ አገባቡ ማብራራት ነው።” ራሺ የአንድን ጥቅስ ትርጉም ወይም አጠቃላይ ሐሳብ ግልጽ ለማድረግ ይረዳሉ ያላቸውን ሚድራሺም በመምረጥና በማዘጋጀት ተቃርኖና መደነጋገር የሚፈጥሩትን ሚድራሺሞች ለቅሞ አውጥቷቸዋል። በዚህ የለቀማ ሥራ ምክንያት ቀጥለው የመጡት አይሁዳውያን ትውልዶች ራሺ ከመረጣቸው የሚድራሺም ክፍሎች ጋር ይበልጥ ሊተዋወቁ ችለዋል።
ራሺ ለአስተማሪዎቹ የላቀ ግምት ቢኖረውም በአንድ ጥቅስ ላይ የሰጡት ማብራሪያ ምክንያታዊ ከሆነው ግልጽ ሐሳብ ጋር በሚቃረንበት ጊዜ አለመስማማቱን ከመግለጽ ወደ ኋላ አይልም ነበር። አንድ ምንባብ ካልገባው ወይም ቀደም ሲል በጉዳዩ ላይ የሰጠው ማብራሪያ ስህተት መስሎ ከተሰማው መሳሳቱን አምኖ ለመቀበል ፈቃደኛ የነበረ ሲሆን ተማሪዎቹ እንኳን ሳይቀር አመለካከቱን ያረሙበት አጋጣሚ እንደነበር ጠቅሷል።
በጊዜው የነበረው ሁኔታ ተጽእኖ አሳድሮበታል
ራሺ ከጊዜው ጋር አብሮ የሚራመድ ሰው ነበር። አንድ ደራሲ በዚህ መንገድ ጠቅለል አድርገው አስቀምጠውታል:- “[ራሺ] ለአይሁድ ሕይወት ያበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከአይሁድ ሕይወት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ምንባቦች በሙሉ ግልጽ በሆነና ጥርት ባለ ቋንቋ፣ የጋለ ስሜት በሚንጸባረቅበትና ሰብዓዊነት በተላበሰ መንገድ፣ ብርቅ ከሆነ ክህሎትና ምሁራዊ ችሎታ ጋር በጊዜው ወደነበረው ቋንቋ እንደገና መተርጎሙ ሲሆን ይህም ማብራሪያዎቹ እንደ ቅዱስ ጽሑፍ እንዲከበሩና እንደ ሥነ ጽሑፍ እንዲወደዱ አድርጓቸዋል። ራሺ ዕብራይስጥን ይጽፍ የነበረው ፈረንሳይኛን በሚጽፍበት ግሩምና ውብ በሆነ መንገድ ነበር። ትክክለኛውን የዕብራይስጥ ቃል በሚያጣበት ጊዜ የፈረንሳይኛ ቃል ተጠቅሞ በዕብራይስጥ ፊደላት ይጽፈው ነበር።” ራሺ የተጠቀማቸው ከ3,500 በላይ የሚሆኑት በዕብራይስጥ ፊደላት የተጻፉ ፈረንሳይኛ ቃላት የፈረንሳይኛን ቋንቋ ጥንታዊ ታሪክና አነባበብ ለሚያጠኑ ተማሪዎች ጠቃሚ ምንጭ ሆነዋል።
ራሺ ያደገው አንጻራዊ የሆነ ሰላም በሰፈነበት አካባቢ ቢሆንም በኋለኛው የሕይወት ዘመኑ በአይሁዶችና በክርስቲያን ነን ባዮች መካከል እየጨመረ የሄደ አለመግባባት ተመልክቷል። በ1096 የተደረገው የመጀመሪያው የመስቀል ጦርነት ራሺ በተማረባት በራይንላንድ የሚገኘውን የአይሁዶች ማኅበረሰብ አወደመ። በሺህ የሚቆጠሩ አይሁዶች ተጨፈጨፉ። የእነዚህ ጭፍጨፋዎች ዜና በራሺ ጤንነት ላይ ተጽእኖ ያሳደረ ይመስላል። (በ1105 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ጤንነቱ እያሽቆለቆለ ሄዶ ነበር።) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቅዱስ ጽሑፉ ላይ የሚሰጣቸው ማብራሪያዎች ጉልህ የሆነ ለውጥ ታይቶባቸዋል። አንዱ ጉልህ ማስረጃ በሥቃይ ላይ ስለነበረው የይሖዋ አገልጋይ የሚናገረው ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ነው። ቀደም ሲል ራሺ ታልሙድ ከሚለው ጋር በመስማማት እነዚህ ጥቅሶች መሲሑን ያመለክታሉ ብሎ ነበር። ሆኖም ከመስቀል ጦርነቶቹ በኋላ እነዚህ ጥቅሶች ተገቢ ያልሆነ ሥቃይ የደረሰበትን የአይሁድ ሕዝብ ያመለክታሉ ብሎ ያሰበ ይመስላል። ይህ ወቅት አይሁዳውያን እነዚህን ጥቅሶች የሚተረጉሙበት መንገድ አዲስ አቅጣጫ እንዲይዝ አድርጓል።d ስለዚህ የሕዝበ ክርስትና ክርስቲያናዊ ያልሆነ ድርጊት አይሁዶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ከሚናገረው እውነት እንዲርቁ ምክንያት ሆኗል።—ማቴዎስ 7:16-20፤ 2 ጴጥሮስ 2:1, 2
በመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ላይ ምን ተጽእኖ አሳድሯል?
ራሺ ያሳደረው ተጽእኖ ከአይሁድ እምነት አልፎ መሄዱ በግልጽ መታየት የጀመረው ወዲያውኑ ነበር። ፈረንሳዊው የፍራንሲስካን መጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የላይራው ኒኮላስ (1270-1349) የ“ረቢ ሰሎሞን [ራሺ]” አስተያየቶችን አዘውትሮ ይጠቅስ ስለነበር “ዳግማዊ ሰሎሞን” የሚል ቅጽል ስም ወጥቶለት ነበር። ላይራ ደግሞ በተራው በብዙ ተንታኞችና ተርጓሚዎች ላይ ተጽእኖ አሳድሮ የነበረ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የእንግሊዝኛው የኪንግ ጄምስ ቨርሽን ተርጓሚዎችና በጀርመን ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዲስፋፋ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደረገው የለውጥ አራማጁ ማርቲን ሉተር ይገኙበታል። ሉተር ድጋፍ የሚሆኑ ሐሳቦች ለማግኘት በላይራ ላይ በእጅጉ ተመክቶ ስለነበር “ላይራ ባያቀነቅን ኖሮ ሉተር ባላሸበሸበ ነበር” የሚል በሰፊው የሚነገር ምሳሌያዊ አባባል አለ።
ራሺ ከክርስትያናዊው እውነት ጋር ፍጹም ስምምነት የሌለው የረቢዎች አስተሳሰብ ከፍተኛ ተጽእኖ አድርጎበት ነበር። ሆኖም ስለ መጽሐፍ ቅዱሱ የዕብራይስጥ ቃላት፣ አጠራርና ሰዋስው በነበረው ጥልቅ ማስተዋል እንዲሁም የአንድን ጥቅስ ግልጽና ቀጥተኛ ትርጉም ለመረዳት የማያቋርጥ ጥረት በማድረጉ ራሺ ለመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎችና ተርጓሚዎች ለንጽጽር የሚያገለግል ትርጉም ያለው ሥራ ትቶላቸው አልፏል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ራሺ” የዕብራይስጥ ምህጻረ ቃል ሲሆን “ራባይ ሽሎሞ ዪትስሃቂ [ረቢ ሰሎሞን ቤን አይሳክ] ከሚሉት ቃላት የመጀመሪያዎቹን ፊደላት በመውሰድ የተገኘ ነው።”
b “ሚድራሽ” የሚለው ቃል “መጠየቅ፣ ማጥናት፣ መመርመር” እና ከዚያም አልፎ “መስበክ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው።
c አጋዳ (በብዙ ቁጥር ሲጻፍ አጋዶት) ቃል በቃል ሲተረጎም “ትረካ” ማለት ሲሆን በረቢ ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙ ሕግ ነክ ያልሆኑ ጉዳዮችን፣ አብዛኛውን ጊዜም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎችን ወይም ስለ ረቢዎች የሚነገሩ አፈ ታሪኮችን የሚያወሱ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ተረቶችን የሚያመለክት ነው።
d በእነዚህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምንባቦች ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በታተመው ጦርነት የሌለበት ዓለም ይመጣ ይሆን? (እንግሊዝኛ) በተባለው ብሮሹር በገጽ 28 ላይ የሚገኘውን “አገልጋዬ” የተባለው ማን ነው? የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ጽሑፍ:- Per gentile concessione del Ministero dei Beni Culturali e Ambientali