ለልጆቻችሁ አንብቡላቸው
ቬዣ የተባለው የብራዚል መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ በትጋት የሚያነቡ ወላጆች ያሏቸው ልጆች መጽሐፍ ለማንበብ ፍቅር የማዳበራቸው አጋጣሚ በቤታቸው ውስጥ መጻሕፍት በማንበብ ምሳሌ የሚሆን ወላጅ ከሌሏቸው ልጆች በእጅጉ የበለጠ ነው። “ለልጆች ማንበብ በወላጆችና በልጆች መካከል ያለውን ትስስር ከማጥበቁም በላይ ልጁ ከመጽሐፉ ይዘት ጋር በቶሎ እንዲተዋወቅ ይረዳዋል” በማለት በልጅ አስተዳደደግ ስፔሺያሊስት የሆኑት ማርታ ሆፕ ይናገራሉ።
ለልጆቻችሁ ጮክ ብላችሁ ማንበባችሁ ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንድትሰጡ አጋጣሚ ይከፍትላችኋል። በጽሑፉ ውስጥ በሰፈሩት ሥዕሎች ላይ ልትወያዩ ትችላላችሁ። “አንድ ልጅ ከመጻሕፍት ይዘት ጋር በይበልጥ እየተዋወቀ በሄደ መጠን የማወቅ ፍላጎቱን ማርካት በሚፈልግበት ጊዜ ወደ መጻሕፍት ዞር የማለት ፍላጎቱ የዚያኑ ያህል ከፍ ይላል” በማለት ሆፕ ገልጸዋል።
የይሖዋ ምሥክር የሆኑ በርካታ ወላጆች ለልጆቻቸው ያነቡላቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ፣ ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ እና እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰውa የተባሉ መጻሕፍትን የመሳሰሉ ጽሑፎችን ለልጆቻቸው ሊያነቡላቸው ይችላሉ። እንደነዚህ ያሉት መጻሕፍት ልጆቹ ጥሩ አንባቢ እንዲሆኑ ከመርዳታቸውም በላይ በዓለም ዙሪያ በብዛት በመሸጥ አቻ ያልተገኘለትን መጽሐፍ ማለትም መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ፍላጎታቸውን ያጎለብትላቸዋል። ስለዚህ ወላጅ ከሆናችሁ የአምላክን ቃል በትጋት በማንበብ ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ ሁኗቸው። (ኢያሱ 1:7, 8) በተቻለ መጠን ጊዜ ወስዳችሁ ለልጆቻችሁ አንብቡላቸው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a * ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙ።