ፍሬያማ የሆነው የቬንዳ ምድር
ላለፉት አሥር ዓመታት እኔና ባለቤቴ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነን ቬንዳዎች በሚኖሩበት አካባቢ ስናገለግል ቆይተናል። ቬንዳዎች የሚኖሩት በሰሜናዊ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው የሊምፖፖ ወንዝ በስተ ደቡብ ሲሆን የቬንዳ ብሔር ባለፉት መቶ ዘመናት ሊምፖፖን ተሻግረው ከመጡ በርካታ ጎሳዎች የተዋቀረ ነው። አንዳንድ ቬንዳዎች ቅድመ አያቶቻቸው እዚህ ቦታ የሰፈሩት ከዛሬ 1,000 ዓመት በፊት እንደሆነ ይናገራሉ።
እርግጥ ይህ አካባቢ በአንድ ወቅት የማፑንጉብዌ መንግሥት በሚል የሚታወቅ የአንድ ጥንታዊ ሥልጣኔ አካል ነበር። ቦታው በስተ ምዕራብ ከቦትስዋና አንስቶ በስተ ምስራቅ እስከ ሞዛምቢክ ድረስ የተንጣለለውን የሊምፖፖ ወንዝ ሸለቆ የሚይዝ የደቡብ አፍሪካ ቀደምት ሰፊ የመኖሪያ አካባቢ ነበር። ከ900 እዘአ አካባቢ አንስቶ እስከ 1100 እዘአ ድረስ ማፑንጉብዌ ከአረብ ለሚመጡ ነጋዴዎች የዝሆን ጥርስ፣ የአውራሪስ ቀንድ፣ ቆዳ፣ መዳብ አልፎ ተርፎም ወርቅ ያቀርብ ነበር። ማፑንጉብዌ ከሚባል ከአንድ ኮረብታማ የነገሥታት መቃብር የላቀ ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው በወርቅ የተለበጡ ቅርጻ ቅርጾች በቁፋሮ ተገኝተዋል። አንድ ኢንሳይክለፒዲያ እነዚህ ዕቃዎች “ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የወርቅ ማዕድን ማውጫ መኖሩን ከሚጠቁሙ ጥንታዊ” ነገሮች መካከል መሆናቸውን ጠቁሟል።
አሁን በዚህ ቦታ የወርቅ ቁፋሮ አይካሄድም። ዛሬ የቬንዳ ምድር በፍሬያማነቱ የታወቀ ሆኗል። ከሶትፓንስበርግ ተራራዎች በስተ ደቡብ እንደ አቮካዶ፣ ሙዝ፣ ማንጎና ዘይቱን የመሳሰሉ ፍራፍሬዎች በገፍ የሚመረትበት ለም ሸለቆ ይገኛል። እንደ ፒካንና ማካዳሚያ ከመሳሰሉ የለውዝ ዓይነቶች በተጨማሪ የተትረፈረፈ የአትክልት ምርት ይገኛል። ይህ ደግሞ የጎመን ጣዕም ያለውንና በአካባቢው ነዋሪዎች በጣም ተወዳጅ የሆነውን ሙሮሆ የሚባለውን የጫካ ተክል ያጠቃልላል።
ቬንዳዎች ሰላማውያንና እንግዳ ተቀባይ ሕዝቦች ናቸው። አንድ ያልታሰበ እንግዳ ቤታቸው ከመጣ የቤተሰቡ ራስ ዶሮ ይታረድልህ ብሎ መጠየቁ የተለመደ ነው። ዶሮው ቡስዋ ከሚባል ከበቆሎ የሚዘጋጅ ባሕላዊ ምግብ ጋር ይበላል። እንግዳው ቆይታውን አጠናቅቆ ጉዞውን ሲጀምር የቤቱ ባለቤት ጥቂት መንገድ ይሸኘዋል። ይህ ለአንድ እንግዳ አክብሮት የሚሰጥበት ባሕላዊ መንገድ ነው። ልጆች እንግዳ በሚመጣበት ጊዜ ትንሽ ሸብረክ በማለትና በዝግታ እጃቸውን በመስበቅ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ሰላምታ እንዲሰጡ ሥልጠና ይሰጣቸዋል። በዚህ ገጽ ላይ ሁለት ሴቶች በዚህ ባሕላዊ መንገድ ሰላምታ ሲሰጣጡ ትመለከታለህ።
አስቸጋሪ ቋንቋ
የቬንዳ ቋንቋ አንድ አውሮፓዊ በቀላሉ የሚለምደው ቋንቋ አይደለም። አንዱ ችግር አብዛኞቹ ቃላት ተመሳሳይ አጻጻፍ ቢኖራቸውም አነባበባቸው ግን የተለያየ መሆኑ ነው። አንድ ቀን በይሖዋ ምሥክሮች የቬንዳ ጉባኤ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ስሰጥ አድማጮች አገልግሎት ላይ እያንዳንዱን ሰው እንዲያነጋግሩ ማበረታታት ፈለግሁና “ከሰው ወደ ሰው” እላለሁ ብዬ “ከጣት ወደ ጣት” በማለቴ ስብሰባው ላይ የነበረ አንድ ሰው ከት ብሎ ሳቀ።
በምሥክርነቱ ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ በቬንዳ ቋንቋ ለመናገር ስሞክር አንዲት የቬንዳ ሴት “እንግሊዝኛ መናገር አልችልም” ስትል መለሰችልኝ። በእኔ ቤት በቬንዳ ቋንቋ በትክክል መናገሬ ነበር እርሷ ግን ጭራሽ በእንግሊዝኛ የማነጋግራት መሰላት! በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ከቤት ወደ ቤት ስሰብክ በሩን ለከፈተልኝ ልጅ የቤቱን ባለቤት እንዲጠራልኝ ጠየቅሁት። የቤቱን ባለቤት ለማመልከት የሚሠራበት የቬንዳ ቃል ቱሆ ሲሆን እኔ ግን በስህተት ቶሁ አልኩ። ይህም ቤት ውስጥ ያለውን ዝንጀሮ ጥራልኝ ማለት ነበር! እንዲህ ዓይነት ስህተቶች ተስፋ ቢያስቆርጡኝም እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በጽናት በመቀጠላችን አሁን በቬንዳ ቋንቋ ጥሩ አድርገን መግባባት ችለናል።
መንፈሳዊ ፍሬ
የቬንዳ ምድር በመንፈሳዊ ሁኔታ ፍሬያማ ሆኖ ተገኝቷል። በ1950ዎቹ በመሲነ ከተማ በሚገኘው የመዳብ ማውጫ ለመሥራት ከጎረቤት አገሮች የመጡ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አቋቁመው ነበር። ቅንዓት የተሞላበት እንቅስቃሴያቸው በርካታ ቬንዳውያን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲያውቁ አስችሏል። ከአሥር ዓመታት በኋላ ሲባሳ በሚባል ከተማ ቬንዳ ምሥክሮች በግል መኖሪያ ቤት ውስጥ ስብሰባዎች ያካሂዱ ነበር።
በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ እድገቱ እንዲፋጠን ፍሬያማ ወደሆነው ወደዚህ መስክ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ላከ። ብዙም ሳይቆይ የሲባሳ ቡድን አድጎ ትልቅ ጉባኤ ሆነ። በዚያን ጊዜ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች የሚደረጉት ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። ሆኖም በስተ ደቡብ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በፒተርስበርግ አካባቢ በሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ድጋፍ በአቅራቢያው በምትገኘው የቶሆያንዶኡ ከተማ የመንግሥት አዳራሽ ተገንብቷል።
በሰሜናዊ ደቡብ አፍሪካ የሚኖረው ቬንዳ ተናጋሪ ሕዝብ ብዛት ከ500,000 ይበልጣል። በ1950ዎቹ በዚህ ቦታ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ሲጀመር አንድም ቬንዳ ምሥክር አልነበረም። አሁን ከ150 የሚበልጡ ምሥክሮች አሉ። ሆኖም አሁንም ቢሆን ብዙ ያልተዳረሱ አካባቢዎችና መሠራት ያለበት ብዙ ሥራ ይቀራል። በ1989 ሐሙትሻ በምትባል የቬንዳ መንደር ማገልገል ስንጀምር በዚያ የሚኖር አንድ የይሖዋ ምሥክር ብቻ ነበር። አሁን በዚያች መንደር ውስጥ ከ40 የሚበልጡ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች አሉ። በፒትስበርግ በሚገኙ ጉባኤዎች ያሉ ምሥክሮችና ሀብታም በሆኑ አገሮች የሚኖሩ ወንድሞች ለሰጡን የገንዘብ ድጋፍ ምስጋና ይድረሳቸውና የመንግሥት አዳራሻችንን ግንባታ ለማጠናቀቅ በመረባረብ ላይ እንገኛለን።
የምንኖረው በአንድ የእርሻ ቦታ ባቆምነው ተጎታች መኪና ውስጥ ነው። ኑሯችንን ቀላል በማድረግ ምሥራቹን ለአካባቢው ሰዎች የምናዳርስበት ሰፊ ጊዜ አግኝተናል። (ማርቆስ 13:10) ይህም በመሆኑ ብዙዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ አምላክ እንዲወስኑ የመርዳት መብት በማግኘታችን በእጅጉ ተባርከናል። ለአብነት ያህል በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ከጓደኛው ቤት ያገኘው ሚካኤል የሚባለውን ሰው መጥቀስ እችላለሁ።a መጽሐፉን ማንበብ ጀመረና ወዲያውኑ እውነትን እንዳገኘ ተገነዘበ። በመሆኑም ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መጻሕፍት እንዲላክለት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ደብዳቤ ጻፈ። ሚካኤል በደብዳቤው ላይ በአካባቢው የሚገኝ የሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን አባል በመሆን በቅርቡ መጠመቁን ገልጿል። በመቀጠልም “የአምላክን መንግሥት ለማግኘት በተሳሳተ መንገድ ስጓዝ እንደነበር ተገንዝቤአለሁ። የእናንተ አባል ለመሆን ወስኛለሁ፤ ሆኖም ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም” ብሏል። ከዚያም አድራሻውን በመላክ ሊረዳው የሚችል አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲላክለት ጠየቀ። ሚካኤልን በአድራሻው መሠረት ካገኘሁት በኋላ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመርኩለት። ዛሬ ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግል የተጠመቀ ምሥክር ሆኗል።
በታኅሣሥ 1997 በቶሆያንዶኡ በሚገኝ ስታዲዮም “በአምላክ ቃል ማመን” የተባለውን የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ አደረግን። በስብሰባው ላይ 634 ሰዎች የተገኙ ሲሆን 12 ተጠማቂዎች ደግሞ ነበሩ። በዚያም በቬንዳ ቋንቋ ሁለት ንግግሮች የመስጠት መብት አግኝቻለሁ። በእርግጥ ይህ በዚህ ፍሬያማ አገር ባሳለፍናቸው አስደሳች አሥር ዓመታት አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነበር!—ተጽፎ የተላከልን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።